በብሉይ ኪዳን ከአንዲት ሚስተ በላይ አግብተዋል ከሚባሉት እነ አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ዳዊት እና ሰሎሞን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከአንድ በላይ አግብተዋል ማለት ግን እግዚአብሔር ፈቅዶላቸዋል በሥራቸውም ተደስቷል ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዳቸውን እያሳጠርን መመልከት እንችላለን፡-
1. አብርሃም፡- አብርሃም የደረሰባትና እስማኤልንም የወለደላት አጋር ሚስቱ ሳትሆን ገረዱ የነበረች ናት፡፡ ከእርሷ እንዲወልድ የተደረገው እንኳ ሚስቱ ሣራ ልጅ ስላልነበራት አስገድዳው እንጂ እርሱ ራሱ ሊደርስባት ፈልጎ አልያም ደግሞ እግዚአብሔር ይህን እንዲያደርግ ስለፈቀደለት አልነበረም፡፡ አብርሃም ይህን ያደረገው ዝሙት ለመፈጸም ወይም ሌላ ሚስት ለመጨመር ብሎ ሳይሆን የሚስቱን ቃል ሰምቶ ነው /ዘፍ.16፡3/፡፡ ሊቃውንት ሣራ አብርሃምን ለምን እንዳስገደደችው ሲያመሰጥሩት፡- እግዚአብሔር “ከጉልበትህ የሚወጣ ልጅ እንጂ ከአንተ ጋር ያለው ባርያ አይወርስህም” የሚል ቃል ገብቶለት ስለነበረ /ዘፍ.15፡4/ እርሷ ደግሞ ልጅ ስላልነበራትና እግዚአብሔር የገባውን ኪዳን ያስቀረ ስለመሰላት በሰውኛ ጥበብ ልጅ እንዲወልድ ማድረጓ ነበር ይላሉ፡፡ አብርሃም በመጨረሻ ያገባት ሚስት ኬጡራ ትባላለች /ዘፍ.25፡1/፡፡ ነገር ግን ኬጡራን ያገባት ሣራ እያለች ሳይሆን ከሞተች በኋላ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በመሐመዳውያን ዘንድ የምናየው ዓይነት አይደለም፡፡
2. ያዕቆብ፡- በዘፍጥረት መጽሐፍ ያዕቆብ ራሔልንና ሊያን እንዳገባ እናነባለን፡፡ ነገር ግን ያዕቆብ ሊያን ያገባት በአጐቱ በላባ አታላይነነት እንጂ እርሱ ስለፈለገ ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ስለፈቀደለት አልነበረም /ዘፍ.29፡25/፡፡
3. ዳዊት፡- መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ሚዛን ስለሆነ ዳዊት በቅድስና በተመላለሰባቸው ጊዜያት ከአንበሳ አፍ በጐችን ማስጣሉ፣ በአንዲት ጠጠር ሕዝበ እስራኤልንና እግዚአብሔርን የወቀሰ ጐልያድን መግደሉ፣ ሳውልን በይቅርታ ማሸነፉ፣ ሲሞት እንኳን “እሰይ እንኳን ሞተ” ሳይሆን ማልቀሱንና ማዘኑን፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ዛሬ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ምግብ የሆነውን መዝሙር መዘመሩ ቢጽፍልንም ከዚያ በኋላ ያደረገውን ኃጢአትም አያስቀርብንም፡፡ እናም ዳዊት ወደ ንግሥና ከወጣ በኋላ የሰውነት ድካም ታይቶበታል፡፡ ከአንድ ኃጢአት ወደ ሌላ ኃጢአት ሲሸጋገርም እንመለከታለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ስንፍና ሕሊናንና አስተሳሰብን ያደነዝዛል፤ የማይወዱትንም ኃጢአት እንዲያደርጉ በርን ይከፍታል” እንዳለው ዳዊት በዚያን ጊዜ ከአሞናውያን ጋር በነበረው ጦርነት ሠራዊቱን አዝምቶ መጸለይ ሲገባው እርሱ በስንፈና አልጋ ተኝቶ ነበር፡፡ መተኛቱም ሳያንሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ በሰገነቱ ሲመላለስ አንዲት መልከመልካም ሴትን ቢመለከት በዝሙት ጾር ተነድፏል፡፡ መነደፍ ብቻም ሳይሆን ደረሰባት፡፡ እናም አረገዘች፡፡ በኋላም ይህን ኃጢአቱ ለመሸፈን ብሎ ባሏን ጠርቶ ከእርሷ ጋር እንዲተኛና ከባሏ እንደጸነሰች ማስመሰል ፈልጐ ነበር፡፡ ኦርዮ ግን ወደ ሚስቱ ወደ ቤርሳቤህ አልሄደም፡፡ ለኦርዮ ወደ ቤቱ ሄዶ ከሚስቱም ጋር መተኛት ማለት እግዚአብሔርን (ታቦተ ጽዮንን)፣ ሕዝቡን (እስራኤልን)፣ ነገደ ይሁዳን፣ አለቃው ኢዮአብን እና በጦር ሜዳ ያሉትን ጓደኞቹን ሁሉ እንደ መሳደብ ነበረ፡፡ ዳግመኛ በመላ ፍትወቱ እንዲነሣሣበት ፈልጐ ቢያሰክረውም ኦርዮ በጌታው ምንጣፍ ከባሮቹ ጋር ተኛ እንጂ ወደ ሚስቱ አልሄደም፡፡ ከዚህ በኋላ ዳዊት ያሰበው ሁሉ እንዳልተፈጸመለት ባየ ጊዜ ኦርዮን ማስገደል መርጧል፡፡ እናም አስገደለው፡፡ መጽሐፍ ዳዊት ያደረገው ሁሉ ማለትም ከቤርሳቤህ ጋር መድረሱ፣ ይባስ ብሎም አንዱን ባሏ ኦርዮን ማስገደሉ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ” ይላል /2ሳሙ.11፡27/፡፡ ምንም እንኳን ዳዊት መንፈሳዊ ልምምዶችን የተለማመደ፣ ሕግ አዋቂ፣ በሕዝብ ላይ የሚፈርድ ንጉሥ፣ የእግዚአብሔርም ነብይ ቢሆንም ከዚህ ኃጢአቱ ሊመለስ ባለመቻሉ ሌላ ነብይ አስፈልጐታል፡፡ ስለዚህም ነብዩ ናታን በጥበብ ገስጾታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ዳዊት ያለ ምንም ማመካኘት ኦርዮን ወይም ቤርሳቤህን ሳይሆን “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ንስሐ ገብቷል /2ነገ.12፡13/፡፡ እንዲህ በማድረጉም “እግዚአብሔር… ኃጢአትህን አርቆልሃል” ተባለ፡፡ ስለዚህ ዳዊት በግልጽ ቋንቋ አመነዘረ እንጂ ሌላ ሴት አገባ አይባልም፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንት “የዳዊት ቅድስና ከንስሐ እንጂ ካለመበደል የተገኘ አይደለም” የሚሉት፡፡
4. ልጁ ሰሎሞንም ቢሆን ብዙ ሚስቶችን ቢያገባም መጽሐፍ ቅዱስ “እንዲህ በማድረጉ እግዚአብሔርን አሳዘነው” እንጂ “አስደሰተው” ብሎ አልመዘገበልንም፡፡ እንዲያውም እንዲህ በማድረጉ ዕድሜው አጥሯል፤ መንግሥቱ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ይህን ታሪክ በ1ነገ.11 ሙሉውን ማንበብ ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ ከአንዲት በላይ ሚስት ማግባት ከሕገ እግዚአብሔርና ከስነ ተፈጥሮ አንጻር ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ከሕገ እግዚአብሔር አንጻር ስናየው አንድ ወንድና አንዲት ሴት አድርጐ ፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ መተባበር እንዳለባቸውም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህ ፈቃዱም ትዕዛዙም ባይሆን ኖሮ ወይም ደግሞ አንዱ ወንድ ከአንዲት ሚስት በላይ ማግባት ተፈቅዶለት ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአንድ አዳም ብዙ ሴቶችን በፈጠረለት ነበር፡፡ ወይም በግልባጩ አንዲት ሴት ከአንድ ወንድ በላይ ማግባት ተፈቅዶላት ቢሆን ኖሮ ብዙ ወንዶችን ፈጥሮ ከአንዲቷ ሴት ጋር ባጣመራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ አላደረገም፡፡ ስለዚህ ከአንድ ሚሰት በላይ ማግባት ይህን ሕገ እግዚአብሔር የሚጻረር ነው፡፡ ከሕገ ተፈጥሮ አንጻር ስናየው ደግሞ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው፡፡ የአንድ አዳም አካል የአንዲት ሔዋን አካል ነው፡፡ ይህ የአንድ አዳም አንድ አካል ከአንድ በላይ ሚስት አገባ ማለት ግን ከአንድ በላይ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሕገ ተፈጥሮን የሚጻረር ነው፡፡ ስለዚህ ከአንዲት በላይ ሚስት ማግባት በመሐመድ የተሰበከ የሰይጣን ትምህርት እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመርያው ያዘዘው ትእዛዝ ወይም በተፈጥሮ የሰጠው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እንድናገባ የፈቀደልን አንዲት ሚስትን ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ አንድ ነው፤ ሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ብቻ ናት፡፡ በክርስቶስ የተመሰለው ባልም ልትኖሮው የሚገባት አንዲት ሚስት ብቻ ናት /ኤፌ.5፡23/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!!