Sunday, December 25, 2011

ጸጋና እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ!!

(የዮሐንስ ወንጌል የአምስተኛው ሳምንት ጥናት)!!

“ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።” ዮሐ.1፡15-18

የወንጌላዊውን ጥበብ ተመልከቱ! ምክንያቱም ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ደጋግሞ እየነገረን ያለው መጥምቁ በአይሁድ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስለነበረው ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ ክርስቶስን ላለመቀበላቸው ምክንያት ያጡ ዘንድ ስለሚወዱት ሰው ምስክርነት አብዝቶ ይነግራቸዋል /ማቴ.14፡4፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም መጥምቁ ዮሐንስ ከጌታ 6 ወር አስቀድሞ ነበር የመጣው /ሉቃ.3፡2-6/፡፡ ሲመጣም በቀስታ ሳይሆን እየጮኸ፣ በድብቅ ሳይሆን በግልጥ፣ ተገድዶ ሳይሆን ስለ ሰው ልጆች መዳን ብሎ ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ ይመሰክርላቸው ነበር /ኢሳ.40፡3/፡፡ ብዙዎችም ተከትለውታል፡፡ አማኑኤል ከመጣ በኋላ እንኳን ሕዝቡ የጌታን አምላክነት ባለመረዳታቸው “ዮሐንስ ይበልጣል” ብለው ስላሰቡ ከእርሱ አልለይ ያሉትን ደቀ መዛሙርቱ በጥበብ ወደ ሙሽራው ይልካቸው ነበር /ማቴ.16፡14፣ ማቴ.11 ሙሉ፣ ቅ.ቄርሎስ/፡፡ መጥምቁ በእነርሱ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም እርሱ ግን “የጫማውን ማዘብያ እንኳን መፍታት አይገባኝም” እያለ ራሱን ዝቅ ዝቅ በማድረግ ከእርሱ ወደሚልቀው ጌታ ሁሉም ዘወር ይሉ ዘንድ ይተጋ ነበር /ዮሐ.3፡22-30/፤ ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ዕድል የነበረው ቢሆንም ትሕትናው ግን ይህን ያደርግ ዘንድ አልፈቀደለትም /ዮሐ.1፡26፣ አውግስጢኖስ/፡፡

ወንጌላዊው ይቀጥልና “እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናል” ይላል፡፡ እንዲህ ማለቱም ነበር፡- “ሦስት ዓመት ሙሉ ከክርስቶስ ጋር የተመላለስን ብቻ አይደለንም፡፡ አሥራ ሁለታችን፣ መቶ ሀያችን፣ ሦስት ሺው፣ ስምንት ሺው፣ አምስት ገበያው ሕዝብ ከክርስቶስ በረከት ተካፍለናል፤ የጸጋ ሥጦታው ከሆነው ከማዕዱ ተካፍለናል፤ ከሙላቱም ተቀብለናል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ምስክሮቹ ነን” /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም መጥምቁ ዮሐንስ ሲመሰክርለት የነበረው ጌታ ከጸጋ ተራቁተን ለነበርን ሁላችን ከመለኰታዊ ባሕርይው ሳይጐድል ጸጋውን ያድለን ዘንድ የመጣ ባለጸጋ ነው፤ ለዚህ የተገባን ሳንሆን ጸጋውን አደለን /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ የሕይወታችን ምንጭ፣ የነፍሳችን ብርሃን ክርስቶስ! ጸጋውን ቢያድለንም ከራሱ ቀንሶ አይደለም፡፡ እርሱ የማይጐድልበት ባለጸጋ ነውና፤ የሚጐድለንስ ከእርሱ የተቀበልን እኛው ነን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡
“በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀበልን” ማለትስ ምን ማለት ነው? በእምነት ላይ የዘላለምን ሕይወት፣ በአእምሮ ጠባይዕ ላይ መንፈሳዊ አእምሮን፣ በአሥርቱ ቃላት ላይ ወንጌልን ተቀበልን ማለት ነው፡፡ አስቀድመን ክርስቶስን ስናምን ወደ ሕይወት ጐዳና እንገባለን፤ ቀጥለንም እምነታችንን ፍሬ እንዲያፈራ በፍቅር በሚሠራ እምነት ስናደርገው ቸርነቱ በዝቶልን የዘላለምን ሕይወት እንቀበላለን /ገላ.5፡6/፡፡ ስለዚህ በእርሱ ቸርነት በሚሠራ እምነት ላይ የዘላለምን ሕይወት ተቀበልን /አውግስጢኖስ/፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እርሱ የእኛን ባሕርይ ስለተዋሐደ እኛም በመንፈሰ ረድኤት ላይ መንፈሰ ልደትን ተቀበልን /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ/፡፡

የሁለቱም ዮሐንስ ጥበብ ታስተውሉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ!! ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ ራሱን ከጌታ ኢየሱስ ጋር ካነጻጸረልን በኋላ ወንጌላዊው ደግሞ ሙሴንና ክርስቶስን በንጽጽር በማስቀመጥ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ጥበባቸውም ከእምነት ወደ እምነት እያሳደጉን ነው፡፡ መጥምቁ “እንደ ሰውነቱ ከእኔ በኋላ ይመጣል” ብሎ “እንደ አምላክነቱ ግን ከእኔ በፊት የነበረ ነው” ብሎ ከፍ ሲያደርገን፣ ወንጌላዊው ደግሞ “ሕግ በሙሴ ተሰጥቶን ነበረ” ይልና “ጸጋንና እውነትን ግን በክርስቶስ ተሰጠን” በማለት ያሳድገናል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ ከሙሴ እንደሚበልጥ ሁሉ ወንጌልም ከኦሪት ትበልጣለች /ዕብ.3፡3/፡፡ ምንም እንኳን ኦሪት ራሷ ጸጋ ብትሆንም ክርስቶስ የሰጠንን ጽድቅና ፍጽምና ግን ልታመጣ አልቻለችም /ኢሳ.64፡6/፡፡ ከዚያ ይልቅ ኦሪት የምታስፈራራ ስትሆን ወንጌል ግን የምትፈውስ ናት /ገላ.3፡22፣ ዮሐ.12፡47/፡፡ ኦሪት ለፍርሐት የሚሆን የባርነትን መንፈስ ትሰጣለች፤ ወንጌል ግን አባ አባ የምንልበትን የልጅነትን መንፈስ ትሰጣለች /ሮሜ.8፡15/፡፡ ኦሪት በሥጋ የሚደረግ መገረዝን ታዝዛለች፤ ወንጌል ግን በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝን /ሮሜ.2፡29፣ 1ቆሮ.7፡19/፡፡ ኦሪት የረከሰውን በውኋ ብቻ ሰውነትን ታጠራለች፤ ወንጌል ግን በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ አጥርታ ልጅነትን ትሰጣለች /ማቴ.3፡11/፡፡ ብዙ ማለት እንችል ነበር፤ ነገር ግን ጊዜ ሁናቴ ይገድበናል፡፡ በጥቅሉ ግን ሐዋርያው እንዲህ ይለናል፡- “ኃጢአትን ለምታስቆጥርና ለምታስኰንን ኦሪት ብዙ ክብር ከተደረገላት የጽድቅ መልእክት ለሆነችው ወንጌልማ ምን ያህል ትከብር ትመሰገን ይሆን?” /2ቆሮ.3፡9/፡፡ ይህም ማለት የሙሴ አገልግሎት “የኵነኔ አገልግሎት” ነበረች፤ በክርስቶስ የተቀበልነው ጸጋ ወንጌል ግን “የጽድቅ አገልግሎት” ነው /ቅ.ቄርሎስ/፡፡ በእርግጥም አሁን የተቀበልነው ጸጋ ኦሪት የያዘችውን ምሳሌና ጥላ ሳይሆን ወንጌል የያዘችውንና እውነት የሆነውን ክርስቶስን ነው /ጄሮም/፡፡

ወንጌላዊው፡- “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም” ስላለ “የማይታይ ታየ” ብለን ከምናስተምረው ጋር የሚጋጭ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ቅዱሳን አበው ወእማት በአንጽሖ መንፈስ አይተውታል፤ ሆኖም ግን በሚገባቸው ዓይነት፣ ምሳሌና ጐዳና እንጂ በመለኰታዊ ባሕርይው አይደለም /ዕብ.1፡1፣ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ/፡፡ “መላእክቶቻቸው ሁል ጊዜ የአባቴን ፊት ያያሉ” የሚል ቃል እንኳን ብንሰማ መላእክት ሙሉዕ በኵለሄ የሆነውን እግዚአብሔር ለእነርሱ በሚመጥናቸው መጠን ይታያቸዋል ማለት እንጂ በውሱን ባሕርያቸው ጠንቅቀው ያዩታል ማለት አይደለም /ማቴ.18፡10/፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን የሚመስል ሐሳብ አስቀምጦልናል /1ጢሞ.3፡16፣ ቴዎዶሬት ዘስይርጥ/፡፡ ሕገ ኦሪትን የተቀበለ ሙሴ እንኳን ምንም እንደ ባልንጀራ ከእግዚአብሔር ጋር ቢነጋገርም ክብሩን እንጂ መለኰታዊ ባሕርዩን አላየም /ዘጸ.33፡11፣20/፡፡ አስቀድሞ ሕግን ለሙሴ የሰጠ ወልድ ግን አሁን ጸጋንና እውነትን ተመልቶ ወደ እኛ መጣ /አውግስጢኖስ/፡፡ መቼም ቢሆን ታይቶ የማያውቅ እግዚአብሔር አብም ልጁ ልጅ ሆኖ በባሕርዩ አይቶ ነገረን /ሄሬኔዎስ/፡፡ 

የተገለጠውና አባቱንም የገለጠልን ልጅ አንድ ነው፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፡፡ እርሱ የባሕርይ ልጅ ነው (By Nature)፤ እኛ ግን አባ አባ የምንልበት መንፈስ የተቀበልን የጸጋ ልጆች ነን (By Adoption) /ሮሜ.8፡15/፡፡ አዎ! አካላዊ ቃል አባቱ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጐ የሰጠን አንድ ልጅ ነው /ሮሜ.8፡32፤ አውግስጢኖስ/፡፡ ስለዚህ አብን ያየው ይህ በአብ ዕሪና ያለው አንዱ ልጁ ብቻ ነው /ዮሐ.6፡46፣ ቅ.ቄርሎስ/፡፡ ከእርሱ ውጪ የአባቱን እቅፍ ጠንቅቆ የሚያውቅ የለም /ማቴ.11፡27፣ አውግስጢኖስ/፡፡ የአባቱ እቅፍ ስንልም መለኰታዊ ባሕርይውን ማለታችን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ራሱን ለዓለም የገለጠው በልጁ በኩል ብቻ ነው ማለት ሳይሆን ከሌሎች መገለጦች ይልቅ በልጁ በኩል የተገለጠው መገለጥ ፍጹም ነው፤ እንደሌሎቹ መገለጦች ሕጸጽ የለበትም ማለታችን እንጂ /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ 

ተወዳጆች ሆይ! የተደረገልንን ውለታ ተመልከቱ፡፡ እግዚአብሔር እንደ ድሮው በነብያት አልተናገረንም፤ በአንድ ልጁ በኵል እንጂ /ዕብ.1፡1/፡፡ የእነዚያ መምህር ሙሴ ነበር፤ የእኛ መምህር ግን የሙሴ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንግዲያስ ለዚሁ ጌታ የተገባን ሆነን ልንገኝ ያስፈልጋል፤ በዚሁ ምድር መንፏቀቅ ሊበቃን ይገባል፡፡ እርሱ ከልዕልናው ዝቅ ብሎ ያናገረን እኛ ከምድራዊ አስተሳሰብ እንላቀቅ ዘንድ ነውና፤ እርሱ በሄደበት ጐዳና እንድንመላለስ ነውና፡፡ “ይህንን እንዴት ማድረግ እችላለሁ?” ብላችሁ አትጨነቁ፡፡ ከእኛ የሚፈለገው ፍቃድ ብቻ ነው፤ ሠሪው ግን እግዚአብሔር ራሱ ነው /ዮሐ.15፡5/፡፡ ስለዚህ እርሱ እንደ ወደደን እርስ በእርሳችን እንዋደድ፡፡ “እኔ እንዲህ ዓይነት ሰው አልወድም፤ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ያሥጠላኛል፤ እኔ እርሱን ልወደው አልችልም” እያልን ራሳችንን አናታልል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ የምንለው ሰውዬ እንደ እኛ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ፣ ክርስቶስም ዋጋ የከፈለለት ክቡር ሰው ነውና፡፡ ክርስቶስ ለሁለታችን መዳን መጣ እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንደ እግር፣ እጅ፣ አፍንጫ… በአንድ ክርስቶስ ያለን ብልቶች እንጂ የተለያየን አይደለንም፡፡ ሐዋርያው “እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል” እንዲል /1ቆሮ.12፡13/፡፡ እንግዲያስ “ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” /ኤፌ.5፡29/ በአንዲት ተዋሕዶ ሥር ሆነን ሳለ አንቦጫጨቅ፤ አንነካከስ፤ አንድ እንሁን፤ እንደ ቅርጫ ሊከፋፈሉን የሚያሰፈስፉ ክፉ መናፍስትን ከእኛ እናርቅ፡፡ እኛ ስንዋደድ የሰማዩ አባታችን እግዚአብሔር ይከብራል፤ እንዲህ ካልሆነ ግን በአሕዛብ ዘንድ ስሙን እናሰድባለን፡፡ መልካሙን ሁሉ እንድናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!
 
ሰላም ወሰናይ (በስድስተኛው ሳምንት ሰላም ያገናኘን)!

የዮሐንስ ወንጌል የ2ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የ3ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የ6ኛ ሳምንት

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount