Thursday, October 2, 2014

ሰላም ተዋሕዶ

በብጹዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩ


ሰላም ተዋሕዶ ሰላም ኦርቶዶክስ
የአትናቴዎስ ሐውልት የዲዮስቆሮስ፡፡
  የአዳም መመኪያ የሔዋን ሀገር
  አንቺ አይደለሽም ወይ የቅዱሳን ክብር?
በከንቱ የሞተው የአቤል መሥዋዕት
የኄኖክ ሃይማኖት የአዳንሽው ከሞት
አንቺ የኖኅ መርከብ የሴም በረከት፡፡
  በአብርሃም ድንኳን ተወልደሽ ያደግሽ
  የይስሐቅ መዓዛ ወደር የሌለሽ
  ያዕቆብ በሕልሙ በቤቴል ያየሽ
  የዮሴፍ አጽናኙ ተዋሕዶ አንቺ ነሽ፡፡

የሙሴ ጽላት ነሽ የአሮን በትር
የኢያሱ ሐውልት የጌዴዎን ጸምር፡፡
  የሳሙኤል ሙዳይ የእሴይ ትውልድ
  የዳዊት በገና የሰሎሞን ዘውድ
  የታተመች ገነት የምስጢር ጕድጓድ፡፡
ቡኣዴና ኅድረት የኬልቄዶን ዘር
ቱሳሔና ሚጠት ውላጤም ጭምር
ያልተቀላቀለሽ ንጽሕቲቱ ምድር
ኢሳይያስ አይቶ በሩቅ መነጽር
ስለ ቅድስናሽ ኾነ ምስክር፡፡
  የንስጥሮስ ወንድም ልዮን ያልደፈረሽ
  የዳንኤል ድንግል ተዋሕዶ አንቺ ነሽ፡፡
በነኤልያስ ቤት የወርቅ መሶብ
በውስጥሽ የተሞላ የምስጢር ምግብ
የኤልሳዕ ማሰሮ የሕይወት መዝገብ፡፡
  ፋራን የምትባል የዕንባቆም ተራራ
  ኹሉን የምታሳይ ከቀኝም ከግራ፡፡
የሕዝቅኤል እልፍኝ ባለአንድ በራፍ
የማትከፈቺው በኬልቄዶን ቁልፍ፡፡
  የሕግ መፍለቂያ የነጻነት ቦታ
  የሚክያስ ሀገር አንቺ ነሽ ኤፍራታ፡፡
ዕፀ ሕይወታችን የኤፌሶን ቅርስ
የተፈወሱብሽ እነ አቡነ ቄርሎስ፡፡
  ለተፈወስንብሽ ከኬልቄዶን ቁስል
  ተዋሕዶ ለአንቺ ዕልል እንበል፡፡
አንቺን በማየቱ በብርሃን ተቋም
ደስ አለው ከልቡ ዘካርያስም፡፡
  በውስጥም በውጭም የሌለብሽ እንከን
  የሕይወት መዝገብ ነሽ ተዋሕዶአችን፡፡
ሐዋርያት ይምጡ ያውሩን ያንቺን ዜና
የሚያውቅ ሲናገር ደስ ያሰኛልና፡፡
  ሰማዕታት ልጆችሽ የጻፉሽ በደም
  የሕይወት መጽሐፍ ነሽ የጽድቅ የሰላም፡፡
አንቺን ለመጠበቅ እስከ ዓለም ፍጻሜ
ቃል እንገባለን ባለንበት ዕድሜ፡፡
  እናምናለንና በፈጣሪያችን
  ከአንቺ እንደማንለይ ምን ጊዜም ቢኾን፡፡


ምንጭ፡- መለከት መጽሔት፣ ጥር 1985 ዓ.ም.

1 comment:

  1. "ካዲሳባ ዝዋይ በግዜ ለመግባት እየተጣደፉ:
    ብጹዕ ጎርጎርዮስ በሚያስደንቅ ግርማ በመኪና
    አለፉ።"
    ወርቅነሽ ቱፋ

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount