ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ጳጉሜ 4 ቀን፥ 2007 ዓ.ም.)፦ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ሁለት ዓይነት ጊዜ እንዳለ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ አንደኛውና ይህ ዛሬ "እንኳን ከዘመን ዘመን... " የምንባባልበትና ፍጥረትና ድርጊቱ በቅደም ተከተል የሚሰነዱበት ጊዜ ነው፡፡ ይህንን ጊዜ ከዚህ በኋላ " የፍጥረት ጊዜ" ወይም ታሪካዊ ጊዜ (Historical time) የምንለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሥነፍጥረትም በፊት በፍጥረትም ጊዜ ከፍጥረት ማለፍም በኋላ የሚኖረውና በፈጣሪ ሕልውና የሚለካው (አስተውሉ እርሱ ራሱ ይለለካል እንጂ የፈጣሪን ድርጊት የሚለካ አይደለም) ከአሁን በኋላ "ዘላለማዊ ጊዜ " ወይም እንደኛ ሊቃውንት "ዮም " የምንለው ሌሎቹም በእንግሊዝኛ "የተቀደሰ ወይም ዘላለማዊ ጊዜ" (Sacred time) የሚሉት ጊዜ ነው፡፡ ዮም የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ዛሬ ማለት ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ጊዜ በእኛ ሊቃውንት ዘንድ "ዮም" የሚባልበት ምክንያት ከመዝሙረ ዳዊት "እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ፤ ወአነ ዮም ወለድኩከ" ፤ እግዚአብሔር አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ (መዝ 2፤7)የሚለውን ጥቅስ መነሻ አድርገው ትርጓሜውን ሲያብራሩ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የገለጸው የጊዜ መጠሪያ ዮም ወይም ዛሬ መሆኑን ስለሚያመሰጥሩ ነው፡፡ ይህም ማለት በእግዚአብሔር ዘንድ ትናንት እና ነገ፤ አምናና ከርሞ፤ ጥንትና መጪው ጊዜ ወይም ከዚህ ዘመን በኋላ የሚባል ነገር የለም ማለት ነው፡፡ ለእርሱ ሁሉም "ዛሬ" ነው፤ ምክንያቱም እርሱ በፍጥረት ጊዜ ሊለካና ሊታወቅ የሚችል አይደለምና፡፡ ስለዚህም ነው ስለ እግዚአብሔር ሲሆን "ዮም" ወይም ምዕራባውያን እንደሚሉት ልዩ፤ ቅዱስ ጊዜ (sacred time) የሚለውን ለመጠቀም የምንገደደው፡፡ ከላይ በተገለጸው ጥቅስ ላይ ‹‹እኔ ዛሬ ወለድሁህ›› የሚለው የሚገልጸውም የወልድን ሁለቱንም ልደታት ነው፡፡ በእኛ ሊቃውንት ዘንድ ይህ ኃይለ ቃል ሲብራራ ሁለቱም ጊዜዎች አብረው የሚነሡትም ለዚህ ነው፡፡ የጌታችንን ሁለት ልደታት የመጀመሪያው ‹‹ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት›› ሁለተኛውን ደግሞ ‹‹ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ይህ አገላለጽ ሙሉ በሙሉ በፍጥረት ጊዜ ማለትም እኛ ድርጊቶችን በምንለካበትና እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ሲፈጥር በፈጠረው ጊዜ ከላይ እንዳልነው በታሪክ መለኪያው ጊዜ (Historical time) የተገለጸ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ ›› / ዕብ 1 ፤ 1-2/ እያለ የሚናገረው በዚሁ ጊዜ ስሌት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በፍጥረት ጊዜ ሲለካ የእግዚአብሔር ወልድ ቀዳማዊ ልደት ‹‹ቅድመ ዓለም›› ወይም ከዓለም መፈጠር በፊት ከሚለው ውጭ መግለጫ የለውም፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በፊት ያለውን የሚለካ የፍጥረት ጊዜ ( Historical time ) የለምና፡፡ ከዚሁ ጋር አብረውም ልክ የእርሱን ቀዳማዊ ልደት በፈጣሪ ቅዱስ ጊዜ እንደገለጹት ሁለተኛውን ልደቱን ማለትም ከእመቤታችን በታወቀ ጊዜ የተወለደውንም በእኛ አቆጣጠር የሚገልጹትን ያህል በእግዚአብሔር ቅዱስ ጊዜ ‹‹ዮም›› ዛሬ ብለው ከታሪካዊው ወይም ከታሪክ መነገሪያው ፍጥረታዊ ጊዜ አውጥተው ይነግሩናል፡፡ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ዛሬ ነውና፡፡ ‹‹ዛሬ ወለድኩህ›› ማለትም ቀዳማዊ ልደቱም ደኃራዊ ልደቱም በእርሱ ዘንድ ዛሬ ስለሆነ ነው፡፡ ለሊቃውንቶቻችን ምስጋና ይድረሳቸውና ‹‹ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት›› የሚለው ግሩም አገላለጻቸውም በዘላለማዊ ጊዜ ያለው በፍጥረታዊው ወይም በታሪክ መሰነጃው ጊዜና ዓለም ውስጥ መገለጹን የሚያስረዱበት እጅግ ድነቅ አገላለጽ ነው፡፡