በዲ/ን ብርሃኑ
አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ማግሰኞ መጋቢት
15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ
የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባብያን እንዴት አላችኁ? ይኽ ዛሬ የምናቀርብላችኁ ጽሑፍ ዲ/ን ብርሃኑ
አድማስ ማኅበረ ቅዱሳን መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በኦሎንኮሚ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ባዘጋጀው 8ኛው
የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ላይ የሰበከው ስብከት ነው፡፡ ስብከቱ 44 ደቂቃን የፈጀ በመኾኑ ወደ ጽሑፍ ሲቀየር ትንሽ ረዘም ይላል፡፡
ነገር ግን የሐሳቡ ፍሰት እንዳይቆራረጥ ብዬ በክፍል በክፍል ላቀርበው አልመረጥኩም፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ በስብከቱ ውስጥ የሚደጋገሙ
ዐረፍተ ነገሮችንና በጉባኤው ላለ ሰው ካልኾነ በቀር ለአንባቢ የማይረዱ ጥቃቅን ሐሳቦችን ከማውጣት ውጪ ምንም የቀነስኩትም የጨመርኩትም
ነገር የለም፡፡ ስለ ኹሉም መልካም ንባብ ይኹንላችኁ!!!
መነሻ የምናደርገው ኃይለ ቃል የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ
የፊልጵስዮስ መልእክት ምዕራፍ 4፡15 ላይ ያለውን ነው፡፡ ቃሉ እንዲኽ ይላል፡- “ኾኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመዠመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፡፡ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ኹለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ነገር ግን ኹሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚኾነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ኹሉ ይሞላባችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይኹን፤ አሜን።”
ፊልጰስዮስ
ከተማ በጥንቱ ሰሜናዊ ግሪክ፣ አኹን አውሮጳ ውስጥ ራሱን ችሎ መቄዶንያ እየተባለ በምናውቀው ሀገር የምትገኝ ጥንታዊት የወረዳ
ከተማ ናት፡፡ ሐዋርያት ከእስያ ወደ አውሮጳ ገብተው መዠመሪያ የወንጌልን ትምህርት ያስተማሩባት ከተማ ይኽቺ ከተማ ናት፡፡ ያስተማረውም
ራሱ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ታሪኩን የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 ላይ በዝርዝር እናገኟለን፡፡ በዚኽች ከተማ ቅዱስ
ጳውሎስና ቅዱስ ሲላስ ሲገቡ ሰው የሚያገኙበትን ቦታ ሲያስቡ የሔዱት ሴቶች ውኃ ወደሚቀዱበት ቦታ ነበር፡፡ በዚያ ውኃ
የሚቀዱትን ሴቶች ሲያስተምሩ ውኃ ከሚቀዱት የአንዷን ሴት ልብ እግዚአብሔር ከፈተው፡፡ ይኽቺ ሴት ቀይ የሐር ፈትል እየሸጠች
ትተዳደር የነበረ ልድያ የምትባል ሴት ናት፡፡ ርሷ ወደ ቤቷ ወሰደቻቸው፤ ማረፊያ አገኙ፤ ወንጌልን አስተማሩ፡፡ ከዚኽ በኋላ
ብዙ ገድልና ተአምራት ፈጽመዋል፤ ታስረዋል፡፡
ከዚያ ቀጥሎ የሔዱት ወደ ተሰሎንቄ ነው፡፡ ተሰሎንቄ
የግሪክ ኹለተኛዋ ታላቅ ከተማ ናት፡፡ አኹንም ሰሜናዊ ግሪክ ነው የምትገኘው፡፡ ከዚያ በኋላ የሔዱት ወደ አቴና ነው፤ ከአቴናም
ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ቆሮንቶስ፤ ከዚያም ወደ ሮም፡፡ እንዲኽ እያሉ ነው የሰበኩት፡፡
ታድያ በጣም አስገራሚው ነገር እነዚኽ የፊልጵስዮስ
ሰዎች ወንጌልን ከተማሩ በኋላ ሐዋርያው ራሱ ደጋግሞ እንደሚመሰክርላቸው የተማሩትን ወንጌል የተገበሩ፣ ራሳቸው ሔደው ባያስተምሩ
እንኳን የሚያስተምሩትን እንዲያስተምሩ የሚያደርጉ አስተዋይ፣ ጠንካራ፣ አርአያና ምሳሌ የሚኾኑ እንደ መቄዶንያ ምእመናን ያሉ
ምእመናን ናቸው፡፡ እስከ አኹን ድረስ በመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት የተሰጠላቸው ይኼ ነው፡፡ ሌሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ ግን እነርሱን የሚያክል የለም፡፡
ኢየሩሳሌም (እስራኤል) ያሉ ድኾችን ምግባቸውን
እንኳን የሚችሉት እነዚኽ የመቄዶንያ ሰዎች፣ የፊልጵስዮስ ሰዎች ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይኽቺን መልእክት የላከላቸው ይኽን የአውሮጳውን
ተልእኮ ጨርሶ ኢየሩሳሌም ሲገባ ነው፡፡ እዚያ ገብቶ አይሁድ በቅናት ይዘዉት ከሰዉት ታስሮ ነበር፡፡ ብዙ ክርክር ከተደረገ
በኋላ ይግባኝ ብሎ (ያን ጊዜ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ግዛቱ የሮማ ግዛት ስለነበረ) ወደ ሮማ መናገሻ ከተማ ወደ ታላቂቱ ሮም
ተላከ፡፡
ሲላክም አኹን በሜድትራንያን ባሕር መካከል የምትገኘውን
ማልታ (በመጽሐፍ ቅዱስ መላጥያ) የምትባለውን ሀገር ሰብኮ ያለፈው ታስሮ በመንገድ ላይ ሳለ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚያ ሲደርስ
መርከቡ ተሰበረ፤ ማዕበል ብዙ አስጨነቃቸው፡፡ ከዚያ ወጡ፡፡ ሦስት ወር በደሴቲቱ ተቀመጡ፡፡ እዚያ አንዷን ደሴት ላይ
ሲያስተምር ሌሎች ደሴቶች ላይ ያሉትን ሰዎች በተአምራት እግዚአብሔር ቃሉን እንዲሰሙ አድርጎ ማልታን በሙሉ በዚያ የእስር ወቅት
ነው የሰበከው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስን አስረዉታል፤ እግዚአብሔር ግን ቃሉ ሌሎች ደሴቶች ላይ እንዲደርስ እንዲሰማ
እያደረገ ክርስቲያን እንዲኾኑ አደረጋቸው፡፡
ከዚኽ በኋላ ሮም ገባ፡፡ ሮም ሲደርስም የቁም እስር
ኾኖ ኹለት ዓመት ተቀምጧል፡፡ እስረኛም ኾኖ ግን የቄሳርን ቤተ ሰቦች አሳምኖ ቅዱሳን አድርጓቸዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በዚኽ ወቅት ታስሮ ሮም በተቀመጠበት
ጊዜ መታሰሩን ሰሙና እነዚኽ የፊልጵስዮስ ሰዎች ገንዘብ አዋጥተው በጠያቂ፣ አፍሮዲጡ በሚባል ደቀ መዝሙር ሮም ድረስ ላኩለት፡፡
የተባረኩ ክርስቲያኖች! ስለ አገልግሎት የሚያስቡ፣ የሚቀኑ፣ የሚጨነቁ፣ የሚቆረቆሩ፣ በመከራው እንኳን እንካፈል ያሉ
ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ለዚኽም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “ኾኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ” የሚላቸው፡፡ እነዚኽ ክርስቲያኖች
ደጋግመው ቅዱስ ጳውሎስን ያስቡታል፡፡ እኛስ እናስባለን? እናስባለን ወይ? ዛሬ ዕለቱ ገብር ኄር ነው፤ ታማኝ አገልጋይ ማለት
ነው፡፡ እግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይና የሚታመን አማኝ ለመኾን ያብቃን፡፡
እነዚኽ የፊልጵስዮስ ሰዎች የገባቸው ሰዎች ናቸው፡፡ የምንማርበት
መሠረታዊ ዓላማ ሥራ መሥራት ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25ን ስናነብ መክሊት ስለተሰጣቸው ሰዎች እናነባለን፡፡ ለአንዱ
አምስት፣ ለአንዱ ኹለት፣ ለአንዱ አንድ መክሊት ተሰጣቸው ይላል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ላይ ይኼን ታሪክ ጌታ በሌላ
መንገድና ምሳ ተናግሮት እናገኟለን፡፡ በሉቃስ ወንጌል ለሦስቱም ዐሥር ዐሥር መክሊት ሰጣቸው ይላል፡፡
አምስት መክሊት የተባሉት አምስቱ የስሜት ሕዋሳት
ናቸው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ዐሥር መባሉም ያው ነው፡፡ ምክንያቱም አምስት የውስጥ አምስት የውጪ ሕዋሳት አሉንና፡፡ አኹን ይኼ
መክሊት ያልተሰጠው ሰው አለ ወይ? ዐሥር ሕዋሳት ያልተሰጠው ሰው የለም፡፡ ከርእሳችን እንዳነሣነው እግዚአብሔር ሰጥቶናል፤
ደግሞ ይቀበለናል፡፡ እኛም እንሰጣለን፤ እንቀበልማለን፡፡
ችግሩ እዚኽ ጋር ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ለአንድ
ጉዳይ ገንዘብ እንድናዋጣ በተፈለገ ጊዜ በሚያባብል መንገድ ስለሚቀርብ የእናንተን ምእመናን ኅሊና ይሻክራል፡፡ አላስፈላጊ የኾኑ
ቃላትን እንጠቀማለን፡፡ እናታልላለን፡፡ እንዋሻለን፡፡ እናባብላለን፡፡ እንደዚኽ ግን መኾን የለበትም፡፡
ከቤተ ክርስቲያን ዐበይት ምሥጢራት አንዱና ዋናው
መስጠት ነው፡፡ በካቶሊኮች የትምህርት ሥርዓት ተጽዕኖ ከድንጋጌ የተገኙ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሰባት እንደኾኑ እንዘረዝራለን
እንጂ ስምንተኛውና ዋናው መስጠት ነው፡፡ ትልቁ ምሥጢር መስጠት ነው፡፡ ለዚኽም ነው ቅዱስ ጳውሎስ የፊልጰስዮስ ሰዎችን ደጋግሞ
የሚያመሰግናቸው፡፡
በጣም የሚያስደንቀው ነገር (ቅዱስ ጳውሎስ) የእኛ
ዘመን ሰው ይመስል በዚያ ዘመን ከፊልጵስዮስ ሰዎች ወረድ ብሎ ግሪክ በተለይም ቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ስለ መስጠት ሲነግራቸው
ይኮሰኩሳቸዋል፤ ይጨንቃቸዋል፡፡ ሐዋርያት ወደነርሱ የሚመላለሱት ራሱ ገንዘባቸውን ፈልገው ይመስላቸው ነበር፡፡ አንዳንድ ሰው
እንደዚኽ ይጨነቃል፡፡ ነገር ግን በእንደዚኽ ዓይነት ነገር የሚጨነቅ ሰው አይኑር፡፡ ግድ የለም አታስቡ፡፡ ነገሩ ይግባን፡፡ መስጠትም
አለመስጠትም ኹሌም ወሳኞቹ እኛው ነን፡፡
በጣም የሚገርመው አንዳንድ የግሪክ ሰዎች ሐዋርያት
የነርሱን ፍላጎት እንዲያሟሉላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ለምሳሌ ከቆሮንቶስ ሰዎች ሚስት እንዲጨመራቸው የሚፈልጉ ወንዶች ነበሩ፡፡ ሀብት
ስላላቸው “ገንዘብ እንስጥና የፈለግነውን ሚስት እንጨምር” የሚሉ ነበሩ፡፡ በሌላ አገላለጽ ወንጌልን በነርሱ ሐሳብ ሊገዟት፣
ሊያጣምሟት፣ ተጽዕኖ ሊፈጥሩባት ይፈልጉ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች! ስንሰጥ የኛን ሐሳብ መፈጸም መፈለግ የለብንም፡፡ መስጠት
ያለብን መስጠት ከምሥጢራት አንዱ ስለኾነ ነው፤ የድኅነት በር ስለኾነ ነው፤ እውነት ስለኾነ ነው፡፡ መስጠት ያለብን ስሌቱን
አስበን ነው፡፡ ታድያ ምንድነው ስሌታችን? ምንድነው የምንፈልገው?
በዚኽም ምክንያት ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
እነዚኽን የፊልጵስዮስ ሰዎችን ደጋግሞ ደጋግሞ የሚያመሰግናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ቸገረኝ አላለም፡፡ ከላይ እንደሰማነው ግን “ወንጌል በመዠመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ” ይላቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከሌላ ቤተ ክርስቲያን
አይቀበልም፡፡ በአገልግሎቱ ኹሉ የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን የሚቀበለው ከእነዚኽ ከገባቸው፣ ከተረዱት
የፊልጵስዮስ ሰዎች ብቻ ነው፡፡ ካልገባቸው አይቀበልም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መስጠት ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ያስተማረበት፣
ብዙ ጥቅሶችም ያሉባቸው ኹለቱም የቆሮንቶስ መልእክታት ናቸው፡፡ ከእነዚኽ የግሪክ ሰዎች ግን ለራሱ ተቀብሎ አያውቅም፡፡ እንዲጠቀሙ
ይፈልጋል፤ እንዲጠቀሙ ሲፈልግ ግን “እኛ እየሰጠነው ነው እንዲኽ የሚያደርገው” ብለው እንዳይመኩ እንዲሰጡት አይፈልግም፡፡
ለራሱ ሲኾን ይከለክላቸዋል፡፡ ለዚኽም ነው ሲቸግረው ድንኳን ሰፍቶ እየሸጠ ያስተምር የነበረው፡፡ እስኪ ራሱ ያስረዳን፡- “ወይስ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ስለ ሰበክሁላችሁ፥ እናንተ ከፍ እንድትሉ ራሴን እያዋረድሁ ኃጢአት አድርጌ ይኾንን? እናንተን ለማገልገል ደመወዝ እየተቀበልሁ ሌሎችን አብያተ ክርስቲያናት ዘረፍሁ። ከእናንተም ጋር ሳለኁ በጎደለኝ ጊዜ፥ በማንም አልከበድሁበትም፤ ከመቄዶንያ የመጡት ወንድሞች የጎደለኝን በሙሉ ሰጥተዋልና፤ በነገርም ኹሉ እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅሁ እጠነቀቅማለሁ። የክርስቶስ እውነት በእኔ እንዳለ፥ ይኽ ትምክሕት በእኔ ዘንድ በአካይያ ሀገር አይከለከልም። ስለ ምን? ስለማልወዳችሁ ነውን? እግዚአብሔር ያውቃል” /2ኛ
ቆሮ.11፡7-11/።
እንግዲኽ ተመልከቱ! “እናንተን ለማገልገል ከሌሎች
ዘረፍሁ” ፤ “እንዳልከብድባችሁ ተጠነቀቅኩ፤ እጠነቀቅማለሁ” ነው የሚላቸው፡፡ “ስለማልወዳችሁ ነወይ?” ይላቸውና “እግዚአብሔር ያውቃል” ብሎ መልሱን ይነግራቸዋል፡፡ ይወዳቸዋል፤
ግን ደግሞ ይመካሉ፡፡ ስለ ሰጡ ይታበያሉ፡፡ አጋንነው ይናገራሉ፡፡ ስለ ሰጡ ኃጢአት እንዲፈቀድላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ስለ ሰጡ
የነርሱ ሐሳብ ብቻ እንዲፈጸም ይፈልጋሉ፡፡ ስለ ሰጠ ብቻ የፈለገውን እንዲፈጸምለት ከሚፈልግ ሰው ቀድሞ መቀበል በጣም አስቸጋሪ
ነው፡፡ ከእንዲኽ ያለ ሐሳብ እግዚአብሔር አምላካችን ይጠብቀን፡፡
ክርስቲያኖች ተመልከቱ! የመቄዶንያ ሰዎችን
ይቀበላቸዋል፡፡ የፊልጵስዮስ ሰዎችን ይቀበላቸዋል፡፡ ደጋግሞ ይቀበላቸዋል፡፡ ለምን? ስለገባቸው!!! አኹን ጥያቄ እንጠይቅ! ዛሬ
የመስጠትና የመቀበል ስሌታችን ምንድነው? ገብቶናል ወይ? ለምንድነው የምንሰጠው? እንዴት ነው የምንሰጠው? ምንድነው ማድረግ
ያለብን? ምንድነው የምናሰላው?
የአብነት ትምህርት ቤት ስንሠራ ምንድነው የምናሰላው?
ገዳማትን ስንረዳ ምንድነው የምናሰላው? ለስብከተ ወንጌል ተልእኮ ስንረዳ ምንድነው የምናሰላው? ምን እንዲኾን ነው
የምንፈልገው?
ማኅበረ ቅዱሳን እነዚኽ ፕሮጀክቶች ቢሠሩ ምን ሊመጣ
እንደሚችል፥ ባይሠሩ ምን ሊከሰት እንደሚችልና ቅድም የማኅበሩ
ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ ቅንጭብ አድርጎ ነግሮናል፡፡ ግንኮ መነገር አልነበረበትም፡፡ ለምን? ዐሥር ሕዋሳት ተሰጥቶናላ!
በእውነት ዐይናችን አያይም ወይ? አብያተ ክርስቲያናት ሲዘጉ
አናይም? ሊቃውንቱ ስንቸገር አናይም? ዦሮአችን አያደምጥም? የትምህርቱ መዓዛ ሲለወጥ አናደምጥም? እንዴ! በእኛው ቤተ
ክርስቲያን፣ በእኛው ዓውደ ምሕረት የሌሎቹ ሲዘፈንኮ እየሰማን ነው፡፡ ታድያ ምንድነው ስሌታችን? ሌሎችኮ ያሰላሉ፡፡ እኛስ
ምንድነው የምናሰላው?
ለመኾኑ እናስባለን? እናቅዳለንን? የዛሬ ዐሥር ዓመት ምን ኾኖ ነው ማየት የምንፈልገው? የዛሬ አምስት ዓመት ምን ኾኖ
ነው ማየት የምንፈልገው? የቅዱስ ጳውሎስ ጥያቄ፡- “ስሌታችሁ ምንድነው?” የሚል ነው፡፡
በአጭሩም ቢኾን ስሌታቸው እንደ ወንጌል፣ ስሌታቸው
እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የነበረ፣ አስበውና አቅደው ይሠሩ የነበሩ ምስጉን፣ ባለ አምስቶቹን፣ ባለ ዐሥሮቹን ማስታወስ እፈልጋለኁ፡፡
ከርሱ በፊት ግን በባለ አንዱ መክሊት ላይ አንዲት ነጥብ ብቻ ላንሣ፡፡
ባለ አንዱ መሬት ወስዶ ምን አደረጋት ነው የሚለው?
ቀበራት፡፡ እግዚአብሔርስ ሰውን ከምን አበጀው ነው የሚለው? ከመሬት አፈር፡፡ ስለዚኽ መሬት ውስጥ ቆፍሮ ቀበረው ማለት እንዲኹ
በመሬት መቅበር እንዳይመስላችኁ፡፡ ለመሬታዊ፣ ለራሱ ፍላጎት በማድረግ ሰውነቱ ውስጥ ቀበረው ማለት ነውኮ፡፡ አንዳንዶቻችን የተሰጠንን
ስሜት፣ የተሰጠንን ዕውቀት፣ የተማርነውን ትምህርት፣ የተሰበክነውን ስብከት በሙሉ ለእኛው ጥቅም ብቻ መጠቀም እንፈልጋለን፡፡
ለእኛው ዕድገት፣ የተሻለ ገቢ ለማምጣት እንፈልጋለን፡፡ መክሊታችንን ሰውነታችን ውስጥ ብቻ እንቀብሯለን፡፡ ለእኛው ዕድገት፤
ለእኛው ኑሮ፤ ለእኛው ቤት ብቻ እንዲውል እንፈልጋለን፡፡ ይኼ ነው መሬት ውስጥ መቅበር ማለት እንግዲኽ! ለራስ ፍላጎትና ጥቅም
ብቻ ማዋል!
መክሊታችንን ለማን ጥቅም ነው የምናውለው? እግዚአብሔርኮ
ለሰውነታችን ጥቅም የማያዝን አምላክ አይደለም፡፡ ሰውነታችን እንዲጎዳ የሚፈልግ አምላክ አይደለም፡፡ ኑሯችን እንዲጎሰቁል፣
ከሰው እንድናንስ የሚፈልግ አምላክ አይደለም፡፡ ሐሳባችን ግን ለሰውነታችን እንዲውል አይፈልግም፡፡ ሐሳባችን ለሰጪው፣ ለባለቤቱ፣
ለባለ መክሊቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲኾን ይፈልጋል፡፡
አኹን አኹን ቅዱሱን አገልግሎት፣ ለነፍሳት ድኅነት የሚፈጸመው
ሳይቀር ለኑሯችን መደጎምያ ብቻ አልመን የምንሠራ መሬት ቀባሪዎች አለን፡፡ ስለ ሰበኩ ብቻ መሬት ቀባሪዎች እንዳልኾኑ የሚያስቡ
ሰዎች አሉ፡፡
አገልግሎቴ ለሰውነቴ ጥቅም ካዋልኩት መቅበር ነው፡፡
ምክንያቱም የምሰብከው ለሕዝቡ ድኅነት ብዬ አይደለምና፡፡ አገልግሎቴ ለነፍስ ድኅነት እስካላደረግኩት ድረስ የምዘምረው፣
የምሰብከው፣ የምቀድሰው፣ የማገለግለው፣ የምወጣው የምወርደው የራሴን ስም፣ የራሴን ዝና፣ የራሴን ኑሮ ለማሸነፍ ከኾነ ከዚኽ
በላይ መሬት ቆፍሮ መቅበር የለም፤ እንደዉም አደገኛው መቅበር ይኸው ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያን ዓላማ ስም፣ ወንጌልን በማስፋፋት
ስም የራስ ጥቅምን ማስከበር ከኾነ ሩቅ ቆፍሮ መቅበር ማለት ይኼ ነው፡፡ ከእንዲኽ ያለው ጉድጓድ እግዚአብሔር አገልግሎታችንን
ይጠብቀው፡፡
ክርስቲያኖች! በመጽሐፍ ቅዱስ ገብር ኄር የሚባሉ፣
ታማኞች፣ ዐይናቸው ያየ፣ ዦሮአቸው የሰማ፣ እጃቸው የዳሰሰ፣ አፍንጫቸው ያሸተተ፣ አፋቸው ቃለ እግዚአብሔርን የበላ፣ ያላመጠ፣
ያደቀቀ፣ የተረጐመ፣ “ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወለሊተ” የተባለውን የፈጸሙ፣ በመዓልት በሌሊት ቃለ እግዚአብሔርን ያነበበ፣
በአጠቃላይ በአምስቱ ሕዋሳታቸው የሠሩ፣ በአምስቱ መክሊቶቻቸው የወጡ የወረዱ፣ ያተረፉ፣ የመስጠት ሕዋሳትን በመቀበል በነርሱ
የመስጠት ትርጕም ምሥጢር የገባቸው ብዙ ቅዱሳን አሉ፡፡ ኹለት ሰዎችን ብቻ አነሣለኁ፡፡
የመዠመሪያው
ብሩኩን፣ ንጹሑን ዮሴፍን ነው /ዘፍ.42/፡፡
እግዚአብሔር ሰባት ዓመት ጽኑ ረሀብ እንደሚመጣ
በራዕይ፣ በሕልም ለፈርዖን ነገረው፡፡ ሕልሙን መተርጐም ለዮሴፍ ሰጠው፡፡ ዮሴፍ ሕልሙ ከተረጐመ በኋላ ግን ምን ላድርግ የሚል
ጥያቄ ከፈርዖን ቀረበለት፡፡ ከሰባት ዓመት የጥጋብ ዘመን በኋላ ሰባት ዓመት የረሀብ ዘመን የሚመጣ ከኾነ ምን ላድርግ ብሎ
ፈርዖን ጠየቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጥጋብ ላይ ነበረች፡፡ ቅኔ ለመስጠት ፉክክር ነው፡፡
ግሥ ለማውረድ ፉክክር ነው፡፡ ጥጋብ ላይ ነበርን፡፡ ለስብከቱ፣ ለትርጓሜው እንደ አራተኛው ክፍለ ዘመን የቁስጥንጥንያ ሊቃውንት
እያማረጥን እንጠቀም ነበር፡፡ ጥያቄ ከማጣት የተነሣ “በአንድ መርፌ ጫፍ ስንት መልአክ ይቆማል?” የሚል ክርክር ኹላ ይከራከሩ
ነበር፡፡ ይኼ ጉንጭ ማልፋት ይባላል፡፡ ለምንም የማይኾን (የማይጠቅም) ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የጥጋብ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች!
ፈርዖን እንዳየው ሕልም እጅግ አስፈሪ ዘመን ከፊት ለፊታችን አለ፡፡ የረሀብ ዘመን ከፊት ለፊታችን አለ፡፡ የምን ረሀብ? የቃለ
እግዚአብሔር የረሀብ ዘመን፣ የሊቃውንት ረሀብ ዘመን፣ የካህናት ረሀብ ዘመን ሩቅ አይደለም፡፡ ከደጃችን ላይ ነው ያለው፡፡ ምኑን
ነው የምናወራው? ጉቦውን ነው የምናወራው፡፡ ደጅ ጥናቱን ነው የምናወራው፡፡ አይደለምን? ይኽ ግን ጥጋብ ስለኾነ ያልፋል፡፡ የነበረ
መኾኑን እስከምንረሳው ድረስ ይኾናል፡፡ ጽኑ ረሀብ ከፊት ለፊታችን አለ፡፡ 150፣ 160 አብያተ ክርስቲያናት እንደተዘጉ
ሲነገረን እንሰማለን፡፡ ገና ከዚኽ የከፋ አለ፡፡ እንዴ! ሌሎችኮ የሚሉን ምንድነው? ሕንፃዉን ሥሩት፤ እንወርሷለን የሚል
ነው፡፡
የኢትዮጵያ
ቤተ ክርስቲያን ከ35,000 በላይ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት አሏት፡፡ 35,000 አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት አሏት ማለት እንደው 5 ልኡካን ተዉትና
ከ20 ዓመት በኋላ እነዚኽ ሽማግሌዎች ሲያልፉ እየቀደሰ፣ እያቆረበ፣ እየሰበከ የሚኖር ትክክለኛ ካህን አንድ ቄስ አንድ ዲያቆን
ብቻ ይበቃናል እንኳን ብንል አኹን ስንት ካህን ያስፈልገናል ማለት ነው? 70 ሺሕ፡፡ ታድያ አኹን 70 ሺሕ ተማሪ አለ? 70
ሺሕ የሚያስተምር ቦታ አለ? ስሜት ማለትኮ ይኼ ነው፡፡ ማየት ማለት ይኼ ነው፡፡
ይኼን እየሰማን ሳለ በሌላው በኩል ያለውን ድግስ
ደግሞ እናውቋለን፡፡ ታድያ ይኼን እያየ የማያስብ ኦርቶዶክስ ካለ ምን መኾን ይሻለናል? እስኪ ከእኛ መካከል ገብረ ሃካይ
(ሐኬተኛ አገልጋይ) ያልኾነ ማን ነው? እየሰማ ያልቀበረ፣ እያየ ያልቀበረ፣ ስሜት የማይሰጠው ስንቱ ነው? የመጪዎቹ አብያተ
ክርስቲያናት አገልጋዮች እነማን ናቸው ብሎ የማያስብ ስንቱ ነው በእውነት?
መንግሥት በሚለንየም የልማት ዕቅድ መሠረት በዓለም
ላይ የሚደረገውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን ለማስፋፋት ሲል እስከ ኦሞ ሸለቆ አስፋፍቶ እያንዳንዱ ዜጋ ልጁን በትንሹ
እስከ 4ኛ ክፍል የማስተማር ግዴታ አለበት፡፡ ሰሜን ብትሔዱ የድሮ ቄስ ተማሪ አይሔድም፡፡ እንዴ! እንዴት ነው የማናስበው? ምን ብለን ነው ገብር ኄርን የምናከብረው? የኛ የስሜት ሕዋሳት መቼ ነው
የሚሠራው? የኛ ዲግሪ ለመቼ ነው የሚጠቅመን? የኛ ዕውቀት ለመቼ ነው? ትችት ብቻ ምን ያደርግልናል ወገኖቼ? አንዳንድ ቄሶችን
መንቀፍ? አንዳንድ መነኮሳትን መንቀፍ? አንዳንድ ሰባክያንን መንቀፍ? ይኼማ ቆፍሮ መቅበር ነው፡፡
“በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንደሚባለው
እንደዉም ተደናብረናል ጭራሽ ታደናብሩናላችኁ፡፡ ይኼማ አደጋውን መጨመር ነው፡፡ ይኼማ ለጠላት መሥራት ነው፡፡ መተቸት አይደለም መፍትሔው፡፡ ማውራት አይደለም መፍትሔው፡፡ መሥራት
ነው መፍትሔው፡፡ እኔ መክሊት የለኝም፤ እኔ ሊቅ አይደለኹም፤ እኔ ካህን አይደለኹም፤ እኔ ጳጳስ አይደለኹም፤ እኔ ዲግሪ
የለኝም ለምን ትላላችኁ? እኩል የስሜት ሕዋሳት እኮ ነው የተሰጠን፡፡ እኩል ነው የምናየው፡፡ እኩል ነው የምንሰማው፡፡ እኩል
ነው የምንኖረው፡፡ እኩል ነው በዓለም የምንጋፋው፡፡ ማሰብ የጋራ ነው፡፡ ዮሴፍ “ሰባት የጽኑ ረሀብ ዓመታት
እንዴት በጥጋብ እታደጋለኁ? እንዴት ሕዝቡ ይድናሉ?” ብሎ አሰበ፡፡ ከዚያ በኋላ አቀደ፤ ሠራ፡፡ ግብሩ ምን መኾን እንዳለበት፣
እኽሉ እንዴት መሰብሰብ እንዳለበት አሰበ፡፡ የጥጋብ ጊዜ የሚያስብ ሰው የለማ፡፡ እኛኮ አኹን የተዘለልነው እንደዚኽ ነው፡፡ በጥጋብ
ጊዜ እንደ ዮሴፍ የሚያስብልን ሰው አላገኘንም፡፡ አኹን ረሀቡ አፍጦ መጣ፤ የት እንድረስ?
የምናወጣው ገንዘብ ምንድነው የሚሠራው? ወገኖቼ ድቃቂ
ሳንቲምኮ ማውጣታችን አይቀርም፡፡ ግን የምናወጣው ትርጉም ያለው ሥራ ይሠራል ወይ? የረሀቡ ዘመን ስንቅ ይኾናል ወይ? ነፍስ
ያድናል ወይ? ጥያቄው ይኼ ነው፡፡
ክርስቲያኖች! ስለ ራሳችን መሮጥ ብቻ አይደለም፡፡ ግድ
የለም እንውጣ እንውረድ፡፡ እንሥራ፡፡ እናቅድ፡፡ እናግኝ፡፡ ግን ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ልንረሳ አይገባም፡፡ ዮሴፍ አቀደ፡፡ አማከረው፡፡
ፈርዖንም ሾመው፡፡ ዐቀደ፤ ሠራ፤ ተሳካለት፡፡ ወገኖቹ እስራኤልን ሳይቀር ከዚያ ጭንቅ የረሀብ ዘመን ታደገ፡፡ ግብጻውያንን
አዳነ፡፡ እንደው የዮሴፍን ነገር ምኑን እንናገሯለን? አንዷን ነገር ብቻ አንሥቼ የሱን ነገር ልዝጋው፡፡
ግብጻውያን ረሀቡ ሲጸናባቸው በመዠመሪያ ዓመት ገንዘባቸውን
በኹለተኛው ዓመት ከብታቸውን አመጡ፡፡ ከዚያ በኋላ ረሀቡ ሲጸና ምን እናድርግ? ነው ያሉት፡፡ “እንዳንሞት እንዳንጠፋ ብለን ገንዘባችንም
ከብታችንም ሰጥተናል፡፡ አኹን ምድራችንንና እኛን ግዛ፡፡ ለፈርዖን ባርያዎች አድርገን፤ ውረሰው፡፡ እንዳንሞት ብቻ ግን እኽል
ስጠን” አሉት፡፡ ግብጻውያን በሀገራቸው ላይ፣ በርስታቸው ላይ
በረሀብ ምክንያት ስላላሰቡ፣ ስላልተዘጋጁ ወደው ፈቅደው ባሮች ኾኑ፡፡ ግብጽ የሲዖል ምሳሌ የኾነችው በዚኽ ምክንያት ነው፡፡ ምንም እንኳን
ባርነቱ በኋላ ባይቀርላቸውም እስራኤላውያን በዚኹ ሰዓት ባሮች አልነበሩም፡፡ እስራኤል ወደ ግብጽ ከገቡ በኋላ በዮሴፍ ምክንያት
በነጻ ነው መሬት የተሰጣቸው፡፡ እስራኤል ግብጽም ወርደው ነጻ ሕዝብ ነበሩ፡፡ ለዚኽም ነው እነ አብርሃም ሲዖልም ወርደው ነጻ
የነበሩት፡፡ በኋላ ግን “የኃጥእ ዳፋ ጻድቅ ያዳፋ” እንዲል የግብጽ ወዶ ባርነት እስራኤልን ለተገዶ ባርነት አብቅቷቸዋል፡፡
ክርስቲያኖች! እኛ አኹን ግብጾችን ነው የምንመስለው፡፡ ወደን ወደ ባርነት እየገባን ነው፡፡ በነበረን ጊዜ
የማናውቅበት፣ ማሰብ እየቻልን፣ ማቀድ እየቻልን፣ መሥራት እየቻልን፣ ማጠራቀም እየቻልን፣ ማየት እየቻልን አእምሮ እንደሌለው ሰው
ኾነናል፡፡ እንደ ግብጻውያን በራሳችን ምድር፣ በራሳችን ቤተ ክርስቲያን፣ በራሳችን ሀገር ወዶ የነፍስ ባርነት እየገባብን ነው፡፡
እግዚአብሔር ከዚኽ ባርነት ነጻ ያውጣን፡፡
ማሰብ ነው ክርስቲያኖች፡፡ መተኛት ይበቃናል፡፡ በዚኽ
ጉባኤ ትጽናናላችሁ፡፡ እውነት ነው ያጽናናል፡፡ ግን ምን አለው ይኼ? እስኪ ንገሩኝ ምን አለው ይኼ? ምንድነው ይኼ? የዚኽ
ዐሥር ዕጥፍኮ ሌሎች ይሰበሰባሉ፡፡ ይኼን ታውቃላችኁ?
እናስብ፡፡ መውጣት እንችላለን፡፡ ከረሀቡ ማለፍ
እንችላለን፡፡ ማዳን እንችላለን፡፡ መሥራት እንችላለን፡፡ ማቀድ እንችላለን፡፡ ተባብረን ግን እንሥራ፡፡
ኹለተኛው አብድዩ ነው /2ኛ ነገ.4/፡፡
በርግጥ ታሪኩ በሚስቱ በኩል ነው የተቀመጠው፡፡ ታሪኩ
ግን የአብድዩ ነው፡፡ አብድዩ ከኤልያስ ደቀ መዛሙርትና ትንቢተ አብድዩ የሚባል ከደቂቀ ነቢያት መጻሕፍት አንዱን የጻፈልን ከዐሥራ
ኹለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ነው፡፡ የመዠመሪያ ሥራው በቤተ መንግሥት ውስጥ የንጉሡ በጅሮንድ (ገንዘብ ያዥ) ኾኖ ታላቅ ባለ
ሥልጣን የነበረ ሰው ነው፡፡
አብድዩ የተሰጠውን መክሊት የተጠቀመ ሰው ነው፡፡ በርሱ
ዘመን አክአብ የሚባል ጨካኝ ንጉሥ ኤልዛቤል የምትባል በትውልዷ ከሶርያ ወገን የኾነችን ሴት አግብቶ እስራኤልን በሙሉ ከእግዚአብሔር
ለመለያየት አቀደ፡፡ “እስራኤል እግዚአብሔርን ማምለካቸው የሚቀጥሉት ምን ስለኾኑ ነው?” ብሎ ሲያስብ ሰይጣን ለኤልዛቤል
አሳሰባት፡፡ “እስራኤል እግዚአብሔርን በማምለክ ጸንተው የሚኖሩት የተለዩ ሰዎች ስለኾኑ ሳይኾን ብዙ ነቢያትና ብዙ መምህራን
ስላሏቸው ነው፡፡ ስለዚኽ እስራኤልን ከእግዚአብሔር ለመለየት ምን ላድርግ?” ብሎ አሳሰባት፡፡ የእግዚአብሔርን ነቢያት እየያዘች፣
እያሳሰረች እንድታስገድል አሳሰባት፤ ኤልዛቤልን፡፡
የሰይጣን ትልቁ ሐሳቡ መምህራንን ማጥፋት ነው፡፡ ጉባኤ
ቤቶችን መዝጋት ነው፡፡ ተተኪ እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ ይኼ የኹል ጊዜ የሰይጣን ስልት ነው፡፡
ታድያ ይኽቺ አልዛቤል ነቢያትን ስታስጨርስ ሲወለድ
በእሳት ተጠቅልሎ የተወለደው፣ ሲኖር በቅናት እሳት እየተቃጠለ የኖረው፣ ሲያርግም በእሳት ሰረገላ ያረገው እሳታዊው፣ ነዳዲው
ኤልያስ እጅግ ይጨነቅ ነበር፡፡ በጣም የሚገርማችኁ ግን ከኤልያስ
ቅናት በላይ ቤተ እስራኤልን፣ አቅሌስያን የጠበቃት የአብድዩ ዕቅድ ነበር፡፡ አብድዩ የሚኖረው ከጨካኙና የእግዚአብሔርን ነቢያት
እያደነ ከሚገድለው ከአክአብ ጋር ቤተ መንግሥት ነው ፡፡ ነገር ግን ሕሊናውን ተጠቀመበት፡፡ ምን አለ? ይኼ ዘመን ያልፋል፡፡ ዘመኑ
ባለፈ ጊዜ ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያስተምሩ መምህራን አይገኙም፡፡ ስለዚኽ አለና 50 ነቢያትን አንድ ዋሻ ውስጥ፣ 50
ነቢያትን ሌላ ዋሻ ውስጥ ደበቀ፡፡ በድብቅም 100 ነቢያትን ብቻውን ምሥጢር አድርጎ መመገብ፣ መቀለብ ዠመረ፡፡
ይቻላልኮ ክርስቲያኖች! የምናስብ ከኾነ ይቻላል፡፡ አንድ
ሰው ሕዝብን የሚወድ ከኾነ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚወድ ከኾነ የሚጠብቀው መምህራንን ነው፡፡ የሚጠብቀው ትምህርት ቤቶችን ነው፡፡
የሚጠብቀው ምንጩን ነው፡፡ አብድዩ ያደረገው ይኸንኑ ነው፡፡
ያ የመከራ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ በድብቅ፣ ማንም
ሳያውቅ 100 ነቢያትን ዕድሜ ልኩን ይመግብ ነበር፡፡ ዕድሜ ልክስ ይቅርና አንድ ቀን ብቻ እንኳን 100 ሰዎችን በቤታችን
መጋበዝ እንዴት ከባድ እንደኾነ እናውቋለን፡፡ የሚገርመው አብድዩ ከመቸገሩ የተነሣ ከቤተ መንግሥቱ እየተበደረ፣ ከሌሎች ሰዎችም
ጭምር እየተበደረ እነዚያን 100 ነቢያት ሳያቋርጥ መቀለብ ቀጠለ፡፡
ኤልያስ 3 ዓመት ተኩል ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድር የዘሩባትን
እንዳታበቅል የተከሉባትን እንዳታጸድቅ ገዝቶ ነበር፡፡ ይኼ ግዝት ተነሥቶ አክአብ ወደ ልቡ እስኪመለስ፣ እስራኤልም የማምለክ
መብታቸው እስኪከበር ድረስ አብድዩ እነዚኽን 100 ነቢያት በድብቅ ይቀልብ ነበር፡፡
አብድዩ ከአክአብ ከወጣ በኋላ በነቢይነት ነበር
ያገለገለው፡፡ ነገር ግን ዕዳውን አልለቀቀውም ነበር፡፡ ዕዳውን ሳይመልስም አገልግሎ ሞተ፡፡ በሞተ ጊዜም የአብድዩ ሚስት በዕዳ
ተያዘች፡፡ በኦሪቱ ትእዛዝ መሠረት አንድ ሰው ዕዳውን መክፈል ካልቻለ ልጆቹን የዕዳውን ክፍያ አድርጎ ይሰጣል፡፡ የአብድዩ
ሚስት፣ የዚኽ አሳቢ ሚስት፣ የዚኽ አእምሮውን የተጠቀመበት ሚስት፣ የዚኽ የውስጡውም የውጪውም ዓይኑ የተጠቀመበት ሚስት፣ የዚኽ
ጭንቅላቱን የተጠቀመበት ሚስት የቤቷን ዕቃ ኹሉ አውጥታ ብትሸጥም ዕዳውን ግን መክፈል አቃታት፡፡ በቤቷ የቀረው የዘይት ጭላጭ
ያለባት አንዲት ማሰሮ ብቻ ነበር፡፡
አኹን ወደ ዘመዱ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ ሔደች፡፡ “ጌታዬ
ሆይ! ባሌ እግዚአብሔርን ይፈራ እንደነበር ታውቃለኅ፡፡ አኹን ግን ባለ ዕዳ መጥቶ ልጆቼን ሊወስዳቸው ነው፡፡ አንድ ነገር
ርዳኝ” ብላ ለመነችው፡፡ “በቤትሽ ውስጥ ምን አለ?” አላት ኤልሳዕ፡፡ “ከዘይት ጭላጭ በቀር ምንም የለኝም” አለችው፡፡ “ሒጂ
ወደ ሰፈር ውጪ፡፡ ከሜዳ ማድጋዎችን ሰብስቢ” አላት፡፡ ከሜዳ ማድጋ ያውም ድንጋይ ይሰበሰባል እንዴ? ኤልሳዕ ግን እንደዚያ
አላት፡፡ ጨምሮም “አታሳንሻቸው፡፡ ከዚያ በኋላ በርሽን ዝጊ፡፡ ካንቺ የዘይት ማሰሮ ዘይት ይመነጫል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሌሎቹ
ማሰሮዎች ገልብጪ፡፡ ኹሉም ይሞላሉ” አላት፡፡ ሔደች፤ ብዙ ማድጋዎችን ሰበሰበች፡፡ ከልጆቿ ጋር ኾና ቤቷን ዘጋች፡፡ እንደተባለውም
ከዘይቷ ማሰሮ ዘይት መፍለቅ ዠመረ፡፡ ሲሞላ ትገለብጣለች፤ ሲሞላ ትገለብጣለች፡፡ እንዲኽ እያደረገች የሰበሰበቻቸውን ማድጋዎች
በሙሉ ሞላቻቸው፡፡
ከሞላች በኋላ በሯን ከፈተች፡፡ ፈጥናም ወደ ኤልሳዕ
ሔደች፡፡ “ሞልቷል፤ እንዳልከኝ ኾኗል፡፡ ምን ላድርግ?” ብላ ጠየቀችው፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ ዝም ብሎ አይበላምና ባርክልኝ
ማለቷ ነበር፡፡ ርሱም “ሒጂ፡፡ ሽጪ፡፡ ዕዳሽን ክፈዪ፡፡ በተረፈውም አንቺና ልጆችሽ ተመገቡ” አለና ከዕዳ ነጻ አወጣት፡፡
አስቡ ክርስቲያኖች! አብድዩ እዚኽ ድረስ የደረሰው፣
እዚኽ ዕዳ ውስጥ የከተተው ስላሰበ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደሚከፍል ያውቃል፡፡ ልጆቹ እንደማይሸጡ ያውቃል፡፡ ያምናል፤
ያገለግላልም፡፡ ርሱ ራሱ ግን ልጆቹ እስከሚሸጡበት ደረጃ ድረስ ተበድሮ የእግዚአብሔርን ነቢያት አተረፈ፡፡ አምልኮተ
እግዚአብሔር በእስራኤል ጸና፡፡ ወገኖቼ! መምህራንን አትርፈን፣ አምልኮተ እግዚአብሔርን በምድራችን ለማጽናት ያብቃን፡፡
እስኪ እንጠያየቅ! ከእኛ መካከል እንደ አብድዩ ባለ
ዕዳ እስከ መኾን ደርሶ የሰጠ አለ? መዠመሪያ ግን እናስባለን ወይ? የመከራ ዘመን እንዴት እንደሚታለፍ እናስባለን? አብድዩ
አክአብን እንዴት እንደሚያልፈው አሰበ፡፡ እኛስ እናስባለን? የቴሌቪዥኑ ጎርፍ፣ የኢንተርኔቱን ጎርፍ ለመሻገር እንዴት ነው
እያሰብን ያለነው?
የአብድዩ ታሪክ አበው ተርጉሞውታል፤ በተለይም ቅዱስ
ኤፍሬም ሶርያዊ፡፡ የአብድዩ ሚስት የቤተ ክርስቲያን፣ ልጆቿ የእኛ የምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ ባለ ዕዳ የተባለውም ዲያብሎስ ነው፡፡
ዲያብሎስ ኹሌ ኃጢአትን ያበድራልና፤ ያሠራናልና፤ ያዘናጋናልና፡፡ ስለ ኑሯችን፣ ስለ ዕድገታችን ብቻ ያሳስበናል፤
ያስጨንቀናል፡፡ ስለምንበላው፣ ስለምንጠጣው፣ ስለምንኖረው እናቅዳለን፡፡ “ከዚኽ በኋላ ይኼን አሠራለኁ፤ ልጆቼን በዚኽ ትምህርት
ቤት አስተምራለኁ፤ እንዲኽ አደርጋለኁ” እንላለን፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንስ? የቤተ ክርስቲያን መምህራንስ? ካህናትስ? አኹን
ካላሰብን ቅድም የተናገርኩትን ሰባ ሺሕ ሰው እንዴት ነው የሚኖረን? ወደፊትኮ አምስት ካህን አይደለም የምንችለው፡፡ ኹለት ሰው
ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ታድያ ይኼን እያየን እንተኛ እንዴ? ረሀቡ እየመጣ እያየን በአኹኑ በጥጋብ ዘመን እንደ ግብጻውያን
እንዘናጋ እንዴ?
ኤልሳዕ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን
እንደ አብድዩ ሚስት ድኻ ትመስላለች፡፡ ነገር ግን ኹሉንም ማሰሮ ሊሞላ የሚችል የዘይት ምንጭ አላት፡፡ የዕውቀት ምንጭ
አላት፡፡ የተአምራት ምንጭ አላት፡፡ የጸጋ ምንጭ አላት፡፡
ባዶ ማድጋዎች የተባሉት አሕዛብ ናቸው፡፡ ስለዚኽ
ሰብስቡ የተባለው እነዚኽን ማሰሮዎች፣ እነዚኽን አሕዛብ ነው፡፡ ጌታም በዘይት መንፈስ ቅዱስ፣ በዘይት ጥምቀት፣ በዘይት ቃለ
እግዚአብሔር ይሞላቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም ከዕዳ ነጻ ያወጣታል ነው እያለ ያለው፡፡
እኛ ግን ማሰሮውን፣ መሰብሰብ አልቻልንም፡፡ አሕዛብን
ከሜዳው (ከአሕዛብ ኑሮ) መሰብሰብ አልቻልንም፡፡ ክርስቲያኖች እናስብ፡፡ ገብር ኄር ነው ብለን ስናከብር ገብር ኄር ማን ነው
ብለን እንጠይቅ፡፡ ገብር ኄር ዮሴፍ ነው፡፡ ገብር ኄር ሙሴ ነው፡፡ ገብር ኄር አብድዩ ነው፡፡ ገብር ኄር እነዚኽን የመሰሉ
ናቸው፡፡ እኛስ እነማን ነን? እኛማ ኹሉንም ነገር ለኑሯችን በማስላት የእግዚአብሔርን አገልግሎት በሰውነታችን፣ በቤታችን
ቆፍረን የቀበርን ሰዎች ነን፡፡ የሚነግረን አጥተን ነው እንጂ ከእኛ በላይ ገብረ ሃካይ (ታካች አገልጋይ) የለም፡፡ የሚሠሩ፣
የሚያስቡ ሰዎች የሉም ለማለት አይደለም፤ አብዛኛዎቻችን ግን ገብረ ሃካይ ኾነናል፡፡
እስኪ ኑና እንሰብሰብ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደ አንድ ዕድል እንጠቀምበትና እንሰብሰብ በእውነት፡፡ አንዳንድ ሰዎች
ማኅበረ ቅዱሳን መጥተው እንኳን እንደ ቆሮንቶስ ሰዎች ሊመኩ የሚፈልጉ አሉ፡፡ ኑ እስኪ፡፡ የምንሠራው እኮ የጋራ ሥራ ነው፡፡ አብድዩ
የቀለባቸው 100 ነቢያትኮ የአብድዩ አገልጋዮች አይደሉም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሚረዳቸው መምህራንኮ
የማኅበረ ቅዱሳ አገልጋዮች አይደሉም፡፡ የእናንተ አገልጋዮች ናቸው፤ የእናንተን ካህናት አስተማሪዎች ናቸው፤ የእናንተ የነፍስ
አባቶች አስተማሪዎች ናቸው፤ የእናንተ ቤት ጸበል ረጪዎች ናቸው፡፡ እንዴ! እነማንን የምትረዱ ይመስላችኋል? ራሳችንን ነውኮ
የምንረዳው፤ ራሳችንን ነውኮ የምንጠብቀው፡፡ ራሳችንን ነውኮ ነጻ የምናወጣው፡፡ ታድያ እስከ መቼ እንተኛለን? እስከ መቼ
እናንቀላፋለን? የመስጠትና የመቀበል ስሌታችን ምንድነው? እንዴት ነው መስጠት ያለብን? እንዴት ነው ማቀድ ያለብን? እንዴት
ነው መሥራት ያለብን?
በአክአብ ቤተ መንግሥት ለአብድዩ፣ በፈርዖን ቤተ
መንግሥት ለዮሴፍ ልቡና የሰጠ እግዚአብሔር እኛም በዚኽ ጥፋት በነገሠበት ዓለምም አስበን እንድንሠራ አእምሮ ማስተዋል ያድለን፡፡
አስበን ለመሥራት ያብቃን፡፡ ትምህርት ቤቶቻችን ለመጠበቅ ያብቃን፡፡ የቅዱሳኑ ምንጮች፣ የሊቃነ ጳጳሳቱ ምንጮች፣ የቆሞሳቱ
የመነኮሳቱ ምንጮች፣ የመምህራኑ ምንጮች ገዳማቶቻችንን ለመጠበቅ ያብቃን፡፡ ጠብቀን ለመጠቀምም ያብቃን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
Kale hiwot Yasemalin. Amen!!!
ReplyDeleteአቤቱ ሰምተን ለመስራት አብቃን ገ/እግዚአብሔር ላንተም የነፍስ ዋጋ ያድርግልህ ለመምህራችንም ቃለ ህይወትን ያሰማልን በእውነት ትልቅ ትምህርት እንግዲህ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ
ReplyDeleteቃለ ህይወት ያሰማልን
ReplyDeleteበድምፅ ብትለጥፉልን ጥሩ ነው
ReplyDeleteየቀዳኹት በተንቀሳቃሽ ስልክ ስለኾነ ጥራት የለውም፡፡
Deleteወደ ጽሁፍ እንድ ትቀይረው ያስቻለህ እግዚኣብሄር ይመስገን :እንካን በስብከት ብቻ አልቀረ.ልብ የሚነካ ትምህርት ነው .ቃለ ህይወት ያሰማልን.
ReplyDeleteAmena
ReplyDeleteAmena
ReplyDeleteI've shared it with many people. EgziAbHer Yistilin!
ReplyDeleteAM
Frist of all, I appreciate for your great service and honestly advice about our futures. I was invited a couple or more meetings about this issue as a member of the church and I saw what, where those plans are prepared to apply. That is good, it covers some part of the country and I mentioned why a lot of works accomplished in one region and a few works done in some part of the country. In addition other part of the countryside aren't yet included as part of the plan that you have. I mean we don't have wast our limited power and potential on already developed and organized places like Gondar.i was there and the churches has enough money to pay the organization and the employee under it but when we go other part of the country it is null. So if we concerned honestly we are not yet targeted on the pivot point of the problem. Instead we work in more orginated and cooperated part of the countryside. If we need to continue the service and other things in this churches, we have to first identify and focused where and how to apply this energy and fairly distribute the resources that we have today. Besides we have to contact those reach churches to participate in such good ideas. We know some churches hide billions dollars in their account and others still bagging for daily necessities, so we have to preach and aleart the people to show the other part of the countryside side churches real image. Thanks for having me.
ReplyDelete