Wednesday, October 8, 2014

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል ሦስት)



በዲ/ ያረጋል አበጋዝ

 
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 28 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡


የቀጠለ…


4. ምሥጢር
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የምናየው በብሉይና በሐዲስ የተነገረውን እያመሰጠረ፣ በብዙ አምሳልና ትንቢት ይነገር የነበረውን የአምላክን ከድንግል መወለድ፣ ትንቢቱን ከፍጻሜው ጋር እያዛመደ የሚናገረውን ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናያለን፡፡


4.1 «
ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
 ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዑ ለአብርሃም አብ
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ
ማርያም ፅፀ ሳቤቅ ወምሥራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርግው/ለስግው/ ኮከብ»

«
አሕዛብ በአንቺ የተባረኩብሽ የአብርሃም የግዝረትና የዘሩ ምልክት አንቺ ነሽ፡፡ የድንግልናሽ ጽጌ በግዕ /በግ/ የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ ተሰጠ፡፡ ማርያም ሆይ የተወደደውን ኮከብ የወለድሽ የያዕቆብ ምሥራቅ ነሽ፡፡»
እግዚአብሔር አብርሃምን ከሀገሩና ከወገኑ ተለይቶ እርሱ ወደ ሚያሳየው ሀገር እንዲሄድ ካዘዘው በኋላ «በዘርዕከ ይትባረኩ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር፤ በዘርህ የምድር አሕዛብ ይባረካሉ» /ዘፍጠ12.3/ ብሎ ቃል ኪዳን፣ ከአሕዛብ የሚለይበትና እግዚአብሔርን የሚያመልክ መሆኑ የሚታወቅበት ምልክት የሚሆን ግዝረትን ሰጠው፡፡ እንዲህ ሲል «በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፡፡ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ በእኔና በአንተ ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል» /ዘፍ.17.911/፡፡ «አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ» የሚለው ተስፋ በይስሐቅ አልተፈጸመም፡፡ ምክንያቱም በሰው ላይ የተጣለው ፍርድ በይስሐቅ አልተወገደም፡፡ በይስሐቅ የሚወገድ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ በተሠዋና ዓለምን ባዳነ ነበርና፤ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መምጣትና መሞት ባላስፈለገው ነበርና፡፡ ስለዚህ በዘርህ አሕዛብ ይባረካሉ ተብሎ ለአብርሃም የተነገረው ተስፋ የተፈጸመው ክርስቶስ ከእመቤታችን በድንግልና ሲወለድ ሰው ሲሆን ነው፡፡ አምላክ ሊዋሐደው የሚችል ንጹሕ ሥጋና ነፍስ ይዛ ተገኝታ ለአብርሃም የተነገረውን ተስፋ እንድናገኝ አድርጋለችና፡፡
ለአብርሃም የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ያንጊዜ ያመነና ያላመነ የሚለው በግዝረት እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል መለያው ምልክቱ ጥምቀት ነው፡፡ ከአሕዛብ የሚለየንን፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች የሚያደርገንን ጥምቀት ተጠምቆ ተጠመቁ ያለንን ክርስቶስን ያገኘነው ከእመቤታችን በመወለዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው፡-
«ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዓ ለአብርሃም አብ» ያለው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከአብርሃም ዘር ነው፡፡ /ዕብ.2.16/፡፡ ክርስቶስን ያስገኘች እመቤታችን የአብርሃም ዘር መሆኗን ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ አንድ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ በእርሱ አማናዊ መሆኑንም ያጠይቃል፡፡

4.2
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ወሁብ
ማርያም ፅፀ ሳቤቅ ወምስራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርግው ኮከብ
 ይስሐቅ ለመሥዋዕት በቀረበ ጊዜ ከመሞት ያዳነው በግ ከዚህ መጣ ሳይባል በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል፡፡ /ዘፍ.22፡13/፡፡ አብርሃም በጉን ሠውቶ የታሰረውን ይስሐቅን ፈትቶታል፡፡ ይስሐቅ የዓለሙ ምሳሌ ሲሆን በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በጉ የተያዘበት ዕፀ ሳቤቅ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉ በዕፀ ሳቤቅ ታስሮ እንደተገኘ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከእመቤታችን ነው፡፡ በግ ቤዛ ሆኖ ይስሐቅን ከሞት እንዳዳነው ሁሉ ክርስቶስም ስለ ዓለሙ ኃጢአት ሞቶ ለዓለሙ ቤዛ ሆኖአል፡፡ /ዮሐ.3.1617/፡፡
 ደራሲው የምሳሌውን መፈጸም ካስረዳ በኋላ «ወምሥራቅ ዘያዕቆብ» ይላል፡፡ በለዓም « ኮከብ ይሠርቅ እም ያዕቆብ ወየአትት ኃጢአተ እም እስራኤል፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ኃጢአተኝነትንም ከእስራኤል ያስወግዳል. . .» ብሎ ትንቢት የተናገረለትን ኮከብ የወለደች እርሷ መሆኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ /ዘኁል.22.17 ፤ኢሳ.27.959.20 ሮሜ.11.26/ ፡፡

4.3. «
ሰመዩኪ ነቢያት እለርእዩ ኅቡአተ፣
ገነተ ጽጌ ዕፁተ ኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፣
እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተ ዳዊት ትእምርተ
ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ
ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ፡፡»
ትርጉም
«ምሥጢርን ያዩ ነቢያት የተዘጋች የምሥራቅ በር የታተመች ገነት እያሉ ጠሩሽ፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ በኢሳይያስ አማካኝነት በግልጽ ተናገረ፡፡»
ከሩቅ ያለውንና ወደፊት የሚሆነውን በትንቢት መነጽር አቅርበው ያዩና ሥውሩ ምሥጢር የተገለጠላቸው ነቢያት «ገነተ ጽጌ ዕፁተ፤ ወልኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፤ የታተመች ምንጭ የተዘጋች የምሥራቅ በር» እያሉ ጠሩሽ፡፡
ሰሎሞን በመኃልዩ «እኅቴ ሙሸራ የተቆለፈች ገነት የተዘጋ ምንጭ ናት» ይላታል፡፡ በዚህም እመቤታችንን በውስጥዋ አትክልት ሲኖር ነገር ግን ወደዚህች ቦታ የሚደርስ የለም ተቆልፎአልና፡፡ እመቤታችንም በንጽሕናና በድንግልና የታጠረች ስለሆነች ከእርስዋ የተወለደ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
  የተክል ቦታ ዘር ሳይዘራባት ወይንም ተክል ሳይተከልባት እንዲሁም የሚንከባከበው ሳይኖር ሊያፈራ አይችልም፡፡ ይህች ገነት ምንም ነገር የማይደርስባት የተቆለፈች ስትሆን አትክልት ግን አለባት፡፡ እመቤታችንም በድንግልናና በንጽሕና የፀናች ስትሆን እንበለ ዘር ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡
 / የታተመች ምንጭ
 ምንጩ የታተመ ሲሆን ነገር ግን ውኃ ያለው ነው፡፡ እመቤታችንም በድንግልና የፀናች ስትሆን በእናትነት ክርስቶስን ወልዳለች፡፡ ሕዝቅኤልም «ወርኢኩ ኅተ በምሥራቅ፣ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦኦ ዘእንበለ እግዚእ ኃያላን ቦአ ውስቴታ ወወጽኣ. . . ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡» አለኝ ይላል፡፡ /ሕዝቅ.44.1 3/፡፡
 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ማለቱ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ፍፁም ሰው ሆኖ ከእርስዋ ተፀንሶ ተወልዷልና ነው፡፡
 ይህ ሕዝቅኤል ያየው ሕንፃ በጥሬ ትርጉሙ ተወስዶ ቤተመቅደስ ነው እንዳይባል ቤተመቅደስ የሚሠራው ሕዝቡ አምልኮቱን ሊፈጽምበት ስለሆነ ከተሠራ በኋላ ለምን ይዘጋል) «በመካከላቸው አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝእንዲል፡፡/ዘጸ.25.8፡፡/
 ይኸው ነቢይ ስለ ቤተመቅደስ በተናገረበት ቦታ «. . . ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን ፡፡ የደኅንነቱን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት» ይላል፡፡ /ምዕ.46.12/፡፡ ሰሎሞንና ሕዝቅኤል ስለእርስዋ የተምሳሌትነትና በትንቢት የተናገሩላት እርስዋ ድንግል ማርያም መሆንዋን ከዘከረ በኋላ ነቢያት ብቻ ሳይሆኑ ራሱ እግዚአብሔርም ምልክት መስጠቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ «እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተ ዳዊት ትእምርተ ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ» ይላል፡፡
 ነቢዩ ኢሳይያስ «ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል. እነሆ ድንግል ትፀንሳለች.ወንድ ልጀም ትወልዳለች. ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች» /ኢሳ.7.1314/ በማለት እግዚአብሔር ሰውን ይቅር የማለቱና የሰጠውን ተስፋ የመፈጸሙ ምልክት በድንግልና መውለድ መሆኑን ተናገረ፡፡ መልአኩ ለእረኞች የጌታን መወለድ ብሥራት ከነገራቸው በኋላ ሄደው እንዲያገኙት ሲልካቸው «ይህም ምልክት ይሆንላችኋል» ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ» ነበር ያላቸው፡፡ /ሉቃ.2.12/፡፡ ሰብአ ሰገልም «ሕፃኑን ከእናቱ  ከማርያም ጋር አዩት»/ማቴጠ2.11/፡፡ የድኅነታችን ምልክት የክርስቶስ በድንግልና ከእመቤታችን መወለድና መታየት ነው፡፡ እኛም እንደ ሰብአ ሰገል እውነተኛውን ክርስቶስን የምናገኘው ከእናቱ ጋር ነው፡፡ የእውነተኛ ሃይማኖት ምልክትም ናት፡፡ ክርስቶስን በእኛ ባሕርይ ከመውለዷም በላይ በስደቱ፣ በመዋዕለ ትምህርቱ በስቅለቱ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ሲያድል ሁሉ አልተለየችም፡፡ ስለዚህ እኛም ረቂቅ ምሥጢርን ዐይተው በተለያየ ስያሜ እንዳመሰገኗት ነቢያት ልናመሰግናት ይገባል፡፡ ይኸውም የሚጠቅመው ራሳችንን ነው፡፡ እርስዋማ ምን ጊዜም የተመሰገነች ናት፡፡
ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount