Wednesday, October 1, 2014

ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ርዕይ፡-
ሕፃናትና ወጣቶች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ዐውቀውና አክብረው በሃይማኖትና በምግባር ጸንተው ሲኖሩ ማየት፤

ተልዕኮ፡-

ለሕፃናትና ለወጣቶች ወንጌልን በማዳረስ ለቤተክርስቲያን ተተኪዎችን ማፍራት፤

ዓላማ፡-

ወቅቱን ያገናዘቡ መንፈሳዊ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕፃናትና ወጣቶች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት ሥርዓተ እምነትና ክርስቲያናዊ ትውፊት እንዲያውቁና እንዲጠብቁ ማስተማር፤


አመሠራረትና ታሪክ
የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት በፈቃደ እግዚአብሔር በብፁዕ  አቡነ እንድርያስ አሳሳቢነት በገዳሙ  የተወሰኑ ዲያቆናት በጥቂት የአጥቢያው ወጣቶች  አማካኝነት በ1957 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡ “ዓምደ ሃይማኖት መንፈሳዊ  የወጣቶች ማኅበር” የሚል ሥያሜም ተሰጠው፡፡ በወቅቱ ወላጆችን አሳምኖ ወደ ቤተክርስቲያን ልጆቻቸውን እንዲያመጡ ለማድረግ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይም የወቅቱ የገዳሙ አስተዳዳሪ የነበሩት የሰንበት ት/ቤቱ መሥራች መምህር ቀጸላ ሰይፈ ሥላሴ (በኋላ ብጹዕ አቡነ እንድርያስ) ለወላጆች (ለምእመናን) ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ወላጆች ልጀቻቸውን ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ያመጡ ጀመር፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሲመሠረት የነበሩት ጥቂት አባላት ቢሆኑም ከጊዜ ወደጊዜ የአባላቱ ቁጥር እየጨመረ መንፈሳዊ አገልግሎቱም እየሰፋ መጣ፡፡ የሃይማኖት ትምህርት ከመማራቸው በተጓዳኝም የመዝሙር፣ የልማትና የበጎ አድራጎት ሥራና ሥነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይተገበሩ ጀመር፡፡ በዓበይት በዓላት በንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት በመገኘት ጭምር በመገናኛ ብዙኀን በሚተላለፉ ዝግጅቶች ላይ የመዝሙር አገልግሎት ያቀርቡ ነበር፡፡ 
በተለይ በዚያን ዘመን ወጣት ሴቶች  መቋሚያ ተሸክመው፣ ጸናጽል ይዘው ሲዘምሩ የተመለከቱ ምእመናን እና ጥቂት አገልጋዮች ሥርዓት ተጣሰ፣ ሕግ ተፋለሰ ብለው እንግዳ በሆነባቸው ነገር ተደናግጠው ተቃውሞ ቢያቀርቡም በአባቶች የግንዛቤ ትምህርት  ተሰጥቷቸው አገልግሎቱ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡  ለወጣቱ መጠንከርና በሥነምግባር መታነጽ የሰንበት ትምህርት ቤቱ መሥራች የነበሩት መምህር ቀጸላ ያበረከቱት አስተዋጽዎ እጅግ የላቀ ነበር፡፡ ትውልድ በሃይማኖት እንዲጸና፣ በምግባር እንዲጎለብትና ለሀገር ለወገን የሚጠቅም መልካም ዜጋ ሆኖ እንዲያድግ፤ በአበው  እግር ተተክቶ ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግል ሆኖ ይቀረጽ ዘንድ ከወጣቱ ጋር በጉባኤ በመታደም በቅርበት ሆኖ በመከታተልና ችግሮቻቸውን በመፍታት በመኀከላቸው ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጉ ነበር፡፡

አገልግሎት

ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ትውልድን በሃይማኖት በምግባር እያነ ለአምስት ዓሥርት ዓመታት ተጉዟል፡፡ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ለዲቁና ለቅስና ለመምህርነትለቤተክርስቲያን አስተዳዳሪነት የበቁ ካህናት፣ በሥጋዊ ትምህርት ደረጃቸውም አንቱ የተባሉ ለአገር ለወገን የሚበጁ አገር (ሕዝብ) የጣለባቸውን አደራ በአግባቡ የሚወጡ ታማኝ ዜጎች ተገኝተውበታል፡፡ በቅዱስ ጋብቻ ጻንተው እየኖሩ ያሉ ምእመናን ፈርተውበታል፤ ሕፃናት በሥነምግባር እየተኮተኮቱ አድገውበታል፤ ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት በ50 ዓመት ጉዞ በርካታ አገልግሎቶችን አከናውኗል እያከናወነም ይገኛል፡፡ ራዕዩ ምእመናን በሃይማኖት ማጽናት በምግባር ማጎልበት ለቅዱስ ቁርባን ማብቃትተልኮውም ወንጌልን መስበክ አድርጎ የሚገጥሙትን መሰናክሎች በፈጣሪ ቸርነት በድንግል ማርያም ምልጃ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት  እየተቋቋመ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን አበርክቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ፡-

 

የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት

 

መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ” ማቴ 10፡7

 

ሰንበት ትምህርት ቤት የተመሠረተበት ዋነኛ ዓላማ የአበውን ፈለግ በመከተል የምሥራቹን ወንጌል ላልሰሙት ማሰማት፣ የሰሙትም በተማሩት ወንጌል ጸንተው እንዲቆሙ ማስቻል እንደመሆኑ መጠን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ቃለ ወንጌል ለምእመናን እያስተላለፈ ይገኛል፡፡ መደበኛ የሰንበት ጉባኤያትን በመዘርጋት ለሕፃናትና ለወጣቱ  ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማስተማር፣ በሃይማኖት ጸንተው በምግባር ታንጸው  የእግዚአብሔርን ሕግና ሥርዓት አክብረው በንስሓ ታድሰው(ነጽተው) በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ሕይወታቸውን  ይቀድሱ ዘንድ፣ እንዲሁም ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን የሚያስተምሩ ተተኪ ሰባኪያነ ወንጌል በማፍራት ቃለ እግዚአብሔር እንዲተላለፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡  እንዲሁም ልዩ ልዩ ጉባኤያትን በማዘጋጀት ምእመናንን እያስተማረ በሃይማኖት ለማጽናት በምግባር ለማነጽ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
·        በተለያዩ ምክንያቶች በቤተክርስቲያን ተገኝተው ለመማር ሁኔታዎች አላመች ላላቸው ምዕመናን ባሉበት ቦታ ሆነው የምሥራቹን ወንጌል ያደምጡ ዘንድ  ፣ትምህርተ ሃይማኖት ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ክብረ ቅዱሳን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የቤተክርስቲያን ታሪክ እና ሌሎችንም ትምህርቶች በመጽሐፍ (በሞጁል) አዘጋጅቶ በርቀት (በተዕኮ) ትምህርት ያስተምራል፡፡
·        ሰንበት ትምህርት ቤቱ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች መንፈሳዊ ጉዞዎችን በማዘጋጀት ምዕመናን ከቅዱሳት መካናት በረከት እንዲያገኙ ከማድረጉም በተጨማሪ ተጓዦች  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓትና ትውፊት እንዲያውቁ እያደረገ ይገኛል፡፡
·        ተማሪዎችን ከአስኳላው( ከዘመናዊ) ትምህርታቸው ጎን ለጎን ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ሳምንታዊ ጉባኤ በመዘርጋት ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ርቀው በጉብዝናቸው ወራት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡና  ሀገር ተረካቢዎች እንዲሆኑ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋራ በተጓዳኝም መደበኛ የሠራተኛ ጉባኤ፣ የባለትዳር ጉባኤና የነዳያን ጉባኤ በመዘርጋት ያስተምራል፡፡
·         ኤፍራታ ልዩ መጽሔት በተለያዩ ጊዜያት በማሳተም የሰሌዳ መጽሔቶች በማዘጋጀት፣ በዓላትን አስመልክቶ በራሪ ወረቀቶችንና  አነስተኛ መጽሔቶችን እያዘጋጀ ቃለ እግዚአብሔርን ያስተምራል፤ በይዘቱ ለየት ያለ መንፈሳዊ መጽሐፍ በማሳተምም ለንባብ አብቅቷል፡፡



የመዝሙር አገልግሎት

እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ---”መዝ 46፡7

ምስጋና (ዝማሬ) የሰው ልጅ የተፈጠረበት ተቀዳሚ ዓላማው ነው፡፡ ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤትም መንፈሳዊ ሥርዓታቸውን የጠበቁ  የግእዝና የአማረኛ መዝሙራትን በካሴት፣ በሲዲና በቪሲዲ በማዘጋጀት ለምእመናን አሰራጭቷል፣ እንዲሁም ከሕፃናት ጀምሮ ለአባላቱ በማስጠናት በተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት ላይ የመዝሙር አገልግሎት ይሰጣል፡፡
አዲስ ለሚቋቋሙ ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቁ መዝሙራትን የማሰጠናት አገልግሎት ይሰጣል፡፡

 ሥነ ጥበባዊ አገልግሎት

“እግዚአብሔር በአንድ መንገድ  በሌላም ይናገራል ” ኢዮ 33፡14

 ሥነ ጥበባዊ ዝግጅት መንፈሳዊ ትምህርት ከሚተላለፍባቸው  መንገዶች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ሰንበት ትምህርት ቤቱ  በርካታ መንፈሳዊ ቲያትሮችን( ድራማዎችን) በማዘጋጀት ለምእመናን አቅርቧል፡፡ ከዚህ ጋራ በተጓዳኛ ወደ ተለያዩ ሰንበት ት/ቤቶች በመጓዝ ይሄንኑ ተግባር ያከናውናል፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቱ ወጣቶች የሥነ ጽሑፍ ተሰጧቸው እንዲጎለብት የተለያዩ የመንፈሳዊ የሥነ ጽሑፍ ኮርሶች በማዘጋጀት ለአባላቱና በአጥቢያው ለሚገኙ ሰንበት ት/ቤቶች ጭምር እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡ ተጨማሪም ምሴተ ጥበብ (የግጥም ምሽት ) መርሐ ግብር በማዘጋጀት አባላት ተሰጥኦአቸውን እንዲያጎለብቱ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
 በልማትና በበጎ አድራጎት አገልግሎት
እርስ በእርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ማድረግ ትጉ” 1ተሰ 5፡15
ሰንበት ትምህርት ቤቱ ከሚያከናውናቸው መንፈሳዊ አገልግሎቶች አንዱ የበጎ አድራጎት ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በልማትና በጎ አድራጎት ዘርፍ በርካታ አገልግሎቶችን እያበረከተ ሲሆን፤ ነዳያንን ከልመና እንዲወጡ የሚያግዝ ፕሮጀክት በመንደፍና ምዕመናንን በማስተባበር የመሥራት አቅም ያላቸውና መንቀሳቀሻ  ገንዘብ ያጡ ወገኖችን ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ሥራ ሠርተው እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ ጥቂት የነዳያን ልጆችንም ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን የአስኳላ (ዘመናዊ)ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በየዓመቱ  በዓላትን (የቅዱስ ዮሐንስ፣ /የዘመን መለወጫ/፣ የልደትና የትንሳኤ) አስመልክቶ ነዳያንን ይመግባል፡፡
አባላቱንና ምእመናንን በማስተባበር በጸበል ቦታዎች የሚገኙ ሕሙማንን እንዲሁም የአረጋውያን እና ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት መረጃ ተቋማት በመሄድ እና በመጠየቅ እንዲሁም ቃለ እግዚአብሔርን በማሰተማር የበኩሉን አስተወጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ሰንበት ትምህርት ቤቱ ምእመናንን በማስተባበርና ከአቻ ሰንበት ት/ቤቶች ጋር በመሆን አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጿል፡፡እንዲሁም አቅሙ በፈቀደው መጠንም ለተለያዩ ገዳማት አድባራት የጧፍ፣ የዕጣንና የንዋየ ቅድሳት አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡


እንግዲህ ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት እጅግ ብዙ የሚባሉ አገልግሎቶችን ያከናወነ ቢሆንም ለማሳያ ያህል ከላይ ያነሣነቸውን ጠቅሰናል፡፡ በቀጣይም አምላካችን ልዑል እግዚብሔር በፈቀደ መጠን ከዚህ በበለጠ አገልግሎቱን ለማስፋት ለማጠናከር እንቅስቃሴ በማደረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከእነዚህም መካከል፡-
·        የተልእኮ ትምህርትን ይበልጥ በማጠናከር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በከፍተኛ ሽፋንና ጥራት የእግዚአብሔርን ቃል በስፋት ማዳረስ፤
·        ተተኪ ሰባክያነ ወንጌልን በብዛትና በጥራት ማዘጋጀት፤
·         ከአቻ ሰንበት ት/ቤቶች ጋር በጥምረት በመሥራት የጋራ ርዕይና ተልዕኮ ይዞ መንቀሳቀስ እንዲሁም አዲስ ለሚቋቋሙ ሰንበት ት/ቤቶች በልዩ ልዩ መልክ ድጋፍ ማድረግ፤
·        ወንጌልን በጸሑፍ ከማዳረስ አኳያም መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፤ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ለምዕመናን እንዲዳረሱ ማድረግ ፤
·        ሕፃናት መሠረታዊ የቤተክርስቲያን ትምህርቶችን እንዲያገኙ በማድረግ በሃይማኖትና በምግባር የጠነከሩ ተተኪዎችን ማፍራት፤
       ለዚህም ፡-
·        የአብነት / በስፋትና በተከታታይ መስጠት
·        የተጠና ሥርዐተ ትምህርት በመዘርጋት ዘለቄታዊ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ
ያሬዳዊ ዜማን ለማስጠበቅ የበኩሉን መወጣት፤
      ለዚህም ፡-
·        ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቁ መዝሙራትን በሲዲና በቪሲዲ በማዘጋጀት ለምእመናን ማሰራጨት፣ አባላትን በማስጠናት በልዩ ልዩ ጉባኤያት ላይ እንዲቀርቡ በማድረግ እንዲሁም መዝሙራቱን በጥራዝ በማዘጋጀት ለሌሎች ሰንበት ት/ቤቶች በማዳረስና በማስጠናት የተጠናከረ አገልግሎት መስጠት፤ 
·        በልማትና የበጎ አድራጎት ዘርፍም ችግረኛ ሕጻናትን በተጠናከረ ሁኔታ መርዳት እንዲሁም የገጠር አብያተ ክርስቲያናት የልማት ሥራ ላይ መሳተፍ፤



ከላይ የጠቀስናቸው አገልገሎቶች በቀጣይ ሰንበት ት/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመሥራት ካሰባቸው ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
 በመሆኑም የአገልግሎት ዘርፉ ብዙ ነውና ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ በሙያው፣ ጊዜ ያለው በጊዜው፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ ከምንም በላይ ደግሞ በጸሎት እንድታስቡን አደራ እያልን፤ ሰንበት ትምህርት ቤቱ የሚያከናውናቸውን አገልግሎቶች በሚቻልዎ አቅም በመደገፍ የበኩልዎን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መልክታችን ነው፡፡

የክርስቶስ ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለኛ ደግሞ ጸልዩ”    ስ. 4፡3

ስልክ 011 123 34 19 /// 0921 59 93 44

ፖ.ሳ.ቁ. 30710 አ.አ ኢትዮጵያ

ኢ. ሜይል  amdehaymanot19@gmail.com





No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount