Wednesday, May 9, 2012

አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ =+=በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ =+=


ወንድሞቼ ሆይ! ወደ ቤተ ክርስቲያን ውድ ስጦታዎችን ይዛችሁ ስትመጡ አያለሁ፡፡ መልካም አድርጋችኋል፡፡ ነገር ግን ስትመለሱ ደግሞ መበለቶችን፣ ደሀ አደጎችንና ሕጻናትን ስትበድሉ አያችኋለሁ፡፡ ታድያ ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ምሥዋዕና ጽዋዕ ብታቅረቡ ምን ይጠቅማችኋል? ለምንስ መሥዋዕቱን ማክበር ስትፈልጉ አስቀድማችሁ ልባችሁን መባ አድርጋችሁ አታቀርቡም? ልባችሁ በጭቃ ተጨማልቆ ምሥዋዑ እንኳን ወርቅ ፕላቲንየምስ ቢሆን ምን ይረባችኋል? ምንስ ይጠቅማችኋል?

       ተወዳጆች ሆይ! አመጣጣችን በወርቅ የተለበጠ መሠዊያ ለማቅረብ ሳይሆን ይኸን ከልብ በመነጨ ለማቅረብ ይሁን፡፡ ከልባችን የምናቀርበው ነገር ሁሉ ከወርቅ የበለጠ መባ ነው፡፡ ልብ በሉ! ቤተ ክርስቲያን የወርቅ ወይም የነሐስ ማቅለጫ ቦታ አይደለችም፤ ለቅድስና የተጠሩ ሁሉ እና የመላእክት ኅብረት እንጂ፡፡ ስለዚህ ከስጦታችሁ በፊት ልባችሁን ይዛችሁ ኑ፡፡ እግዚአብሔር ሥጦታችንን የሚቀበለው ደሀ ሆኖ ሳይሆን ስለ ነፍሳችን ብሎ ነውና፡፡
 ክርስቶስን ማክበር ትወዳላችሁን? እንግዲያስ ዕራቆቱን ስታዩት ችላ አትበሉት፡፡ እናንተ ወደ ቤተ መቅደስ ስትመጡ እጅግ ውድ በሆኑ ልብሶች አጊጣችሁ ስትመጡ እርሱ በብርድና በመራቆት ሊሞት ነውና ብያንስ ትንሽ እንኳን እዘኑለት፡፡ ቤተ መቅደስ ረግጣችሁ ቤተ መቅደስ አትምጡ፡፡ በቃሉ “ይህ ሥጋዬ ነው” ያለው ጌታ በተመሳሳይ ቃሉ “ተርቤ ስታዩኝ አላበላችሁኝም፤… ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” ይለናል /ማቴ.25፡42፣45/፡፡ በእውነት ይህ ምሥዋዕ ልብሳችሁን ሳይሆን ልባችሁን ነው የሚፈልገው፤ እነዚህ የተራቡት ግን ልብስም ምግብም ያስፈልጋቸዋል፡፡
ስለዚህ በሕይወታችን ክርስቶስ እርሱ እንደሚወደው ማክበርን እንማር፡፡ እከብር አይል ክቡር የሆነው እርሱ ደስ የሚያሰኘው ክብር እኛ ውድ ነው ብለን የምናቀርበው ሳይሆን እርሱ ሊቀበለው የወደደውን ስናቀርብለት  ነው፡፡ ጴጥሮስ ጌታን ያከበረ መስሎት እግሩን መታጠብ እምቢ አለ፤ ይህ ግን በጌታ ዐይን ማክበር ሳይሆን ተቃራኒው ነበር፡፡
        ስለዚህ ጌታን ማክበር ስትፈልጉ ገንዘባችሁን አስቀድማችሁ በድሆች ላይ አውሉት፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚፈልገው ወርቃማ ምሥዋዕን ሳይሆን ወርቃማ ነፍሳትን ነውና፡፡ ይህን ሁሉ የምላችሁ ግን መባ እንዳትሰጡ እየከለከልኳችሁ አይደለም፤ ይልቁንም ከዚሁ ጐን ለጐን እንደውም አስቀድማችሁ መመጽወትን እንድትለማመዱ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለምሥዋዑ ያመጣችሁትን መባ ይቀበላል፤ ለድሆች የምትሰጡትን ደግሞ ከዚሁ በበለጠ ይቀበላችኋል፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ብታመጡ ተጠቃሚዎች እናንተ ብቻ ናችሁ፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ድሀውም እናንተም ትጠቀማላችሁ፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ስትሰጡ ውዳሴ ከንቱ ሊያመጣባችሁ ይችላል፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ርኅራኄንና ሰው ወዳድነትን ያመጣላችኋል፡፡ ጌታ ተርቦ ሳለ ምሥዋዑ በወርቅ ቢንቆጠቆጥ ምን ጥቅም አለው? ከሁሉም በፊት ጌታ ተርቦ ስታገኙት አብሉትና ከዚያም ምሥዋዑን አስጊጡት፡፡ ነገር ግን እርሱ አንድ ኩባያ ውኃ እንኳን ሳያገኝ እናንተ ጽዋውን የወርቅ ጽዋ ታደርጉታላችሁን? እርሱ ገላውን የሚሸፍንባት ቁራጭ ጨርቅ እንኳን አጥቶ እናንተ ምሥዋዑን በወርቅ ልብስ ታስጌጡታላችሁን? ከዚሁ የምታገኙት መልካም ነገርስ ምንድነው? እስኪ ንገሩኝ! እርሱ የሚበላውን ዳቦ አጥቶ እናንተም ረሀቡን ሳታስታግሱለት ወደ ቤተ መቅደሱ መጥታችሁ ምሥዋዑን በብር ስታስጌጡት የሚያመሰግናችሁ ይመስላችኋልን? የማይቆጣችሁስ ይመስላችኋልን? እንደገና አንድ ሰው ቁራጭ ጨርቅ ለብሶ ብርድና ሐሩር እያፈራረቀ ሲያቆራምደው እየተመለከታችሁ ምንም ልብስ ሳትሰጡት በቤተመቅደስ መጥታችሁ “ይህ ሥጦታ ለጌታዬ ክብር ነው” ብላችሁ ምሥዋዑን በወርቅ ብታስጌጡት ጌታ፡- “ፌዘኞች!” ብሎ እንደሰደባችሁት የማይቈጥረው ይመስላችኋልን?
 እርሱ መጠለያ ፈልጐ እንግዳና መንገደኛ ሆኖ ሲዞር እናንተ ግን ባለ ብዙ ክፍል ቤት እያላችሁ ችላ ብላችሁታል፡፡ ቤታችሁ በተለያዩ የመብራት ዓይነት አጊጦ ሳለ ክርስቶስ ግን በእስር ቤት ነው፤ ልታዩት እንኳን አልወደዳችሁም፡፡ ወንድማችሁ በጣም ተቸግሮ እያያችሁት እናንተ ግን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ለማስጌጥ ትሮጣላችሁ፤ ነገር ግን አማናዊው ቤተ መቅደስ ከሕንጻው የበለጠ ወንድማችሁ ነበር፡፡
                       ወንድሞቼ! ልንገራችሁና እናንተም አድምጡኝ! ለሕንጻው ቤተ መቅደስ የምታመጧቸው ጌጣጌጦች አንድ ኢአማኒ ንጉሥ፣ ወይም ጨካኝ መሪ፣ ወይም ሌባ ሊዘርፋቸው ይችላል፡፡ ወንድማችሁ ሲራብ፣ እንግዳ ሆኖ ሲመጣ እና ሲታረዝ የምታደርጉለትን ማንኛውም ነገር ግን እንኳንስ ጨካኝ መሪ፣ እንኳንስ ጨካኝ ሌባ የጨካኞች አባት የሆነው ዲያብሎስም መውሰድ ይቅርና ሊያይባችሁም አይችልም፡፡ ገንዘባችሁ ሁሉ በአስተማማኝ ቦታ ይከማቻል፡፡
                 ምጽዋት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ትከፍታለች፡፡ “ጸሎትህ እና ምጽዋትህ ለመታሰብያ እንዲሆን ዐረገ” እንዲል /ሐዋ.10፡4/፡፡ ምጽዋት ከመሥዋዕት ሁሉ ትበልጣለች፡፡ “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማውቅ እወዳለሁ” እንዲል /ሆሴ.6፡6/፡፡ ምጽዋት ኃጢአትን ታነጻለች፡፡ “የሚወደድ ነገርስ ለምጽዋት ስጡ፤ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል” እንዲል /ሉቃ.11፡41/፡፡ እንግዲያስ አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ፡፡
 ይህን ሁሉ እንድናደርግና የሚመጣውን ዓለምም በቸርነቱ እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!

1 comment:

  1. Kale Hiwet Yasemalin Wendmachin betam girum tsihuf new. Kidus Yohanis Afwerek be tselotu ayeleyen.

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount