Tuesday, April 1, 2014

ገብር ኄር ዘረቡዕ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 23 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 የሕልውናው መሠረት በማይገኝ፣ በቁጥርም በማይቆጠር በእግዚአብሔር አብ ስም፣ የከዋክብት ብርሃን ሳይታይ የናጌብም ባሕር ጥልቅ ሳይሆን በፊት ከእርሱ ጋር በነበረና ያለ ሩካቤ ከድንግል ማኅጸን በተወለደ በአንድያ ልጁ ስም ሰላም ይሁንላችሁ::(መጽሐፈ ምሥጢር)


 ዛሬም በጠዋት ከእንቅልፋችን ነቅተን የእናታችንን የቤተክርስቲያንን ጡት እንጠባ ዘንድ ይለናል ሊቁ ቅዱስ ያሬድ:: “ነግሀ ነቂሐነ እምንዋምነጋ ከእንቅልፋችንም ነቃን፤ ወደ ቤተክርስቲያን እንገስግስ፡፡ የንጹሐን ቅዱሳን ማደሪያ የአማኞች እናተ ነች፤ እርሷ መድኃኒት የሕይወት በር የሆነች ነች፤ ያማረች የተዋበች ፍሬም የምታፈራ ቅድስት ቤተክርስቲያን ነች::” እያለ እናቱን በጠዋት እያወደሰ እኛንም በምሥጋናው ቃና ይጠራናል:: እኛም እንገባለን፤ ከማያልቀው ምሥጋና ባሕር ከአንተ ጋር የመላእክትን ውዳሴ እንጀምራለን:: አደባባይሽን ተመልከቺ፤ በሕዝብሽ ደስ ይበልሽ፤ በውስጥሽ ያሉ ምዕመናን ደስ ይበላቸው:: በሰንፔር እና በከርከዴን ዕንቊ ግድግዳዎችሽ የተሰሩ አንቺ ጽዮን መጠጊያ መድኃኒት ሕይወት ትባያለሽ:: ዐይንሽን አንሺ፤ ሕዝብሽን ተመልከቺ፤ እመቤት የሆንሽ አንቺ ልጆችሽ በአንቺ ተጠልለው ራስሽ ክርስቶስን ያመሰግናሉ:: እንዲህም ይላሉሰላማ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ንስእለከ እግዚዞ ወናስተበቊዓከየቅድስት ቤተክርስቲያን ሰላሟን እንለምንኀለን፤ በሕዝብህ ላይ ሁሉ ብዙ ሰላምህን ትሰጥ ዘንድ ክርስቶስ ሰላምን የምትሰጥ ስለሆንክ::…እግዚኦ መኑ ከማከ መሐሪአቤቱ እንደ አንተ ይቅር ባይ ማነው? ሁሉ ይቻልሃል፤ የሚሳንህ የለም::” እያሉ በደምህ በመሠረትካት ቤት ያመሰግኑሃል:: አንተም በዚህ ቤት የሚደረገውን ጸሎት ቸል አትልም::

 ሰሎሞን ቆመ በየማነ ምስዋዑሰሎሞን በእግዚአብሔር መስዋዕት ቀኝ ቆመ ወደላይ ወደ ሰማይ ተመለከተ፤ ጸለየም፡፡ እንዲህ አለ፡- በሰማይ በላይ በምድር በታች ከአንተ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ዓይንህን በቀንና በሌሊት አትመልስ፤ አቤቱ ለስምህ በዚህ ቤት በሰገዱና በተገዙ ጊዜ የአገልጋዮችህን ጸሎት ስማ:: ሃሌ ሉያ እያልን በቀናች ሃይማኖት በነጋ ጊዜ ምሕረትህን ትሰጠን ዘንድ እንለምንሃለን:: አንተ አምላካችን የማዳን አምላክ ነህና::

 ኄር አንተ እግዚኦ ወመሐሪአቤቱ ቸር መሐሪ የሆንክ በምሕረትህ ብዛት የእጅህን ሥራ ሕዝብህን ይቅር በል:: አዎ ቃልህ ሃሰት እንደሌለበት እናምናለን፤ ለአንተ ፈጽሞ እንገዛለን፤ ወደ አንተ እንጮሃለን::... በደላችንን አስወግድልን::”

 ዜመኛው ቀጥሏል! አቤቱ የልዑላን አባት የፍርድህ ወንበር መቀመጫዋ እውነት ብቻ የሆነ በምሕረትህ በቅን ፍርድህ የራቁትን የምታቀርብ የተበደሉትን የምትክስ አትራቀን:: ምሕረትህን ተስፋ አደርጋለሁ ስለዚህም ሁልጊዜ ወደ አንተ እጮሃለሁ:: አቤቱ ራሴን ትቼ አንተንና መስቀልህን ተሸክሜያለሁ:: ለነፍሴ ከአንተ ሌላ ምን ቤዛ እሰጣታለሁ? የዚህ ዓለም ንብረትስ አያድናትም፤ አንተ በተናገርክ ጊዜ ይጠፋልና:: እኛም ከሊቁ ጋር ይህንን ሁሉ እናስተውል::

 ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነአቤቱ መሬት (አፈር) እንደሆንን አስብ፤ የምሕረትህ ባሕር ወሰን የለው::” በየደቂቃው ሰላማችን አንተ ብቻ ሁን::

 መሐረነ እግዚኦ አምላክነ ወተሰሐለነ በብዝኃ ምሕረትከ ደምስስ አበሳነ ሰላመከ ሀበነ…. አቤቱ አምላካችን ማረን፤ ይቅርም በለን፡፡ በምሕረትህም ብዛት በደላችንን አጥፋ ሰላምህን ስጠን::” አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount