Saturday, May 19, 2012

የዮሐንስ መጥምቅ ምስክርነት (የዮሐንስ ወንጌል የስድስተኛው ሳምንት ጥናት)!!

“አይሁድም አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው” /ቁ.19/፡፡  ቅናት ክፉ ነገር ነው፡፡ ክፋትነቱም ለአድራጊው እንጂ ለሚደረግበት ሰው አይደለም፡፡ ሐዋርያውስ፡-“ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?” አይደል ያለው /1ቆሮ.6፡7/? ወንጌላዊው እነዚህ አይሁድ ከየት እንደመጡ የሚነግረን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከዋናው ቤተ መቅደስ የመጡ እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ለመናገር እንጂ፡፡ ዮሐንስ ማን መሆኑን እማ “ይህ ሕጻን ምን ይሆን” እያሉ ሲደነቁ ነበርና /ሉቃ.1፡66፣ St. John Chrysostom homily on the Gospel of John, homily 16/፡፡ ተራው ሕዝብ ግን መጥምቁ በሚናገረው ሁሉ በጣም ስለሚማረኩ በቀላሉ የሚለውን ሁሉ ያምኑት ነበር፡፡ ስለዚህም ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ዕድል ነበረው፤ “አዎ መሲሑ ነኝ” ቢላቸው እንኳን ባላንገራገሩ ነበር፤ አላደረገውም እንጂ /Augustin sermon 289:4/፡፡ ካህናቱና ሌዋውያኑ ግን አይቀበሉትም፡፡ በእውነትም የእፉኝት ልጆች ናቸው፡፡ ወደ ወንዙ እየመጡ ሲጠመቁ የነበሩ ሰዎች አሁን ከሕዝቡ የሚቀበሉትን ከበሬታ ስለቀነሰባቸው “ማን ነህ” ይሉት ጀመር፡፡ ብጹዕ ዮሐንስ ግን ተራው ሕዝብ “መሲሑ ሊሆን ይችላል” የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤአቸው ለማቅናት ሳይክድ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ይላቸው ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የእነዚህ ክፉ እረኞች ምክንያታዊነትም ከንቱ ለማድረግ ወንጌላዊው “ዮሐንስ መሰከረ” እያለ ሦስት ጊዜ ይነግረናል /ቁ.8፣ 15፣ 20/፡፡
 ከዚያ በኋላ ወደ ሌላ ጥያቄ ያመሩና፡- “እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ይሉታል /ቁ.20/፡፡ ምክንያቱም ከመሲሑ በመቀጠል በጉጉት የሚጠብቁት ኤልያስ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ኤልያስ የዳግም ምጽዓት አዋጅ ነጋሪ በመሆን ከዮሐንስ ጋር ቢመሳሰልም “እኔ ኤልያስ አይደለሁም” ይላቸው ነበር /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡
 ምናልባት ከእናንተ መካከል ጌታ፡- “`ኤልያስስ መጥቷል` ካለው ጋር አይጋጭምን?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል /ማቴ.17፡10/፡፡ በፍጹም! ምክንያቱም ቅዱስ ገብርኤል ይህንን ሐሳብ ግልጽ ሲያደርግልን “እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ… በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል” ብሎናል /ሉቃ.1፡17/፡፡ ይህም ማለት “ዮሐንስ በኤልያስ መንፈስ መጣ እንጂ በቁሙ ኤልያስ አይደለም” ማለት ነው፡፡ እውነት ነው! ኤልያስ የዳግም ምጽዓት አዋጅ ነጋሪ እንደሆነ ሁሉ በኤልያስ መንፈስ የመጣው ዮሐንስም ለመጀመርያው ምጽዓት አዋጅ ነጋሪ ነበርና /Gregory the Great, Forty Homelies, 4/፡፡
  አሁንም ይቀጥሉና፡- “ታድያ ኤልያስ ካልሆንክ በኦሪት ዘዳግም ሙሴ ይመጣል ያለው ነብዩ ነህን?” ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ይጠቁታል /ዘዳ.18፡15፣ Origen: commentary on the Gospel of John/፡፡ እርሱ ግን “ነብይ አይደለሁም” ሳይሆን “እናንተ የምትሉት ነብይ አይደለሁም” ይላቸው ነበር /ማቴ.11፡9፣ ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 የሚገርመው ግን እነርሱም ጥያቂያቸውን ሳይሰለቹ ይጠይቁታል እርሱም ሳይሰለች ይመልስላቸዋል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ “እንኪያስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት” /ቁ.22/፡፡ እርሱም በሕዝቡ ልቡና ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤና በእነዚያ ያለውን ተንኰል ከንቱ ካደረገ በኋላ እነርሱ ከሚቀበሉት መጽሐፍ እየጠቀሰ፡- “እኔ በበረሀ የሚጮህ ድምጽ ነኝ፤ ከእኔ በፊት የነበረውና አሁን ሥጋ ለብሶ በመካከላችሁ የቆመው ቃል ግን የምትጠብቁት መሲሕ ነው” እያለ የነቢዩ ኢሳይያስን የትንቢት ፍጻሜ ይነግራቸው ነበር /ቁ.23፣ ኢሳ.40፡3፣ ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒ ከማሁ 6/፡፡ እንዲህ እያደረገም ልቡናቸውን የንስሐ ፍሬ አፍርቶ ለጌታ እንዲያዘጋጁ አጥብቆ ያስተምራቸው ነበር፤ ሁሉም እንዲሰሙትም ጮክ ብሎ ይናገር ነበር፤ ከእግዚአብሔር ጸጋ ተራቁታ የነበረችው ነፍስ ከአምላኳ ጋር እንድትገናኝ ያዘጋጅ ነበር /አርጌንስ ዝኒ ከማሁ 6፡100/፡፡
 “የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት” /ቁ.24/፡፡ አስቀድመን ቅናት ያልነው እንግዲህ ይኸው ነው፡፡ ምክንያቱም መጥምቁ ማንነቱን በትክክል እየነገራቸው እንኳን ይሰናከሉበት ነበርና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡ ዮሐንስ ግን የእርሱ ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ለምትመጣው ፍጽምት ጥምቀት የማዘጋጀት አገልግሎት እንደሆነች “እኔ በውኃ የንስሐ ጥምቀት አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት ልጅነትን በምታሰጥ ጥምቀትም የሚያጠምቅ በመካከላችሁ ቆሞአል” እያለ ይነግራቸው ነበር /St. Cyril of Alexandria Commentary on the Gospel of John 1:10/፡፡ በእርግጥም የዮሐንስ ጥምቀት ለንስሐ የምታዘጋጅ እንጂ መንፈስ ቅዱስን የምታሰጥ አልነበረችም /ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒከማሁ 4 /፡፡
 እነዚህ ክፉዎች ይዘውት ለመጡት ተንኰልና በሕዝቡ ልብ የነበረውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቃወምና በጣቱ እያመለከተ፡- “እነሆ እናንተ በመለኰቱ አይታችሁት የማታውቁ አሁን ሥጋ ለብሶ በእናንተ መካከል አለ፤ እርሱ በመጀመርያ ቃል የነበረ ነው፤ አሁን ግን በምልዓት ያልተለየውን ዓለም ሥጋ ለብሶ ጎብኝቶታል፤ እርሱ ከእኔ ይበልጣል፤ እኔ ግን የጫማውን ጠፍር እንኳን መፍታት የማይገባኝ ወራዳ ነኝ፤ ዮሐንስ ይበልጣል የሚለው የተሳሳተ ግንዛብያችሁ አስወግዱና ከእኔ ይልቅ ወደ እርሱ ዘወር በሉ፤ እኔ ሚዜ ነኝ እርሱ ግን ሙሽራ ነው” እያለ ለሁሉም ይመልስላቸው ነበር /Apolinaris of Laodicea, Fragments on John 5/፡፡ በጥንት ጊዜ፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ /ሩት.4፡7/፡፡ ሙሽራይቱ (ቤተ ክርስቲያን) ያለችው ደግሞ እርሱ ክርስቶስ እንጂ ዮሐንስ አይደለም፡፡ ስለዚህ መጥምቁ “እንኳንስ ሙሽራ ልሆን ቀርቶ እርሱ የረገጣትን ኮቴ እንኳን ልረግጥ አይገባኝም” ማለቱ ተገቢ ነበር /ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒከማሁ 4/፡፡
 ይህ ሁሉ በሰዋራ ቦታ ሳይሆን ሕዝቡ በተሰበሰበበት ዮሐንስም ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ እና በቤተ ራባ ሆነ /ቁ.28፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ወንድሞቼ! ሴቶች ከወለዷቸው ሁሉ ከእርሱ የሚበልጥ የሌለ ዮሐንስ የጌታን የጫማ ማዘብያ መንካት አይገባኝም ካለ እኛማ ምን ያህል ያልተገባን እንሆን ይሆን? ዓለም ለእርሱ ያልተገባችው ይልቁንም ዕድሜውም በሙሉ እግዚአብሔርን በማገልገል አንገቱ የተሰየፈው ዮሐንስ እንዲህ ካለ በኃጢአት የጨቀየን እኛማ ምን እንል ይሆን? ትሕትናው እንዴት ከፍ ከፍ እንዳደረገችው ታስተውሉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ! እርሱ የጫማውን ማዘብያ እንኳን “አልነካም” ቢልም ሰውን አፍቃሪ ጌታ ግን “እንኳንስ ጫማዬ ገና እኔን ታጠምቀኛለህ” ብሎታል፤ “አጥምቆታልም”፤ ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ ራቅ” ቢለውም ሰው ወዳጁ ጌታ ግን “ገና ቤተ ክርስቲያኔን በአንተ ላይ እመሠርታታለሁ” ብሎታል፡፡ እውነት ነው! ትዕቢት ቅዱሳን መላእክትን ርኩሳን መላእክትን ታደርጋለች፤ ትሕትና ግን ወደ ሕይወት ዛፍ የምታስወጣ መሰላል ነች፡፡ ምንም ያህል ጾመኞች፣ ጸሎትን የምናዘወትር፣ ሌላም ሁሉ ብናደርግ ትሕትና ግን ከሌለን የትሕትና ጌታ ከእኛ ጋር የለም፡፡ በሰው ዘንድ ከፍ ከፍ ያለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የረከሰ ነውና /ሉቃ.16፡15/፡፡ አቤቱ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደ በደላችን አይሁን፡፡ አሜን!!  

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount