በመምህር ብርሃኑ አድማስ
(ከመጽሓፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጳጉሜን 04 /
2011 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
አቤቱ እውነትና መንገድ ሕይወትም የሆንከው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለእውነትና ስለ ጽድቅ ስለሰላምና ስለአንድነት፤ ስለመግባባትና በስምህ አንድ ስለመሆን ብቻ እመሰክር ዘንድ አንተ በምታውቃቸው በጽኑ ወዳጆችህና ስምህን ተሸክመው ዐለምን በዞሩ በቅዱሳንህ ስም እማጸንሃለሁ፡፡ ልዩነት፣ ሥጋዊ ጥቅም፣ ዝናና የበላይነት ስሜት ወደ ማንኛችንም ልጆችህ እንዳይመጣ ትጠበቀንም ዘንድ ኃጢአተኛው ባሪያህ በእውነት አለምንሃለሁ፡፡ አቤቱ በዙሪያችን የከበበውን ጨለማ አርቅ፤ ብርሃንህንም ግለጽልን፤ ስለእውነትና በእውነት ብቻ እንድናገርም ርዳን፡፡ አቤቱ በጠላታችን በዲያብሎስ አንናቅ፤ ይልቁንም ስለ ስምህ አንድ መሆንንና እርሱን መርገጥን ስጠን፤ በቅዱሳን ሁሉ ጸሎትና ከሁሉም በላይ በምትሆን በባሕርያችን መመኪያ በእናትህ በቅድስት ድንግል ማርያም ጽኑ አማላጅነት፤ አሜን፡፡
የአንድ ፓስተር ኑዛዜ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በሀገሪቱ የነበረው ሽኩቻና ውጥረት እንዲሁም የሕዝቡ ጭንቀት ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ብዙ ነበሩ፡፡ ብዙዎች መፍትሔ የመሰላቸውን ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳላሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በወቅቱ ለመፍትሔ ይሯሯጡ ከነበሩት አካላት አንድ የሽማግሌዎች ቡድን ለመመሥረትና ባለሥልጣናትን በማናገር ወደ መግባባትና ሰላም ለማምጣት ሕብረ ብሔርና ሕብረ ሃይማትን ታሳቢ ያደረገ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ማሰባሰብ ይጀመራል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ከኮሚቴዎቹ ሁለቱ እገዛ እንዳደርግ ሲያወያዩኝ የነገሩኝ ሽማግሌዎችን ሲያናግሩ ከገጠማቸውና ካስገረማቸው ታሪክ አንዱ የሚከተለው ነበር፡፡