Monday, October 6, 2014

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል ሁለት)



በዲ/ ያረጋል አበጋዝ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 26 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡


የቀጠለ…


2. ታሪክ

በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እያነሣ የሚሔድና በዚያውም ከታሪኩ ጋር አብሮ ጸሎትና ምሥጢር የያዘ ነው፡፡ ታሪክን ከሚያነሡት መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡


2.1. «እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦተ ሕግ ከመ ዘፈነ፣
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ስነ፣
ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐተኪ ቁርባነ፣
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ፡፡

ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው ባስመጣ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሲዘምር ሜልኮል ተመልክታ በልብዋ ናቀችው፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ስላዘነባት ልጅ ሳትወልድ ሞታለች፡፡ ሳሙ.612-23፡፡ ደራሲውም ይህንን ታሪክ ካስታወሰ በኋላ «ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ - ዳዊት ለእመቤታችን ምሳሌ በሆነች በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘመረ እኔም በሥዕልሽ ፊት ላንቺ እዘምራለሁ» «ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ ሜልኮል፡- በዳዊት ይቀርብ የነበረውን የታቦተ ጽዮንን ምስጋና በመናቋ እንደተረገመች ያንቺንም ተአምርሽንና ምስጋናሽን የሚንቅ ሁሉ በሰውና በመላእክት አፍ የተረገመ ይሁን» የሚል ነው፡፡ ሜልኮል የምሳሌዋን የታቦተ ጽዮንን ምሥጋና በመናቋ ከተረገመች ዛሬ የአማናዊቷን ታቦተ ጽዮን የእመቤታችንን ምሥጋና የሚንቁና ምሥጋና የሚያቀርቡትን የሚነቅፉ ሰዎች ምን ያኽል የተረገሙ ይሆኑ? እነዚህም «በድፍረትና በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ» /መዝ.3 18/ ባለው ርግማን የተረገሙ ናቸው፡፡

2.2. እንበይነ አውሎጊስ ለዳንኤል አመ አርአዮ ስቅለተ፣
ከመ እገሪሁ ሰዓምኪ ወሰአልኪዮ ምሕረተ፣
ለተአምረ ሣህል ወልድኪ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ዘሞተ፣
እንዘ ታዘክሪዮ ድንግል ይምሐረኒ ሊተ፣
ከናፍሪሁ ጽጌ አንኂ ስዕመተ፡፡

አውሎጊስ የሚባል የወፍጮ ድንጋይ እየጠረበ በመሸጥ ከዚያ በሚያገኘው ትንሽ ገቢ የሚተዳደር ደኃ ሰው ነበር፡፡ የሚያገኘውንም ገንዘብ ለራሱ ትንሽ ለዕለት ኑሮው ካስቀረበ በኋላ ከርሱ የባሰባቸው ችግረኞችን እየረዳ ይኖር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ግብር ሳለ አባ ዳንኤል የሚባል ባሕታዊ ያየዋል፡፡ ይህም ባሕታዊ አውሎጊስ በዚህ በድህነት ኑሮው እንደዚህ ድሆችን የሚረዳ ከሆነ ብዙ ገንዘብማ ቢያገኝ ምን ያክል ብዙ ሰው በረዳና መልካም ሥራ በሠራ ነበር» ብሎ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ብዙ ሀብት እንዲሰጠው ሱባኤ ያዘ፡፡ እግዚአብሔርም ሀብት ለዚህ ሰው /ለአውሎጊስ/ እንደማይጠቅመው ቢነግረውም አባ ዳንኤል በራሱ ሀሳብ ብቻ በመጓዝ ሀብቱን እንዲሰጠው አጥብቆ ስለተማፀነ እንደለመነው ሊያደርግለት ጸሎቱን ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ አውሎጊስ እንደልማዱ ድንጋይ ሲቆፍር በማሰሮ የተቀበረ ወርቅ አገኘ፡፡ ወርቁን ወስዶ ለንጉሡ ሰጠ፡፡ ንጉሡ ወርቅ ሲያገኝ ለራሱ ሳያደርግ ለንጉሥ የሚያመጣ ሰው ምን ያክል ታማኝ ቢሆን ነው ብሎ በዚያው በቤተ መንግሥቱ እንደራሴ አድርጎ ሾመው፡፡ አውሎጊስ ከተሾመ በኋላ አጃቢው ክብሩና ሀብቱ ሲበዛ ትሩፋት መጨመሩ ቀርቶ የቀደመ ሥራውንም ተወ፡፡ ለተበደለ የማይፈርድ ባለጉዳይ የሚያጉላላ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዳንኤል በሕልም እግዚአብሔር ሲቆጣውና ሲፈርድበት አየ፡፡ የማይገባ ልመና ለምኖ አውሎጊስን የቀደመ ትሩፋቱን እንዲተውና አሁን እንዲበድል ምክንያት ሆኗልና፡፡ አባ ዳንኤል በደሉ ገብቶት ከሥዕለ ማርያም ሥር ወድቆ ተማፅኖ እመቤታችን ልጇን ተማጽና ይቅር አስባለችው፡፡
አባ ዳንኤል በሕልም ያየው ነገር ስለከበደው ምናልባት አውሎጊስ ድሀ በድሎ ፍርድ አጓድሎ እንደሆነ ብሎ ሊያየው ቢሄድ እርሱንም የማያናግረው ሆነ፡፡ «ስለ ሰው ፍቅር የሞተ ልጅሽን ስለ አባ ዳንኤል ለምነሽ እንዳስማርሽው እኔንም ይቅር እንዲለኝ የጽጌ ልጅሽን ምሕረት ለምኝልኝ» በማለት እኛንም ባላወቅነው እየገባንና እየፈረድን ለሚመጣብን ቅጣት እንድታስምረን የሚያመለክት ነው፡፡

2.3. ረዳኢተ ድኩማን ዘይረድአኪ ኢትኃሥሢ፣
እምንበረ ላዕክኪ በምዕር ከመ ገፍታዕኪዮ ለወራሲ፣
ለገፍትዖ ፀርየ ድንግል ኃይለ ጽጌኪ ልበሲ፣
እንዘ ይሣለቅ ተአምረኪ ወሐሰተ ይሬሲ፣
መፍትውኑ ከመ ይህየው ከይሲ፡፡

የእመቤታችንን ተአምር አሰባስቦ የጻፈው ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ እመቤታችንም ለዚህ ውለታው ሌላ ሰው የማይቀመጥበት ሰማያዊ ወንበር እና ሌላ ሰው የማይለብሰው አጽፍ ሰጥታዋለች፡፡ ከደቅስዮስ ዕረፍት በኋላ በእርሱ ቦታ የተሾመው ኤጲስ ቆጶስ በዚህ መንበር ለመቀመጥና አጽፉን ለመልበስ ሲል «ተው ይህ ለደቅስዮስ ብቻ የተሰጠ ነው» ቢሉት «እኔም እንደርሱ ኤጲስ ቆጶስ ነኝ ከእርሱ በምን አንሳለሁበማለት ከወንበሩ ሲቀመጥ ወዲያው ሞቷል፡፡ ከላይ የተጻፈው ድርሰትም የሚያስረዳው ይህንን ነው፡፡ «ድኩማንን፣ ችግረኞችን የምትረጅ አንቺ ግን ረዳት የማትሽ ሆይ ከወዳጅሽ ከደቅስዮስ ወንበር ላይ በትዕቢትና በድፍረት የተቀመጠውን እንደተቀበልሽው የእኔንም ጠላቶች አጋንንትን እኩያት ኃጣውእን ለማስወገድ የጽጌሽን ማለት የልጅሽን ኃይል ይዘሽ ተነሽ» በማለት ለወዳጆቿ የምትቆም እመቤታችን ከጠላታችን እንድትታደገን ከታሪኩ አንጻር የቀረበ ጸሎት ነው፡፡

2.4. «በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፌል ዘአጸዋ፣
እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣
ተፈሥሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣
በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አቲዋ
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ጼዋ፡፡

አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ከገነት ተባረው ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው ገነትን ሱራፌል መልአክ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ ይጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀት ገነትን «እንበለ ጽጌከ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፤ ያለ አንቺ ጽጌ ያለ ክርስቶስ በሱራፌል ስትጠበቅ የነበረችውን ገነት ሊከፍታት የቻለ ማንም ፍጥረት የለም» ዘፍ.324፡፡ ካንቺ በተገኘ በክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሯና ቦታዋ የተመለሰች ሔዋን የእናቱን ጡት ጠብቶ ደስ እንደሚሰኝ እንደሚዘል እንቦሳ ደስ ተሰኘች፡፡ በአጠቃላይ ይህ የሚያስረዳው ያለ ክርስቶስ ሰው መሆንና በመስቀል ተሰቅሎ ቤዛ መሆን ማንም የገነትን በር ሊከፍት እንደማይችል ሲሆን የተዘጋውን የገነት በር የከፈተና የሰው ልጅ ያጣውን የልጅነት ጸጋ የመለሰ ክርስቶስ ደግሞ ከእመቤታችን የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት «መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ» ኢሳ.461፡፡ እንዳለ የተዋረደው የሰው ልጅ የከበረበትና የዳነበት መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽዮን ከተባለች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ለዓለሙ ያበረከተች እርሷ ናት፡፡
3. ተግሣጽ

አባ ጽጌ ድንግል ይህንን ማኅሌተ ጽጌ ሲደርስ ለመስቀልና ለእመቤታችን ክብርና ስግደት አይገባም የሚሉ ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ መናፍቃን ተነሥተው ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጉባኤ አሠርተው አከራክረው መናፍቃኑ ተረትተዋል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ውስጥ እነዚህን የእመቤታችንን ተአምርና ክብር በመግለጽ መናፍቃንን በመገሰጽ በዚህ የተግሣጽ ድርሰታቸው አስተምረዋል፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑትን እንመልከት  
ከመ ይትፌሣሕ ጻድቅ ሶበ ይሬኢ በቀለ፣
በተበቅሎ ፀር ያርኢ ዘተአምርኪ ኃይለ፣
እፎ የሐዩ እመአምላክ እንተ ኪያከ ፀአለ፣
አኮኑ በፍትሐ ጽጌኪ ይሙት ተብህለ፣
ላዕለ አቡሁ ወእሙ ዘአሕስመ ቃለ፡፡

 ጻድቅ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሲበቀልለት ሲያይ ደስ ይለዋል፡፡ ይኸውም የአንቺን ተአምር ኃይል ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ያንቺን ተአምር የሚንቁና አንቺን የማያከብሩ ከሐድያን እንዴት በሕይወት ሊኖሩ ይገባቸዋል? ምክንያቱም «በልጅሽ በክርስቶስ ትእዛዝ «እናቱን ወይም አባቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል» /ዘጸ.2117/ ተብሎ ተፈርዷልና፡፡ እናት አባቱን የሰደበ ሞት የሚገባው ከሆነ ክርስቶስ ሰማያዊውን አምላክ ወልዳ፣ ጡቷን አጥብታ፣ አዝላ፣ ተሰዳ ለዓለም ሕይወት ባበረከተችው በድንግል ማርያም ላይ ቃልን የተናገረማ እንዴት ያለ መከራ ይጠበቀው ይሆን?
  ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount