ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን
ሲያሰተምር እንዲህ አለ፡- “ማንም ከእናንተ ታላቅ መሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን… ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ
ባርያ ይሁን… ታላቅ መሆንን ማሰብ የክፉዎች ሐሳብ ነው… የመጀመርያነትን ስፍራ መፈለግ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው… ታላቅነትን መፈለግ
ታናሽነት ነው፡፡
ስለዚህ ይህን ልቡና ከእናንተ ገርዛችሁ ጣሉት… በእናንተ በክርስቲያኖች
ዘንድ እንዲህ አይደለም… በአሕዛብ ዘንድ የመጀመርያነትን ስፍራ የሚይዙ በሌሎች ዘንድ አለቆች እንዲሆኑ ነው… በእኔ ዘንድ ግን
የመጨረሻውን ስፍራ የሚይዝ እርሱ የመጀመርያ ነው፡፡
ይህን ከእኔ መማር ትችላላችሁ… እኔ ምንም የነገሥታት ንጉሥ የአለቆችም
አለቃ ብሆንም በፈቃዴ የባርያዎቼን የእናንተን መልክ እይዝ ዘንድ አልተጠየፍኩም… በሰዎች ዘንድ የተገፋሁ ሆንኩ… ተተፋብኝ… ተገረፍኩኝ…
ይህም ሳይበቃኝ በመስቀል ሞት ሞትኩኝ፡፡ ነገር ግን ላገለግል ስለ ብዙዎችም ነፍሴን ቤዛ ልሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉኝ አልመጣሁም፡፡
ቤዛነቴም ለወዳጆቼ ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉኝም ለሚወግሩኝም ለሚያሰቃዩኝም ጭምር ነው፡፡ የእናንተ አገልጋይነት ግን ለእናንተ ለራሳችሁ
እንጂ ለሌሎች ቤዛነት የሚሆን አይደለም፡፡
እንዲህ አድርጌ ስነግራችሁ ክብራችሁ ዝቅ ዝቅ ያለ መስሎ አይታያችሁ… ምንም ያህል ዝቅ ዝቅ ብትሉም እኔ የተዋረድኩትን
ያህል አትዋረዱም… እኔ ይኼን ያህል ከመጨረሻው የክብር ጠርዝ ወደ መጨረሻው የውርደት ጠርዝ ብወርድም ለብዙዎች መነሣት ሆንኩኝ…
ክብሬ ከመቃብር በላይ ሆነ… ክብሬ በዓለም ላይ ከአጥብያ ኮከብ በላይ ደመቀ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመወለዴ በፊት
መታወቄ በመላእክት ዘንድ ብቻ ነበር… አሁን ሰው ከሆንኩኝ በኋላ ግን ክብሬ በመላእክት ብቻ ሳይሆን በሰው ዘንድም የታወቀ ነው፡፡
ስለዚህ ትሕትናን ገንዘብ ስታደርጉ ክብራችሁ እንደተነካ አድርጋችሁ አትቁጠሩት…
ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ ስታደርጉ ወደ ክብር ማማ የሚያወጣ መሰላልን መርገጥ ጀምራችኋል ማለት ነው… እንዲህ ስታደርጉ የታላቅነታችሁ
ጉዞ ጀምራችኋል ማለት ነው… የመንግሥተ ሰማያት ደጁ ይሄ ነውና፡፡ እንግዲያውስ ልጆቼ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ አትሂዱ… ከራሳችሁ
ጋር ጠብ የምትገጥሙ አትሁኑ፡፡ ታላቅ መሆንን ስትሹ ታላቅ አትሆኑም… ከዚያ ይልቅ ከሁሉም በላይ ታናሽ ትሆናላችሁ እንጂ፡፡
ስለዚህ ከሁሉም በላይ ታላቅ መሆንን የሚፈልግ… ከሁሉም በላይ የከበረ መሆንን የሚወድ የመጨረሻውን ስፍራ ይምረጥ… ታላቅ
መሆንን ስትፈልጉ ታላቅ መሆንን አትፈልጉ ከዚያም ታላቅ ትሆናላችሁ፡፡
በልቡ ትዕቢትን ያስቀመጠ ሰው ከሁሉም ይልቅ ታናሽ ነው… በልቡ ትሑት የሆነ ሰው ግን ከሁሉም ይልቅ ታላቅ ነው፡፡ በልቡ
ትዕቢትን ያስቀመጠ ሰው ከውጭ ሲታይ ታላቅ ይመስላል… በልቡ ትሑት የሆነ ሰውም ከውጭ ሲያዩት ታናሽ ቢመስልም ከስሙ በላይ ግብሩ
ስለሚመሰክር ከማንም በላይ ታላቅ ነው፡፡ ይህ በልቡ ትሑት የሆነ ሰው እኔን አርአያ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ለጊዜው በማንም
ዘንድ የታወቀ ባይሆንም… በማንም ዘንድ ውዳሴ ባያገኝም ታላቅነቱ ግን መቼም መች አይከስምም፡፡ በልቡ ትዕቢተኛ የሆነ ሰው ግን
በእልፍ ሠራዊት ተከቦ ቢሄድም ታናሽ ነው፡፡ ትዕቢተኛ ሰው ለጊዜው ቢወደስም ውዳሴውና ታላቅነቱ ቀጣይነት የለውም፡፡ ልበ ትሑታን
ግን እንዲህ አይደሉም… ቅዱሳን ሰማዕታት ነብያት ሐዋርያት ለልጅ ልጅ የሚደነቁት የሚወደሱት ታላላቅም የሆኑት ልበ ትሑታን ስለሆኑ
ነው… ደግሞም ታላቅነታቸው እስከ ዓለም ፍጻሜ ብቻ የሚዘልቅ ሳይሆን በሚቀጥለው ዓለምም የሚቀጥል ነው፡፡
ታላቅ መሆንን ስትፈልጉ ታላቅ መሆንን አትፈልጉ ከዚያም
ታላቅ ትሆናላችሁ፡፡” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ!!
No comments:
Post a Comment