Tuesday, March 10, 2015

ኹለት መንፈሳውያን መጻሕፍት ተመረቁ



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ረቡዕ 02 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- “ሰማዕትነት አያምልጣችሁ” እና “ነጽሮተ ሀገር” በሚል ርእስ የተዘጋጁ ኹለት መንፈሳውያን መጻሕፍት የካቲት 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው አበው ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል እና የመቅረዝ ዘተዋሕዶ ድረ ገጽ አንባብያን በአጠቃላይ ከ400 በላይ ታዳምያን በተገኙበት ደማቅ መርሐ ግብር ተመረቁ፡፡ “ሰማዕትነት አያምልጣችሁ” የሚል ርእስ የተሰጠው አንደኛው መጽሐፍ በመቅረዝ ዘተዋሕዶ ድረ ገጽ ዋና አዘጋጅ በገ/እግዚአብሔር ኪደ የተተረጐመ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥራ ሲኾን ኹለተኛው መጽሐፍ ደግሞ በመምህር ዘሪኹን መንግሥቱ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ በጸሎት የተከፈተ ሲኾን ዘማሪት ጽጌ ወቅቱን የተመለከተ ያሬዳዊ መዝሙር አቀረበች፡፡

አንደኛው መጽሐፍ
ቅድሚያ የቀረበው ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ ነበር፡፡ የመጽሐፍ ተርጓሚም መጽሐፉ የተዘጋጀበትን ምክንያትና ለምን ሰማዕትነት አያምልጣችሁ ብሎ ርእስ እንደሰጠው ማብራርያ ሰጠ፡፡
ከዚኽ በኋላ የዕለቱን መርሐ ግብር ሰፊውን ሽፋንና ድምቀት የሰጠው የመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍና ዳሰሳ ነበር፡፡ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ያቀረቡት ጥናትና ዳሰሳ እጅግ ጠቃሚ ከመኾኑ የተነሣም “እንደወረደ” እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የመጽሐፍ ግምገማ
ርዕስ፡-ሰማዕትነት አያምልጣችኊ እና ሌሎች
ትርጉም፡- በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
የመጽሐፉ ዳሰሳ አቅራቢ፡- መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (Phd candidate)
ቀን፡- የካቲት 28/2007 ዓ.ም.
ቦታ፡- ገነተ ጽጌ ቅ.ጊዮርጊስ ቤ/ክ.

የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሕይወቱና ሥራው
·        “ለዘያነብብ ቅድመ ይዝክር ስሞ ለበዓለ መጽሐፍ ወእምዝ ያንብብ ወይምሐር”
·        በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ታላቅ ሊቅ ነበር (349-407 ዓ.ም)
·        ከትምህርቱ ታላቅነት የተነሣ አፈ ወርቅ የሚል ሥያሜ ተሰጥቶታል፡፡
·        የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ነበር (ታሪኩ በመጽሐፈ ስንክሳር በተግሣጹ ላይ ተመልከት)፡፡
የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሥራዎቹ
·        እጅግ በርካቶች መጻሕፍትን የጻፈ በመኾኑ እኔ ሊቁን እደ ወርቅ ብዬዋለሁ
·        በአንጾኪያ የተማረ በመኾኑ የቃል በቃል ፍቺና ጥልቅ ስብከቶች በመጻሕፍቱ ውስጥ ይገኛሉ፡- የሃይማኖት ድርሳናትን፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ፤ የሃይማኖት ደብዳቤዎችን ጽፏል፡፡
ከትርጓሜ ሥራው ጥቂቱን ብንመለከት የብሉይና የሐዲሰ ኪዳን ትርጓሜ ሲገኙ፡-
·        67 የትርጓሜ ድርሳናት በኦሪት ዘፍጥረት
·        59 የትርጓሜ ድርሳናት በመዝሙረ ዳዊት
·        የኢሳይያስ ትንቢት ምዕ 1 ሐተታ
·        የመጽሐፈ ኢዮብ የተወሰኑ ክፍሎች
·        የመጽሐፈ ምሳሌ የተወሰኑ ክፍሎች
·        የትንቢተ ኤርምያስና ዳንኤል የትርጓሜ ድርሳናት እና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡
·        90 የትርጓሜ ድርሳናት በማቴዎስ ወንጌል ላይ
·        88 የትርጓሜ ድርሳናት በዮሐንስ ወንጌል ላይ
·        55 የትርጓሜ ድርሳናት በግብረ ሐዋርያት ላይ
·        32 የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ሮሜ ሰዎች
·        44 የትርጓሜ ድርሳናት በ1ቆሮንቶስ ላይ
·        30 የትርጓሜ ድርሳናት በ2ኛ ቆሮንቶስ ላይ
·        24 የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ኤፌሶን ሰዎች
·        15 የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
·        12 የትርጓሜ ድርሳናት ወደ ቆላስይስ ሰዎች
·        11 የስብከት ድርሳናት በ1ኛ ተሰሎንቄ
·        5 የትርጓሜ ድርሳናት በ2ኛ ተሰሎንቄ
·        18 የትርጓሜ ድርሳናት በ1ኛ ጢሞቴዎስ
·        10 የትርጓሜ ድርሳናት በ2ኛ ጢሞቴዎስ ላይ
·        6 የትርጓሜ ድርሳናት ለቲቶ
·        3 የትርጓሜ ድርሳናት ለፊልሞና
·        34 የትርጓሜ ድርሳናት ለዕብራውያን ሰዎች
·        ሌሎች 36 የትርጓሜ ድርሳናት አሉት፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ጽሑፎች በቤተ ክርስቲያናችን
በጥበብና በዕውቀት የተመሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ቅድሳት መጻሕፍትን በጥልቀት በመመርመራቸው ምክንያት በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ ጥበብ መንፈሳዊና ጥበብ ሥጋዊን የያዙትን መጻሕፍት ብራና ዳምጠው፣ ቀለም በጥብጠው፣ ብርዕ ቀርጠው በብዙ ድካም ጽፈውና ተርጉመው ዐልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሊቃውንት የተተረጎሙ የሊቁ ሥራዎች
 . ድርሳን ዘልደት ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ፡- “ዮም ተወልደ ቀዳማዊ ወኮነ በዘዚኣሁ ውእቱ አምላክ ቀዳማዊ…” (ቀዳማዊ አምላክ ዛሬ ተወለደ፤ ጥንቱን ገንዘቡ ባይደለ ባሕርይ ተገኘ፤ ርሱ ቀዳማዊ አምላክ ነው፤ ሰው በመኾኑም ባሕርዩ አልተለወጠም…) ይላል
፪. ድርሳን በእንተ እስጢፋኖስ ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ
፫. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ኤጲፋንያ
፬. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘሳኒታ ጥምቀት
፭. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘሣልስ ጥምቀት በእንተ ቃና ዘገሊላ
፮. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ሕፃናት ዘቀተሎሙ ሄሮድስ
፯. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ብእሲት ዘቀብዐቶ ዕፍረተ
፰. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ስምዖን ዘዖሮ
፱. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ሰንበተ ሆሣዕና
፲. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ትንሣኤሁ
 ፲፩. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘበዓለ ትንሣኤ
፲፪. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ አንስት
፲፫. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ፋሲካ
፲፬. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ካልዕ በእንተ ፋሲካ
፲፭. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ አልዓዛር
፲፮. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ሳምራዊት
፲፯. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ቶማስ
፲፰. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘርክበ ካህናት
፲፱. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘበዓለ ፶
፳. ድርሳነ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ካልዕ በእንተ ቁርባን (ማረኝ ብሎ ይግባ የሚል)
. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ዘገብርኤል ወዘዘካርያስ በገሊላ
. ድርሳን ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ዕርገት
. በሃይማኖተ አበው ላይ የሚገኝ ምዕራፍ ያለው ከተለያዩ ትርሜዎቹ ከዮሐንስ ወንጌል ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ትርሜያቱ የተውጣጡ
. የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ፍሬ ቅዳሴው
፴. በእንተ ዕፀ በለስ ዘረገማ እግዚእ በቢታንያ (በ፻፳ ቁጥር የተከፈለ) “እንዘ ሀሎ ዕራቆ በውስተ ገነት በአይኑ ቆጽል ሰፍዮ ዘተከድነ ወለብሰ እምኔሃ ዐጽፈ…” (አዳም በገነት ዕርቃኑን ኹኖ በየትኛው ቅጠል ነበር መሸፈኛ ሠፍቶ ዕርቃኑን የሸፈነ?ይኽቺ ቅጠል እንዴት እንደደረቀች አየኽን? አዳም የለበሳት ዕርቃኑን የሸፈነባት አይደለችምን? ጌታ ኢየሱስ ወደ ለመለመችው የበለስ ዛፍ መጥቶ አዳም ዕርቃኑን የሸፈባትን ቅጠል በቃሉ አደረቃት፤ አዳምን ድኻ ኹኖ ስለ አገኘው ንጹሕ የኾነ የብርሃንን ልብስ ሰጠው፤ ይኸውም ብርሃን ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ የተሠራ ነው፤ የበለስን ቅጠል አድርቆ የነፍሱን ድኅነትን ሰጠው) ( 50-53)
. ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በእንተ ዐሥሩ ደናግል” (፹ ቁጥር ያለው) “አይ ውእቱ ግምዔ ዘወደያ ውስቴቱ ቅብዐ ዘእንበለ ዳዕሙ ከርሦሙ ለርኁባን ነዳያን እለ ግዱፋን በኀዋኅወ አብያተ ክርስቲያን…” (በውስጡ ዘይት የጨመሩበት ማሰሮ የቱ ነው? በየአብያተ ክርስቲያኑ ደጅ በየዐደባባዩ በየገበያው የወደቁ የተራቡ ድኆች ኾዳቸው ነው እንጂ፤ ለጦም አዳሪዎች ምጽዋትን ባደረጉ ጊዜ በርኅራኄያቸው ዘይትነት መብራታቸውን አበሩ)
፴፪. ወዘተርፈ
በማንና እንዴት ይተርጎሙ????????
መጋቤ ሐዲስ ይኽን አጭር ጥናት ካቀረቡ በኋላ ቀጥለው የሰማዕትነት አያምልጣችሁን መጽሐፍ ዳሰሳ እንደሚከተለው አቅርበዋል፡፡
የመጽሐፉ ዳሰሳ
·        ርዕሱ፡- ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች
·        የገጽ ብዛት 201
·        ለአራት ክፍል የተከፈለ ሲኾን
·        በመዠመሪው ክፍል 8 ስብከቶች
·        በኹለተኛው ክፍል 6 ስብከቶች
·        በሦስተኛው ክፍል 31 ስብከቶች
·        በአራተኛው ክፍል 11 ስብከቶች
በአጠቃላይ 56 ትምህርቶች ተካትተውበታል፡፡
ጸሓፊው መጽሐፉን ያዘጋጀበት ዓላማ
·        2003 ዓ.ም በቅ/ሥ/ም/ኮ ተማሪ ሳለ “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ፤ ጅብን ሲወጉ በአህያ ይጠጉ” እንዲሉ ጥቂቶች በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስም ክሕደትን ሲያስፋፉ “እውነት ይኾን እንዴ” በማለት የሊቁን ሥራዎች ማንበብ እንደዠመረ ገልጦታል፡፡
ወደ ዝርዝሩ ሲገባ
·        በክፍል አንድ ላይ ስምንት ትምህርቶች ያሉ ሲኾን
·        በዐዲስ ዓመት ርዕስ ውስጥ ሊቁ ዐዲሱን ዓመት እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ በቅድስናዊ አከባበር ማክበር ይገባል እንጂ በስካር በዘፈን በኀጢአት ማክበር እንዳይገባ በስፋት ያስተምረናል (ከገጽ 13-16)
·        በምትረተ ዮሐንስ ርዕስ ውስጥ ሊቁ በዘፈን ምክንያት ሄሮድስ የዮሐንስን አንገት እንዳስቆረጠ ዛሬም ዲያብሎስ በዚኽ ግብር ትውልዱን የነፍሱን አንገት እያስቆረጠ እንደኾነ ይተነትናል (ከገጽ 37-38)
·        የትዕቢት መዠመሪያ በሚለው ርዕስ፡- ዲያብሎስ ከክብሩ የተዋረደው በትዕቢቱ እንደወደቀና ትዕቢት ከማመንዘር በላይ የከፋ ስለመኾኑ (ከገጽ 39-40)
·        ውዳሴ ከንቱን የመሻት መዘዝ፡- ውዳሴ ከንቱ የገሃነመ እሳት እናት እንደኾነች ሰዎች ድኻ እየተራበ እነርሱ ግን በውዳሴ ከንቱ በመጠለፋቸው ለሐውልታቸው እንደሚጨነቁ ይጽፋል (ገጽ 41)
·        ልዩ ፍርድ ቤት፡-በሰው ላይ ከመፍረድ ይልቅ በሠራነው ኀጢአት በራስ ላይ መፍረድ እንደሚገባ (ከገጽ 42-43)
·        እኛ ለራሳችን የምን ምክንያቶች ነን፡- እኛው ለራሳችን የልማታችን ኾነ የጥፋታችን ምክንያቶች እንደኾንን በብዙ ጥቅሶች አጅቦ ይገልጻል (ከገጽ 44-45)
·        ታላቅ መኾንን ስትፈልጉ፡- የጌታን ትምህርትና የትሕትና ሥራን በመግለጽ ትሕትናን በጥልቀት ይገልጻል (ከገጽ 46-48)
·        የኅሊና ዳኛ፡- አምላክ በኅሊናችን ውስጥ ትጉ ዳኛ እንዳስቀመጠና፤ ዕንቅልፍ የለሽ ወቃሽ ዳኛ እንደኾነ ምጥ ከያዛት ሴት ጋር አነጻጽሮ ይገልጣል (ከገጽ 49-50)፡፡
ክፍል 2 የያዛቸው ስድስት ስብከቶች
·        እውነተኛ ሐሴት ትፈልጋላችኹን፡- የተፈጠርነው ለመብል ለመጠጥ ብቻ እንዳልኾነ ይልቁኑ ጾምን ማዘውተር እንዲገባን ያስተምራል፡፡
·        ከዚኽ ቀጥሎ አራት ርዕሶችን ዳስሶ በመጨረሻም ውርጃን ያነሣል፡-
·        ውርጃ፡- የሴትን ማሕፀን በምድር ይመስላል፡- በዝሙት ላይ ውርጃን ፈጽሞ ሰውን መግደል ከፍተኛ ነውር እንደኾነ
·        ስካር- ሴተኛ አዳሪ- ዘማዊ-ነፍሰ ገዳይ እንደሚያደርግ ይጽፋል፡፡
ክፍል ሦስት፡- 31 ርዕስ የያዘ ነው
·        8ኛው ርዕስ፡- ሰማዕትነት አያምልጣችኊ
·        የጥንት ሰማእታት ስለምድራዊ ኑርዋቸው ብዙም ባለመጨነቅ ግማሹ ከዓላውያን ነገሥታት ጋር ታገሉ፤ ግማሾቹ ነፍሳቸውን ለማትረፍ በየበረሓው መኼዳቸውን እናቶችም መኖራቸውን ይጠቅሳል፡፡
·        የእኛ ሰማዕትነት፡-
ሀ)እምነትን ካድ ከሚሉ
ለ) ከምቾታችን 
ሐ)ከስግብግብነት
መ)ከእንቅልፍ
ሠ)ከዋዛ ፈዛዛ
ረ)ከስንፍና፣ ከውሸት፣ ከሐሜት ጋር ወዘተርፈ እንደኾነ መጽሐፉ ያብራራል፡፡ ይኽም የሽፋኙ ገጽ ስዕል ላይ ያለውን ያብራራል፡፡

የመጽሐፉ ጠንካራ ጎን
·        ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራችን በደከመበት ፍቅረ ንዋይ፣ ውዳሴ ከንቱ፣ ትዕቢት፣ ሥጋዊ ተድላ ደስታ በዝቶ የነፍስ ደስታዋ በተረሳበት ዘመን የሊቁ ት/ት ስለሚያንጸን
·        ለሰባክያን ማጣቀሻነት ስለሚረዳ
·        በተለይ ወጣቱ ትውልድ ያለበትን ሥጋዊ ጾር ለይቶ የሚያሳይና መፍትሔውን ስለሚጠቁም
·        የፊደሉ መልክኣት በተቻለው መጠን ማስተካከሉ
·        የቅዱሱን ምክር እና እዝናት እንድንረዳው ስላስቻለን
መጽሐፉ ወደ ፊት የሚያስተካክለው
·        በርካቶች ባዶ ገጾች የገጽ ብክነትን ያስከትላሉና ቢታሰብበት
·        የሥርዐተ ነጥቦች ከገጽ ዐልፈው መኼድ
·        መጽሐፉ ዋቢ መጻሕፍት ቢኖረውም ነገር ግን የግርጌ ማስታወሻ ስላልያዘ ይኽ ስብከቱ ከየትኛው መጽሐፉ እንደተወሰደ ምንም አያሳውቅምና ወደ ፊት ይኽ ቢሠራ

ምስጋና
ለወደፊቱ በርካቶች ሥራዎችን እንድትሠራ አምላከ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይርዳኽ፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ 

†††
ኹለተኛው መጽሐፍ
የአንደኛው መጽሐፍ ዳሰሳ በዚኽ መልኩ ካለቀ በኋላ ቀጥሎ የቀረበው “ነጽሮተ ሀገር/ ሀገርን ማየት” በሚል ርእስ በመምህር ዘሪኹን መንግሥቱ የተዘጋጀው የኹለተኛው መጽሐፍ ዳሰሳ ነበር፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ ስለ መጽሐፉ ዝግጅት አቀረቡ፡፡
የመጽሐፉን ዳሰሳ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ቢኾንም ርሱ ሊገኝ ስላልቻለ ዳሰሳውን ያቀረቡት ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ ነበሩ፡፡
ቀሲስ ሰሎሞን አስቀድመው የመጽሐፉን ጠንካራ ጎን ያነሡ ሲኾን፡-
·        ለብዙ ወጣት ጸሐፊያንና ተመራማሪዎች እንደ ምንጭነት ሊያገለግል የሚችል መኾኑ፤
·        መጠቁም /Index/ መያዙ፤
·        ባጭሩ ለማስታወሻነት እሚያገለግል
·        ለተጨማሪ ንባብ የሚያነሳሳ
·        ወጥነት ያለው የመልክአ ፊደላት አጠቃቀም
·        ጸሐፊው ለምንጭነት የተጠቀመባቸው ከጋዜጣ እስከ መጽሐፍ የሀገር ውስጥም የውጭም የግርጌ ማስታወሻ ማስቀመጡ፤
·        ሥዕላት በተገቢው ቦታ መጠቀሙ፤
·        የጽሑፉ ፍሰት ምቹ መኾኑ ግሩም ብለዉታል፡፡
ቀጥለዉም ጸሐፊው ለወደፊቱ ቢስተካክላቸው መልካም ነው ያሏቸውን ነጥቦች አንሥተዋል፡፡ ካነሧቸው ነጥቦች መካከልም፡-
·        በገጽ 188 ላይ “መጽሐፉ (ርቱዐ ሃይማኖት) በ፲ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአገራችን ወደ ግእዝ ቋንቋ እንደተተረጐመ ይታመናል” ተብሎ የተገለጸው መጽሐፉ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የተደሰና በ13ኛው መ.ክ.ዘ. አከባቢ በጣና ቂርቆስ አከባቢ የነበረ በመኾኑ ይኽ ቢስተካከል፤
·        የዐረፍተ ነገር መርዘም፤
·        አልፎ አልፎ የፊደላት ግድፈት ታይተውበታል፤ ይኽ ክፍተት በኹሉም መጻሕፍት ላይ የሚከሰት ችግር ቢኾንም አርትኦት ላይ ጥንቃቄ ቢደረግ፤ በቀጣዩ ኅትመት ላይ ተስተካክሎ ቢወጣ፤ ብለው የተዘጋጁበትን የዳሰሳ ጥናት ቋጭተዋል፡፡


†††
በመጨረሻም በኹለቱም መጻሕፍት ዙርያ ከታዳምያን ለተሰጠው አስተያየትና ጥያቄ የመጻሕፍቱ አዘጋጆችና ዳሰሳ አቅራቢዎች ምላሽ ከሰጡበት በኋላ መርሐ ግብሩ በአባ አሥራተ ማርያም ደስታ በጸሎት ተዘግቷል፡፡
 †††


የተከናወነው መርሐ ግብር በፎቶ፡-

 



4 comments:

  1. dess yemil mergagbir nber ye megabi hadisn tnatawi tshuf edewerede blogu bemagignetem dess bilognal beeerta....

    ReplyDelete
  2. ሰማዕትነት አያምልጣችሁን መጽሐፍ የምታገኙባቸው ቦታዎች፦
    ✔ 5 ኪሎ ቅድስተ ማርያም ዙርያ ባሉት ኹሉም መጻሕፍት ቤቶች
    ✔ ተዋሕዶ መጻሕፍት ቤት (መርካቶ)
    ✔ አጋፔ መዝሙር ቤት (መርካቶ)
    ✔ አይናለም መጻሕፍት ቤት (ብሔራዊ ቴአትር አከባቢ)
    ✔ ቅዱስ ራጉኤል ሰ/ት/ቤት
    ✔ ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ሰ/ት/ቤት
    ✔ ፒያሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ዙርያ ባሉት መጻሕፍት ቤቶች

    ReplyDelete
  3. የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሀፍት ገና ምንም ያልተተረጎሙ በርካታ ከመሆናቸው አኳያ ብዙ መስራት የሚጠበቅብን መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባ ሲሆን እንደጅምር ስራ ግን ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount