Wednesday, September 9, 2015

ዘመን እና ሰው

ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ጳጉሜ 4 ቀን፥ 2007 ዓ.ም.)፦ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ሁለት ዓይነት ጊዜ እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ አንደኛውና ይህ ዛሬ "እንኳን ከዘመን ዘመን... " የምንባባልበትና ፍጥረትና ድርጊቱ በቅደም ተከተል የሚሰነዱበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ጊዜ ከዚህ በኋላ " የፍጥረት ጊዜ" ወይም ታሪካዊ ጊዜ (Historical time) የምንለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሥነፍጥረትም በፊት በፍጥረትም ጊዜ ከፍጥረት ማለፍም በኋላ የሚኖረውና በፈጣሪ ሕልውና የሚለካው (አስተውሉ እርሱ ራሱ ይለለካል እንጂ የፈጣሪን ድርጊት የሚለካ አይደለም) ከአሁን በኋላ "ዘላለማዊ ጊዜ " ወይም እንደኛ ሊቃውንት "ዮም " የምንለው ሌሎቹም በእንግሊዝኛ "የተቀደሰ ወይም ዘላለማዊ ጊዜ" (Sacred time) የሚሉት ጊዜ ነው፡፡ ዮም የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ዛሬ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ጊዜ በእኛ ሊቃውንት ዘንድ "ዮም" የሚባልበት ምክንያት ከመዝሙረ ዳዊት "እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ፤ ወአነ ዮም ወለድኩከ" ፤ እግዚአብሔር አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ (መዝ 2፤7)የሚለውን ጥቅስ መነሻ አድርገው ትርጓሜውን ሲያብራሩ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የገለጸው የጊዜ መጠሪያ ዮም ወይም ዛሬ መሆኑን ስለሚያመሰጥሩ ነው፡፡ ይህም ማለት በእግዚአብሔር ዘንድ ትናንት እና ነገ፤ አምናና ከርሞ፤ ጥንትና መጪው ጊዜ ወይም ከዚህ ዘመን በኋላ የሚባል ነገር የለም ማለት ነው፡፡ ለእርሱ ሁሉም "ዛሬ" ነው፤ ምክንያቱም እርሱ በፍጥረት ጊዜ ሊለካና ሊታወቅ የሚችል አይደለምና፡፡ ስለዚህም ነው ስለ እግዚአብሔር ሲሆን "ዮም" ወይም ምዕራባውያን እንደሚሉት ልዩ፤ ቅዱስ ጊዜ (sacred time) የሚለውን ለመጠቀም የምንገደደው፡፡ ከላይ በተገለጸው ጥቅስ ላይ ‹‹እኔ ዛሬ ወለድሁህ›› የሚለው የሚገልጸውም የወልድን ሁለቱንም ልደታት ነው፡፡ በእኛ ሊቃውንት ዘንድ ይህ ኃይለ ቃል ሲብራራ ሁለቱም ጊዜዎች አብረው የሚነሡትም ለዚህ ነው፡፡ የጌታችንን ሁለት ልደታት የመጀመሪያው ‹‹ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት›› ሁለተኛውን ደግሞ ‹‹ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ይህ አገላለጽ ሙሉ በሙሉ በፍጥረት ጊዜ ማለትም እኛ ድርጊቶችን በምንለካበትና እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ሲፈጥር በፈጠረው ጊዜ ከላይ እንዳልነው በታሪክ መለኪያው ጊዜ (Historical time) የተገለጸ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ ›› / ዕብ 1 ፤ 1-2/ እያለ የሚናገረው በዚሁ ጊዜ ስሌት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በፍጥረት ጊዜ ሲለካ የእግዚአብሔር ወልድ ቀዳማዊ ልደት ‹‹ቅድመ ዓለም›› ወይም ከዓለም መፈጠር በፊት ከሚለው ውጭ መግለጫ የለውም፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት ያለውን የሚለካ የፍጥረት ጊዜ ( Historical time ) የለምና፡፡ ከዚሁ ጋር አብረውም ልክ የእርሱን ቀዳማዊ ልደት በፈጣሪ ቅዱስ ጊዜ እንደገለጹት ሁለተኛውን ልደቱን ማለትም ከእመቤታችን በታወቀ ጊዜ የተወለደውንም በእኛ አቆጣጠር የሚገልጹትን ያህል በእግዚአብሔር ቅዱስ ጊዜ ‹‹ዮም›› ዛሬ ብለው ከታሪካዊው ወይም ከታሪክ መነገሪያው ፍጥረታዊ ጊዜ አውጥተው ይነግሩናል፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ዛሬ ነውና፡፡ ‹‹ዛሬ ወለድኩህ›› ማለትም ቀዳማዊ ልደቱም ደኃራዊ ልደቱም በእርሱ ዘንድ ዛሬ ስለሆነ ነው፡፡ ለሊቃውንቶቻችን ምስጋና ይድረሳቸውና ‹‹ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት›› የሚለው ግሩም አገላለጻቸውም በዘላለማዊ ጊዜ ያለው በፍጥረታዊው ወይም በታሪክ መሰነጃው ጊዜና ዓለም ውስጥ መገለጹን የሚያስረዱበት እጅግ ድነቅ አገላለጽ ነው፡፡

ስለ ጊዜ ምንነት እጅግ በቅንጭቡ ይህን ያህል ካልን ዋናው ነገር የእኛ የዘመን ዘመን ሽግግር በእግዚአብሔር ዘንድ ትርጉም የሚኖረው ምን ስናደርግ ነው የሚለው መሆን ይገባዋል፡፡ ዘመኑን ወይም ጊዜውን የኽኛውና ያኛው፤ ያለፈውና የሚመጣው የሚያሰኘው የራሱ የሰው ድርጊት ብቻ ነውና፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድማ ቀደም ብለን እንዳያነው ያው ‹‹ ዛሬ›› ብቻ ነው፡፡ በመጽሐፍም ‹‹ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና›› / መክ 7፤10/ ተብሎ የተጻፈው ምስጢሩን እንደተባለው በወጉ ስለማንረዳው ነው፡፡ ስለዚህ የሚጠበቅብን ከተቻለን ደግሞ የሚጠቅመንም በፍጥረዊው ጊዜያችን ውስጥ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ወይም በዘላለማዊው ጊዜ ( Sacred time) የሚኖር ሥራ መሥራት ማለት ነው፡፡ ቀደም ብየ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሁሉም ጊዜ ለእግዚአብሔር ዛሬ ስለሆነ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያሰጥ ሥራ የምንሠራ ከሆነ ዘላለማዊው ጊዜ ገና የሚመጣ ሳይሆን ያለ ነውና ሥራችንን በታሪካዊው ጊዜ ብቻ ሳይሆን በዘላለማዊው ጊዜም ይሰፍራል እኛንም ዘላለማዊ ወደ መሆን ያሸጋግረናል ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ሥራ ሲገልጽ ‹‹ ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ›› / ሐዋ 13 ፤ 36/ በማለት የተጠቀመበት አገላለጽ ይህንን በደንብ የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ ሐዋርያው እንደገለጸው ዳዊት በዘመኑ ማለትም በፍጥረታዊው ጊዜ ያገለገለው ‹‹ የእግዚአብሔርን አሳብ ›› ማለትም በዘላለማዊ ጊዜ የሚኖረውን የእግዚአብሔርን ሥራ ፈጽሞ ወደ ዘላለማዊው አምላክ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ተሸጋገረ ማለት ነው፡፡
ቅዱሳንም ይህን የእኛን ታሪካዊውን ወይም ፍጥረታዊውን ጊዜ እያወቁት እየኖሩበትና እየሠሩበት ሳለ የጊዜ ማስላትና መለዋወጥን ማወቅ ማጥናትና ማወጅ ጥንቱንም ያስፈለገውና የተጀመረው ወደ ዘላለማዊው ጊዜ ( ሕይወት) ለመድረስ ስለሆነ በዚህ ምድር እያሉም የመዓልቱና የሌሊቱ፤ የአውራህ፤ የወቅቶችና የዘመናትም መሽከርከር ትልቅ ነገር የማይሆንባቸው ራሳቸውን በዚያኛው ጊዜ ውስጥ ለማኖር ስለሚጋደሉ ነው፡፡ ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና›› /1ኛ ጴጥ 4 ፡10/ ዓይነት አገላለጾች በሙሉ የተለየ ጊዜ መሰጠትና የበዓል ማክበር ትርጉሙ ሁልጊዜም ሰማያዊ ደስታ የሚፈጸምበት ዘመን መኖሩን እንድናስታውስና ቢቻል ዛሬም በዚህ ምድር ሁልጊዜም ለዚያ ዓላማ እንድናውለው ካልተቻለም በዓሉን ስናከብር ለውጥ የማይቀር መሆኑን እንድናስብ ነው፡፡ በተለይ የዘመን መለወጫ በዓል ‹‹ ዘመን ተለወጠ›› የሚባለው ወደ ፊት ይህ ፍጥረታዊ ጊዜ በዘላለማዊ ጊዜ የሚለወጥና አዲስ ዘመንም ማለት በሚመጣው ዓለም ያለው አዲስ ሕይወት የማይቀር መሆኑን እንድናውቅና እንድንረዳ ለማስገንዘብ የሚውል ትልቅ ደውል ነው፡፡ ‹‹ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው ›› / ኤፌ 1 ፤10/ ተብሎ የተጻፈውም የዘመን ሁሉ መጨረሻው ይኼው በክርስቶስ መጠቅለል ማለትም በዘላለማዊ ጊዜ ውስጥ በሥራችን መሠረት በሚሰጠን የፍርድ ዋጋ ውስጥ ሆነን መኖር ስለሆነ ነው፡፡ ካለበለዚያ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችሁ›› / ገላ 4፤ 10/ ሲል እንደ ወቀሳቸው የገላትያ ሰዎች በሚወጣልን የበዓላትና የአጽዋማት መቁጠሪያ ካሌንደር ተመሥርተን ቀኑን ወሩን ዘመኑን ከመቁጠርና በዚያም ከመብላትና ከመጠጣት በተራ ነገር ብቻ ከመደሰትም በቀር ለምን እንደምንቆጥርና እንደምናከብር ግን የማናውቅ እንሆንና በምድር በቅዱሳንም በሰማይ በእግዚአብሔርም ተወቃሾች እንሆናለን፡፡
የዘመን መለወጥ በዓል ማክበር ትርጉሙም ሆነ ዋናው መልእክቱም በተሰጠን ዘመን ውስጥ እስካሁን ለበጎ ነገር ያልተጠቀምንበትን አስበን ለመጪው ዓመት ብቻ ሳይሆን ለመጪው ዘመናችን ለበጎ ሥራዎች እንድንዘጋጅበት ለሥራ የተሠጠንም ዘመን ባከበርናቸው በዓላት ቁጥር መጠን እየቀነሰ መሆኑን የምንረዳበት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል ›› / ቲቶ 2 ፤ 13/ ሲል ፍጥረታዊውን ጊዜ እንደገለጸው ይህ ጊዜ እግዚአብሔርን ለመምሰል ወይም እርሱን የመሰሉ / 1ኛ ቆሮ 11 ፤1/ ቅዱሳንን ለመምሰልና ወደዚያኛው የፍጹምነት ሕይወት ለመሸጋገር ቅዱስ ተግባርን ለመለማመድ የተሰጠ ጊዜ ነው ማለት ነው፡፡ ቅዱሳኑ ሁሉ ስለዘመናት ስለበዓላት በተናገሩባቸው አንቀጾች ሁሉ ጉዳዩ የሰዎችን የሕይወት ለውጥ የሚመለከት እንደሆነ አጽንዖት የሚሰጡት ጊዜ ሁልጊዜም የሥራ መሥሪያ ይሆን ዘንድ የተሰጠ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር /1ኛ ጴጥ 1 ፤ 11/›› ሲል ቅዱስ ጴጥሮስ እንደገለጸው ዓበይት በዓላት በሙሉ የሚያሳስቡትም ዘላለማዊው እግዚአብሔር በፍጥረታዊ ጊዜ ምን ዓይነት የማዳን ሥራ እንደሠራ ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት በዓላት የሥራ መታሰቢያዎች ናቸው፤ ሥራ ትተን የምናከብራቸውም ዘመኑ የተሠጠን ለመልካም ሥራ በመሆኑና ያ በዓል በተደረገበት ዕለት ግን እኛ ለራሳችን ልንሠራው የማንችለውን እግዚአብሔር በልጁ ከዚያም በቅዱሳኑ ስለሠራው ይህ መሆኑን አምነንና እርሱን እያሰብን ስናከብረው በዚያ የማዳን ሥራ የተፈጸመውን ለእኛ ማድረግ ስለምንችል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ይህም ያንን የተሠራውን ሥራ ለእኛ አድርገን በመቀበል ዋጋውን የምናተርፍበት መንፈሳዊ ሥራ ነው እንጂ መዘለል ( ሥራ ፈትነት) አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዘመን የሥራ መሥሪያ እና የምንሠራው ሥራ መለኪያ እንጂ ትርጉም የለሺ ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ለቅዱስ ጢሞቴዎስ ‹‹ እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው›› / 1ኛ ጢሞ 6 ፤ 18 - 19 / ሲል የገለጸለት ዘመንን እንዲህ ለመልካም ሥራ የዚህን ዓለም ንብረት ብንሰበስብ እንኳ ለሌላቸው በማካፈል በዚህ ገንዘብ በኩል ሰማያዊ መዝገብን ለመሰብሰብ እንድንጠቀምበት ለማሳሰብ ነው፡፡ ካለበለዚያ ድልቡን ሁሉ ትተነው መሔዳችን አይቀርምና እንጎዳበታለን እንጂ አንጠቀምበትም፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና›› / 1ኛ ጴጥ 4 ፤ 12/ እያለ የሚመክረን ከዘመናችን የቀረውን ማለትም የዘመን መለወጫ በዓላችን ስናስብ እንደቀረን የምናስበውን ዘመናችን በጎ ለመሥራት ሳናስብ እንዳናሳልፈው ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ ይህን ፍጥረታዊ ጊዜ ለዘላለማዊው ጊዜ መሸጋገሪያ እናደርገዋለን፡፡ ቅዱሱ ይሁዳም ‹‹ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን›› /ይሁ 1 ፤ 25/ ሲል የገለጸው ዘመን የሚቆጠርለት ጌታ በማይቆጠር ዘመን ወይም በዘላለማዊነት የሚኖርና እኛንም በዚህ ለማኖር የመጣ ስለሆነ ነው፡፡
እንግዲያውስ በእኛ የጊዜ አቆጣጠር የምንቀበለውን አዲሱን ዘመንና ከዚህ በኋላ የሚመጣውን ዘመናችን ሁሉ እንደ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ የእግዚአብሔርን አሳብ ›› የምናገለግልበት ዘመን ያድርግልን፡፡ እንኳን አደረሳችሁ፤

3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን እንኳን አብሮ, ደረሰን ።

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን እንኳን አብሮ, ደረሰን ።

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን እንኳን አብሮ, ደረሰን ።

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount