(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 25
ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ
ሃይማኖት - ክፍል 18
ዓርብ ዐረበ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን ተካተተ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓርብ ማለት መካተቻ
መደምደሚያ ማለት ነው። ምዕራብ ስንል መግቢያ፣ መጥለቂያ (ለምሳሌ የፀሐይ መግቢያን ምዕራብ እንደምንለው) ማለት ሲኾን ዐረብ
ሲባልም ተመሳሳይ ነው - ከኢየሩሳሌም ምዕራባዊ አቅጣጫ ያሉ ሀገራት የዐረብ ምድር ይባላሉና። ዐርብ የተባለበት ምክንያት
በዕለተ እሑድ መፈጠር የጀመሩት ፍጥረታት ተፈጥረው ያበቁበት፣ የተካተቱበት ቀን ስለ ኾነ ነው፡፡
በዚህ ቀን እግዚአብሔር “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ እንስሳትን ተንቀሳቃሾችን የምድር
አራዊትንም እንደ ወገኑ ታውጣ” ብሎ አዘዘ /ዘፍ.1፥24/፡፡ በዚሁም መሠረት ልክ እንደ ሐሙስ ፍጥረታት በእግራቸው የሚሔዱ፣ በልባቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ፍጥረታት ናቸው፡፡ የሐሙስና የዓርብ መኾናቸውን የምንለየውም በአኗኗራቸውና በግብራቸው ሲኾን የሐሙስ ፍጥረታት በባሕር፣
የዓርብ ፍጥረታትም በየብስ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ቀን በአራተኛ አዳምን ፈጥሯል። ይህንን በኋላ እንመለስበታለን፡፡
በሳይንሳዊ መንገድ ሔደን ምድር እነዚህን ፍጥረታት እንዴት ልታስገኛቸው ቻለች ብለን ብንጠይቅ
መልስ የለውም፡፡ የተገኙት እግዚአብሔር ስላዘዘ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምድሪቱን አዘዛት፤ እርሷም አረገዘች፤ ወለደቻቸውም፡፡
ዛሬም ይህ እውነት እንደ ኾነ የምናይበት ኹናቴ አለ፡፡ ዝናብ ወደ ሰኔ አከባቢ መዝነብ ሲጀምር አስቀድመን ያላየናቸው ፍጥረታት
ከምድር ወጥተው ሲበሩ፣ እንዲሁም እንደ እንቁራሪት ያሉ ፍጥረታት ወደ መኖር ሲመጡ እናያቸዋለን፡፡ አስቀድሞ ባልተጣለ ዕንቁላል
የተለያዩ ዓይነት ትላትሎች ከጭቃ ውስጥ ሲፈጠሩ እናያቸዋለን፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ጥበብ ታያላችሁን?