Saturday, December 24, 2011

የቃል ሰው የመሆን ምሥጢር (የዮሐንስ ወንጌል የአራተኛው ሳምንት ጥናት)!!

(አዘጋጅ፡- ገብረ እግዚአብሔር ኪደ)!

“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” ዮሐ.1፡14

የሰው ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ፤ ከጸጋ ርቀን በጨለማ ለነበርን ሁላችንም ወደማይነገር ክብር ከፍ ከፍ አደረገን /መዝ.88፡27/፡፡ አንድ ባለ ጸጋ ንጉሥ ከዙፋኑ ወርዶ ድሆችን እንደሚጐበኝና ምንም ሳይጸየፍና ሳያፍር አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው አካለዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድም በኃጢአት ምክንያት ከጸጋ ተራቁተን ለነበርን ሁላችን ሳይንቀንና ሳይጸየፈን በምሕረቱ ጐበኘን፤ ባለ ጸጋ ሲሆን ስለ እኛ ድሀ ሆነ /2ቆሮ.8፡9፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ነገር ግን የጨው ሐውልት እንደ ሆነች እንደ ሎጥ ሚስት አይደለም /ዘፍ.19፡26/፤ የበረሀ አውሬ እንደሆነ ዳግመኛም ሰው ወደ መሆን እንደተለወጠው እንደ ከላውዴዎስ ንጉሥ እንደ ናቡከደነጾር አይደለም /ዳን.4፡28-34/፤ ወይን እንደሆነ እንደ ቃናም ውኃ አይደለም /ዮሐ.2፡6-9፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ የእግዚአብሔር ቃልና የሥጋ ባሕርይ በተዋሕዶ አንድ ሆነ እንጂ /ቅ.ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ/፡፡

ዘመን የማይቈጠርለት የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ እንደሆነ እናውቃለን፤ ነገር ግን እንዴት ወንድ ከማታውቅ ድንግል እንደተወለደ፤ ረቂቅ ሲሆን እንዴት እንደገዘፈ፤ በረድኤት ሳይሆን እንዴት የኵነት ሥጋ እንደሆነ እንመረምረው ዘንድ አይቻለንም፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እንኳን “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” አለን እንጂ እንዴት እንደሚወለድ አልነገረንም /ኢሳ.7፡14፣ ጀሮም/፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ያለመጠፋፋት፣ ያለመለወጥ፣ ያለመመለስ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለ ኅድረት፣ ያለ ትድምርት ይልቁንም በተዓቅቦ እንደተወሐደ ግን እናውቃለን /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ በልቡናችን ያለ ቃል ከድምጻችን ጋር ተዋሕዶ እንደሚገለጥ ሁሉ አካላዊ ቃልም ሥጋን ተዋሕዶ እንደ ተገለጠ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የእኛ ቃል ከድምጻችን ጋር ይዋሐዳል እንጂ ወደ ድምጽነት አይቀየርም፤ አካላዊ ቃልም ከሥጋ ጋር እንደተዋሐደ እንጂ ወደ ሥጋነት እንዳልተለወጠ እናውቃለን /አውግስጢኖስ/፡፡ 

“ይህ ሁሉ ግን ለምን ሆነ?” ብለን ስንጠይቅም በሰው ልጆች ላይ ነግሦ የነበረው ሞትና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው መፍረስና መበስበስ የሚነቀለው በሞት ብቻ እንደ ሆነ እንገነዘባለን /ዕብ.9፡22/፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችል ፍጡር ደግሞ ፈጽሞ አልተገኘም /ኢሳ.59፡16/፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ራሱ በመለኰታዊ ባሕርይው ስለማይሞት ሞት የሚስማማውን የእኛን ደካማ ሥጋ ነሣና ሞትን በትንሣኤው ገደለው (N.B.፡- ክርስቶስ የነሣው ሥጋ ከመለኰት ጋር ከመዋሐዱ በፊት ሀልዎት-Existence የለውም)፡፡ የተዋሐደውን ሥጋዉም ከበደል ንጹሕ የሆነ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብና ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ሞትን ከወገኖቹ አስወገደ /ኤፌ.5፡2፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ በአዳም ምክንያት ያገኘን ድቀትም ፈወሰልን /ቅ.ኤፍሬም/፡፡ (ማስታወሻ፡- በኦርቶዶክስ አስተምህሮ “ጥንተ አብሶ- Original Sin” አይባልም /ይህ የካቶሊክ አስተምህሮ ነውና/፤ ይልቁንም “የባሕርይ መጐሳቆል፣ ድቀት- Failure of Nature” ነው የሚባለው /ቅ.አትናቴዎስ/)፡፡ ብረት በእሳት ውስጥ ብንጥደው እሳቱን አይጠቀልለውም፤ ነገር ግን ብረቱ የእሳቱን ባሕርይ ለራሱ ገንዘብ ያደርጋል፡፡ እሳቱ መጠኑ አይቀንስም፤ ነገር ግን ብረቱ የእሳቱን ባሕርይ ለራሱ ባሕርይ ያደርጋል፡፡ አካላዊ ቃልም ከመለኰታዊ ምልዓቱ ሳይወሰን ሥጋ ሆነ፡፡ በምልዓቱ ያልተለየውን ምድር ሰው ሆኖ ጎበኘው፡፡ የነሣው ሥጋም የመለኰትን ባሕርይ ለራሱ ገንዘብ አደረገ፤ በተዋሕዶም የባሕርይ አምላክ ሆነ፡፡ እንግዲያስ ፀሐይ በተገለጠች ጊዜ ጨለማና ሌሊት እንደሚወገዱ ሁሉ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስም ከእኛ ጋር ተዋሕዶ የነበረውን ሞት ይገድል ዘንድ ከኃጢአት በቀር የእኛን ደካማ ባሕርይ በሙሉ ገንዘብ እንዳደረገ እናስተውል /ዕብ.2፡14-15፣ ቅ.ባስልዮስ/፡፡ ወንጌላዊው አስቀድሞ ቀዳማዊነቱን ከነገረን በኋላ አሁን ደግሞ እውነተኛው ብርሃን ወደ ቀደመ ክብራችን ይመልሰን ዘንድ ሥጋ እንደለበሰ የሚነግረን ለዚሁ እንደሆነ ልብ እንበል፡፡ የሰው ልጅ ሕያዊት የሆነች ነፍስና ሟች የሆነች ሥጋ አሉት፡፡ መጀመርያ ሲፈጠር ሞት የሚስማማው ባሕርይ ነበረው፡፡ በኋላም ፈጣሪ የሕይወትን እስትንፋስ “እፍ” ስላለበት የእግዚአብሔርን ሕይወት (ኢመዋቲነትን- Immortality) ተካፋይ ሆነ /ዘፍ.2፡7/፡፡ የተሰጠውን ትእዛዝ ሲተላለፍ ግን “አፈር ነህና…” ተብሎ ተቀጣ፤ አልተረገመም /ዘፍ.3፡19/፡፡ ነገር ግን ይህ ቅጣት በነፍስ ላይ የተነገረ አልነበረም ማለትም ነፍስ መበስበስን ታይ ዘንድ አልተቀጣችም /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ ስለዚህ ሕያውና የማይሞት ቃል የሚሞት ሥጋን ለበሰ፤ ያንን የሚሞት ሥጋም የማይሞት አደረገው፡፡ ይህ የማይጠፋ ኃይል የሚጠፋ ሥጋን ለበሰ፤ ያንን የሚጠፋ ሥጋም የማይጠፋና የሚናገር አደረገው /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/፡፡ አማልክት ዘበጸጋ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ፤ ከማይታየው እግዚአብሔር እንወለድ ዘንድ ከሚታየው ባሕርያችን ተወለደ፤ ዘላለማውያን እንሆን ዘንድ ሟች ባሕርያችንን ነሣ፤ ለሞት ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፤ መዋቲ ሥጋችንን ተዋሕዶ በመገለጥ በኢመዋቲነቱ መዋቲነትን አጠፋልን /ፊል.2፡8፣ ቅ.አትናቴዎስ/፡፡ የእርሱ የሆነውን ሳይተው የእኛ የሆነውን ተዋሐደ፤ የእኛ ደካማ ባሕርይ ከፍ ከፍ ያደርግ ዘንድ የእርሱ ባሕርይ ሳይጐድል መጣ /ታላቁ ጐርጐርዮስ/፡፡ 


ስለዚህ ተወዳጆች ሆይ! ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የምንቀበለው ኅብስትና ወይን (ቅዱስ ቁርባን) በመጀመርያ ቃል የነበረ ነገር ግን እንበላውና እንጠጣው ዘንድ የተሰጠን ነፍስ የተለየው መለኰት የተዋሐደው የወልደ እግዚአብሔር ሥጋና ደም ነው /ማቴ.26፡27/፡፡ ክርስቶስ ፍቅሩን የገለጠልን በመሞት ብቻ ሳይሆን እንበላውም ዘንድ ምግበ ሥጋና ምግበ ነፍስ አድርጐ ራሱን ለእኛ በመስጠት ነውና /ዮሐ.6፡35-54፣ አውግስጢኖስ/፡፡ አቤት! ይህን ቸርነት መናገር የሚችል አንደበት ምን አንደበት ነው?! መመርመር የሚችል ልቡናስ ምን ልቡና ነው?! ባለጸጋው ስለ እኛ መዳን ብሎ ደሀ ሆነ፤ ስጠን ሳንለውም እንዲሁ ሥጋዉንና ደሙን ሰጠን! /ቅ.ኤፍሬም/፡፡ እናት ልጇን ደምና ወተት እንደምትመግበው ሁሉ ክርስቶስም ያለ ማቋረጥ ሕይወቱን ለሰጠን ለሁላችን የራሱን ደም መገበን፤ ምንም አይሁድ የሠዉት በግ ቢሆንም የሕይወት መዝገብ ሆነልን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእውነት ለዚህ ፍቅር አንክሮ ይገባል! በእውነት ለዚሁ ቸርነት ዕልልታ ይገባል! በእውነት ለዚህ ጸጋ ሽብሸባ ይገባል! በእውነት ለዚሁ ጌታ ቅርቅርታ ይገባል! ባለጸጋ የሆነ ሰው ወርቅ ሊይዝ ይችላል፤ ነገር ግን ወርቅን ሊፈጥር አይችልም፡፡ ሁሉንም የፈጠረ ባለጸጋው ጌታ ግን እኛን ባለጸጐች ያደርግ ዘንድ ደሀ ሆነና ሥጋዉንና ደሙን ቆርሶ “እንኩ” አለን፤ የዕዳ ደብዳቢያችንም ቀደደውና በደሙ ያለመሞት ጸጋን አደለን /ቈላ.2፡14፣ አውግስጢኖስ/፡፡

ኃጢአትን የሚያስተሰርይ ቀዳማዊ ቃል ጸጋንና እውነትን ተመልቶ አማኑኤል ሆነ /ማቴ.1፡23/፤ በረድኤት ሳይሆን በኵነት በመካከላችን አደረ /ዮሐ.1፡26/፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ መንፈሱን ያሳድር ዘንድ የማይታይ ታየ /ኢዩ.2፡28፣ ቴዎዶር ዘማውፕሳስትያ/፡፡ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን፤ አብ በደመና ሆኖ “የምወደው ልጄ እርሱ ነው” ሲል ክብሩን አየን /ማቴ.3፡17/፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ ሲወርድ ክብሩን አየን /ማቴ.3፡16/፤ በደብረ ታቦር ተራራ መልኩ ሲለወጥ፣ ፊቱ እንደ ፀሐይ ሲያበራ ልብሱም እንደ በረዶ ጸዐዳ ሲሆን ክብሩን አየን /ማቴ.17፡2/፤ ስለ እኛ ብሎ በመስቀል ላይ መከራ እየተቀበለ ሳለ በተደረጉ ተአምራት ክብሩን አየን /ማቴ.27፡51-54፣ ቅ.ኤፍሬም፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በዚሁ ብቻ ሳይሆን በኃጢአት ጐስቁሎ የነበረው ባሕርያችን እርሱ ሲፈውሰው እኛም ክብሩን አየን /አውግስጢኖስ/፡፡ ቀዳማዊ ልደቱ የማይመረመረው አካላዊ ቃል ከመጨረሻው የክብር ጠርዝ ወደ መጨረሻው የውርደት ጠርዝ ወርዶ በበረት ተኝቶ ሳለ ነገሥታ ምስራቅ ሲሰግዱለት እጅ መንሻም ሲያቀርቡለት ክብሩን አየን /ማቴ.2፡11፣ አውግስጢኖስ/፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ በአደረጋቸው ገቢረ ተአምራት ሁሉ ከአባቱ ጋር የሚተካከለውን ክብሩን አየን /ዮሐ.10፡30፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ/፡፡ 

አልፋና ኦሜጋ፣ ቀዳማዊና ደኃራዊ፣ ጥንትና ፍጻሜ የሆንከው አምላክ ሆይ! በቸርነትህ ስለ ጐበኘኸን እናመሰግንሃለን፤ በቃልህ ሁሉን የፈጠርክ፣ የሚታየውም የማይታየውም ሁሉ በአንተ የሆነ ንጉሥ ሆይ! ስለ እኛ ብለህ ለሞት እንኳን ስለታዘዝክ ከፍ ከፍ በል፤ በዘመናት የሸመገልክ ቅዱስ አባት ሆይ! ስለ በደላችን መተላለፍ ጸጋንና እውነትን ተመልተህ መጥተህ በጸጋ ላይ ጸጋ ስላጐናጸፍከን እናመሰግንሃለን፡፡ ከምስጋና ውጪስ ለአንተ የሚሆን ስጦታ ምን አለን?!!

ሰላም ወሰናይ (በአምስተኛው ጥናታችን ለመገናኘት ያብቃን)!!!

ተመሳሳይ ገጾች 

የዮሐንስ ወንጌል የ20ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የ21ኛ ሳምንት ጥናት

የዮሐንስ ወንጌል የ22ኛ ሳምንት ጥናት

እየሱስ አማላጅ ነውን?
ከአንድ በላይ ሚስት ለምን

ካህናተ ደብተራ
 

2 comments:

  1. Dear Gebregziabher,
    Thank you for posting these interesting articles. These are truly our church believes and biblical articles. But my question is that do you mind tell me where the other articles were posted. I'm asking that u'r beginning from fourth week research on St. Johns Gospel. Pleas, tell me the address of the other articles or post them in your site. I love it.
    Thanks in advance.

    ReplyDelete
  2. It's wonderful course. I know u previosly 4ur genius writing on our mk web. Plse Would clarify, if z soul didn't punished, how would it be sent to 'siol'?

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount