Tuesday, May 8, 2012

“እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት- ሙሽሪት ከሊባኖስ ትወጣለች!”

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ! 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዛሬ 2019 ዓመት በፊት ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ተወለደች፡፡ ቅድመ አያቶቿ ጴጥርቃና ቴክታ ይህ ቀራቸው የማይባሉ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ እጅግ ባለጸጐች ነበሩ፡፡ 
ከዕለታት በአንዳቸው ቀን ጴጥርቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፡- “እኅቴ ሆይ! እኔ መካን፤ አንቺም መካንይህ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት፡፡ እርሷም፡- “ወንድሜ ሆይ! እግዚአብሔር ከእኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ እርሱም፡- “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃልአላት፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱም አዘኑ፤ አለቀሱም፡፡ በዚህ ጊዜ እንባቸው ወደ እግዚአብሔር ደረሰ፡፡ እንባቸውም እንዲሁ አልተመለሰም፡፡ ወዲያው ራዕይ ይዞ መጣ እንጂ፡፡ ራዕዩ ለጊዜው ባይገባቸውም ቴክታ ሴት ልጅ በስተእርጅናዋ ፀነሰች፡፡ ስሟንም እግዚአብሔር ስእለቴን ሰማ ስትል ሄኤሜን አለቻት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ቅድስት ሐናም አካለ መጠን ስታደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡


 ነገር ግን እነዚህ ቅዱሳንም እንደ ቅድመ አያቶቻቸው በተቀደሰ ጋብቻ ጸንተው ቢኖሩም መካን በመሆናቸው ያዝኑ ነበር፡፡ አብዝተውም እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ይማጸኑ ነበር፡፡ በስተእርጅናቸውም እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው እንዲህ ብለው ብጽዓት ገቡ፡- “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ነግዶ አትርፎ ይርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር አንጣፊ ጋራጅ አገልጋይ ሆኖ ይኖራል እንጂ፡፡ ሴትም ብንወልድ እንጨት ሰብራ እንጀራ ጋግራ ውኃ ቀድታ ወፍጮ ፈጭታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር ውኃ ቀድታ መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ትኑር እንጂ፡፡ እግዚአብሔርም የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትንም የማይነሳ ቸር አምላክ ነውና ነሐሴ ሰባት ቀን መልአክ መጥቶደግ ልጅ ትወልዳላችሁአላቸውና በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ እመቤታችን ተጸነሰች፡፡ በተፀነሰች ጊዜ ብዙ ገቢረ ተአምራት ቢፈጸሙ አይሁድ ምቀኝነት ያዛቸው፡፡ ስለዚህም፡- “ቀድሞ ከእነዚህ ወገን የሚሆኑ ዳዊት ሰሎሞን አርባ አርባ ዘመን እንደ ሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙን፡፡ ደግሞ ከዚህች የተወለደ እንደምን ያደርገን ይሆን?” ብለው በጠላትነት ተነሣሡባቸው፡፡ መልአኩም ኢያቄምን፡- “አድባረ ሊባኖስ ይዘሃት ሂድ!” ብሎት አድባረ ሊባኖስ ሄዳ የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት አንድ ወልዳታለች፡፡ እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት- ከሊባኖስ ሙሽሪት ትወጣለች ያሰኘው ቅሉ ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የእመቤታችን ታላቅ በዓል በደስታ ታከብሯለች፡፡ ለአባ ሕርያቆስና ለቅዱስ ኤፍሬም፣ ለቅዱስ ያሬድና ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች እመቤታችን እኛንም በበረከቷ በረድኤቷ ትጎብኘን፡፡ ከልጇ ከወደጇም ታማልደን፡፡ አሜን!!


 ዋቢ ድርሳናት፡-

  ቅዳሴ ማርያም
 ማኅበረ ቅዱሳን ድረገጽ የአሜሪካ ማዕከል
 ስንክሳር- የዲያቆን መልአኩ እዘዘው

1 comment:

FeedBurner FeedCount