በመምህር ብርሃኑ አድማስ
(ከመጽሐፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
ባለፉት ስምንት ዐመታት (ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እና ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት) ወዲህ ኢትዮጵያ ባልተቋረጠ የለውጥ፣ የውዝግብና የነውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሁለቱም ታላላቅ መሪዎች ያረፉት በዘመነ ዮሐንስ ማጠቃለያ ወር ላይ ነበር፡፡ የእነርሱን ዕረፍት ተከትሎ እንዳሁኑ ጎልቶ ባይነገርላቸውም ብዙ ለውጦችም ነውጦችም በተከታዮች ዐመታት ውስጥ ነበሩ፡፡ ከዐራት ዐመታት በኋላ ልክ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ አሁን ላለንበት ለውጥም እንበለው ምስቅልቅል የዳረገን አብዮት ተቀሰቀሰ፡፡ አሁን ባለቤቱ እኔ ነኝ እኔ ነኝ የሚባልለት ያ ሕዝባዊ ጫናን መሣሪያ ያደረገ (ከየት እንደሆነ ግን ከግምት በቀር ብዙዎቻችን በትክክል የማናውቀው) ለውጥ ተፈጠረ፡፡ አራቱን ዐመታትም የማንጠበቃቸውና ሊተነበዩ የማይችሉ ተከታታይ ለውጦች ከጥፋቶችና ምስቅልቅሎች ጋር በሀገራችን ተከሰቱ፡፡ ሁኔታዎቹም ለከፊሉ ደስታ ለከፊሉም ሐዘን የሆኑበት ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ደስታና ሐዘን በፍጥነት የተፈራረቁበት ሆነ፡፡ እንዲህ ያሉ ክስተቶች ሳያቋርጡ ያለፉበት የዐራት ዐመታት አንድ የለውጥ ወቅት ሊፈጸም ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል፡፡