Sunday, October 12, 2014

ስለ አዳምና ሔዋን (ለሕፃናት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 03 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
       
የእግዚአብሔር ልጆች እንደምን ሰነበታችኁ? ደኅና ናችኁ? ትምህርት እንዴት ነው? ጐበዞች፡፡

ባለፈው ጊዜ ስለ ምን እንደተማርን ታስታውሳላችኁ ልጆች? ጐበዞች፡፡ የተማማርነው ስለ ሥነ ፍጥረት ነው አይደል? እስኪ ካስታወሳችኁ አዳምና ሔዋን መቼ ተፈጠሩ ነበር ያልነው? ጐበዞች፡፡ ልክ ናችኁ፡፡ ዓርብ ነበር የተፈጠሩት፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ አዳምና ስለ ሔዋን ታሪክ እነግራችኋለኁ፡፡ እናንተም ለመስማት ዝግጁ ናችኁ አይደል? ጐበዞች፡፡ 

 እግዚአብሔር አምላካችን አዳምንና ሔዋንን ከፈጠራቸው በኋላ በጣም በምታምርና በልዩ ልዩ ዕፅዋት በተዋበች ገነት አስቀመጣቸው፡፡
አዳምም እግዚአብሔር ስላደረገለት ኹሉ እያመሰገነና እየተደሰተ በተድላ በገነት ይኖር ዠመር፡፡ አንድ ቀንም እግዚአብሔር ወደ አዳም መጣና ለአዳም ማስጠንቀቂያ ሰጠው፡፡ “አዳም ሆይ! በገነት ካበቀልኩልህ ዛፍ ኹሉ ትበላለኽ፡፡ የማትበላው አንዲት ዛፍ ብቻ ነው፡፡ እንኳን መብላት ወደ ርሷም አትቅረብ፡፡ እንደነዚኽ ዕፅዋት ለምልመህና አብበህ በገነት ከእኔ ጋር እንድትኖር ከፈለግህ ትእዛዜን ጠብቅ፤ እሺ?! እኔ በጣም እወድኻለኹ፡፡ ስለዚኽ ትእዛዜን ተላልፈህ እንዳትሞትብኝ አደራ፡፡ ልጄ አዳም! አንተ እኮ ለእኔ ልዩ ፍጥረት ነኽ፡፡ በጣም የምታምር ገነትን ያዘጋጀኹልኅም ላንተ ነው፡፡ ስለዚኽ ለመብላት እንዳትሞክር፡፡ ከተድላ ገነት አውጥቼ ወደ ምድር እንዳልጥልህ ትእዛዜን እንዳትተላለፍ፤ እሺ?!” አለው፡፡ አዳምም እሺ ብሎ ለሰባት ዓመት እያመሰገነና እየተደሰተ ከሚስቱ ጋር ኖረ፡፡

 ሰይጣን ግን እጅግ ተንኮለኛ ስለኾነ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ጸጋና ክብር አይቶ ከፍተኛ ቅናት አደረበት፡፡ አዳምን ማሳሳት አለብኝ ብሎም አሰበ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ እባብ ሔደና በዠርባዋ ተሸክማው ወደ ገነት እንትገባ ጠየቃት፡፡ እባብም እሺ አለችውና ወደ ገነት ገባ፡፡
 ከዚያም ያ ሰይጣን በእባቧ አንደበት ሔዋንን ጠራትና “እግዚአብሔር አንቺንና ባልሽን አዳምን ምንድነው ያዘዛችኁ?” ብሎ ጠየቃት፡፡ ሔዋንም “እግዚአብሔር ጌታዬ አዳምን በገነት መካከል ካለችው አንዲት ዛፍ ፍሬ እንዳትበላ፡፡ ርሷን በበላኅ ቀን የሞት ሞት ትሞታለኅ ብሎ አዝዞታል” አለችው፡፡
ሰይጣንም “እግዚአብሔር አትብሉ ያላችኁ እኮ ከርሷ በበላችኁ ቀን እንደ እግዚአብሔር ስለምትኾኑ እንጂ ስለምትሞቱ አይደለም፡፡ ሔዋን ሆይ! እግዚአብሔር ከአዳም በኋላ ፈጥሮሻልና ርሱ የበላይሽና ገዢሽ ኾኖ ይኖራል፡፡ ምክሬን ተቀብለሽ ብትበዪ ግን ክብርሽ ከፍ ይልና ለአዳም አምላኩ ትኾኝዋለሽ” አላት፡፡
 ሔዋንም የሰይጣን ምክሩን በሰማች ጊዜ ዛፏን ለመብላት ጓጓች፡፡ እየሮጠች ሔዳም ቆረጠችና በላች፡፡ ለአዳምም ሰጠችው እና በላ፡፡

 እግዚአብሔር አትብሉ ያላቸውን ዛፍ በበሉ ጊዜም አዳምና ሔዋን ለብሰዉት የነበረው የብርሃን ልብሳቸው ተገፈፈ፡፡ ራቁታቸውም ኾኑ፡፡ ከዚያ በኋላ የበለሱን ቅጠል ሰፍተው እንደ ሽርጥ አገለደሙ፡፡
 እግዚአብሔር አምላክም በገነት መካከል ይመላለስ ነበር፡፡ አዳምና ሔዋንም የእግዚአብሔርን የእግሩን ድምጽ ሰምተው ፈሩ፡፡ በገነት ዛፍ መካከልም ተደበቁ፡፡
 እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ፡- “አዳም! አዳም! ወዴት ነኅ?” አለው፡፡ ከክብሩ የተዋረደውና ምስኪኑ አዳምም “በገነት ውስጥ ድምጽኽን ሰምቼ ዕራቆቴን ስለኾንኩ አፍሬ እንዳታየኝ ብዬ በዛፎች መካከል ተደብቂያለኹ” አለው፡፡ 

እግዚአብሔርም “ዕራቁትኽን እንደኾንክ ማን ነገረኅ? ምናልባት ከዚያች አትብላ ካልኩህ የዛፍ ፍሬ ትእዛዜን ተላልፈህ በላህ እንዴ?” አለው፡፡
አዳምም “ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት አንተ ከከለከልከኝ ዛፍ ርሷ አሳስታ እንድበላ ሰጠችኝና በላኹ” አለው፡፡ 
 እግዚአብሔርም ሔዋንን “አንቺ ሔዋን! ስለምን ትእዛዜን አፈረስሽ?” አላት፡፡ ርሷም “ጌታዬ ሆይ! እባብ አሳተችኝና በላኹ” አለችው፡፡
 እግዚአብሔር አምላክም እባብን “ይኽን የተንኮል ሥራ ሠርተሸልና ከእንስሳትና ከምድር አራዊት ኹሉ ተለይተሸ የተረገምሽ ኹኚ፡፡ በሆድሽም ሒጂ፡፡ አፈርም እየበላሽ ኑሪ” አላት፡፡
 ከዚያም እግዚአብሔር ሔዋንን “ከአዳም በላይ ለመኾን ፈልገሻልና ከአዳም በታች ኹኚ፡፡ ርሱም ይግዛሽ፡፡ በጭንቅ በመከራ ውለጂ” አላት፡፡
 እንዲኹም እግዚአብሔር አዳምን “የሚስትኽን ቃል ሰምተኽ ካዘዝኩኅ ዛፍ በልተኻልና በአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትኹን፡፡ እሾኽና አሜኬላ ታብቅልብኅ፡፡ ወጥተኅ ወርደኅ፣ ላብኽን አንጠብጥበኅ ወዝኅን አፍሰኅ  እስከ ሕይወትኅ ፍጻሜም እንጀራኽን ትበላለኅ” አለው፡፡
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን ከገነት ወደ ምድር አስወጣቸው፡፡ ወደ ገነት ተመልሰው እንዳይገቡም ኪሩብ በሚባል መልአክ የገነትን በር ቈለፋት፡፡

አያሳዝንም ልጆች?! መታዘዝ በደስታ እንድንኖር ያደርጋል፡፡ ሳንታዘዝ ስንቀር ግን ብዙ ችግር ይገጥመናል፡፡ ወላጆቻችን ያዝኑብናል፡፡ እግዚአብሔር ያዝንብናል፡፡ ስለዚኽ ታዛዦች እንኹን፡፡ እሺ ልጆች?! ጐበዞች፡፡
 በሉ ልጆች! ለዛሬ በዚኽ ይበቃናል፡፡ በቀጣይ ክፍለ ጊዜ እስከምንገናኝ ድረስ ደኅና ሰንብቱ፡፡ እግዚአብሔር በሰላም ያገናኘን፡፡ አሜን!!!
እወዳችኋለኁ!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount