በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
መጻጉዑ የተፈወሰበት ቀን ሰንበት (በእኛ ቅዳሜ) ነበረ /ቁ.10/። ጌታችን
መጻጉዑን በዚህ ቀን የፈወሰው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አይሁድ የሰንበትን አከባበር አዛብተውት ስለነበረና እውነተኛው
አከባበር ሊያሳያቸው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ እነዚህ አይሁድ ሰንበትን ሲያከብሩ እነርሱ ራሳቸው በጨማመሩት አከባበር እንጂ እግዚአብሔር
እንዲያከብሩት ባዘዛቸው መንገድ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ነበር የተፈወሰው ሰውዬ አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ ቢያዩት ሰንበትን የሻረ
ስለመሰላቸው፡- “ዛሬ ሰንበት ነውና አልጋህንም ተሸክመህ ልትሄድ አይገባህም” የሚሉት፡፡ እነርሱ ራሳቸው ግን በሰንበት ይገርዙ
ነበረ /ዮሐ.7፡23/፤ እነርሱ ራሳቸው ግን አንድ በግ ወደ ጕድጓድ ቢገባ ያወጡት ነበረ /ማቴ.12፡11/፡፡ ከዚህ በላይ የሚደንቀው
ደግሞ መዝሙረኛው ዳዊት “ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፤ ሊገድለውም ይወዳል” እንዳለው ጌታ የታመሙትን ሲፈውስ እነርሱ ግን የተፈወሱትን
ሊገድሉ ይፈልጉ ነበር /መዝ.37፡32/፡፡ በዚህ ድርጊታቸው አልጋውን ተሸክሞ ከሄደው ሰውዬ፣ 38 ዓመት ሙሉ እንደ ትኋን
ከአልጋው ጋር ተጣብቆ ከነበረው ሰውዬ በላይ እነርሱ ታመው ነበረ፡፡ ምክንያቱም መጻጉዑ ጌታ የነገረውን ምንም ሳያጠራጠር “አሜን”
ብሎ ተፈውሶ ሲሄድ እነርሱ ግን ይህን ሁሉ እያዩ ትንሽ እንኳን አልገረማቸውምና፡፡ ከዚያ ይልቅ ውስጣቸው በቅናት ያቃጠልባቸው ነበር
እንጂ /St. Cyril The Great, K3 F4/፡፡
መጻጉዑ እንዲህ በቅናት ተቃጥለው ቢያያቸው በዚያ ንዴታቸው ላይ
ሌላ ክፉ ንግግርን አልጨመረባቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ እነርሱም ይህን መዳን ቸል እንዳይሉ “ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ
አለኝ፤ ስለዚህ ይህን የማደርገው ጌታዬ ባዘዘኝ መሠረት እንጂ እኔው በራሴ ሥልጣን አይደለም” ይላቸው ነበረ /ቁ.11/። እነርሱ
ግን ሰውዬው በመዳኑ ስላልተደሰቱ “የፈወሰህ ማን ነው?” ብለው ከመደነቅ ይልቅ በክፋት “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን
ነው?” ይሉታል /ቁ.12/። ዳሩ ግን ፈርቷቸው ሳይሆን አሁን ንዴታቸው በእጅጉ ስለጨመረ እስኪያልፍላቸው ድረስ ጌታችን ከዚያ ፈቀቅ
ብሎ ነበረ፡፡ ስለዚህም መጻጉዑ ሰማያዊው ሐኪሙን ሊያሳያቸው አልቻለም /ቁ.13 ፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 37/፡፡ ከዚህ
በኋላ መጻጉዑ አምላኩን ለማመስገን ወደ ምኵራብ ሄደ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ስላደረገለት ነገር፡- “ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን
እሠዋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ፡፡ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ
ኢየሩሳሌም ሆይ በመካከልሽም ሃሌ ሉያ” እያለ ያመሰግን ነበረ /መዝ.116፡17-19/፡፡ ጌታችንም የዳነው መጻጉዕ እዚያው ቤተ
መቅደስ ውስጥ አገኘውና በፍቅር አንደበቱ፡- “ልጄ! እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” ይሏል
/ቁ.14/። እውነት ነው! ይህ መጻጉዕ ከዚህ በፊት ይዞት የነበረው ደዌ ዘሥጋ ነው፤ ከዚህ የባሰ ደግሞ ደዌ ዘነፍስ አለና እንዲህ
አለው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 479/፡፡ ከዚህ በኋላ “ሰውዬው ሄዶ ያዳነው እርሱ ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው”
/ቁ.15/። ይህን የሚያደርገው አይሁድ ጌታን እንዲወግሩት ፈልጐና አሳልፎ እየሰጠው ሳይሆን አስቀድመው “ይህን አድርግ ያለህ ማን
ነው?” ብለውት ስለነበረ እየመሰከረላቸው ነው፡፡ ያዳነው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይነግራቸው ነበር፡፡ አይሁድ ግን “ይህ
ማን ይሆን? ሙሴ ይመጣል፤ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ያሉት መሲሕ ይሆንን? ይህ በኃይልና በሥልጣን ደዌ ዘሥጋ ብቻ ሳይሆን ደዌ
ዘነፍስም የሚፈውስ ሰው ማን ነው?” ብለው ተገርመው ስለ ክርስቶስ መጠየቅና ማወቅ ሲገባቸው የባሰ በሰንበት ድውይን ስላዳነ ያሳድዱት
ነበር፤ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር /ቁ.16/። ኢየሱስ ግን ሁል ጊዜ እንደሚያደርገው እንዲህ ይላቸው ነበር፡- “አባቴ እስከ ዛሬ
ይሠራል፤ እናንተ ስነፍጥረትን በስድስት ቀን ፈጥሮ ጨረሰ፤ ከዚያ በኋላም ዐረፈ ብትሉም አባቴ ግን በሰባተኛው ቀንም ፍጥረቱን መንከባከቡና
መግቦቱን አላቆመም፡፡ ቀና ብላችሁ ይህን መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ፀሐይ መመላለሷን አላቆመችም፤ ነፋሳት መንፈሳቸውን አላቋረጡም፤
ወቅታት መፈራረቃቸውን አልዘገዩም፤ ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ መዝነቡ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አባቴ በዚህች ቀን ይህ መጻጉዕ
በተፈወሰበት የሰሊሆም መጠመቅያ እንኳን አንዳንድ ድውያን መፈወሱን አላቆመም፤ ስለዚህ ይህ ሰባተኛው ቀን አባቴ ፍጥረቱን ደስ የሚያሰኝበት
ፍቅሩንም የሚያሳይበት የሥራ ቀን ነው፡፡ እናንተም ብትሆኑ በዚሁ በሰባተኛው ቀን ወንድ ልጅን ስትገርዙ ኖራችኋል፤ ካህናቶቻችሁ
መሥዋዕትን ሲያቀርቡበት ኖረዋል፤ ልጆቻችሁ በዚሁ ቀን በጐቻቸውን ውኃ እየቀዱ ሲያጠጥዋቸው ኖረዋል፡፡ እነዚህ መልካም ሥራዎች ግን
ሰንበትን አልሻሩትም፡፡ እኔም ደግሞ ይህን የፍቅር ሥራ እሠራለሁ፤ አባቴ ስነፍጥረትን ይንከባከብ እንደነበረ እኔም ደግሞ ይህን
የፍቅር ሥራ ይህን የመንከባከብ ሥራ እሠራለሁ” ይላቸው ነበረ /ቁ.17፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 38፡2/። ይህ ብቻ ሳይሆን
ከአባቱም ጋር የተካከለ እንደሆነ ነገር ግን የሰው ልጅ ከወደቀበት ውድቀት ለማንሣት ብሎ የባርያውን መልክ ይዞ መጣ ይነግራቸው
ነበረ /Augustine, On The Gospel Of St. John, Tracte 20:9/፡፡ ከዚህ በኋላ እንደነርሱ እይታ “ሰንበትን
ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን ራሱንም ከእግዚአብሔር አብ ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፤ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ሥልጣን፣
አንድ መለኰት አለኝ ስላለ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” /ቁ.18/። በእርግጥም አንዳንዶች እንደሚያስቡት እርሱ ወልድ ከባሕርይ
አባቱ ከአብ ያነሠ አይደለም፡፡ ከአባቱ ያንሣል ብለው ዮሐንስ 14፡28ን የሚጠቅሱ እነዚህ ሰዎች እርሱ “የባርያን መልክ ይዞ በሰውም
ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ” የሚለውን የሐዋርያው ቃል ያላስተዋሉ ናቸው፡፡ እንዲህ
ብለው የሚናገሩ ሰዎች “እኔና አብ አንድ ነን” ያለውን ቃል ቢመለከቱ ይጠቅማቸው ነበር /St. Ambrose, Of The
Christian Faith, Book, Ch.18:224/፡፡
ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁን እና ከተዋሕዶ እምነት
ውጪ ያላችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ ይህን የከበረ ቃል ቸል አትበሉት፡፡ እነዚህ አይሁድ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ከአባቱ ጋር እኵል እንደሆነ
ሲነግራቸው ስለ እነርሱም መዳን ብሎ እንደመጣ ሲነግራቸው እነርሱ ግን እንዴት እንዲህ ይላል ብለው ሊገድሉት ድንጋይ እንዳነሡ እንዴት
ሊሆን ይችላል የምንል አንሁን፡፡ እኔና አብ አንድ ነን ካለን አሜን ብለን ማመን መቀበል እንጂ ሊመረመር የማይቻለውን ምሥጢር በአመክንዮ
ለመደገፍ አንሞክር፡፡ እነዚህ ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚከባበሩት ከበሬታ እንዳይቀርባቸው ብለው የሕይወትን ቤዛ እንዳልተቀበሉት
በዘመን መጨረሻ የምንገኝ እኛም ቃሉ ያለ ምክንያት አልተጻፈልንምና ከሰው ደካማ ፍልስፍና ወጥተን ወደ አምላካችን ወደ ክርስቶስ
እንቅረብ፡፡ እርሱ መድኃኒታችን ነው፤ እርሱ ዓለማትን በቃሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ የዘላለም አባት ድንቅ መካር ኃያልም
አምላክ ነው፤ እርሱ ክርስቶስ በሥጋ የመጣ ከሁሉም በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን /ሮሜ.9፡5/፡፡
(እግዚአብሔር
ቢፈቅድ ደግሞም ብንኖር ሳምንት እንገናኛለን!)
ተመሳሳይ ገጾች
የዮሐንስ ወንጌል የ9ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የአራተኛው ሳምንት ጥናት
ድንግል ማርያም
ፕሮቴስታንት ለጠየቀኝ የተለያዩ ጥያቄዎች
No comments:
Post a Comment