Showing posts with label የዮሐንስ ወንጌል የአራተኛው ሳምንት ጥናት. Show all posts
Showing posts with label የዮሐንስ ወንጌል የአራተኛው ሳምንት ጥናት. Show all posts

Saturday, December 24, 2011

የቃል ሰው የመሆን ምሥጢር (የዮሐንስ ወንጌል የአራተኛው ሳምንት ጥናት)!!

(አዘጋጅ፡- ገብረ እግዚአብሔር ኪደ)!

“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” ዮሐ.1፡14

የሰው ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ፤ ከጸጋ ርቀን በጨለማ ለነበርን ሁላችንም ወደማይነገር ክብር ከፍ ከፍ አደረገን /መዝ.88፡27/፡፡ አንድ ባለ ጸጋ ንጉሥ ከዙፋኑ ወርዶ ድሆችን እንደሚጐበኝና ምንም ሳይጸየፍና ሳያፍር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው አካለዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድም በኃጢአት ምክንያት ከጸጋ ተራቁተን ለነበርን ሁላችን ሳይንቀንና ሳይጸየፈን በምሕረቱ ጐበኘን፤ ባለ ጸጋ ሲሆን ስለ እኛ ድሀ ሆነ /2ቆሮ.8፡9፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ነገር ግን የጨው ሐውልት እንደ ሆነች እንደ ሎጥ ሚስት አይደለም /ዘፍ.19፡26/፤ የበረሀ አውሬ እንደሆነ ዳግመኛም ሰው ወደ መሆን እንደተለወጠው እንደ ከላውዴዎስ ንጉሥ እንደ ናቡከደነጾር አይደለም /ዳን.4፡28-34/፤ ወይን እንደሆነ እንደ ቃናም ውኃ አይደለም /ዮሐ.2፡6-9፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ የእግዚአብሔር ቃልና የሥጋ ባሕርይ በተዋሕዶ አንድ ሆነ እንጂ /ቅ.ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ/፡፡

ዘመን የማይቈጠርለት የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ እንደሆነ እናውቃለን፤ ነገር ግን እንዴት ወንድ ከማታውቅ ድንግል እንደተወለደ፤ ረቂቅ ሲሆን እንዴት እንደገዘፈ፤ በረድኤት ሳይሆን እንዴት የኵነት ሥጋ እንደሆነ እንመረምረው ዘንድ አይቻለንም፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እንኳን “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” አለን እንጂ እንዴት እንደሚወለድ አልነገረንም /ኢሳ.7፡14፣ ጀሮም/፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ያለመጠፋፋት፣ ያለመለወጥ፣ ያለመመለስ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለ ኅድረት፣ ያለ ትድምርት ይልቁንም በተዓቅቦ እንደተወሐደ ግን እናውቃለን /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ በልቡናችን ያለ ቃል ከድምጻችን ጋር ተዋሕዶ እንደሚገለጥ ሁሉ አካላዊ ቃልም ሥጋን ተዋሕዶ እንደ ተገለጠ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የእኛ ቃል ከድምጻችን ጋር ይዋሐዳል እንጂ ወደ ድምጽነት አይቀየርም፤ አካላዊ ቃልም ከሥጋ ጋር እንደተዋሐደ እንጂ ወደ ሥጋነት እንዳልተለወጠ እናውቃለን /አውግስጢኖስ/፡፡ 

“ይህ ሁሉ ግን ለምን ሆነ?” ብለን ስንጠይቅም በሰው ልጆች ላይ ነግሦ የነበረው ሞትና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው መፍረስና መበስበስ የሚነቀለው በሞት ብቻ እንደ ሆነ እንገነዘባለን /ዕብ.9፡22/፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችል ፍጡር ደግሞ ፈጽሞ አልተገኘም /ኢሳ.59፡16/፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱ በመለኰታዊ ባሕርይው ስለማይሞት ሞት የሚስማማውን የእኛን ደካማ ሥጋ ነሣና ሞትን በትንሣኤው ገደለው (N.B.፡- ክርስቶስ የነሣው ሥጋ ከመለኰት ጋር ከመዋሐዱ በፊት ሀልዎት-Existence የለውም)፡፡ የተዋሐደውን ሥጋዉም ከበደል ንጹሕ የሆነ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብና ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ሞትን ከወገኖቹ አስወገደ /ኤፌ.5፡2፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ በአዳም ምክንያት ያገኘን ድቀትም ፈወሰልን /ቅ.ኤፍሬም/፡፡ (ማስታወሻ፡- በኦርቶዶክስ አስተምህሮ “ጥንተ አብሶ- Original Sin” አይባልም /ይህ የካቶሊክ አስተምህሮ ነውና/፤ ይልቁንም “የባሕርይ መጐሳቆል፣ ድቀት- Failure of Nature” ነው የሚባለው /ቅ.አትናቴዎስ/)፡፡ ብረት በእሳት ውስጥ ብንጥደው እሳቱን አይጠቀልለውም፤ ነገር ግን ብረቱ የእሳቱን ባሕርይ ለራሱ ገንዘብ ያደርጋል፡፡ እሳቱ መጠኑ አይቀንስም፤ ነገር ግን ብረቱ የእሳቱን ባሕርይ ለራሱ ባሕርይ ያደርጋል፡፡ አካላዊ ቃልም ከመለኰታዊ ምልዓቱ ሳይወሰን ሥጋ ሆነ፡፡ በምልዓቱ ያልተለየውን ምድር ሰው ሆኖ ጎበኘው፡፡ የነሣው ሥጋም የመለኰትን ባሕርይ ለራሱ ገንዘብ አደረገ፤ በተዋሕዶም የባሕርይ አምላክ ሆነ፡፡ እንግዲያስ ፀሐይ በተገለጠች ጊዜ ጨለማና ሌሊት እንደሚወገዱ ሁሉ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስም ከእኛ ጋር ተዋሕዶ የነበረውን ሞት ይገድል ዘንድ ከኃጢአት በቀር የእኛን ደካማ ባሕርይ በሙሉ ገንዘብ እንዳደረገ እናስተውል /ዕብ.2፡14-15፣ ቅ.ባስልዮስ/፡፡ ወንጌላዊው አስቀድሞ ቀዳማዊነቱን ከነገረን በኋላ አሁን ደግሞ እውነተኛው ብርሃን ወደ ቀደመ ክብራችን ይመልሰን ዘንድ ሥጋ እንደለበሰ የሚነግረን ለዚሁ እንደሆነ ልብ እንበል፡፡ የሰው ልጅ ሕያዊት የሆነች ነፍስና ሟች የሆነች ሥጋ አሉት፡፡ መጀመርያ ሲፈጠር ሞት የሚስማማው ባሕርይ ነበረው፡፡ በኋላም ፈጣሪ የሕይወትን እስትንፋስ “እፍ” ስላለበት የእግዚአብሔርን ሕይወት (ኢመዋቲነትን- Immortality) ተካፋይ ሆነ /ዘፍ.2፡7/፡፡ የተሰጠውን ትእዛዝ ሲተላለፍ ግን “አፈር ነህና…” ተብሎ ተቀጣ፤ አልተረገመም /ዘፍ.3፡19/፡፡ ነገር ግን ይህ ቅጣት በነፍስ ላይ የተነገረ አልነበረም ማለትም ነፍስ መበስበስን ታይ ዘንድ አልተቀጣችም /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ ስለዚህ ሕያውና የማይሞት ቃል የሚሞት ሥጋን ለበሰ፤ ያንን የሚሞት ሥጋም የማይሞት አደረገው፡፡ ይህ የማይጠፋ ኃይል የሚጠፋ ሥጋን ለበሰ፤ ያንን የሚጠፋ ሥጋም የማይጠፋና የሚናገር አደረገው /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ አማልክት ዘበጸጋ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ፤ ከማይታየው እግዚአብሔር እንወለድ ዘንድ ከሚታየው ባሕርያችን ተወለደ፤ ዘላለማውያን እንሆን ዘንድ ሟች ባሕርያችንን ነሣ፤ ለሞት ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፤ መዋቲ ሥጋችንን ተዋሕዶ በመገለጥ በኢመዋቲነቱ መዋቲነትን አጠፋልን /ፊል.2፡8፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ የእርሱ የሆነውን ሳይተው የእኛ የሆነውን ተዋሐደ፤ የእኛ ደካማ ባሕርይ ከፍ ከፍ ያደርግ ዘንድ የእርሱ ባሕርይ ሳይጐድል መጣ /ታላቁ ጐርጐርዮስ/፡፡ 

FeedBurner FeedCount