በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
1. “በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ። የተርሴስና
የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።” እና “የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና
የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።” ተብሎ በነብያቱ
የተነገረውን ትንቢት በቀጥታ “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው
እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።” ተብሎ ሲፈጸም ስለምንመለከተው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ጌታ ሲወለድ በቤተልሔም ተመሠረተች
ቢባል ያስኬዳል /መዝ.71፡9-10፣ ኢሳ.60፡6፣ ማቴ.2፡1-11/፡፡ በኋላ ደግሞ የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ እንደሚነግረን፡- “የጌታም
መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው።ተነሥቶም
ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው
ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን።
ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?
አለው። እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።ያነበውም
የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥
ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ
ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።
ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።
ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ
ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና።” ይለናል /ሐዋ.8፡26-39/፡፡ ይህም
የሆነው በ34 ዓ.ም. ነው፡፡ በይፋ በጳጳስ መመራት የጀመረችው ግን በ330 ዓ.ም. በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አማካኝነት ነው፡፡
- “ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል “ኦርቶዶክስያ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ቀጥተኛ (እምነት) ማለት ነው፡፡ የምስራቅና የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናትም ይጠሩበታል፡፡
- “ተዋሕዶ” የሚለው ቃል በግሪኩ “Miaphysis” የሚለውን ቃል የሚተካ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን /ዮሐ.1፡1፣14/፣ መለኰትና ትስብእትም ያለ መለያየት፣ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየት ስለ ተዋሐዱ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ፈቃድ፣ አንድ ግብር መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
2. ምንም እንኳን የባዕድ አምልኮ ቢኖርም ኢትዮጵያ መጀመርያ በሕገ
ልቡና ትመራ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ፍንጭ ይሠጠናል /ዘጸ.2፡21/፡፡ ሕገ ልቦና ማለትም ሕግ በሙሴ ከመሰጠቱ በፊት ያለውን
ጊዜ ሲሆን እነ አቤል፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ጻድቁ ኢዮብ… የተመሩበት ሕግ ነው፡፡ መመርያ ሳይኖር በልቦና ጽላት ባለው እውነት አንድ
እግዚአብሔርን ማምለክ ማለት ነው፡፡ ከዚህም በመቀጠል ኢትዮጵያ ሕገ ኦሪትን እንደ ተቀበለች በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል /1ነገ.10፡10-ፍጻሜ፣
ማቴ.12፡42፣ ሶፎ.2፡12፣ ኢሳ.20፡3/፡፡ ሕገ ኦሪት ማለትም በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የተሰጠ የእግዚአብሔር ሕግ
ነው፡፡
3. የብሉይ ኪዳን ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት ማለት የብሉይ ኪዳን
መጻሕፍት በአንድ ጊዜ እንዳልተጠረዙ የሚያመለክት ነው፡፡ የመጀመርያዎቹ የቀኖና መጻሕፍት ከትንቢተ ዳንኤል ውጪ አይሁድ ራሳቸው
የሚቀበልዋቸው ሲሆኑ ሁለተኞቹ ግን በቀጥታ ስለ ክርስቶስ የሚወለድበትን ጊዜና ቦታ ስለሚናገሩ በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላገኙ
ናቸው፡፡ ምክንያቱም አይሁድ ጌታ ገና ይወለዳል ስለሚሉ እነዚህን መጻሕፍት አይቀበልዋቸውም፡፡ በመሠረቱ እነዚህን መጻሕፍት መጀመርያ
ወደ ግሪክ ቋንቋ ባይተረጐሙ ኖሮ ሐዋርያትም ራሳቸው እንኳንስ እነዚህ ዋናውን ብሉይ ኪዳን እንኳን ባላገኙት ነበር፡፡ ምክንያቱም
አሁን በአይሁድ እጅ የሚገኘው ብሉይ ኪዳን የተበረዘ እና ስለ ክርስቶስ የሚናገሩትን ቃላት የተጠመዘዙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እነዚህ
የቀኖና መጻሕፍት ከፕሮቴስታንት አማኞች በስተቀር በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት አላቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መልክ ግን
አልጠረዝዋቸውም፡፡ የፕሮቴስታንት አማኞች እነዚህን ተጨማሪ መጻሕፍት የማይቀበልዋቸው ብሉይ ኪዳንን አይሁድ ካሻሻሉት ብሉይ ኪዳን
ስለ ተረጐሙት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ተብለው የተዘጋጁት በጣም ብዙ ሲሆኑ የመለየት ሥራ የተሠራው በመንፈስ
ቅዱስ መሪነት በኦርቶዶክሳውያን አባቶች አማካኝነት ነው /ሉቃ.1፡1-4/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ላይ ተጠርዞ አገልግሎት መስጠት
የጀመረው በ4ኛው ክ.ዘ. ነው፡፡
4.የኢ/ኦ/ተ/ቤ.ክ. ለጸሎትና ለቅዳሴ የምትጠቀምባቸው መጻሕፍት
መሠረታቸው የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው /ኢሳ.24፡5፣ መዝ.118፡118፣ 1ተሰ.5፡14፣ 2ተሰ.3፡6…/፡፡ ለምሳሌ
ውዳሴ ማርያምን ያየን እንደሆነ የክርስቶስን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድን አስፍቶ እና አብራርቶ የሚገልጽ የጸሎት መጽሐፍ
ነው፡፡ ሁል ጊዜ ማየት የሚገባን ነገር ቢኖር የመጽሐፉ አቅጣጫ ከእግዚአብሔር አውጥቶ ለሌላ አካል አሳልፎ የሚሰጠን ከሆነ የጸሎት
መጽሐፍ ሳይሆን የጥንቆላ መጽሐፍ ነው፡፡
5. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ከክርስትና በፊት ብሉይ ኪዳንን ተቀብላ እንደ
ነበረ በተራ ቁጥር 2 ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ ከብሉይ ኪዳን ያገኘቻቸውን ጠቃሚ ነገሮች በክርስትና መንፈስ እየተረጐመች ትጠቀምባቸዋለች፡፡
ከእነዚህም አንዱ ታቦት ነው፡፡ የሐዲስ ኪዳኑ ታቦት በቅርጽም በአገልግሎትም ከብሉይ ኪዳኑ በጣም የተለየ ሲሆን በእርሱ ላይ የተጻፈው
ጽሑፍም “እግዚአብሔር አልፋና ኦሜጋ ነው” የሚል ነው፡፡ በታቦቱ ላይ የክርስቶስ ሥነ-ስቅለት ይሳልበታል፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ሥጋውና
ደሙ ይፈተትበታል (ይቆረስበታል)፡፡ ስለዚህ ታቦት ምእመናን ሥጋዉን የሚበሉበት ደሙንም የሚጠጡበት የምሕረት መሠዊያ ነው፡፡ ክብርና
ስግደትም የሚደረግለት ስለዚሁ ነው /ፊሊ.2፡10/፡፡
6. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ክርስቶስን በድርጊቶቿ ሁሉ ትሰብከዋለች፡፡
ለምሳሌ፡ በቅዳሴዋ፣ በጸሎቷ፣ በሥዕል፣ በመስቀል፣ በባህሏ…፡፡ ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋንና
መርገመ ነፍስን አጥፍቶ ድኅነተ ምእመናንን የፈጸመው በዕፀ መስቀል ስለሆነ ይህ መስቀል የድል አድራጊነቷ አርማዋ ነው፡፡ ለዚህም
ነው በጉልላትዋ ላይ ከፍ አድርጋ የምትሰቅለው፡፡ ጌታ በዚህ መስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ገነትን ከከፈተ፣ ሲዖልንም ከበረበረ ድውያነ
ሥጋን ቢፈውስ አይደንቅም፡፡ ክርስትናን ስንመለከት በእምነት ዓይን መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ፡ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት (መጠመቅ)
“እንዴት ልጅነትን ይሰጣል?” ብለን ሥጋዊና ደማዊ አመክንዮ ከሰጠን ምሥጢሩ ላይገባን ይችላል፡፡ መጸሐፍ እንደ ነገረን ካመንነው
ግን ሕይወት ይሰጠናል፡፡
7. “ቅድስት ድንግል ማርያም ታማልዳለች አታማልድም” የሚለው ክርክር
የተፈጠረው መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ካለመረዳትና የኢየሱስ ክርስቶስን አስታራቂነት በትክክል ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ በመጽሐፍ
ቅዱስ አንዱ አማኝ ለሌላው አማኝ መጸለይ እንደሚችል በግልጽ ቋንቋ ተጽፏል /ያዕ.5፡16/፡፡ የዚሁ አማኝ ጸሎት ግን የክርስቶስን
አዳኝነት የሚተካ ሳይሆን የጸሎት እርዳታ ነው፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ እንዳረጋገጠው የጻድቅ ሰው ጸሎት ከኃጢአተኛው ጸሎት ይልቅ
የበለጠ ተቀባይነት አለው /ምሳሌ.15፡29/፡፡
8. በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ወንድ በ40 ቀን ሴት በ80 ቀን የምትጠመቀው
መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው /ዘሌ.12፡1-2/፡፡ ይህም ማለት በዮሐ.3፡3-5 እንደተገለጠው ማንም ያልተጠመቀ ሰው የእግዚአብሔርን
መንግሥት መግባት አይችልም፡፡ ቃሉም ከሕጻናት በስተቀር ስለማይል ማጥመቁ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ግዝረት የጥምቀት
ምሳሌ እንደ ነበረ ቅዱስ ጳውሎስ ይነግረናል፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው የግዝረት ተቀባይ አብርሃም በ99 ዓመቱ የተገረዘ ቢሆንም ልጁ
ይስሐቅ ግን በ8 ቀኑ ነበር የተገረዘው፡፡ ምክንያቱም የአማኝ ልጅ ስለ ሆነ እንደ አብርሃም መጀመርያ እንዲያምን አይጠበቅበትም፡፡
በሐዲስ ኪዳንም ሕጻናት እንደተጠመቁ ተመዝግቧል፡፡ የክርስትና አባት የሚባለውም የልጁን እምነት የሚመሰክርለት ሰው ነው፡፡ ልጁ
ሲያድግ ግን እምነቱን በራሱ መግለጥ አለበት፡፡ ልጁ ምናልባት ከ40 ቀን በፊት ሊገድል የሚችል በሽታ ቢይዘው አስቀድሞ ሊጠመቅ
ይችላል፡፡ ክርስቶስ ሕጻናትን ጠርቶ የባረካቸው ስለ ልባቸው ንጽህና እንጂ ስላመኑት አልነበረም /ማቴ.19፡14/፡፡ ሕጻናት ቢታመሙ
ወላጆቻቸው ወደ ሐኪም ቤት የሚወስድዋቸው ሕጻናቱ “ሐኪም ቤት ውሰዱን” ስላልዋቸው ሳይሆን ሐላፊነት ስላለባቸው ነው፡፡ ከዚህ በበለጠ
ደግሞ ለነፍሳቸው ሐላፊነት ስላለባቸው ማስጠመቅ ይገባቸዋል፡፡
9.ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ጾም አለ፡፡ በብሉዩም በሐዲሱም ጾም ሲተገበር
እንመለከታለን፡፡ ጌታ እንዳስተማረንም ከርኩስ መንፈስ ቁራኝነት ለመላቀቅ ጾም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያናችንም
ከሐዋርያት የወረሰችው የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡፡ በሕጓ መሠረትም ሰባት የጾም ወራት አሏት፡፡ እነዚህ ሰባቱ የሕግ ጾም ይባላሉ፡፡
ታውጀውም መጾም የሚችል ምእመን ሁሉ የሚጾማቸው ናቸው፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የገና ጾም፡- ይህን ጾም የምንጾመው ነቢያት በየዘመናቸው ስለ መሲሕ ክርስቶስ መምጣት በናፍቆት ይጾሙ ይጸልዩ ስለነበር እኛም የእነርሱን አርአያን ተከትለን የክርስቶስን ልደት ከማክበራችን በፊት እንድንጾም ሐዋርያዊት ቤ/ክ. ሥርዓት ሠርታለች፡፡
- ጾመ ገሃድ፡- ገሃድ ማለት በይፋ መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው፡፡ ከጥምቀት አንድ ቀን በፊት የምንጾማት ጾም ነች፡፡
- ነነዌ፡- የቤ/ክ. አባቶች ይኸንን ጾም የወሰኑት የነነዌ ሰዎች በጾምና ጸሎት ከመዓት ከጥፋት እንደዳኑ ምእመናንም በጾምና በጸሎት ከፈጣሪያቸው ምሕረትና በረከት እንዲያገኙ በማለት ነው /ትንቢተ ዮናስ በሙሉ/፡፡
- ዓብይ ጾም፡- ይህ ጾም ጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው ጾም ነው /ማቴ.4፡1/፡፡ ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡ ይህ ጾም ስምንት ሳምንታት ያሉት ነው፡፡ ከእነዚህም ሳምንታት ውስጥ ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሁድ ይገኛሉ፡፡ አስራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ ከጥሉላት እንጂ ከእህልና ከውኃ ስለማይጾሙ የጾሙ ወራት አርባ ቀን ብቻ ይሆናል፡፡
- የሐዋርያት ,,፡- ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሄዳቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው /ማቴ.9፡11/፡፡ ምእመናንም እነርሱን ተከትለው ከጰራቅሊጦስ በበነጋው ጀምረው ይጾሙታል፡፡
- ጾመ ድኅነት፡- ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ከሚገኙት በስተቀር ዓመት ሙሉ ረቡዕና ዓርብ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ረቡዕ የአይሁድ ሸንጐ ጌታን ለመስቀል የመጨረሻ ውሳኔ ያስተላለፉበት ቀን ስለ ሆነ ክርስቲያኖች ያንን እያሰቡ ይጾሙታል፡፡ ዓርብም ጌታ የተሰቀለበትና የሞተበት፣ ሲጠበቅ የነበረውን ተስፋ የተፈጸመበት ቅዱስ ዕለት ስለ ሆነ በቤ/ክ. በጾምና በጸሎት እንዲከበር ታዟል፡፡
- ፍልሰታ፡- በቤተክርስቲያናችን እንደሚተረከው ይህ ጾም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጥር 21 ቀን 49 ዓ.ም. አርፋ ከስምንት ወር በኋላ ሐዋርያት አስከሬኗን ተቀብለው የቀበሩበትን በማሰብ የሚጾም ጾም ነው፡፡ አስራ አምስት ቀን የሆነበት ምክንያትም ሐዋርያት ትንሣኤዋን ለማየት የሁለት ሳምንት ሱባኤ ይዘው በአስራ ስድስተኛው ቀን ስለተለጠችላቸው ነው፡፡ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም ጾሙ የተከበረ ነው፡፡ ነገር ግን ሞቷም እርገቷም በነሐሴ ነው ይላሉ፡፡
እነዚህ የሕግ
ጾሞች እንደ ተነጋገርነው ምንጫቸው መጽሐፍ ቅዱስ እና የቤ/ክ. ቅዱስ ትውፊት ሲሆን የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ ከኃጢአት ለመንጻት
ስለ ራስ የታሰበውን ለነዳያን በመስጠት የሚጾሙ ናቸው፡፡ በሌሎች መሰል አብያተ ክርስቲያናትም የሚጾሙ ናቸው፡፡
10.የክርስቲያን ሥጋ ማለት እንስሳው ሲታረድ ስመ እግዚአብሔር ተጠርቶ
በሥላሴ ስም የተባረከ ማለት ነው፡፡ የምናደርገው ነገር ሁሉ በእዚአብሔር ስም እንድናደርገው ጌታ አዝዞናል /ዮሐ.16፡23-24/፡፡
ነገር ግን ክርስትና ዕድልን የማይሰጥ ጠባብ ሃይማኖት ስላልሆነ ማረድ በማትችልበት ሁናቴና ለራስና ለሌላ ሰው መሰናክል በማይሆኑበት
አጋጣሚ በሥላሴ ስም ባርኮ መብላት ይቻላል፡፡
11.በዓመት ውስጥ የሚከበሩ በዓላትን በተመለከተ፡-
- የዘመን መለወጫ በዓል፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤል ነጻ ከወጡበት ከመጋቢት ወር ጀምረው ቆጥረው በሰባተኛው ወር አዲስ ዓመት እንዲያከብሩ በፈጣርያቸው ታዘዋል /ዘሌ.23፡24፣ ዘኅ.29፡1/፡፡ በክርስተናው ዓለምም ይህንኑ የብሉይ ኪዳንን ትእዛዝ ተቀብላ አዲስ ዓመት በመስከረም ወር መጀመርያ እያከበረች ብዙ ዘመን ኑራለች፡፡ በኋላ ግን ከ1073-1085 ዓ.ም. የነበሩት የሮማ ፖፕ ጐርጐርዮስ 7ኛ የአዲስ ዓመት መጀመርያ ከልደት እንዲያያዝ ለማድረግ በጥር ወር ይሁን ብለው ወሰኑ፡፡ በዚህ ውሳኔ የካቶሊክ ግዛት የነበረው ምዕራቡ ዓለም በሙሉ ሲስማማ ምሥራቁ የክርስቲያን ዓለም ግን መስከረምን አልለቀቀም፡፡ በፖለቲካና በንግድ ተጸዕኖ ምክንያት መንግሥታት በአቆጣጠር ወደ ምዕራቡ ዓለም ሲሳቡም በምሥራቅ ያለች ቤ/ክ. አዲሱን ዓመት የምታከብረው አሁንም በመስከረም ነው፡፡ ለምሳሌ፡ ሩስያ፣ ግሪክ፣ ሮማንያ እና ሌሎች ይህን በዓል የቤ/ክ. አዲስ ዓመት ይሉታል፡፡
- የመስቀል በዓል፡- ይህ በዓል በክርስቲያኑ ዓለም ሁሉ የሚከበር ሲሆን ከትውፊት የተገኘውን ታሪኩም በመጠኑ እነሆ፡- ጌታ በመስቀል ላይ ሞቶ ከተነሣ በኋላ ሕሙማን መስቀሉን እየዳሰሱና እየታሹ ይፈወሱ ነበር፡፡ በዚህ ተአምራት እየተሳቡም ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች ሆኑ፡፡ ይህንንም ያዩ አይሁድ ግን መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀምያ ቦታ ጣሉት፡፡ በየቀኑ የአከባቢው ኗሪ ሁሉ ቆሻሻ ስለሚጥልበት ያ ቦታ እንደ ጉብታ ሆነ፡፡ ክርስቲያኖቹም ከደረሰባቸው መከራ የተነሣ ኢየሩሳሌምን ጨርሰው ስለ ወጡ የከተማዋም መልክዐ ምድርም ፈጽሞ ስለ ተለወጠ መስቀሉ የተደፈነበት ቦታ ወዴት እንደ ሆነ ማወቅ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ከ300 ዓመት በላይ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር በ4ኛው ክ/ዘ. በነበረችው በንግሥት እሌኒ ከወጣ በኋላ በመላው ዓለም ባሉ ክርስቲያኖች ዘንድ የሚከበር በዓል ሆኗል፡፡
- የገና በዓል፡- ጌታ የተወለደበት ቀን ማቴ.2፡1-11
- የጥምቀት በዓል፡ ጌታ የተጠመቀበት ቀን ማቴ.3፡13-15
- የትንሣኤ በዓል፡ ጌታ የተነሣበት ቀን ማቴ.28፡1-10
- የደብረ ታቦር በዓል፡ ጌታ ግርማ መንግሥቱን ያሳየበት ቀን ማቴ.17፡1-9
12.በቅዱሳን ስም
ማኅበር መሥርቶ ጽዋ መጠጣት ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ትውፊት ነው፡፡ ይኸውም በሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው የመጀመርያዎቹ ክርስቲያኖች
በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋር በነበሩበት ጊዜ ጥሪት ቅሪታቸውን፣ ርስት ጉልታቸውን እየሸጡ እያመጡ ለሐዋርያት ያስረክቡ ነበር /ሐዋ.2፡45-46/፡፡
በፍቅር ሆነውም በአንድነት ይመገቡት ነበር፡፡ በኋላ ግን ምእመናን እየበዙ ስለ ሄዱ ክርስቲያኖቹ ጌታ ሞትን ድል አድርጐ በተነሣበት
ዕለት በዕለተ-ሰንበት፣ የሃይማኖት አርበኞች ወንድሞቻቸው ሳይፈሩ እና ሳያፍሩ በክርስቶስ ያላቸውን እምነት መስክረው በአላውያን
ሸንጐ የተሰየፉበትን ዕለት መታሰብያ በሚያከብሩበት ዕለት ሁሉ ቤቱ ያፈራውን እያመጣ ከጸሎቱ ፍጻሜ በኋላ በቤ/ክ. ገረገራ ውስጥና
በየምእመኑ ቤት እየተሰበሰቡ ከጸሎተ ቅዳሴ በኋላ የአንድነት ማዕድ ይሳተፉ ነበር፡፡ ይኸው ክርስቲያናዊ ትውፊት ቀስ በቀስ መልኩን
እየለወጠ ሄዶ ዛሬ በሌሎች የክርስቲያን ዓለማት በወረቀት ላይ ብቻ ሰፍሮ “ነበር”ን ይዞ ቀርቷል፡፡ በእኛ በኢ/ያ ግን እስከ አሁን
ድረስ ይሠራበታል፡፡ በተለይ በቤ/ክ. ዐውደ ምሕረት ሲደረግ በቤት ከሚቆረጠው ጮማ ይልቅ ይጣፍጣል፤ ይስማማል፤ ረድኤትም አለው፡፡
በፍቅር በእግዚአብሔር ስም የሚደረግ ነው፡፡ በዚሁ ማዕድ ደሀ ሀብታም ተብሎ አይለይም፡፡ ምእመናኑ የአንድ ክርስቶስ አባል መሆናቸውን
የሚገልጽ ምሥጢር አዘል ትምህርትም አለው /1ቆሮ.11፡18-22/፡፡ ስለዚህ በጌታ፣ በእመቤታችን፣ በመላእክት፣ በቅዱሳንና በሰማዕታት
ስም በዓላቸው በሚከበርበት ዕለት ድግስ ተደግሶ ደሀ ሀብታም ሳይባል ብድራትም ሳይሻ ሁሉንም ተጠርቶ ይጋብዛል፡፡ ዝክር (መታሰብያም)
ይባላል፡፡
13. እምነት ወይም
ቅዱስ አፈር ከሥጋ ደዌ የሚፈውስ አፈር ነው፡፡ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠ እውነት እንጂ ዝም ብለው ሰዎች የፈጠሩት ተረት
ተረት አይደለም /2ነገ.5፡17/፡፡ ጸበል (ቅዱስ ውኃም) በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠ እውነት ነው /ዮሐ.5፡2-4/፡፡ ስለዚህ ምንም
ሳንጠራጠር ልንጠቀምበት የሚገባንና እግዚአብሔር የሰጠን የፈውሰ ሥጋ መንገድ ነው፡፡
14.በቤተ ክርስቲያን
ሻማና ጧፍ የምንጠቀመው የወንጌልን ብርሃንነት ለመግለጽ ነው፡፡ እኛም ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣታችንን መመስከራችን ነው፡፡
15.ኃጢአትን ለካህን
መናዘዝ ምሥጢርን ማባከን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራና ኃጢአቱም ለካህኑ ቢነግር
ካህኑም ስለ ኃጢአቱ በጸልይለት ኃጢአቱ ይሰረይለታል /ዘሌ.5፡5-6/፡፡ በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር ለመላእክትም ይሁን ለሊቃነ
መላእክት ያልሠጠውን ሥልጣን ለካህናት ሰጥቷል /ማቴ.16፡19/፡፡ የብሉይ ኪዳኑ ካህን የሥጋን ደዌ ሊፈውስም ላይፈውስም ይችላል፡፡
የሐዲስ ኪዳን ካህናት ግን የነፍስን ደዌ ከእግዚአብሔር በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይፈውሳል፡፡ የሥጋ ወላጆቻችን ወደዚህ ዓለም ይወልዱናል፤
ካህናት ግን ወደ ዘላለማዊ ዓለም ይወልዱናል፡፡ ወላጆቻችን ከሞትም ይሁን ከስቃይ ሊታደጉን አይችሉም፤ ካህናት ግን ነፍሳችንን ከሞትና
ከዘላለማዊ ጥፋት እንድትድን ያደርጉዋታል፡፡
16. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ.
አስተምህሮ መሠረት አንድ ሰው ሲሞት ወደ መቃብሩ በሚጓዝበት ጊዜ በ7 ምዕራፍ 7 ጊዜ ጸሎተ ፍትሐት ይደረስለታል፡፡ ይኸውም እስራኤል
የኢያሪኮን ከተማ 7 ጊዜ እየዞሩ በጸለዩ ጊዜ የብረት ቅጥሩ እንደፈረሰ የዘመነ ሐዲስ ካህናትም ቅዱስ ጳውሎስን ተከትለው እግዚአብሔር
ሟቹን በመጨረሻይቱ ቀን እንዲምረውና ቅጽረ ኃጢአቱን ያፈርስለት ዘንድ ቤተ ክርስቲያኑን 7 ጊዜ እየዞሩ ይጸልዩለታል /ኢያሱ.7፡5፣
2ጢሞ.1፡16-18/፡፡ በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በጸሎተ ቅዳሴዋም ታስባቸዋለች፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ካቶሊካዊት
ቤ/ክ. የሰውየውን ኃጢአት ለመደምሰስ አትጸልይም፡፡ የሰውየውን ኃጢአት በጸሎተ ፍትሐት ይፋቃል ማለት (ሎቱ ስብሐትና) የክርስቶስን
የቤዛነት ሥራ ከንቱ ማድረግ ነው /ሮሜ.3፡24-25፣ 1ዮሐ.2፡1-2፣ 1ዮሐ.4፡10/፤ ነገረ-ድኅነትን ማስተሐቀር ነው /1ዮሐ.1፡7፣
ዕብ.9፡12/፤ የመስቀሉን ሥራ መሳደብ ነው /ዮሐ.3፡16/፤ ምሥጢረ ንስሐንም መና ማድረግ ነው /ሐዋ.3፡19፣ ኢሳ.44፡22፣
ቆላ.2፡13-14፣ ኢሳ.43፡25/፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ
ጌታ ይስጠው” እያለች የመጨረሻይቱ የፍርድ ቀን ከመድረሷ በፊት በሥጋ ከምድራዊቷ ማኅበረ ምእመናን የተለዩትን አማኞች ትጸልይላቸዋለች፡፡
ተዝካርም ታደርግላቸዋለች /ሲራክ.38፡16-23/፡፡
17. ሲጋራን፣ መጠጥንና
ዘፈንን በተመለከተ፡-
- ሲጋራን ማጤስ በተመለከተ፡- ሲጋራን ማጤስ ጤናን እንደ ሚጐዳ ማወቁ ፈላስፋ መሆንን አይጠይቅም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስም አያስፈልገውም፡፡ ማኅበራዊ ግንኝነትንም እንደሚያበላሽ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከስነ ምግባርና ለሰዎች መሰናክል ከመሆን አንጻር የጐላ አደጋ አለው፡፡ በወንጌል እንደተነገረም “ለሰው መሰናክል ከመሆን የወፍጮ ድንጋይ ተጭኖን ወደ ባሕር መጣል ይሻላል” ስለሚል የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. ሲጋራን ማጤስ ትከለክላለች፡፡
- መጠጥን በተመለከተ፡- መጠጥ ሲባል ውኃ ብቻ አይደለም፡፡ መጠጥ ባያሳምም እንኳ ሰካራም ያደርጋል፡፡ ስካር ደግሞ ሌሎች ኃጢአቶችን (ለምሳሌ እንድትዘፍን፣ እንድታመነዝር…) እንድታደርግ ይገፋፋሃል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ስካርን እንጂ ልኩንና መጠኑን የታወቀ መጠጥን አትከለክልም፡፡ ነገር ግን ላለመስከር አለመጠጣትን ታበረታታለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠጥ ጠጥተውና ሰክረው ኃጢአት የሰሩ እንዳሉ ሁሉ ለጤናቸው ብለው ሳይሰክሩ የጠጡም አሉ፡፡
- ዘፈንን በተመለከተ፡- ቤተ ክርስቲያናችን ዘፈንን አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ መጽሐፍም “ደስ ያለው ቢኖር ይዘምር” እንጂ “ይዝፈን” አላለም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስና ሐዋርያትም ይኸንን አጥብቀው ኰንነዋል፡፡
18.
ምንኩስና ወይም ባሕታዊነት ወይም በገዳም መኖር አዲስ ነገር ሳይሆን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ለእግዚአብሔር
ተለይተው የኖሩት ሕይወት ነው፡፡ ኤልያስና መጥምቁ ዮሐንስ ምንም ሰዎች ቢሆኑም በገዳም ኖረዋል /ማቴ.3፡1-2፣ 2ነገ.1፡9/፡፡
ጌታም ወደ ገዳም ሄዶ ጾሟል ጸልዮአል /ማቴ.4፡1/፡፡ ይህንን አብነት አድርገው ብዙ አባቶች እና እናቶች ይህን ሕይወት መርጠዋል፡፡
ትዳርን ከማገልገል ይልቅ ጌታን ማገልገል ይሻለናል በማለት ሕይወታቸውን ሙሉ በጾምና በጸሎት አሳልፈዋል /1ቆሮ.7፡32/፡፡
ማጠቃለያ፡- እንግዲህ ይህንን መልስ ስሰጥህ ፍንጭ ታገኝ እንደ ሆነ እንጂ ይህ ብቻ በቂ ነው ብዬ አይደለም፡፡ አስፍተን
እና አልምተን መነጋገር ቢያስፈልግ በአካል አንድ በአንድ ልንነጋገር እንችላለን፡፡
ከክርስቶስ
ፍቅር ጋር!! አሜን!!
ወንድምህ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ !!
ሚያዝያ
11/ 2003 ዓ.ም አ.አ!!
16. በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. አስተምህሮ መሠረት አንድ ሰው ሲሞት ወደ መቃብሩ በሚጓዝበት ጊዜ በ7 ምዕራፍ 7 ጊዜ ጸሎተ ፍትሐት ይደረስለታል፡፡ ይኸውም እስራኤል የኢያሪኮን ከተማ 7 ጊዜ እየዞሩ በጸለዩ ጊዜ የብረት ቅጥሩ እንደፈረሰ የዘመነ ሐዲስ ካህናትም ቅዱስ ጳውሎስን ተከትለው እግዚአብሔር ሟቹን በመጨረሻይቱ ቀን እንዲምረውና ቅጽረ ኃጢአቱን ያፈርስለት ዘንድ ቤተ ክርስቲያኑን 7 ጊዜ እየዞሩ ይጸልዩለታል /ኢያሱ.7፡5፣ 2ጢሞ.1፡16-18/፡፡ በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በጸሎተ ቅዳሴዋም ታስባቸዋለች፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ካቶሊካዊት ቤ/ክ. የሰውየውን ኃጢአት ለመደምሰስ አትጸልይም፡፡ የሰውየውን ኃጢአት በጸሎተ ፍትሐት ይፋቃል ማለት (ሎቱ ስብሐትና) የክርስቶስን የቤዛነት ሥራ ከንቱ ማድረግ ነው /ሮሜ.3፡24-25፣ 1ዮሐ.2፡1-2፣ 1ዮሐ.4፡10/፤ ነገረ-ድኅነትን ማስተሐቀር ነው /1ዮሐ.1፡7፣ ዕብ.9፡12/፤ የመስቀሉን ሥራ መሳደብ ነው /ዮሐ.3፡16/፤ ምሥጢረ ንስሐንም መና ማድረግ ነው /ሐዋ.3፡19፣ ኢሳ.44፡22፣ ቆላ.2፡13-14፣ ኢሳ.43፡25/፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ “በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው” እያለች የመጨረሻይቱ የፍርድ ቀን ከመድረሷ በፊት በሥጋ ከምድራዊቷ ማኅበረ ምእመናን የተለዩትን አማኞች ትጸልይላቸዋለች፡፡ ተዝካርም ታደርግላቸዋለች /ሲራክ.38፡16-23/፡፡
ReplyDeleteቃለ ሂወት ያሰማልን
ReplyDeleteቃለ ሂወት ያሰማልን
ReplyDelete