Saturday, April 12, 2014

ሰሙነ ሕማማት



በሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 5 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት እጅግ ከሚወደዱ እና ከሚናፈቁ ወቅቶች አንዱ ሰሙነ ሕማማት ነው፡፡ በዕለተ ሆሳዕና ጀምሮ በዕለተ ትንሣኤ የሚጠናቀቀው እጅግ ላቅ ያለ መንፈሳዊ ሕይወት የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ በላቲን Hebdomas Sancta or Hebdomas Maior በግሪክ ደግሞ γία κα Μεγάλη βδομάς, Hagia kai Megale Hebdomas  ታላቁ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ በኛ ደግሞ ሰሙነ ሕማማት፡፡

የሕማማትን ወቅት ከመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች ያከብሩት እንደነበር የሚያሳዩ ጥንታውያን መዛግብት አሉ፡፡ በሕግ ደረጃ ክርስቲያኖች በሰሙነ ሕማማት ከማንኛውም ሥራ ነጻ ሆነው፣ ፍርድ ቤቶችም ተዘግተው እንዲከበሩ የወሰነው ደግሞ ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ነው፡፡
 እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አዳዲስ ክርስቲያኖች ለመጠመቅ ይመርጡት የነበረው ጊዜ የትንሣኤን ቀን ነበር፡፡ ለዚህም ሁለት ዓይነት ምክንያቶች ነበሯቸው፡፡ የመጀመርያው ሰሙነ ሕማማትን በልዩ ሁኔታ ጾመው በትንሣኤው ቀን መጠመቁ ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ኃይል ስለሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት መጠመቅ ከክርስቶስ ጋር ሞቶ ከክርስቶስ ጋር መነሳት ነውና ጥምቀቱን ከትንሣኤው ጋር አያይዘውት ነበር፡፡
የሕማማት ሰሞን የኦሪት ጊዜን የሚያስታውስ ሰሞን ነው፡፡ አዳዲስ ክርስቲያኖቸም ይህንን ሰሞን ያለፈ ሕይወታቸውን ለማስታወስ እና ለማልቀስ ብሎም ራሳቸውን ወደ ሐዲስ ዘመን ለመለወጥ ይጠቀሙበት ነበር፡፡
በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ከዓርብ ጀምሮ ሰሙነ ሕማማትን ማክበር የተዘወተረ ነበር፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ስድስቱንም ቀን ማክበር የክርስቲያኖች ሥርዓት እየሆነ መጣ፡፡ ለዚሀም መነሻ የሆነው የአባቶቻችን ቀኖና የተሰኘው ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የተደነገጉ ቀኖናት መዝገብ  በቦታው መዳረስ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ ዐንቀጽ 5 ቁጥር 19 ላይ «በሰሞነ ሕማማት ከሳምንቱ ሁለተኛ ቀን (ሰኞ) እስከ ቅዳሜ የሰንበት መዘጋጃ ቀን ድረስ ጹሙ፡፡ በእነዚህም ጊዜያት ከእንጀራ እና ከጨው፣ ከማባያም በቀር ሌላ ነገር አትብሉ፡፡ ለመጠጥም ውኃ ብቻ ይሁንላችሁ» ይላል፡፡
የኛም ግብረ ሕማማት ይህንኑ የሐዋርያት ቀኖና በመጥቀስ በክፍል አንድ ሠላሳ አንደኛ ትእዛዝ በሚለው ርእስ ሥር «በሕማማት ሰሞን ከእንጀራ፣ ከጨው እና ከውኃ በቀር ምንም ምንም አትብሉ» ይላል፡፡
260 ዓም ለባሲሊደስ በጻፈው ደብዳቤ እያንዳንዷን የሰሞነ ሕማማት ቀን እና ሰዓት ከክርስቶስ መከራ ጋር በማያያዝ ገልጾ ነበር፡፡ 2ኛው ወይንም 3ኛው መክዘ ተሰባስቦ መጠረዙ የሚነገርለት የሶርያው ዲድስቅልያም ሰሙነ ሕማማት እንዴት መጾም እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ አቡሊዲስ ዘሮም በጻፈው የሐዋርያት ትውፊት (215 ዓም) ስለ ሰሙነ ሕማማት ሥርዓት ይደነግጋል፡፡ እያንዳንዷንም ሰዓት ከክርስቶስ መከራ ጋር ያገናኛታል፡፡
ሰሙነ ሕማማት አሁን ያለውን መልክ የያዘው 4ኛው መክዘ በኢየሩሳሌሙ ፓትርያርክ በቄርሎስ ዘመን ነው፡፡ ፓትርያርክ ቄርሎስ በመጨረሻዎቹ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከሚከበረው የጌታችን ትንሣኤ በፊት ያለውን ሰሙነ ሕማማት እያንዳንዱን ቀን በማሰብ የሚከበርበትን ሥርዓት ሠርቶ ነበር፡፡ 381 እስከ 385 ወደ ኢየሩሳሌም ለመሳለም የሄደችው ኤገርያ የተባለች ስፔናዊ በኢየሩሳሌም እንዴት ሰሙነ ሕማማት ይከበር እንደነበር የታሪክ መዝገብ ትታልናለች፡፡
ኤገርያ በጉዞ ማስታወሻዋ እንዲህ ትተርክልናለች
«በዓሉ የሚጀምረው በዕለተ እሑድ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ስለ ዓልዓዛር ትንሣኤ የሚገልጠው የወንጌል ክፍል ጠዋት ይነበባል፡፡ በሆሳዕና ዕለት ከሰዓት በኋላ ሁሉም ሰው ወደ ደብረ ዘይት ይወጣል፡፡ ከዚያም በጸጥታ የዘንባባ ዛፍ ተሸክሞ ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሳል፡፡ ይህንንም በመጀመርያዎቹ ሦስት ቀናት ይፈጽማሉ፡፡ ይህም ጌታችን ማታ ማታ ከከተማዋ ወጥቶ በደብረ ዘይት ያደረገውን ጸሎት ለማስታወስ ነው፡፡
በጸሎተ ኀሙስ ጠዋት ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ (ይህም በዓመቱ ውስጥ በመስቀሉ መቅደስ ላይ የሚደረግ ቅዳሴ ነው)፡፡ ከሰዓት በኋላ ሌላ ቅዳሴ ተቀድሶ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቆስጠንጢኖስ ባሠራው በኤሊዎና ቤተ ክርስቲያን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መብራት ያበራሉ፡፡ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ደግሞ ወደ ጌቴ ሴማኒ ይጓዛሉ፡፡ በዚያም እስከ ንጋት ቆይተው የዓርብ ማለዳውን ወንጌል ለማንበብ ወደ ጎልጎታ ይመለሳሉ፡፡
ዓርብ ማለዳ ሁሉም መስቀሉን (በኢየሩሳሌም የነበረውን የጌታን መስቀል ነው) ቤተ ክርስቲያን አልባሳት ያስጌጡታል፡፡ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በጎልጎታ በተሰቀለበት ላይ ሁሉም ተሰብስቦ ጸሎት ያደርሳል፣ ያለቅሳል፣ ያዝናል፡፡ በሠርክ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ወደ ስቅለቱ ቦታ በመጓዝ በዚያ ስለ ስቅለቱ እና መቃብሩ የሚገልጠው ወንጌል ይነበባል፡፡ ቅዳሜ ዕለት በየቤተ ክርስቲያኑ መብራት ይበራል፡፡»
ሰሙነ ሕማማትን ልዩ በሆነ ሁኔታ የማክበሩ ሥርዓት ከኢየሩሳሌም በተሳላሚዎች አማካይነት ወደ ልዩ ልዩ ሀገሮች መግባቱ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አበው ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ዘመን አንሥቶ ወደ ኢየሩሳሌም የመጓዝ ሥርዓት ነበራቸውና ይህንን ሥርዓት ቀድመው ሳይወስዱት አይቀሩም፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዚህ ሰሙን የሚሆን ሥርዓት መሥራቱን ስናይም ይበልጥ ያጠናክርልናል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ አሁን በምናየው መልኩ የሰሙነ ሕማማት ምንባባትን ያዘጋጁት የገዳመ መቃርስ መነኮሳት መሆናቸውን ግብረ ሕማማት ይገልጥልናል፡፡ በእነዚህ የገዳመ መቃርስ አባቶች በመታገዝ የእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ገብርኤል 2 (1131-1145) (የኛ ግብረ ሕማማት "ጸሐፊ የነበረው የታሪክ ልጅ አባታችን አባ ቅብርያል" ይለዋል፡፡ ኢብን ቱርያክ የሚለውን ተርጉሞ ሳይሆን አይቀርም፡፡) በእርሱ አስተባባሪነት ሊቃውንቱ ለየቀኑ እና ለየሰዓቱ የሚሆኑትን ምንባባት ከብሉይ እና ከሐዲስ እያውጣጡ አዘጋጇቸው፡፡
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ደግሞ የብሕንሳው ጳጳስ አቡነ ቡትሮስ ምንባባቱን ለየሰዓታቱ በተመጣጣኝ ሁኔታ በማካፈል ሁሉም ቀናት ተመጣኝ የሆኑ ሁሉም ዓይነት ምንባባት እንዲኖሯቸው አድርገዋል፡፡ ግብረ ሕማማታችንም «ከኦሪት እና ከነቢያት፣ ከነዌ ልጅ ከኢያሱ፣ ከንጉሥ ሰሎሞን መጽሐፍ ወስዶ ሁላቸው ትክክል እስከሆኑ ድረስ በየሰዓቱ ሁሉ የሚገባውን አደረገ፡፡ አባቶች ከተናገሩት ሁለት ሁለት ተግሣፅ እና ምክር አንዱ በነግህ አንዱም በማታ እንዲነበብ አደረገ» ይላል፡፡
ግብረ ሕማማት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የተተረጎመበትን ራሱ ግብረ ሕማማት ይነግረናል፡፡ በመጽሐፉ መጨረሻ በሰላማ መተርጉም ጊዜ (1340 ( 1380) ገብቶ መተርጎሙን ያሳያል፡፡ በግብረ ሕማማቱ ያለው ምንባብ አንዳንድ ጊዜ ከግብፁ ግብረ ሕማማት ይበልጣል፡፡ በግብፁ ግብረ ሕማማት የሌሉት ተአምረ ማርያም እና ተአምረ ኢየሱስም ተካተተዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ሊቃውንት እጅ በትርጉሙ እና በዝግጅቱ ሥራ ላይ መኖሩን ያመለክተናል፡፡
በግብረ ሕማማት ውስጥ የሚገኙ ባዕድ ቃላት
በግብረ ሕማማት ውስጥ ወደ ግእዝም ሆነ በኋላ ወደ አማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የዕብራይስጥ፣ የቅብጥ እና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡
ኪርያላይሶን
ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ «ኪርዬ ኤሌይሶን» ነው፡፡ «ኪርያ» ማለት «እግዝእትነ» ማለት ሲሆን «ኪርዬ» ማለት ደግሞ «እግዚኦ» ማለት ነው፡፡ ሲጠራም «ኪርዬ ኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡ ትርጉሙም «አቤቱ ማረን» ማለት ነው፡፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ይኼውም ኪርዬ ከሚለው «» ኤላይሶን ከሚለው ደግሞ «» በመሳሳባቸው በአማርኛ «» ፈጥረው ነው፡፡
ናይናን
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ፣ ማረን» ማለት ነው፡፡
እብኖዲ
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲ ናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው
ታኦስ
የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «ጌታ፣ አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡
ማስያስ
የዕብራይስጥ ቃል ሲሆነ ትርጉሙ «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው
ትስቡጣ
«ዴስፓታ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው
አምነስቲቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ
Em-nees the-tee mo-ki-riey enti vasilia so
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ- አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ» ማለት ነው፡፡
አምንስቲቲ መዓግያ አንቲ ፋሲልያሱ
Em-nees the-tee  mo-a-geh-e enti vasilia so
የቅብጥ ቃል ሲሆን «ተዘከረነ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ - ቅዱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው
አምንስቲቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ
Em-nees the-tee mo-zess-pota enti vasilia so
የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ- የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡
ሥርዓተ ሕማማት
በሐዋርያት ቀኖና እንዲህ ይላል «ይልቁንም በእነዚህ በስድስቱ ቀኖች መጾም የሚችል ቢኖር ሁለት ሁለት ቀን ይጹም፡፡ የማይችል ግን አንድ አንድ ቀን ይጹም፡፡ ሌሎችን ቀኖች እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይጹሙ፤ እችላለሁ የሚል ግን ፀሐይ እስኪገባ ይጹም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስባችሁ መጻሕፍተ ኦሪትን እና መጻሕፍተ ነቢያትን፣ የዳዊትንም መዝሙር እያነበባችሁ በምስጋና በጸሎት ዶሮ እስከሚጮኽ ድረስ የሌሊቱን ሰዓት ጠብቁ፡፡
አንድ ምእመን የታመመ ቢሆን ወይም ክርስቲያን በሌለበት አገር ሆኖ ሳያውቅ የሕማማት ሰሞን ቢያልፍበት ወይንም በደዌ ውስጥ ሆኖ ቢቀርበት ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ሰውነቱን በማድከምም ደስታን ያድርግ፡፡ ባለመፍራት እንዳይጠፋ ውስጣዊ ሰውነቱን ይመርምር፡፡
ጾምን ከመፍታታቸው በፊት ገላቸውን ይታጠቡ፤ ሁሉም መብራት የሚያበሩ ይሁኑ፡፡
የቻለ ዓርብ እና ቅዳሜ ሁለት ቀን ይጹም፤ ሁለት ቀን መጾም የማይችል በሽተኛ ቢሆን ግን ቀዳም ሥዑርን ይጹም፡፡ የኀዘን ቀን ስለሆነች፡፡ እንጀራ እና ጨውም አይቅመስ፡፡»
© ይኽ ጽሑፍ በቀጥታ ከዳንኤል እይታዎች ድረገጽ (http://www.danielkibret.com/2012/04/v-behaviorurldefaultvmlo.html) የተወሰደ ነው!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount