Monday, May 21, 2012

የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ- የዮሐንስ ወንጌል የ20ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡16-26)!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ሳምራይቱ ሴት ያንን የሕይወት ውኃ፣ ያንን ዳግመኛ የማያስጠማ ምንጭ፣ ያ በደስታ የሚቀዱት መለኰታዊ ማየ ሕይወት ለመጠጣት ጎምጅታለች፡፡ ከወራጁ ውኃ ይልቅ ዕለት ዕለት ከሚፈልቀው ማየ ገነት፣ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ትጠጣ ዘንድ ቸኩላለች፡፡ ስለዚህም፡- “ከዚህ አንተ ከምትለኝ ውኃ እንዳልጠማ ስጠኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አባቴ ያዕቆብ ካስረከበኝ ጕድጓድ ይልቅ አንተ ከምትሰጠኝ ምንጭ እጠጣ ዘንድ እሻለሁ” ትሏለች፡፡ እንዴት ያለች ጥበበኛ ሴት ነች? እንዴት ያለች የምትደንቅ ሴት ነች? እንዴት ያለች እውነትን የተጠማች ነፍስ ነች? የጥበብ ባለቤት የሆነው ጌታችንም ሴትዮዋ ይበልጥ ኃጢአቷን እንድትናዘዝ፤ እንደ አለላ የሆነው ማንነቷ እንደ አመዳይ ነጽቶላት የሰላሙን ንጉሥም በልቧ ትሾመው ዘንድ በጥበብ ፡-“ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ” ይላታል/ቁ.16፣ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily.32/።
 
 ስለዚህም ሴቲቱባል የለኝም” ስትል ያለሐፍረት ትናገራለች፡፡ ጌታችንም ወደሚፈልገው አቅጣጫ ስለመጣችለት የሕይወቷን ምሥጢር፡- “ባል የለኝም በማለትሽ ውሸት አልተናገርሽም፤ ከዚህ በፊት አምስት ባሎች ነበሩሽና፡፡  አሁን ከአንቺ ጋር ያለው እንኳን ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ” በማለት ይነግራታል /ቁ.18፣ አባ ሄሮኒመስ, Letter 108፡13/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ልጄ! እንዲህ በማለትሽ እውነት ተናግረሻል፡፡ ምክንያቱም አንቺ የምትመኪባቸው አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ድኅነተ ነፍስን ሊሰጡሽ አልቻሉምና፤ ጽምዓ ነፍስሽን ሊያረኩልሽ አልቻሉምና፡፡ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ በዚህ በሰማርያ የምታመልኪው ስድስተኛው ጣዖትም ሊያድንሽ አልቻለም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ትተሸ፣ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ተፋተሽ ከነፍስሽ እጮኛ ከእኔ ጋር መጋባት ይኖርብሻል”፡፡


 ሴትዮዋስ ምን አለች? “እንዴት ክፉ ሥራዬን ይናገራል” ብላ ትበሳጫለች፤ ባይሆን እንኳን ጥላው ትሄዳለች ተብሎ ሲጠበቅ ይበልጥኑ እጮኛዋን ወደደችው፤ በሚነግራት ነገርም አደነቀችው፡፡ ስለዚህም፡- “ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ፤ አንተ ማእምረ ሕቡአት (ሁሉንም የምታውቅ አዋቂ) ትመስለኛለህ” በማለት ለእኛ ነቀፋ የሚመስለው ንግግሩ በአንክሮ ትመልስለታለች /ቁ.19/።  አቤት ጥበብ! ጌታ በዚህ ንግግሩ እንደ ካፍያ ዝናብ ቀስ እያደረገ ነፍሷን በቃሉ ያረሰርስላታል፡፡ እርሷም መልካሙ ገበሬ በሚዘራባት ዘር እንደ መልካም እርሻ ትጠጣዋለች፡፡ ጌታችን አይሁዳውያንን እንዲህ በመሰለ የፍቅር ቋንቋ ሲያናግራቸው “አንተ ጋኔን አለብህ” ሲሉት ይህች ሳምራይቱ ሴት ግን የውስጧን ሲነግራት የበለጠ ስለ እርሱ ያላትን እውቀትና እምነት እየጨመረ ይሄዳል፤ ደግሞም አንተ ነብይ እንደሆንክ አያለሁ ትሏለች /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ዝኒ ከማሁ/፡፡ 


 ትቀጥላለች! “ስለ ባሎቼ ነግሮኛልና፤ አዋቂ እንደሆነም ተረድቻለሁና ስለ ጤንነቴ፣ ስለ ወደፊት ምድራዊ ሕይወቴ ልጠይቀው” አትልም፡፡ ይልቁንም በሰቂለ ሕሊና እውነትን ፍለጋ ትደክማለች፡፡ ስለዚህምአብርሃም መሠዊያውን የሠራው በዚህ ተራራ ነበር፤ መልከጼዴቅን ያገኘው በዚህ ተራራ ነበር፤ ሙሴ አባቶቻችን ባሕረ ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ሕዝቡን ይባርኩ ዘንድ ይቁሙበት ያለው ተራራ ይህ የገሪዛን ተራራ ነበር፤ በአጠቃላይ አባቶቻችን ሁሉ የሰገዱት በዚሁ ተራራ ነው /ዘዳ.27፡11-13/፤ እናንተ አይሀዳውያን ግን ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ፡፡ ይህ እንዴት እንደሆነ ብታስረዳኝ?” በማለት የገሪዛን ተራራ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንደሚበልጥ ማስረጃዎችን በማምጣት ትጠይቋለች /ቁ.20/። ይህ ሁሉ እያደረገች ያለችው በጠራራ ፀሓይ መሆኑን አንርሳ! ሐሩሩ ጉዳይዋ አይደለም /አውግስጢኖስ, On the Gospel Of John, Tractes15:25/፡፡ 


 ሊቀ ትሑታን የሆነው ጌታችንም ትሕትናዋን ወደደ፡፡ ስለዚህም ለኒቆዲሞስም ይሁን ለናትናኤል ያልነገራቸውን ምሥጢር ይነግራታል፡፡ ስለዚህም ፡-“አንቺ ሴት እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። ስለምን ብለሽ ብትጠይቂኝም መላእክት እግዚአብሔርን የሚያመልኩት በኢየሩሳሌም ወይም አንቺ በምታመልኪበት በዚሁ በገሪዛን ተራራም አይደለም፡፡ የትንሣኤ ልጆችም እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እንዲህ ይሆናል፡፡ እናንተ ሳምራውያን እግዚአብሔር ሙሉዕ በኵለሄ መሆኑን ዘንግታችሁ የሚገኘውም የሚመለከውም በዚሁ ተራራ ብቻ ነው በማለት ለማታውቁት አምላክ ትሰግዳላችሁ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ከሌላ የአንዲት አውራጃ ጣዖት ጋር አተካከላችሁት፤ አይሁድ ግን ብያንስ ብያንስ እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ጌታና ሙሉዕ በኵለሄ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ አዎ! እኛ በትንቢተ ነብያት ለተነገረለት፤ በተለየ አካሉ ከድንግል ተወልዶ አማኑኤል ይሆናል ለተባለለት፤ መዳን ከአይሁድ ማለትም ከነገደ ይሁዳ ይሆናል ለተባለለትና ለምናውቀው እንሰግዳለን፡፡ እኛ ብዬ እኔም እንደምሰግድ መናገሬም አንቺ እንደ አምላክ ሳይሆን እንደ ነብይ ስለተመለከትሽኝ በመረዳትሽ መጠን መናገሬ እንጂ አብሬ የምሰግድ ሆኜ አይደለም” ይላታል /ቁ.21-22/። ጌታችን በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ “አንቺ ሴት እመኚኝ! እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ረቂቅ ነው፡፡ በዚህ አለ በዚህም የለም የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህም በመንፈስና በጽድቅ ማለትም በአብራከ ነፍስ ሆነው በንጽሐ ጠባይዕ ጸንተው በእውነት ለአብ የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፡፡ ይህም ማለት በገሪዛን ተራራ የነበረው ብቻ ሳይሆን የኢየሩሳሌሙ ሥርዓተ አምልኮም (በአንድ ቦታ ብቻ ተወስኖ የሚደረግ አምልኮ) ያበቃል፡፡ አብ ሊሰግዱለት አሥር ጊዜ ሥጋቸውን ብቻ በማለቅለቅ የሚመጡትን ሳይሆን በአብራከ ነፍስ በንጽሐ ጠባይዕ የሚያመልኩትን ይሻልና፡፡ ይህ ሁሉ አሁን ሆኗል” ይላታል /ቁ.23-24/፡፡ በዚህ ንግግሩ በሐዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮ እየነገራት ነበር፡፡

 ከዚህ በኋላ ሴቲቱ፡-ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ በመጣም ጊዜ አሁን የምትነግረኝ ሁሉን እንደሚነግረን አውቃለሁ” በማለት ዘዳ.18፡15ን ትጠቅስለታለች /ቁ.25/። ሰው ወዳጁ ጌታም የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ” አላት /ቁ.26/።  የሚደንቅ ነው! አይሁድ “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ ታቆየናለህ” ሲሉት “የምናገራችሁ እኔ እርሱ ነኝ” አላላቸውም /ዮሐ.10፡24/፡፡ ምክንያቱም አመጣጣቸው እንደዚህች ሴት ለማመን ሳይሆን ለተንኰል ነበርና፡፡ ለዚህች ቅን ሴት ግን “ለዘመናት የናፈቅሽኝ ንጉሥሽ፤ ለዘመናት የጠበቅሽኝ መሲሕ የምናገርሽ እኔው ነኝ” በማለት ልቧን አሳረፈላት፤ ጥሟን አረካላት /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 የትሕትና አባት ሆይ! ጽምዓ ነፍሳችንን አላረካ ያሉ ብዙ ባሎች አሉንና እነዚህን ጥለን ካንተ ጋር ለዘላለም እንኖር ዘንድ እርዳን፡፡ አባት ሆይ! ፍቅርህ የዚህችን ሴት ኃጢአት አናዝዞ እንደፈወሰ እልከኛ ከሆነው ዐለት ልባችንም የንስሐ ውኃ ይወጣው ዘንድ ስበርልን! ከአንተ ከነፍሳችን እጮኛ ውጪ ከሌላ ጋር እንዳናመነዝርም እርዳን! የፍቅር ንጉሥ ሆይ! ለዚህች ሴት የገለጽከውን እውነት ልጆችህ መባል ለማይገባን ለእኛም ግለጽልን! በእውነትና በመንፈስ ሆነን አንተን ብቻ እንድናመልክም እርዳን! ጌታ ሆይ! በእውነት ፈልጋህ “የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ” ብለህ እንደነገርካት እኛን እንድትናገረንም ሆነ እንድትገለጥልን አንሻም፡፡ ለእኛ ማሰብህ ብቻ በቂያችን እንደሆነ እናምናለንና፡፡ አሜን!


No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount