Wednesday, May 16, 2012

ዮሐንስ ወንጌልን ከአባቶች ጋር!!

የመግቢያ ጸሎት!
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ቃልህን ለምትወደው ደቀመዝሙር ለዮሐንስ እንደገለጽክለት ለእኛም ለባሮችህ ትገልጥልን ዘንድ እንማልድሃለን፤ ሕይወታችንን ሙሉ እስከ መስቀል ድረስ እንድንከተልህ፤ እናትህንም እንደ ዮሐንስ ወደ ቤታችን እንድንወስዳት፤ እንደ ንስር ሰማየ ሰማያትን በረን ከቅዱሳን መላእክትህ ጋር እናሸበሽብልህ ዘንድ ቅዱስ መንፈስህን ስጠን፡፡ ከእኛ መልካም ነገር አግኝተህ ሳይሆን እንዲሁ ወደኸን የእኛን ሥጋ የተዋሐድከው ቀዳማዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ከአንተና ከባሕርይ አባትህ ከአብ ከባሕርይ ሕይወትህም ከመንፈስ ቅዱስ ፊት ቆመን ዕልል እያልን እናመሰግንህ ዘንድ ፍቀድልን፡፡ በዚሁ ቅዱስ ቃልህ አማካኝነት ቅዱስ መንፈስህ ወደ ቀራንዮ ይወስደን ዘንድ እርዳን፡፡ ጌታ ሆይ! እኛ የምንፈልገው ሕዝቡ ቢታመሙ እንድትፈውሳቸው፣ ቢታረዙ እንድታለብሳቸው፣ ቢሞቱ እንድታነሣቸው፣ ለመሳሰለው ሁሉ እንድትነግሥላቸው እንደፈለጉት ሳይሆን በሕይወታችን ላይ ነግሠህ እንድናመሰግንህና ቃልህን እንመገብ ዘንድ ነው፡፡ በእውነት አንተ ኃጢአታችንን ያስወገድክ የእግዚአብሔር በግ ነህ! አቤቱ ፈጣርያችን ሆይ! ወደ ቃና ሠርግ ቤት ውሰደንና ከፍቅርህ ወይን አጠጣን፤ ከኒቆዲሞስ ጋር ስለ አዲስ ልደት ምሥጢር ታስተምረን ዘንድ አንተ ምራን! ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ እንጠጣ ዘንድ ከሳምራይቱ ሴት ጋር ጨምረን! አንተን እናይ ዘንድ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር ከነበረው ልጅህ ጋራ ቀላቅለን! 38 ዓመት ታሞ ነገር ግን አንተ ስታነሣው ቀጥ ብሎ እንደሄደው የቤተሳይዳው ታመሚ ጋር ወደ አማናዊው ቤታችን እንሮጥ ዘንድ እርዳን! “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ እውነትና መንገድ እኔ ነኝ፤ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የበጐች በር እኔ ነኝ፤ ቸር እረኛ እኔ ነኝ፤ እውነተኛው የወይን ግንድ እኔ ነኝ” ስትለን “አሜን” ብለን እስከ መስቀል ድረስ እንከተልህ ዘንድ እርዳን፡፡ ትንሣኤህን ለዓለም ሁሉ እንመሰክር ዘንድ አበርታን፡፡ በእውነት አንተ የዘላለም ቃል አለህ! ጌታ ሆይ! አንተን ትተንስ ወደ ማን እንሄዳለን? የፍቅር አባት ነህና አትለየን፡፡ ከዚህ በረት ያልሆኑትን በቃልህ እናመጣቸው ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ሁን፡፡ አሜን!!!!!

1 comment:

  1. This comment has been removed by a blog administrator.

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount