Wednesday, May 30, 2012

አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋል- የዮሐንስ ወንጌል የ25ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡18-28)=+=


     ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እነርሱ መዳን ብሎ ወደ ቤታቸው ቢመጣም፣ በኃይልና በሥልጣን የሚያደርገውን ሁሉ ሲያደርግ ቢመለከቱትም መጻሕፍትን ከመመርመር ይልቅ፣ ትንቢተ ነብያትን ከማገናዘብ ይልቅ አይሁድ የራሳቸውን ወግ በመጥቀስ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ የሚናገረውን እንኳን ባያምኑ የሚያደርገውን አይተው ወደ እርሱ እንዲመጡ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ይባስኑ ውስጣቸው በቅናት ይቆስል ነበር፡፡ ስለዚህም “ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚያስተካክል ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም” ለማለት ደፈሩ /ቁ.18/፡፡ ጌታችን ግን አንዳንድ ልበ ስሑታን እንደሚሉት “ስለምን ልትገደሉኝ ትፈልጋላችሁ? እኔ ከአብ ጋር የተካከልኩ አይደለሁም” ወይም “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም አገለግላለሁ” ሳይሆን “አባቴ እስከ ዛሬ (ቅዳሜ ቅዳሜ) ይሠራል (አንዳንድ ድውይ ይፈውሳል) እኔም እንዲሁ እሠራለሁ (መጻጉዕን ፈወስኩ)” ይላቸዋል /ቁ.17/፡፡ ወንጌላዊው እዚህ ጋር የአይሁዳውያኑ አባባል ትክክል ስለነበረ በሌላ ቦታ /ዮሐ.2፡19/ እንደሚያደርገው ማስተካከያ አላደረገበትም፤ ከዚህ በፊት እንዳደረገውም “አይሁድ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እንዳስተካከለ ቢያስቡም ክርስቶስ ግን እንዲህ ማለቱ ነበር” አይልም /Saint John Chrysostom Homilies on St. John, Hom 38./፡፡

   ከዚህ በኋላ ስለ ሰው ልጆች መዳን አብዝቶ የሚሻ ጌታችን እንዲህ ይላቸዋል፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” /ቁ.19/፡፡ ምን ማለት ይሆን? እውነት “ነፍሴን ላኖራትም ላነሣትም ሥልጣን አለኝ” ያለው ጌታ ምንም ሊያደርግ አይችልምን? /ዮሐ.10፡18/፡፡ ወንድሞቼ ይህን በጥንቃቄ ልናስተውለው ይገባል፡፡ ይህ መለኰታዊ ቃል አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሳይሆን እንዲህ ማለቱ ነው፡- “እኔ ከራሴ ብቻ አንቅቼ ምንም ምን ሥራ አልሠራም፤ ከአብ በሕልውና ያየሁትን በህልውና ያገኘሁትም እሠራለሁ እንጂ፡፡ የአብ ፈቃድ የእኔ ፈቃድ ናት፤ የአብና የእኔ ፈቃድ እርስ በእርሷ የምትለያይ አይደለችም፡፡ እስከ ዛሬ አብ የወደደውን ሲያደርግ እንደነበረ እኔም እንዲሁ (በተመሳሳይ ሥልጣን በተመሳሳይ ዕሪና) የወደድኩትን አደርጋለሁ፡፡ አብ ይፈውስ እንደነበረ እኔም እፈውሳለሁ፡፡ ስለዚህ አብ አባቴ ነው ስላልኳችሁ አትደነቁ፤ ከአባቴ ጋር የተካከልኩ ነኝ ስላልኳችሁ አትበሳጩ፡፡ እናንተን ለማዳን ብዬ ምንም ከአባቴ ጋር ያለኝን መተካከል እንደመቀማት ሳልቆጥረው የእናንተ የባርያቼን መልክ ብይዝም አብ የሚያደርገውን ሁሉ እኔ ደግሞ ይህን እንዲሁ አደርጋለሁና /ፊል.2፡6/፤ የአብ የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአብ ነውና /ዮሐ.17፡10/፡፡ የሆነው ሁሉ በእኔ የሆነው አብ መፍጠር የማይችል ሆኖ ሳይሆን በሥላሴ ዘንድ የፈቃድ ልዩነት ስለሌለ ነው” /ዮሐ.1፡3 Saint AmbroseOf the Holy Spirit Book 2:8:69/። በእርግጥም ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣው አብ ምንም አላደረገም አይባልም /ዮሐ.11፡42/፤ ክርስቶስ የዓይነ ሥውሩን ብርሃን ሲመልስለት መንፈስ ቅዱስ ምንም አላደረገም አይባልም /ዮሐ.9፡3/፡፡ የሥላሴ ሥራ በአንድነት በአንድ ፈቃድ የሚደረግ እንጂ በተናጠል የሚደረግ አይደለምና /Saint Augustine. Sermon on N.T. Lessons, 76:9/፡፡

Sunday, May 27, 2012

ታላቅ መሆንን ስትፈልጉ ታላቅ መሆንን አትፈልጉ ከዚያም ታላቅ ትሆናላችሁ


ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያሰተምር እንዲህ አለ፡- “ማንም ከእናንተ ታላቅ መሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን… ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባርያ ይሁን… ታላቅ መሆንን ማሰብ የክፉዎች ሐሳብ ነው… የመጀመርያነትን ስፍራ መፈለግ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው… ታላቅነትን መፈለግ ታናሽነት ነው፡፡
   ስለዚህ ይህን ልቡና ከእናንተ ገርዛችሁ ጣሉት… በእናንተ በክርስቲያኖች ዘንድ እንዲህ አይደለም… በአሕዛብ ዘንድ የመጀመርያነትን ስፍራ የሚይዙ በሌሎች ዘንድ አለቆች እንዲሆኑ ነው… በእኔ ዘንድ ግን የመጨረሻውን ስፍራ የሚይዝ እርሱ የመጀመርያ ነው፡፡
   ይህን ከእኔ መማር ትችላላችሁ… እኔ ምንም የነገሥታት ንጉሥ የአለቆችም አለቃ ብሆንም በፈቃዴ የባርያዎቼን የእናንተን መልክ እይዝ ዘንድ አልተጠየፍኩም… በሰዎች ዘንድ የተገፋሁ ሆንኩ… ተተፋብኝ… ተገረፍኩኝ… ይህም ሳይበቃኝ በመስቀል ሞት ሞትኩኝ፡፡ ነገር ግን ላገለግል ስለ ብዙዎችም ነፍሴን ቤዛ ልሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉኝ አልመጣሁም፡፡ ቤዛነቴም ለወዳጆቼ ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉኝም ለሚወግሩኝም ለሚያሰቃዩኝም ጭምር ነው፡፡ የእናንተ አገልጋይነት ግን ለእናንተ ለራሳችሁ እንጂ ለሌሎች ቤዛነት የሚሆን አይደለም፡፡
  እንዲህ አድርጌ ስነግራችሁ ክብራችሁ ዝቅ ዝቅ ያለ መስሎ አይታያችሁ… ምንም ያህል ዝቅ ዝቅ ብትሉም እኔ የተዋረድኩትን ያህል አትዋረዱም… እኔ ይኼን ያህል ከመጨረሻው የክብር ጠርዝ ወደ መጨረሻው የውርደት ጠርዝ ብወርድም ለብዙዎች መነሣት ሆንኩኝ… ክብሬ ከመቃብር በላይ ሆነ… ክብሬ በዓለም ላይ ከአጥብያ ኮከብ በላይ ደመቀ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመወለዴ በፊት መታወቄ በመላእክት ዘንድ ብቻ ነበር… አሁን ሰው ከሆንኩኝ በኋላ ግን ክብሬ በመላእክት ብቻ ሳይሆን በሰው ዘንድም የታወቀ ነው፡፡

አንድ ፕሮቴስታንት ለጠየቀኝ የተለያዩ ጥያቄዎች በጽሑፍ የሰጠሁት ምላሽ

        በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!  

   1. “በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።”  እና “የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።” ተብሎ በነብያቱ የተነገረውን ትንቢት በቀጥታ “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።” ተብሎ ሲፈጸም ስለምንመለከተው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ጌታ ሲወለድ በቤተልሔም ተመሠረተች ቢባል ያስኬዳል /መዝ.71፡9-10፣ ኢሳ.60፡6፣ ማቴ.2፡1-11/፡፡ በኋላ ደግሞ የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ እንደሚነግረን፡- “የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው።ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን። ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?  ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና።” ይለናል /ሐዋ.8፡26-39/፡፡ ይህም የሆነው በ34 ዓ.ም. ነው፡፡ በይፋ በጳጳስ መመራት የጀመረችው ግን በ330 ዓ.ም. በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አማካኝነት ነው፡፡
  • “ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል “ኦርቶዶክስያ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ቀጥተኛ (እምነት) ማለት ነው፡፡ የምስራቅና የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናትም ይጠሩበታል፡፡
  • “ተዋሕዶ” የሚለው ቃል በግሪኩ “Miaphysis” የሚለውን ቃል የሚተካ የግእዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን /ዮሐ.1፡1፣14/፣ መለኰትና ትስብእትም ያለ መለያየት፣ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየት ስለ ተዋሐዱ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ፈቃድ፣ አንድ ግብር መሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡
     

Wednesday, May 23, 2012

ከሁሉ በታች ቁጫጭ ስንሆን ከሁሉም በላይ አደረገን=+=



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደሚነግረን አሁን ካሣው ተከፍሏል፤ አናቅጸ ሲዖል ተሰባብሯል፣ የሰው ልጅም እንደ ድሮ በዕዳ በቁራኝነት ከመያዝ ነጻ ወጥቷል፤ ጌታችንም ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ እንዴት ያለ ፍቅር ነው?
 ተነሥቶም ለአርባ ቀናት ያህል ደቀመዛሙርቱን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢር ሲነግራቸውና ሲያስረዳቸው ቆየ /ሐዋ.1፡3/፤ [ይህ ትምህርት ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን መጽሐፈ ኪዳን ይባላል!] “ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡ በአባቴ ቤት ብዙ መኖርያ አለ፡፡ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበረ፡፡ ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና” እያለ ከዚህ በፊት የነገራቸውን እየደገመ የደቀመዛሙርቱን ልብ ሰማያዊውን ሕይወት እንዲናፍቅ ያደርገው ነበረ /ዮሐ.14፡1/፡፡ ሆኖም ግን እየተገለጠላቸው እንጂ ከዚህ በፊት ሲያደርገው እንደነበረ ቀንና ሌሊት ሁሉ ከእነርሱ ጋር በመዋልና በማደር አልነበረም፡፡ አሁን ስለ እኛ ብሎ ዝቅ ያለበት ያ ደካማ ማንነቱ የለምና፤ አሁን ያ የለበሠው ባሕርያችን በአዲስ መንፈሳዊ አካል ተነሥቷልና፡፡ 

Monday, May 21, 2012

የገብረ ንጉሡ ልጅ መፈወስ- የዮሐንስ ወንጌል የ22ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡43-ፍጻሜ)!!


  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


“ከሁለቱ ቀኖችም በኋላ፣ ሳምራውያኑ ከእኛ ጋር ሁን ብለውት ለሁለት ቀናት ቃለ እግዚአብሔርን ሲያስተምራቸው ከቆየ በኋላ፣ እነርሱም የአይሁድ ወይም ደግሞ የሳምራውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሁሉ መድኃኒት መሆኑን ካመኑና ለሴቲቱ ከነገሯት በኋላ ጌታችን ከዚያ ወጥቶ ወደ ገሊላ ሄደ” /ቁ.43/። ከተመቸን ብላችሁ በአንድ ቦታ አትኑሩ፤ ወጥታችሁ ወርዳችሁ አስተምሩ እንጂ ብሎ አብነት ለመሆን ከሰማርያ ወደ ገሊላ ሄደ /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 476/፡፡ 


 ነገር ግን ብዙ ጊዜ ወደ ተመላለሰባት በኋላም አልቀበል ሲሉት “አንቺ ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲዖል ትወርጃለሽ“ ብሎ ወደ ተናገረላት ወደ ቅፍርናሆም አልሄደም /ማቴ.11፡23/፤ ምክንያቱም “ነቢይ በገዛ አገሩ እንዳይከበር ኢየሱስ ራሱ መስክሮአልና” /ማቴ.13፡57/ /ቁ.44፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily On The Gospel of John Hom.35/።
 “ወደ ገሊላም በመጣ ጊዜ፥ የገሊላ ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ለገቢረ በዓል ወጥቶ ሳለ በኢየሩሳሌም ያደረገውን ተአምራት ሁሉ አይተዋልና አመኑበት” /ቁ.45፣ ዮሐ.2፡23/። እነዚህ ገሊላውያን ምንም እንኳን እንደ ሳምራውያን ያለ ምልክት ባያምኑም ቃሉም ሰምተው ገቢረ ተአምራቱንም አይተው ካላመኑት የአይሁድ ሰዎች ግን ይሻላሉ /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ 

በእውነት ክርስቶስ የዓለሙ መድኃኒት እንደ ሆነ ዓወቅን፤ አምነንበታልም - የዮሐንስ ወንጌል የ21ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡27-42)


ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ፡፡
 ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር ብለናል /ዮሐ.4፡8/፡፡ አሁን ግን “መጡና ከአንዲት ደሀ ብቻ ሳይሆን ከሳምራይት ሴት ጋር ዝቅ ብሎ በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን በግሩም ትሕትናው ስለተደነቁ ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም” /ቁ.27፣ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily On John,Hom.33:3/።
  ወንጌላዊው እንደነገረን ሴቲቱ ውኃ ልትቀዳ ወደ ያዕቆብ ጕድጓድ መጥታ ነበር፡፡ ነገር ግን የክብር ንጉሥ ወደ ልቧ ሰተት ብሎ ሲገባ “ማድጋዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች” /ቁ.28/፡፡  በሐሴት ሠረገላ ተጭናም ወንጌሉን ለማፋጠን ተሯሯጠች፡፡ “ለሰዎችም ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” እያለች መላ ከተማውን ጠራርጋ ታመጣቸው ነበር። የሚገርመው ሴቲቱ የምታመጣቸው ሰዎች እንደ እንድርያስ ወይም ደግሞ እንደ ፊሊጶስ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ መላ ከተማውን እንጂ፡፡ ትጋቷም ከኒቆዲሞስ በላይ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ በወልደ እግዚአብሔር ቢያምንም እንደ እርሷ ግን በግልጥ ለመመስከር አልወጣም፡፡ በእውነት ይህች ሴት ከሐዋርያት ጋር ብትተካከል እንጂ አታንሥም፡፡ ሐሳብዋን ብቻ ይግለጥላት እንጂ እንዴት እንደምትነግራቸው እንኳን የቃላት ምርጫ አታደርግም፡፡ እናም “ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?”  ትላቸዋለች፡፡ ተጠራጥራ አይደለም፤ መጥተው ራሳቸው ለራሳቸው እንዲወስኑ እንጂ፡፡ ስለዚህም “ኑና እዩ፤ አይታችሁም እመኑ” እያለች ከነፍሳቸው እረኛ ጋር እንዲገናኙ ትፈልጋቸው ነበር፡፡ ሰዎቹም የምትነግራቸውን ነገር ለማየትከከተማ ወጥተው ወደ ጌታችን ይመጡ ነበር” /ቁ.29-30/። የሚገርመው ደግሞ ይህች ሴት አዋልደ ሰማርያን ላለማየት ብላ በጠራራ ፀሐይ ውኃን ለመቅዳት የመረጠች ሴት ነበረች፡፡ አሁን ግን እውነተኛው ፀሐይ ሲነካት ሐፍረቷ እንደ በረዶ ተኖ ጠፋ፡፡ ስለዚህም ቀድሞ ወደምታፍራቸው ሰዎች በመሄድ “አንድ ነብይን ትመለከቱ ዘንድ” ሳይሆን “ያደረግሁትን ሁሉ፣ ምሥጢሬን ሁሉ የነገረኝን ሰው ትመለከቱ ዘንድ ኑ” እያለች ሕዝቡን ጠራቻቸው /St.John Chrysostom, Hom.34:1/፡፡
 ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ “ጌታችን ብዙ መንገድ በመሄድ ደክሟልና፤ ደግሞም ጠራራ ፀሐይ ነውና

የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ- የዮሐንስ ወንጌል የ20ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡16-26)!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ሳምራይቱ ሴት ያንን የሕይወት ውኃ፣ ያንን ዳግመኛ የማያስጠማ ምንጭ፣ ያ በደስታ የሚቀዱት መለኰታዊ ማየ ሕይወት ለመጠጣት ጎምጅታለች፡፡ ከወራጁ ውኃ ይልቅ ዕለት ዕለት ከሚፈልቀው ማየ ገነት፣ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ትጠጣ ዘንድ ቸኩላለች፡፡ ስለዚህም፡- “ከዚህ አንተ ከምትለኝ ውኃ እንዳልጠማ ስጠኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አባቴ ያዕቆብ ካስረከበኝ ጕድጓድ ይልቅ አንተ ከምትሰጠኝ ምንጭ እጠጣ ዘንድ እሻለሁ” ትሏለች፡፡ እንዴት ያለች ጥበበኛ ሴት ነች? እንዴት ያለች የምትደንቅ ሴት ነች? እንዴት ያለች እውነትን የተጠማች ነፍስ ነች? የጥበብ ባለቤት የሆነው ጌታችንም ሴትዮዋ ይበልጥ ኃጢአቷን እንድትናዘዝ፤ እንደ አለላ የሆነው ማንነቷ እንደ አመዳይ ነጽቶላት የሰላሙን ንጉሥም በልቧ ትሾመው ዘንድ በጥበብ ፡-“ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ” ይላታል/ቁ.16፣ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily.32/።
 
 ስለዚህም ሴቲቱባል የለኝም” ስትል ያለሐፍረት ትናገራለች፡፡ ጌታችንም ወደሚፈልገው አቅጣጫ ስለመጣችለት የሕይወቷን ምሥጢር፡- “ባል የለኝም በማለትሽ ውሸት አልተናገርሽም፤ ከዚህ በፊት አምስት ባሎች ነበሩሽና፡፡  አሁን ከአንቺ ጋር ያለው እንኳን ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ” በማለት ይነግራታል /ቁ.18፣ አባ ሄሮኒመስ, Letter 108፡13/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “ልጄ! እንዲህ በማለትሽ እውነት ተናግረሻል፡፡ ምክንያቱም አንቺ የምትመኪባቸው አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ድኅነተ ነፍስን ሊሰጡሽ አልቻሉምና፤ ጽምዓ ነፍስሽን ሊያረኩልሽ አልቻሉምና፡፡ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ በዚህ በሰማርያ የምታመልኪው ስድስተኛው ጣዖትም ሊያድንሽ አልቻለም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ትተሸ፣ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ተፋተሽ ከነፍስሽ እጮኛ ከእኔ ጋር መጋባት ይኖርብሻል”፡፡

=+=ከሳምራይቱ ሴት ጋር የተደረገ ንግግር- የዮሐንስ ወንጌል የ19ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡7-15)=+=

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 ጌታ ለተገፉት ምርኩዛቸው ለተጨነቁትም ዕረፍት ነው፡፡ አዎ! ሳምራይቱ ሴት በጧት ውኃ ልትቀዳ አለመምጣቷ መለኰታዊ ዕቅድ ከመሆኑ በተጨማሪ ውኃ የሚቀዱት ሴቶች በእርሷ ላይ የሚሳድሩት ተጽዕኖ እንዳለ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ አዋልደ ሰማርያ በማታገኝበት ሰዓት ብቻዋን “ውኃ ልትቀዳ መጣች” /ቁ.7/። ይገርማል! ርብቃ ከይስሐቅ፣ ራሄል ከያዕቆብ እንዲሁም የካህኑ የዮቶር ልጅ ከሙሴ ጋር የተገናኙት በውኃ ጉድጓድ ነበር፡፡ ይህች ሳምራይቱ ሴትም ከነፍሷ እጮኛ ከክርስቶስ ጋር የምትገናኘው በያዕቆብ ጕድጓድ ነው፡፡ በዚሁ ሰዓት ነው እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ በሄዱ ጊዜ ውኃን በደመና እየቋጠረ ምድርን የሚያረሰርሳት ጌታ  እንደ ምስኪን “ውኃ አጠጪኝ” የሚላት  /ቁ.8/። እንዴት ያለ ግሩም ንግግር፣ እንዴት ያለ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ ቃል ነው? ምክንያቱም የሴትዮዋን መሻት ይመለከት ዘንድ ውኃ አጠጪኝ ይላታልና፡፡ በእርግጥም ጌታችን ውኃ ተጠምቶ ነበር፡፡ የእምነት ውኃ! የሰው ልጆች የመዳን ውኃ! ስለዚህም “አንቺ ሴት! እምነትሽን ተጠምቻለሁ፤ መዳንሽን ተርቤአለሁ” ይላታል /ቁ.34፣ አውግስጢኖስ- Sermon On New Testamen Lessons, 49:3/፡፡
 ሳማራይቱ ሴትም ጌታን በአለባበሱ አንድም በንግግሩ ብታውቀው “አንተ አይሁዳዊ እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ውኃ አጠጭኝ ብለህ ትለምናለህ? አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በሥርዓት እንደማይተባበሩ አታውቅምን?” ትሏለች /ቁ.9/። ሴቲቱ ይህን የምትለው በቅንነት  እንጂ በክፋት አልነበረም! “እኛ ሳምራውያን ከእናንተ ከአይሁድ ጋር መነጋገር አንችልም” ሳይሆን በመገረም “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ያንን የጥል ግድግዳን አፍርሰህ በፍቅር ልታነጋግረኝ ቻልክ?” ትሏለች /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ-Homilies On St. John,31:4/፡፡
 የፍቅር ጌታም የሴትዮዋን ልብ በሳምራውያንና በአይሁድ መካከል ካለው መለያየት ይልቅ ስለ ማየ ሕይወት እንድታሰላስል ያደርጋታል፡፡ ስለዚህም፡- “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር” ይላታል /ቁ.10/።  እንዲህ ማለቱም ነበር፡-“ልጄ! አሁን ስለዚያ መለያየትና ጥል ሚነገርበት ሰዓት አብቅቷል፡፡ የሚያነጋገረሽ አምላክ ወልደ አምላክ፣ የሰው ልጆች ተስፋ፣ ኃይሉ ለአብ ወጸጋ ዘአሕዛብ እርሱ መሆኑን ብታውቂ ሁለመናሽን ከኃጢአት እድፍ ትርቂበት ዘንድ አንቺው ራስሽ እንደ መዝሙረኛው ዳዊት “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች” እያልሽ በለመንሽው ነበር” ይላታል /መዝ.42፡1፣ St.Ambros-Of The Holy Spirit,1:16;175/፡፡
 ሴቲቱም እንደ ግራ መጋባትም እንደ መደነቅም ብላ፡- “ጌታ ሆይ! ቀድተህ ታጠጣኛለህ እንዳልል መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ከያዝከው ውኃ ታጠጣኛለህ እንዳልልም በእጅህ መንቀል አልያዝክም፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?” ትሏለች/ቁ.11/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው የሴትዮዋ ንግግር እንደ አይሁድ በተንኰል የተለወሰ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው አሁንም በአክብሮት “ጌታ ሆይ!” ስትለው የምናስተውለው፡፡ እንዴት ያለች ልበ ንጹሕ ሴት ነች? ቅንነቷ ምሁረ ኦሪት ከተባለው ከኒቆዲሞስ በላይ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም ምሁረ ኦሪት ቢሆንም አንዳንድ የሚተገብራቸው ነገር ግን ምን ማለት እንደሆኑ የማያስተውላቸው ነገሮች ነበሩ (ለምሳሌ፡- የማንጻት ውኃ እንዴት ያነጻ እንደ ነበር አያውቅም)፡፡ ይህች ሴት ግን “አባታችን ያዕቆብ እና ልጆቹ ከብቶቹም ውኃ የጠጡት ከዚህ ጕድጓድ ነው፡፡ ሌላ የተሻለ የውኃ ጕድጓድ ቢኖራቸው ኖሮ ሁሉም ከዚህ ጕድጓድ ብቻ ባልቀዱ ነበር፡፡ አንተ ግን ሌላ ከዚህ የተሻለ ውኃ እሰጥሻለሁ እያልከኝ ነው፡፡ እንግዲህ ከአባታችን ከያዕቆብ ካልበለጥክ በስተቀር ሌላ የተሻለ ውኃ እንዴት መስጠት ይቻልሃል?” ትሏለች፡፡ ንግግሯ ከቅንነት የመነጨ መሆኑን የበለጠ የምናውቀው ደግሞ ጌታችን እንዲህ ሲላት፡- “ሌላ የተሻለ ውኃ ካለህ እንዴት መጀመርያ አንተው ራስህ አትጠጣም” ማለት ትችል ነበር፡፡ የዋሕነቷ ግን እንዲህ እንድትል አልፈቀደላትም /ቁ.12, St.John Chrysostom,Ibid/፡፡
 ጌታችን ይቀጥላል፡፡ ሴትዮዋ እርሱ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እየመጣች ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ ጊዜ “አዎ! አንቺ እንዳልሽው እኔ ከያዕቆብ እበልጣለሁ” አይላትም፡፡ ከዚሁ ይልቅ ጥበብ በተመላበት ንግግር፡- “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈስ የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ ለዘላለም አይጠማም” ይላታል /ቁ.13-14/። በዚህ ንግግሩ በያዕቆብ ውኃና እርሱ በሚሰጠው የሕይወት ውኃ ያለው ልዩነት ቀስ አድርጎ እየነገራት ነበር፡፡ “በእኔ የሚያምን ሁል ጊዜ ከቶ አይጠማም፤ ጽምዓ ነፍስ አያገኘውም” እንዲል /ዮሐ.6፡35/፡፡  እንዲህ ሲላትም እኔ ያስተማርኩትን ትምህርት እኔ በጥምቀት የሰጠሁትን ልጅነት የተቀበለ ሁሉ ዳግመኛ በነፍሱ አይጠማም ማለቱ ነበር፡፡ እውነት ነው! ይህ ማየ ሕይወት በደስታ የሚጠጡት መለኰታዊ ውኃ ነው፤ ይህ ውኃ ዳግመኛ የሚያስጠማ ውኃ አይደለም፤ ይህን ውኃ የሚጠጣ መጽሐፍ እንደሚል ዳግመኛ አይጠማም፤ ይህ ውኃ እንስራውን ካልሰበረ (ሰውነቱን በኃጢአት ባላቆሸሸ) ሰው ጋር ለዘላለም ይኖራል /ኢሳ.12፡3፣ዮሐ.7፡38፣ ቅ.አምብሮስ, On the Holy Spirit 1:16:181-182/፡፡
 ዕጹብ ድንቅ ነው! ሴቲቱ በዚሁ የጌታ ንግግር ይህ ጥምን የሚቆርጥ የሕይወት ውኃ ትጠጣ ዘንድ ጎመጀች፤ ስትመካበት የነበረው የአባቶቿ ጕድጓድም ናቀችውና፡-“ጌታ ሆይ! እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ” ትላለች /ቁ.15/።  አስቀድሞ “ትለምኝኝ ነበር” ብሏት ነበር፤ ያላት አልቀረ ይሄው ተፈጸመ፡፡ አሁን የሴትዮዋን ሁናቴ በጽሞና አስታውሱ! ሰማያዊውን ውኃ ስትጐነጭ፤ እንስራዋን ስትጥለው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ያዕቆብ ጕድጓድም ትዝ አይላትም፡፡ እንስራዋ የት እንደጣለቸው ትዝ አይላትም፡፡ ተወዳጆች! እምነቷ እንዴት እያደገ እንደሄደ ልብ በሉ፡፡ አስቀድማ ጌታዋን “አይሁዳዊ!” አለችው /ቁ.9/፤ ቀጥላ “ጌታ ሆይ!” አለችው /ቁ.11/፤ ትንሽ ቆይታም ከያዕቆብ እንደሚበልጥ አስተዋለች /ቁ.12/፤ አሁን ደግሞ የሕይወት ውኃ ምንጭ እርሱ መሆኑን ተገነዘበች /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ዝኒከማሁ/፡፡
ወዮ! አባት ሆይ የሳምራይቱን ሴት እንስራ ያስጣለ ፍቅርህ እንዴት ብርቱ ነው?! ጌታ ሆይ! ከደሀይቱና ከተጨነቀችው ሳምራይቱ ሴት ጋር የተነጋገረ ትሕትናህ እንዴት ግሩም ነው?! አባት ሆይ! ዛሬም ነፍሳችን እንደ ዋልያ አንተን ተጠምታለችና የሰጠኸንን ማየ ሕይወት (ክቡር ደምህ) በአግባቡ እንጠጣው ዘንድ እርዳን! በኃጢአታችን ምክንያት እንደ ሳምራይቱ ሴት ያፈርን ብዙዎች ነንና በቸርነትህ ተቀበለን! ከወራጅ ውኃ ጋር የምንታገል ብዙዎች ነንና ከማየ ገነት ታጠጣን ዘንድ እንማጸናሃለን! ፍቅርህ፣ ጥበብህ፣ ትሕትናህ ሳምራይቱን ሴት እንዳንበረከካት እኛንም ያቅፈን ዘንድ ፈቃድህ ይሁን! ሳምራይቱ ሴት ቀስ በቀስ እምነቷ እየጨመረ እንደሄደ እኛም በእምነትና በምግባር እንድናድግ ክንድህ ትርዳን አሜን ለይኩን ለይኩን!

በእንተ ሐዊሮቱ ገሊላ- የዮሐንስ ወንጌል የ18ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.4፡1-6)!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሳምንት እንደተነጋገርነው ብዙ ሰዎች ዮሐንስን ትተው ወደ ክርስቶስና ወደ ደቀመዛሙርቱ ይሄዱ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት  ማለትም ከአርድእተ ዮሐንስ ይልቅ አርድእተ ክርስቶስ አብዝተው እንዳጠመቁ አይተው ፈሪሳውያን ቅንዓት ይዞዋቸዋል፡፡ ጌታችንም ፈሪሳውያኑ ይህን ሰምተው እንዳዘኑ “ባወቀ ጊዜ ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ” /ቁ.1-2/፡፡ ከእናንተ መካከል “ጌታችን ለምን እንዲህ አደረገ?” የሚል ቢኖር እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ጌታችን እንዲህ ያደረገው ፈሪሳውያኑን ፈርቶ ሳይሆን የፈሪሳውያኑ ቅናትና ክፋት መልሶ እነርሱን እንደሚጎዳቸው ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ክፉ አድራጊ ራሱን እንጂ ማንንም ሊጎዳ አይችልምና፡፡ ፈሪሳውያን እርሱን ለመጉዳት ሲመጡ ከእነርሱ በላይ ሊጎዳቸው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በባሕሪይው ፍቅር የሆነው ጌታችን አንድ ቀንስ እንኳ እንዲህ አድርጎ አያውቅም፡፡ ስለዚህም ነገር ሁሉ እንደ እነርሱ ደካማነት ያደርግላቸው ነበር(ለምሳሌ፡- በእነርሱ እይታ ጌታ ፈርቷቸው ሄዷል- ሎቱ ስብሐት)፡፡
የሚገርመው ደግሞ “ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም” /ቁ.3/። ይህም ማለት የተደረገው ሁሉ ስለ እነዚህ ደካማ ሰዎች የተደረገ ነበር፡፡ የሚደረገው ሁሉ ስለ እነርሱ ጥቅም ይደረግ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እነርሱ የባሰ በቅናት ይሰክሩ ነበር፡፡ ጌታ የእነዚህ ቅናተኞች እጅና እግራቸውን አስሮ በይሁዳ መቆየት ቢፈልግ መቆየት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የሰውን ነጻ ፈቃድ የሚጋፋ አምላክ አይደለም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አገልጋይ አሳዳጆቹ ሲበዙ መሸሽ ኃጢአት እንዳልሆነ ለማስተማር ማለትም ፈርቶ ሳይሆን እንደ መልካም አስተማሪ “ሰው የሚጠላባችሁን ሥራ አትሥሩ” ብሎ ለአርአያነት ሀገራቸውን ለቆ ወደ ገሊላ ሄደ /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ Homoly on the Gospel of John, Hom.31:1/፡፡
 አስቀድሞ (ምዕ.3፡26) “እርሱ ያጠምቃል” ተብሎ አሁን ደግሞ “እርሱ አላጠመቀም” ስለተባለ የሚጋጭ ሐሳብ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚጋጭ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጌታ በግዙፉና በሚዳሰሰው እጁ አላጠመቀም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን ያጠምቁ ነበር፡፡ ይህም ማለት በእነርሱ አድሮ ያጠምቅ ነበር ማለት ነው፡፡ መጥምቁስ “እርሱ…ያጠምቃችኋል” ብሎ የለ /ማቴ.3፡11/? አሁንስ መቼ ማጥመቅ አቁሞ ያውቃል? በካህኑ እጅ የሚያጠምቅ እርሱ አይደለምን?
 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ያጠምቁ ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ይሁዳም ያጠምቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ልትደነቁ ትችላላችሁ!! ይሁዳ ያጠመቀው ዳግመኛ አልተጠመቀም፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ ያጠመቀው ግን ዳግመኛ ይጠመቅ ነበር፡፡ ይሁዳ ሲያጠምቅ ጥምቀቱ የክርስቶስ ነበር፤ ዮሐንስ ሲያጠምቅ ግን ጥምቀቱ የዮሐንስ ብቻ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ከይሁዳ ይልቅ ዮሐንስ ጻድቅ ቢሆንም ከዮሐንስ ጥምቀት ግን የይሁዳ ጥምቀት ትበልጣለች /አውግስጢኖስ፣ Tractes on the Gospel of John, 15:2-3/፡፡
 ከዚህ በኋላ ጌታችን ወደ ገሊላ ለመሄድ “በሰማርያ በኵል ያልፍ ዘንድ ግድ ሆነበት” /ቁ.4/።  ይህች ሰማርያ በይሁዳና በገሊላ መካከል የምትገኝ ግዛት ናት፡፡ ስለዚህ በዚህች ግዛት ሳይረገጡ መሄድ አይቻለም ነበር፡፡ እነዚህ ሳምራውያን ጥንተ ነገዳቸው አይሁዳውያን ሲሆኑ ሀገራቸው በአሦር ነገሥታት በስልምናሶርና ሳርጎን ስትያዝ ከአሕዛብ ከመጡ ሰዎች ጋር ተደባለቁ /2ነገ.17፡24-33/፡፡ መደባለቅ ብቻ ሳይሆን ከእነርሱ ጋር ተጋቡ፤ ጣዖታቸውን አምለኩ፡፡ እግዚአብሔርን ስላልፈሩም የአንበሳ መዓት ተሰዶባቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ከዚህ ተመልሰው እግዚአብሔርን ማምለክ ፈለጉ፡፡ ካህን ተልኮላቸውም የሙሴ መጻሕፍትን እንዲያውቁ ተገደረጉ፡፡ አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ ሲመለሱ ከእነርሱ ጋር ቤተ መቅደስን መሥራት ቢፈልጉም በበዘሩባቤልና በነህምያ ተቀባይነት ስላላገኙ በገሪዛን ተራራ ለራሳቸው ቤተ መቅደስ ሠሩ፡፡ “ማንበብ ያለብን አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነው፤ እግዚአብሔርን የምናመልከው በኢየሩሳሌም ሳይሆን በገሪዛን ተራራ ነው፤ የእግዚአብሔር ማደርያም ጽዮን ሳትሆን ሴኬም ናት” አሉ፡፡
 ጊዜው ሲደርስ ግን ጌታችን የሕይወትን ዘር ይዘራባቸው ዘንድ ወደ ሀገራቸው መጣ፡፡ ጌታችን መጥቶ ዘሩን የዘራባት ቦታም ሴኬም (ሲካር) ትባላለች፡፡ ወንጌላዊው፡- “ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ” እንዲል /ቁ.5/፡፡ የቦታው ስም ያለ ምክንያት የተጠቀሰ አይደለም፡፡ እነዚህ የሰማርያ ሰዎች፡- “እኛ የተለየንና የተከበርን ሰዎች ነን፤ እንደ አይሁድ የማንንም ነብይ ደም አላፈሰስንም፡፡ ስለዚህ የአብረሃም ልጆች ነን፤ የልጁም የያዕቆብ ልጆች መባል የሚገባንም እነርሱ ሳይሆኑ እኛው ነን” እያሉ ይመኩ ነበር፡፡ ጌታችንም ይህን ትምክሕታቸው ስለሚያውቅ የያዕቆብ ልጆች የሆኑት ሌዊና ስምዖን በእኅታቸው በዲና ምክንያት የሴኬም ሰዎችን ወደ ገደሉባት ሀገር መጣ፤ የሚያስመካ ነገር እንደሌላቸውም በዘዴ አስተማራቸው፤ እነርሱም ደም እንዳፈሰሱ በጥበብ ነገራቸው /ዘፍ.34፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 “በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ” /ቁ.6/።  የሚገርም ነው! ጌታችን በዚሁ ጕድጓድ የሚያገኛት ሳምራይቱ ሴት በጧት ውኃ መቅዳት ትችል ነበር፡፡ ነገር ግን የእርሷ አመጣጥ መለኰታዊ ዕቅድ አለበትና አንድም ሴትዮዋ ለመሲሑ የሚምበረከክ ልብ አላትና አንድም ይህች ሴት ከያዕቆብ የጕድጓድ ውኃ ይልቅ የማይነጥፍ የውኃ ምንጭ የምትሻ ናትና በተዋሐደው ሥጋ ደክሞ የሚመጣውን ጌታ ትገናኝ ዘንድ እስከዚሁ ሰዓት ሳትወጣ ቆየች፡፡
ወዮ! ስንደክም የሚያበረታን እርሱ ደከመው፡፡ የሕይወት ውኃ ምንጭ እርሱ ውኃ አጠጭኝ አላት፡፡ ከባሕርዪው የሕይወትን ውኃ የሚያጠጣ እርሱ ከወራጁ ውኃ አጠጭኝ አላት፡፡ እንዴት ዕጹብ ነው? የአምላክ ትሕትና እንዴት ያለ ነው? /ቅ.አምብሮስ፣ Of the Holy Spirit 1:16:184-85/፡፡
ውኃ አጠጪኝ አላት አፍላጋት የሠራው፤
እንደተቸገረ ውኃ እንደጠማው ሰው፡፡
     አይሁዳዊ አለችው አወይ አለማወቅ፤
    ሰማያዊው አምላክ ‘ራሱን ቢደብቅ፡፡ (ዘማሪ ይልማ ኃይሉ)!!

ዳግመ ስምዑ ለዮሐንስ- የዮሐንስ ወንጌል የ17ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡22-ፍጻሜ)!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
 ጌታችን አስቀድሞ የአይሁድ ፋሲካ ሲሆን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ የሄደበትም ምክንያት ለበዓሉ የመጡትን ሰዎች ገቢረ ተአምራቱን አይተው አንድም ትምህርቱን ሰምተው እንዲያምኑ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከዮሐንስ ለመጠመቅ ወደ ተሰበሰቡት ሰዎች ወደ ፈለገ ዮርዳኖስ ይሄዳል፡፡ አካሄዱም በዚያ የነበሩት ሰዎች ስለ ወንጌለ መንግሥት ሊሰበክላቸው ይገባ ስለ ነበር ነው፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው፡- “ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር” ይለናል /ቁ.22፣ /። “ያጠምቅ ነበር” ሲባልም በደቀመዛሙርቱ አድሮ ያጠምቅ ነበር ማለት ነው፤ እርሱ ራሱ ግን አላጠመቀምና /ዮሐ.4፡2/፡፡ “ለምንስ አላጠመቀም?” ቢሉ መጥምቁ እንደተናገረው ጌታችን የሚያጠምቀው በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ገና አልወረደም ነበር /ዮሐ.7፡39/፡፡ “ለምንስ ደቀ መዛሙርቱ አጠመቁ?” ቢሉ ደግሞ ሕዝቡ ከዮሐንስ ይልቅ ወደ ሐዋርያት ይመጡ ይገባልና፡፡ “ለምንስ ዮሐንስ ማጥመቁን አላቆመም?” ቢሉም የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት፡- “መምህራችን ዮሐንስ ማጥመቅ ካቆመ  የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደሚያጠምቁ ሁሉ እኛም ማጥመቅ አለብን” ብለው ችግር በፈጠሩ ነበርና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ Homily on the Gospel of John, Hom.29/፡፡
  ስለዚህም “ወሀሎ ዮሐንስኒ ያጠምቅ በሄኖን በቅሩበ ሳሌም በማዕዶተ ዮርዳኖስ- ዮሐንስ ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር፤ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና” /ቁ.23-24/።  በዚህን ጊዜ አርድእተ ዮሐንስ መምህራቸው ያጠመቃቸው ሰዎች ወደ ጌታ ሲሄዱ የጌታ ደቀ መዛሙርት ያጠመቋቸው ግን ወደ ዮሐንስ እንደማይመጡ አስተዋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት “የማን ጥምቀት ብትበልጥ ነው” ብለው ግራ ተጋቡ፡፡ በዮሐንስ እጅ ተጠመምቀው ነገር ግን ዮሐንስ እንደነገራቸው ወደ ጌታ ሲሄዱ የነበሩ አይሁድ አግኝተውም “የእኛ መምህር እያለ ወዴት ትሄዳላችሁ” ይልዋቸዋል፡፡ አይሁድም “የእናንተማ መምህር መስክሮ አለፈ እኮን” ሲልዋቸው “ስለ ማንጻት በመካከላቸው ክርክር ሆነ” /ቁ.25, Augustine, Tractes on the Gospel of John/።
  ከዚህ በኋላ አርድእተ ዮሐንስ “ወደ ዮሐንስ መጡና፡- መምህር ሆይ! በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል፤ ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት” /ቁ26/። በዚሁ ንግግራቸው ለዮሐንስ ያላቸውን ክብር “መምህር ሆይ!” በማለት ሲገልጡ ስለ ጌታችን ግን (ሎቱ ስብሐትና) ስሙን እንኳን ለመጥራት ተጠይፈው በንቀት “ከአንተ ጋር የነበረው ያጠምቃልና ስለዚህ ምን ትላለህ?” በማለት ሊያበሳጩት ይሞክራሉ፡፡
  ዮሐንስ ግን እነርሱ እንደገመቱት ሳይሆን በእጅጉ ሐሴት አድርገ፡፡ አሁንም እንደገና ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክርላቸው ዕድል ስላገኘ ተደሰተ፡፡ በጥበብና በለሰለሰ ንግግርም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- “ከሰማይ ካልተሰጠው ማለትም ከእግዚአብሔር መምህርነትን ካልተሰጠው በቀር ሰው አንዳች ገንዘብ ማድረግ አይቻለውም፤ ይልቅ ክርስቶስን ስትተዉ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ እንዳትገኙ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ /ሐዋ.5፡39/፡፡ እርሱ (ጌታ) ይህን ሁሉ የሚያደርገው በራሱ ሥልጣን ነውና፡፡ ደግሞም፡- ትምህረቴን የምትቀበሉ ከሆነና እኔንም የምትወዱኝ ከሆነ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን መንፈቅ አስቀድሜ ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። እኔ የተላክሁት የእርሱን መንገድ እጠርግ ዘንድ እንጂ ራሴን እሰብክ ዘንድ አይደለም፡፡ እኔ የመጣሁት በእርሱ ከፍ ከፍ እል ዘንድ እንጂ እርሱን ዝቅ ዝቅ እንዳደርግ አይደለም፤ የመጣሁት እንኳን የባሕርይ አባቱ ልኮኝ እንጂ ከራሴ አልነበረም፡፡ የተናገርኩትም ሁሉ ከእኔ ሳይሆን ከእርሱ የተቀበልሁትን እንደሆነ ቅሉ ምስክሮቼ እናንተው ናችሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ታላቅ እንደሆንኩ አታስቡ፡፡ ታላቅስ ዓለማትን በእጁ የያዘ ጌታ በእውነት እርሱ ነው፤ ዘቦቱ መርዓት መርዓዊ ውእቱ- ሙሽራይቱ  ያለችው (ምእመናን ያሉት) እርሱ ሙሽራ (ክርስቶስ) ነው፤ ማለትም የሚያገባው እርሱ ያጨ ነው፡፡ ማለትም ምእመናንን ቤተ ክርስቲያንን ያጨ እርሱ ነው፡፡ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ያጨ አይደለም፡፡ ሚዜው የሙሽራውን ሚስት (ምእመናንን) ለራሱ ቢወስድ እርሱ አመንዝራ ነው፡፡ ስለዚህ ሚዜው በሙሽራው ድምጽ፣ በሙሽራው (በክርስቶስ) ወደ ሚስቱ (ወደ ቤተ ክርስቲያን) መምጣት እጅግ ደስ ይለዋል። የክርስቶስ ባለሟል የምሆን የእኔ ደስታ፣ የእኔ ሐሴት የእርሱ የሙሽራው መምጣትና ምእመናኑም ትምህርቱን ተቀብለዉትና አምነውበት ሲያድርባቸው ሲዋሐዳቸው ማየት ነው፡፡ ይህ ሁሉ ባይሆን ሐዘኔ በበዛ ነበር፡፡ አሁን ግን ስለ መጣ ይህ ደስታዬ ተፈጸመልኝ። የእኔ የማዘጋጀት መምህርነትም አለፈች፤ የእርሱ ግን መቼም መች አታልፍም፡፡ ስለዚህ እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል። እናንተም ከእኔ ይልቅ ወደ እርሱ ዘወር ትሉ ዘንድ ይገባል፡፡ ምንም በኃጢአት ወደ ተጨማለቅነው ያለ ኃጢአት በሥጋ ተገልጦ ቢመጣም ከላይ የመጣው እርሱ ከሁሉ በላይ ነውና ማለትም አማናዊው ሙሽራ የባሕርይ አምላክ ነውና፤ ከምድር የተገኘሁ እኔ ግን ምድራዊ ነኝ፤ አባቴ ዘካርያስ እናቴ ኤልሳቤጥ እያልኩም ምድራዊ ልደቴን አስተምራለሁ። ዓለምን ለማዳን ከእርሱ በቀር ከላይ የመጣ የሌለ እርሱ ግን ከሁሉ የሚበልጥ፣ ሰማያዊ ደግሞም አልፋና ዖሜጋ ነው። ከአባቱ ዘንድ በህልውና ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል፤ ምስክርነቱን ግን የሚቀበለው የለም። ምስክሩን የተቀበለ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ አተመ፤ ተናገረ። እግዚአብሔር የሾመው እውነተኛ መምህርም የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምራል፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና። ማለትም የለበሰው ሥጋ የባሕርይ አምላክ የሆነ እንጂ ልዩ ልዩ ጸጋ እንደተሰጠን እንደ እኛ በተከፍሎ አይደለም /1ቆሮ.12፡4/፡፡ አባት ልጁን እንደ እኛ በፈቃድ ሳይሆን በባሕርይው ይወዷል፤ ሁሉንም በእጁ ጭብጥ በእግሩ እርግጥ አድርጎ ሰጥቶታል። ስለዚህ በእኔ ሳይሆን በዚሁ ሙሽራ በወልድ ያመነ የማታልፍ መንግሥተ ሰማይን ይወርሳል፤ በወልድ ያላመነ ግን  የእግዚአብሔር የቁጣው መቅሰፍት ማለት ፈርዶ ያመጣበትን ፍዳ ሲቀበል ይኖራል እንጂ የማታልፍ መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም” /ቁ.27-36/፡፡
 ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! እኛ ከአንተ እንወለድ ዘንድ አንተ ከእኛ ባሕርይ ስለተወለድክልን እናመሰግንሃለን፡፡ በጥምቀት ከአንተ ጋር ቀብረህ ዳግመኛ ከአንተ ጋር ስላነሣኸንም እናመሰግንሃለን፡፡ አዲስ ልደት፣ አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ልብም ስለ ሰጠኸን እናመሰግንሃለን፡፡ በመርዛማው እባብ በፈቃዳችን ብንሞትም በአንተ ሞት ሞታችንን ስለገደልከው እናመሰግንሃለን፡፡ አባት ሆይ! አሁንም ምንም ኃጢአተኞች ብንሆንም አብሮነትህ አይለየን፡፡ ቅዱስ መንፈስህም አትውሰድብን፡፡ እኛ አንሰን አንተ ግን ከፍ ከፍ እንድናደርግህ ማስተዋሉን ስጠን፡፡ አለማወቃችን እንድናውቅ እርዳን፡፡ አንተ ማን መሆንህን ሳያውቁ ሙሽራይቱን (ቤተ ክርስቲያንን) የሚያሳድዱም አስታግስልን፡፡ እኛንም በምግባር በሃይማኖት እስከ ሕቅታ ድረስ እንድንታመን ደግሞም በፈተና እንድንጸና እርዳን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን!!!!

የዮሐንስ ወንጌል የ16ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡13-21)!!

የዮሐንስ ወንጌል የ16ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡13-21)!!

by Gebregziabher Kide on Wednesday, March 14, 2012 at 5:14pm ·
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
“ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው /ቁ.13/። “ይህ አነጋገር ከኒቆዲሞስ ንግግር ጋር ምን ግንኝነት አለው” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ግንኝነትስ አለው፡፡ ምክንያቱም ኒቆዲሞስ ጌታችንን “ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር” አድርጎ አስቦት ስለ ነበር ጌታ ኒቆዲሞስን “አንተ እንደምታውቃቸው ምድራውያን መምህራን አድርገህ አታስበኝ፤ ምክንያቱም ከእኔ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ደግሞም የወረደ የለም፡፡ በሌላ አገላለጽ እነዚህ መምህራን በዚህ ምድር ስታያቸው እዚህ ምድር ብቻ የሚታዩና ከሰማይ የሌሉ ናቸው፤ እኔ ግን እዚህ በግዙፍ ሥጋ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ብታየኝም ከአባቴ ጋራ በህልውና አንድ ነኝ፤ በሰማይም በምድርም ሙሉዕ ነኝ፤ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ አድርጌ የመጣሁኝ እኔ ብቻ ነኝ” ሲለው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ታድያ እርሱ ሙሉዕ በኵለሄ በመለኰቱ ሳለ እንዴት ወረደና ወጣ ይባላል?” ይላሉ፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- እንዲህ እየተባለለት ያለው ወልድ በመለኰቱ ዙፋኑን ትቶ መውረዱን ለመግለጥ ሳይሆን በሥጋ ማርያም ገዝፎ መታየቱን፣ የባሮቹን መልክ ይዞ መምጣቱን ለማመልከት ነው፡፡ የሰው ልጅ ብሎ ራሱን ሲገልጥም እርሱ ሙሉ ሰውነትን ማለትም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋንና ፍጹም ነፍስን ነስቶ መገለጡን ለማመልከት ነው /St. John Chrysostom on the Gospel of John, hom.27:1/፡፡
 አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ቅዱሳን ወደ ሰማይ ቢወጡም ዓለምን ለማዳን አልወረዱም፡፡ ስለዚህ እኛም መውጣት ከፈለግን ሠረገላም ይሁን አውሮፕላን ሳያስፈልገን እንወጣ ዘንድ እንዲያወጣን የወረደውን ጌታ እንመን፡፡ መውጣት ከፈለግን ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም እንዲል ብቻችንን መውጣት አንችልም፡፡ ዳግም ተወልደን የሙሽራው ብልቶች ከሆንን ግን ከእርሱ ጋር አንድ አካል ስለምንሆን መውጣቱ ቀላል ነው /Augustine, Sermon on the New Testament Lessons 41:7-8/፡፡
 “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ” መጥቷልና፡፡ የዚህ የዳግም ልደታችን ምንጭ አንድም የመውረዱ ምሥጢር መስቀል ነውና /ቁ.14-15/። እነዚህ ሁለቱም ምሥጢራት ማለትም የጥምቀቱና የመስቀሉ ምሥጢር ክርስቶስ ለምንጠላው እንኳን ድንቅ የሆነ ፍቅሩን ያሳየባቸው ምሥጢራት ናቸው፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ኃጢአት ሲያበዙ በመርዘኛ እባብ ተነድፈው ሙሴ በሰቀለው የነሐሱ እባብ ከሞት እንደተረፉ አሁንም በመርዘኛው እባብ (ኃጢአት ፍዳ ባለበት በዲያብሎስ) የተነደፍን ሁሉ በነሐሱ እባብ (ኃጢአት ፍዳ በሌለበት በንጹሐ ባሕርይ በጌታ ስቅለት) እንደምንድን እየተናገረ ነው፡፡ ልናስተውለው የሚገባ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እባብ የክፋት ምሳሌ ብትሆንም ጌታችን (ሎቱ ስብሐትና) በነሐሱ እባብ እየተመሰለ ያለው ክፉ ሆኖ ሳይሆን በፍቃዱ “በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ…ኃጢአትን በሥጋ ለመኰነን” ስለ መጣ ነው /ሮሜ.8፡3፣ St. Gregory of Nyssa, Vita Moysis, PG 44:415/፡፡
ምክንያቱም፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” /ቁ.16/። የዘላለምን ሕይወት የሚሰጠን እርሱ ዘላለማዊ ስለሆነ ነው፤ ትንሣኤ ሕይወትን የሚሰጠን እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ምንም አፈርና ጭቃ ብንሆንም እንዲሁ (ያለ ምክንያት) ወደደን፡፡ እኛን ለማዳንም አንድያ (የባሕርይ) ልጁን እንጂ ከባሮቹ አንዱን፣ ወይም መላእክትን፣ ወይም ሊቃነ መላእክትን አልላከልንም፡፡ ምንም ቸርነቱን ለመቀበል ያልተገባን ብንሆንም እንዲሁ ደሙን አፈሰሰልን /St. John Chrysostom. Ibid/፡፡
 “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና” /ቁ.17/። በሌላ አገላለጥ በሥጋዊው እጅ ለሌለው እጅ፣ እግር ለሌለው እግር፣ ዓይን ለሌለው ዓይን በመንፈሳዊው ቅሉ ደግም ተሐድገ ለኪ ኃጢአትኪ- ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል ተሐድገ ለከ ኃጢአትከ- ኃጢአትህ ተሰርዮልሀል ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ እያለ ሊያድነው ካሳ ሊከፍልለት እንጂ ቀድሞ በፈረደበት ፍርድ ሌላ ፍርድ ሊፈርድበት አልመጣም፡፡ ስለዚህ “በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” /ቁ.18/። ያላመነው ሁሉ ትንሣኤ ቢኖሮውም ትንሣኤ ለዘሐሳር ነው፡፡ አሁን ተፈርዶበታል ሲልም አስቀድሞ ለዚያ ተወስኗል ማለት ሳይሆን አስቀድሞ ባለማመኑ ያው ትንሣኤው ለፍርድ ነው ማለት ነው፡፡/ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
 “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው” /ቁ.19/። “ይህ ማለት” ይላል ክርስቶስ “እኔ ዓለምን እፈርድበት ዘንደ መጥቼ ብሆን ኖሮ ሰዎች ላለማመናቸው ምክንያት ባገኙ ነበር፡፡ ነገር ግን አመጣጤ የሰው ልጅን በሙሉ ከጨለማ ወደ ብረሃን አወጣ ዘንድ ነው፡፡ ወደ ብርሃን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ማለትም በእኔ ያምኑ ዘንድ ፈቃደኞች ያልሆኑ ይፈረድባቸዋል፤ ስለ ተፈረደባቸውም ምክንያት የላቸውም” /St. John Chrysostom. Ibid/፡፡
“ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” /ቁ.20-21/።
 እንግዲያስ ወንድሞቼ ሆይ! ጨለማው እንዳይጋርደን ወደ ብርሃን ለመውጣት እንቻኰል፤ እንድን ዘንድ እንንቃ፤ ጊዜ ሳለልን እንነሣ፤ ቀን ሳለልን ብርሃኑም  ሲያበራልን እንንቃ፤ ቀኑም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወደ እርሱ ብንመጣ ኃጢአታችን ይቅርታ ይደረግለታል፡፡ ምንም ጽድቅ ሳይኖረን በባዶ ራሳችንን ከፍ ከፍ የምናደርግ ሁሉ ትርፉ በጨለማ መቅረት ነውና ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንውጣ፡፡
 ሰው የእግዚአብሔር ፈቃድ ፍጥረት ነው፡፡ ኃጢአት ደግሞ የእኛ ፈቃድ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ አኛ ያደረግነውን ትተን እግዚአብሔር ወዳደረገልን የፍቅር ሥራ እንውጣ፡፡ የእኛ ሥራ ሕጸጽ እንዳለበት ስናውቅ ሕጸጽ ወደሌለበት የእግዚአብሔር ሥራ እንፍጠን፡፡ ንስሐ የመልካም ነገር ጅማሬ ናት፡፡ ሰው በጨለማ ውስጥ መኖሩን ሲያውቅ (በኃጢአት ውስጥ ለማለት ነው) ይቅርታ እንደሚያስፈልገውም ያውቃል፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ ሰውን እንዲሁ በማፍቀር ሰው የሆነው ጌታ ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!!

የዮሐንስ ወንጌል የ15ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡6-12)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
“ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” /ቁ.5/። “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብሎ እንደ ኒቆዲሞስ የሚጠይቅና የሚጠራጠር ሰው ካለ እንዲህ ብለን መልሰን እንጠይቀዋለን፡-  አዳም ከሕቱም መሬት የተወለደው እንዴት ነው? አስቀድሞ አፈር ቆይቶ በኋላ እንዴት ብሎ የተለያየ የሰውነት አካል ያለው ሰው ሆነ? አፈር ብቻ የነበረው በኋላ እንዴት ብሎ አጥንት፣ ጅማት፣ የደም ቧንቧ… ሆነ? ወንድሞች ሆይ! በዘፍጥረት መጀመርያ እንደምናነበው አፈር አፈር ነው፡፡ እግዚአብሔር በእጁ ሲያበጃጀው ግን ሰው ሆነ፡፡ አሁንም ሰው በማኅፀነ ዮርዳኖስ ውስጥ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ሆኖ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ይህ መለኰታዊ አሠራር ስለሆነ ሰዋዊ አመክንዮ እንሰጥ ዘንድ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ የምናምን እንጂ የምንጠራጠር አንሁን /St. John Chrysostom Homily on the Gospel of John Hom.25/፡፡
በእርግጥም አንድ ሰው አዲስ ሕይወትን ለመጀመር አሮጌው ሕይወቱን መጣል አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አሮጌው ሰውነቱ መሞት አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በጥምቀት በኵል ነው /ሮሜ.6፡4-5፣ Basil the Great, On the Spirit 15:35/፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለገባልን የትንሣኤ ተስፋ ዐረቦን እንቀበላለን /2ቆሮ.1፡22/፡፡
“ለምንስ በውኃ አደረገው?” ልትሉ ትችላለችሁ፡፡ ስለ ብዙ ምክንያት፡- አንደኛ “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ” የሚለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ /ሕዝ.35፡25/፡፡ ሁለተኛ ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይፈሳል፤ ጥምቀትም ለሁሉ ነውና፡፡ ሦስተኛ ውኃ ያነጻል፤ ጥምቀትም ያነጻልና፡፡ አራተኛ ውኃ ለወሰደው ፍለጋ የለውም፤ በጥምቀት የተሰረየ ኃጢአትም በፍዳ አይመረመርምና፡፡ አምስተኛ ውኃ መልክ ያለመልማል፤ ጥምቀትም መልክአ ነፍስን ያለማልማልና፡፡ ስድስተኛ በውኃ የታጠበ ልብስ ኃይል ጽንዕ ግዘፍ እየነሣ ይሄዳል፤ ምእመናንም ተጠምቀው ገድል ትሩፋት እያከሉ ይሄዳሉና፡፡ ሰባተኛ “ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ” ተብላ ነበር፤ አሁን ግን ክርስቶስ ገብቶባታልና ሕያውና ለባዊት ነፍስ ያላቸው ሰዎች ይገኝባታልና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ /ዘፍ.1፡20፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ማቴ.3፡17/፡፡ እናም ስለ ሌላ ብዙ ምክንያት፡፡
 ጌታ ይቀጥላል፤ እንዲህም ይላል፡- “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” /ቁ.6/።  ይህም ማለት “ከግዙፍ ሥጋ የሚወለደው ግዙፍ ሥጋ ነው፤  ከረቂቅ መንፈስ ቅዱስ የምትወለድ ነፍስ ግን መንፈሳዊት ናት፡፡ ከሥጋ ብቻ ስንወለድ “አፈር ነህና” የሚለው ማንነታችን ይቀጥላል፤ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ስንወለድ ግን ከማይሞተው እግዚአብሔር የማንሞት መንፈሳውያን ሆነን እንወለዳለን” ማለት ነው /ዮሐ.1፡12፣ Gregory of Nyssa/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ውኃው አሁን አብራከ መንፈስ ቅዱስ ማኅፀነ ዮርዳኖስ ስለሆነ “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” እንጂ “ከውኃ የተወለደ ውኃ ነው” አይባለም፡፡
 ኒቆዲሞስ ግን ነገሩ ረቀቀበት፤ እየተደናገረም ይደነቃል፡፡ ስለዚህም ጌታ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ” ይሏል /ቁ.7/። የሚያየው ነገር ግን የማያስተውለው ምሳሌ በማምጣትም ያስረዷል፡- “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” /ቁ.8/። ይህ ነፋስ “ወደዚህ ሂድ፤ ወደዚህም አትሂድ” የሚለው ሳይኖር እርሱ ወደ ወደደው ብቻ ይሄዳል፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ስንወለድም እንዲህ ነው፡፡ አንድም እንደምንወለድ እናውቃለን፤ እንዴት እንደሚወልደን ግን አናውቅም፡፡ አንድም በበዓለ ኃምሳ እንደ ሆነው መንፈስ ቅዱስ ትንቢት ሲያናግር ምሥጢር ሲገልጥ ሱባዔ ሲያስቈጥር ልናስተውለው እንችላለን፤ እንዴት እንደሚያድር ማወቅ ግን አይቻለንም፤ በሰዋዊ አረዳድም ልንረዳው አይቻለንም /Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 2:3-7/፡፡ ከመንፈስ የሚወለዱትም ልደት እንዲህ ነው፡፡ ይህም ማለት ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው አንተ ከወዴት እንደመጣህና (ከማን እንደተወለድክና) ወዴትም እንደምትሄድ (ሌላ ሀገር እንዳለህ) አያውቅም /ፊል.3፡20፣ Augustine, Tractes on the Gospel of John 12:5/፡፡
 “ኒቆዲሞስም መልሶ፡- ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት የባሰ ግራ ይጋባል/ቁ.9/፡፡ “ጌታችንም መልሶ፡- አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ይሏል /ቁ.10/፡፡ ከእናንተ መካከል “ዳግም ልደትና የኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር መሆን ምን ያገናኘዋል?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ሔዋን ከአዳም አንዲት የጎድን አጥንት እንዴት ተፈጠረች? ኤልሳዕ የሰጠመውን ብረት እንዲሰፍ እንጨቱ ግን ያለ ባሕርዩ እንዴት እንዲሰጥም አደረገው? እስራኤል ባሕረ ኤርትራን እንዴት ተሻገሩ? ንዕማን በፈለገ ዮርዳኖስ ውኃ ተጠምቆ እንዴት ነጻ? /St. John Chrysostom Ibid/ በእርግጥም ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ሲሆን የሂሶጵ ቅጠል ምሥጢር፤ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ሆኖ ነገር ግን ማታ በውኃ ታጥቦ ንጹሕ ይሆናል የሚለውን የኦሪቱ ሥርዓት፤ ያዕቆብ በኵር ሳይሆን ብኵርናን እንዴት እንደተቀበለ፤ ማርያም እኅተ ሙሴ እንዴት ነጻች የሚለውን ሁሉ የአይሁድ መምህር ሲሆን ሊያውቀው ይገባ ነበር /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatians Diatessaron 14:13/፡፡ 
 ከዚህ በኋላ ግን ጌታ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” /ቁ.11-12/ በማለት (ክርስቶስ) የሚናገረው ነገር በሰው ሕሊና ስለማይደረስ በእምነት እንዲቀበለው ይነግሯል፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ በባሕርይ አምላክነቱ ከባሕርይ አባቱና ከባሕርይ ሕይወቱ ጋር የሚናረውን ሁሉ በትክክል ያውቋል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን እንኳንስ ሰማያዊው ልደት ምድራዊው ነፋስ እንኳ ከየት መጥቶ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም፤ ኒቆዲሞስ ብቻ ሳይሆን እኛም አናውቅም /St. Cyril of Alexandria, Commentary on John/፡፡
ወንድሞቼ! እንግዲያስ ይህን ሰማያዊ ምሥጢር የምናምን እንጂ የምንጠራጠር አንሁን፡፡ ታላቁ መምህራችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረን በላይ ሌላ ምድራዊ መምህር ለራሳችን የምናመጣ አንሁን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

የዮሐንስ ወንጌል የ14ኛውን ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡1-4)!!

 (ከቻሉ ጸልየው በትዕግሥትና በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት)!!
“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ” /ቁ.1/። ብዙ የዘመኑ የስነ መለኰት ተማሪዎች ኒቆዲሞስን የማታው (Extension) ተማሪ ይሉታል፡፡ ይህ ሰው አስቀድሞ በኢየሩሳሌም የፋሲካ በዓል የጌታችንን ተአምራት አይተው ካመኑት የፈሪሳውያን ወገን አንዱ ነው /ዮሐ.2፡23/፡፡ ኒቆዲሞስ በአንድ ቦታ ስለ ክርስቶስ አይሁዳውያኑን፡- “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” ብሎ ሲከራከራቸው እናገኘዋለን /ዮሐ.7፡51/፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጌታችን ስለ ሰው ልጆች ፍቅር በመስቀል ላይ ከተሠዋ በኋላ ቅዱስ ሥጋውን አውርዶ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ገንዞ በክብር ሲቀብረው እንመለከተዋለን /ዮሐ.19፡39/፡፡ አሁን ግን ጌታችንን ገና በትክክል ማን መሆኑን ስላልተረዳ አብልጦ ይማር ዘንድ በሌሊት መጣ፡፡ በሌሊት መምጣቱም አይሁዳውያኑን ፈርቶ ነው፡፡ አይሁዳውያኑ አስቀድመው “እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት ተስማምተው ነበርና” /ዮሐ.9፡22/፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ተቀብሎታል፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም የሚተርፍ ታላቅ ምሥጢርን አስተምሮታል /St. John Chrysostom, Homily on the Gospel of John 24/፡፡
 ኒቆዲሞስ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” በማለትና ጌታ ያደረጋቸውን ተአምራት በማድነቅ ብቻ ድኅነት የሚገኝ መስሎት ነበር፡፡ ስለዚህም “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” ይለል /St. Cyril of Alexandria, Commentary on the Gospel of John 2/፡፡
 ጌታችንም “ኒቆዲሞስ! መምህር ሆይ፣ ጌታ ሆይ በማለትህ ብቻ ድኅነትን እንደምታገኝ አድርገህ አታስብ፤ መዳንህን ወደምትፈጽምበት ሕይወት ለመግባት አስቀድመህ ዳግመኛ ልትወለድ ያስፈልገሀል፡፡  እውነት እነግረሃለሁ፥ አንተ ብቻ ሳትሆን ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ይሏል /ቁ.3/።  በሌላ አገላለጽ “ዳግመኛ ካለተወለድክ በቀር፣ ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ ካልታደስክ በቀር /ቲቶ.3፡5/ ስለ እኔ የምታስበው ሁሉ ሥጋዊና ደማዊ ነው፡፡ እኔ ግን አሁን አንተ እንደምታስበው ከዚህ በፊት ወደ እናንተ እንደላክሁላችሁ ነቢያትም መምህራንም አይደለሁም፡፡ ይልቁንም እነዚህ አንተ የምታውቃቸው ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩልኝ መሲሕ መሆኔን ልትረዳ አትችልም፡፡  ዳግመኛም ካልተወለድክ በቀር የልጅነትን ማኅተም ስለማይኖርህ ከእኔ ጋር በመንግሥተ ሰማያት ዕድል ተርታ አይኖርህም፤ መንፈስ ቅዱስ ካላደረብህ በቀር እኔ የባሕርይ አምላክ ነው ብለህ ልታምን አትችልም” ይሏል /1ቆሮ.12፡3፣ St. John Chrysostom, Ibid/፡፡
 አዎ! በሰሌዳ ላይ በተሠራ ሥዕል ከውጭ በመጣ ቆሻሻ ሲዝግና ሲበላሽ የእርሱ ምስል የሆነው ሰው ስለ ሥዕሉ ሲል ሰሌዳውን ይወለውለዋል፤ ይሰነግለዋል፡፡ ይህም ሥዕሉ ያለበትን እንጨት በመጣል ሳይሆን ከውጭ መጥቶ ሥዕሉን ያበላሸውን ቆሻሻ በማስወገድ ወደ ጥንት ሁኔታው ይመልሰው ዘንድ የሚቻለውን ያደርጋል፡፡ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር ቃልም በአርአያው ተሠርቶ የነበረውን ሰው ያድሰው ዘንድ ፣ በኃጢአቱ የጠፋውን ኃጢአቱን በማስተስረይ ይፈልገውና ያገኘው ዘንድ መጣ፡፡ ራሱ በወንጌል “እኔ የጠፋውን ልፈልግና ላድን መጥቻለሁ” እንዲል /ሉቃ.19፡10/፡፡ ስለዚህ ሰው እንደገና ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር “አፈር ነህና” የሚለው አሮጌ ማንነቱን ይዞ ይቀጥላል፡፡ ዳግመኛ መወለድ ማለትም እንደገና ከሴት መወለድ ማለት ሳይሆን ነፍስ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል እንደገና መፈጠሯንና መወለዷን የሚያመለክት ነው /St. Athanasius, On The Incarnation 14:1-2/፡፡
 በእርግጥም ከመንፈስ ቅዱስ አዲስ ልደትን፤ ከአዲሱ ልደታችንም አዲስ የተፈጠረውን ሰውነትን፤ አዲስ ሰውነት ስናገኝም ክርስቶስ እርሱ ማን መሆኑን በትክክል እናውቃለን /St. Gregory of Nazianzus, On the Holy Spirit, Theological oration 5:28/፡፡
ስለዚህም ጌታችን፡- “ኒቆዲሞስ ሆይ! እኔ ከእግዚአብሔር መምህር ሆኜ እንደተላክሁ ካወቅክ፤ ያደርኳቸው ተአምራትም ይህንን ካረጋገጡልህ አሁንም አንድ ነገር ይቀራሃል፡፡ ይኸውም ሰው ሟች ሆኖ ማለትም ዳግመኛ በማይበሰብስ ባሕርይ ሳይነሣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ አይችልም /1ቆሮ.15፡50/፡፡ ስለዚህ ከእኔ ጋር ልትነሣ ከወደድክ እኔ እንደምሞተው ሞት ልትሞት እንደምነሣውም ትንሣኤ ልትነሣ ያስፈልጋሃል፡፡ ይህንንም የምትፈጽመው በጥምቀት በኩል ነው፡፡ ዳግመኛ ወደ ሥላሴ ማኅፀን ልትገባ ያስፈልገሀል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ይህን የምትፈጽመው በጥምቀት ውኃ በኩል ነው፡፡ ይህ ወደ ሥላሴ ማኅፀን የምትገባበት ውኃ እንደ ድሮ አጠራርህ ውኃ አይምሰልህ፡፡ እዚህ ማኅፀን ውስጥ ስትገባ የሥላሴን እንጂ የውኃውን ስም የማትጠራውም ለዚሁ ነው፡፡ አንድ ሕፃን በእናቱ ሽል /ማኅፀን/ እንደሚፈጠረው ሁሉ አንተም በዚሁ ማኅፀን ዳግም ካልተፈጠርክ በቀር የእኔን ሞትና ትንሣኤ አትተባበርም” ይሏል /ሮሜ.6፡5፣ Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 2:3.3/፡፡
 ኒቆዲሞስ ግን ሰው ከአዳምና ከሔዋን ሲወለድ እንጂ ከቅድስት ሥላሴ፣ ከቤተ ክርስቲያን (በምሥጢረ ጥምቀት በኩል) የሚገኘውን ረቂቁን ልደት ምን እንደሆነ ስለማያውቅ ይደናገራል፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያውቀው ሞትን የሚወልዱ እንጂ ሕይወትን የሚወልዱ ወላጆችን አይደለም፤ ምድራዊውን እንጂ ሰማያዊውና ረቂቁን ልደት አያውቅም፤ ከወንድና ከሴት ፈቃድ የሚገኘውን ልደት እንጂ ከአብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚገኘውን ልደት አያውቅም /Augustine, Tractes on the Gospelof John, 11:6/፡፡
ስለዚህም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” ይላል /ቁ.4/።
 የሚገርመው ዛሬም ብዙ ሰዎች እንደ ኒቆዲሞስ ተቸግረው ማየታችን ነው፡፡ “እንዴት ቅድመ ዓለም ከአብ ተወለደ ትሉናላችሁ”፤ “እንዴት እግዚአብሔር ሰው ይሆናል?” ፤ “እንዴት ሰው ውኃ ውስጥ ገብቶ ዳግም ይወለዳል?” በማለት ፍጥረታዊ አመክንዮ ለማምጣት ይጥራሉ፡፡ ጌታ ሰማያዊ ነገር ሲነግረው ኒቆዲሞስ ግን ምድራዊ ነገርን ያወራል፡፡ ዛሬም ሰማያዊዉን ምሥጢር የተረዳነውን ያህል ስንነግራቸው ምድራዊ ማረጋገጫ ይፈልጋሉ፡፡ በሕጻን አእምሮአቸውም “እንዴት ሆኖ” በማለት ራሳቸውን ያስጨንቃሉ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ለመሰሉ ሰዎች እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም” /1ቆሮ.2፡14/፡፡
 ወንድሞቼ! ሰማያዊውን ምሥጢር በምድራዊ አመክንዮ ለመረዳት አንሞክር፡፡  እግዚአብሔር “ይሆናል፤ ይደረጋል” ካለን “አሜን፤ ይሁን፤ ይደረግ” ብለን መረታት እንጂ ሽሽት አያስፈልገንም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይህ አስተሳሰባችን እሾክ ይሆንብንና “ኢየሱስ ጌታ ነው፤ ክርስቶስ መምህር ሆኖ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣ እናውቃለን” እያልን ነገር ግን ወደ መንፈሳዊ መረዳት ሳንደርስ እንደተደናበርን እንቀራለን፡፡ የሚያስፈልገው ግን እምነት ብቻ ነው፡፡

የዮሐንስ ወንጌል የ13ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.2፡18-ፍጻሜ)!!

ወንጌላዊው “ስለዚህ አይሁድ መልሰው፡- ይህን ስለምታደርግ (የምንሸጠውን ስለምትገለባብጥ) ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት” በማለት ይቀጥላል /ቁ.18/። የሚገርም ነው! አይሁድ በዚህ ንግግራቸው፡- “ቤቱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረጋችን አግባብነት አለው፤ አንተ ይህን ቤት የአባቴ የጸሎት ቤት ነው ስትል ግን (ሎቱ ስብሐት) ሕግን ባታውቅ ነው፡፡ ከምድራውያን ነገሥታት ከሌዋውያን ካህናት ሳትሆን ይህን ስለምታደርግስ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ አቤት! ሰው በኃጢአት ሲደነዝዝ ለክፋቱም ምልክትን ይሻል፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሰነፎች፡- “አታጭሱ፤ አትቃሙ፤ አትጠጡ፤ በጾም ወራት ዓሣ አትብሉ… የሚል ጥቅስ የት አለ?” እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ጌታም እዝነ ልቡናቸው ስለታወረ ለጊዜው አልገባቸውም እንጂ እንዲህ በማለት ምልክትን ይሠጣቸው ነበር፡- “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” /ቁ.19/።
 “ሁሉም ላይገባቸው (ደቀ መዛሙርቱም ጭምር) ለምን እንዲህ ማለት አስፈለገው?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስላችኋለን፡- ጌታ እንዲህ የሚያደርገው እርሱ ሁሉንም አዋቂ መሆኑን እንዲገነዘቡ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 23/፡፡ በእርግጥም ለጊዜው ግራ ቢገባቸውም (ደቀ መዛሙርቱ ተጠቅመው እነርሱ አልተጠቀሙበትም እንጂ) ከገደሉት በኋላ  ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶአቸዋል /ማቴ.26፡61፣ አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 10:251-52/፡፡
እዚህ ጋር ሌላ የምንረዳው ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም አንዳንድ መንፍቃን እንደሚሳደቡት ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ አለመሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ቃሉ እንደሚያስረዳን ነፍሱን የማኖርም የማንሣትም ሥልጣን እንዳለው “በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” እያለ በግልጽ እየነገረን ነውና /ዮሐ.10፡18፣ Hilary of Poitiers, On The Trinity 9:12/፡፡
 አሁንም እነዚህ አይሁድ ጌታ በሚናገራቸው ነገር የባሰ ግራ ተጋብተው፡- “ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታንጸዋለህን?” በማለት ይጠይቁታል /ቁ.20/። በሰሎሞን የታነጸው ቤተ መቅደስ የመጀመርያው ቤተ መቅደስ በ20 ዓመት ያለቀ ነው፡፡ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው በዘሩባቤል ዘመነ መንግሥት የተሠራው ግን አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶባቸዋል /ዕዝራ.6፡15/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ሁሉም ባይገባቸውም ጌታ ማኅደር ስለሚባል ሰውነቱ እንጂ ስለዚያ ቤተ መቅደስ እየተናገረ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው እንኳን ወንጌሉን ጌታ ከተነሣ በኋላ ስለሚጽፈው የክርስቶስ ንግግር ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዳ፡- “እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” የሚለው /ቁ.21/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ጌታ ስለ ሰውነቱ እየተናገረ መሆኑን ለምን በግልጽ አልተናገረም?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም “ለጊዜው የሚነግራቸውን በቀላሉ ላይቀበሉት ስለሚችሉ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ተደናገሩት ለዚሁ ነው” ብለን እንመልስለታለን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/።
ስለዚህ ጌታ “ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ያላቸው ማኅደር ስለሚባለው ሰውነቱ እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ማለትም ይነሣል ብለው የተናገሩትን ነብያትንና ኢየሱስ ራሱ አነሣዋለሁ ብሎ የተናገረውን ቃል አመኑ” /ቁ.22/። አዎ! አስቀድመን እንዳልነው፡- “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱትና አባቴ ያነሣዋል” ሳይሆን “እኔ አነሣዋለሁ” እንዳላቸው አሰቡ፡፡ አባቱ አስነሣው ቢባልም የሚጣላ ነገር አይደለም፡፡ እርሱና አብ አንድ ናቸውና፡፡ ስለዚህ እንደተናገረው ተነሣ፤ እነርሱም አመኑበት፤ ሕይወትም ሆናቸው /ሮሜ.1፡4፣ቅ.አምብሮስ Tractes on the Gospel of John 10:11/፡፡
ወንጌላዊው ይቀጥልና፡- “ኢየሱስ በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ” ይለናል /ቁ.23/፡፡ “የትኛውን ምልክት?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ በቤተመቅደስ የነበሩትን ሻጮች ማስወጣቱን እንደ ምልክት አይቶት ሳይሆን ሌላ ያደረጋቸው ነገር ግን በዚሁ መጽሐፍ ያልተጻፉ ተአምራት እንዳደረገ ያስገነዝበናል /አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 10:319/፡፡
“ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር” /ቁ.24/። “ለምን?” ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡ ጌታ እነዚህን ሰዎች ያልተማመነባቸው ከልባቸው አምነውበት ሳይሆን ባሳያቸው ተአምራት ለጊዜው በስሜት ተነድተው “አምነናል” እንዳሉ ያውቃልና፤ ልባቸው ብዙ አፈር የሌለበት ጥልቅ መሬትም እንደሌለው ጭንጫ እንደሆነ ያውቃልና /ማቴ.13፡5/፡፡
 አዎ! እርሱ ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡ “እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ” የሚያውቅ አምላክ ነው /ቁ.25፣ መዝ.32፡15/፤ ጠቢቡ እንዳለው “እርሱ ብቻ የሰውን ልብ ሐሳብ ያውቃል” /1ነገ.8፡39/፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሰዎች፣ በፍጥረታቱ ልብ የሚመላሰውንና የሚታሰበው ምን እንደሆነ ለማወቅ ሌላ ምስክር አይፈልግም፤ ራሱ ፈጣሪ ነውና ይህንን ለማወቅ አባቱን መለመን አያስፈልገውም /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ወንድሞቼ! ዛሬም “ክርስቶስ አምላክ አይደለም” የሚሉ ብዙ ልበ ስሑታን አሉና ይህን እውነት ልንመሰክርላቸው ያስፈልጋል፡፡ “የጾመው እሴተ ጾምን (የጾምን ዋጋ) የሚሰጥ ነው… የጸለየው ምልጃን የሚሰማ ነው… የተራበው የተራቡትን በቸርነቱ የሚያጠግብ ነው… የተጠማው የሕይወትን ውኃ የሚያድል ነው… የደከመው እርሱ ራሱ ሰንበት ነው… ያለቀሰው እርሱ ራሱ ያዘኑትንን ዕምባ የሚያብስ ነው…፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው ግን እኛንም እናተንም ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ እርሱ ዝቅ ዝቅ አድርገን ልናየው የሚገባው ጌታ ሳይሆን ለእኛ ብሎ ደሀ የሆነ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለምም አባት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን ለማመን አትቸገሩ” ብለን እንመስክርላቸው፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ በቸርነቱም መንግሥቱ እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡

የዮሐንስ ወንጌል የአሥራ ሁለተኛው ሳምንት ጥናት!!

“ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” /ቁ.12/፡፡ በዚያ የነበሩት ሰዎች ወንጌለ መንግሥት መስማት ነበረባቸውና፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው “ወንድሞቹ” እያላቸው ያሉት የማን ልጆች ናቸው? እንዲህ ተብለው እየተገለጹ ያሉት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ዝምድና ያላቸው ናቸው እንጂ የእርሷ ልጆች አይደሉም፡፡ ይኸውም አብርሃም ለሎጥ /ዘፍ.13፡8/፣ ላባ ለያዕቆብ /ዘፍ.29፡15/ ወንድሜ እንደተባባሉት ዓይነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ወንደሞቼ እያለ ይጠራቸው እንደነበር ተገልጧል /ማቴ.14፡46-50፣ Augustine, On the Gospel of St. John, Tracte 10:2-3/፡፡ አንድም ዮሴፍ ከሚስቱ የወለዳቸውና ከጌታ ጋር አብረው ያደጉ ናቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
 “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ” /ቁ.13/፡፡ ይህ ፋሲካ ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ የተደረገ የመጀመረያው ፋሲካ ነው፡፡ ሁለተኛው በሉቃ.6፡1፣ ሦስተኛው በዮሐ.6፡4፣ የመጨረሻው ደግሞ በዮሐ.11፡55 ተገልጸዋል፡፡  የሚገርመው ነገር ከዚህ በፊት ይህ ፋሲካ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” ተብሎ ይጠራ ነበር /ዘጸ.12፡11/፡፡ አሁን ግን አይሁዳውያኑ የራሳቸው የሆነ ሰው ሠራሽ ወግና ልማድ ስለጨመሩበት ያ የድሮ ስሙ ተለውጦ “የአይሁድ ፋሲካ” ተብሎ እናየዋለን፡፡ በነብዩ እንዲህ እንደተባለ፡- “በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች” /ኢሳ.1፡14፣ Origen Commentary on the Gospel of John, Book 10:80-81/፡፡
“በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ” /ቁ.14/፡፡ እነዚህ ሻጮች እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ ቤተ መቅደሱን የንግድ ቦታ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ልብ ከእግዚአብሔረ ጋር ሳይሆን ከሚሸጡት ንብረትና ከሚያገብስብሱት ገንዘብ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጌታ ለመገዛት ሳይሆን እርሱን ለመሸጥ የሚሰበሰቡ ናቸው፡፡ ለእነሱስ በዚያ በሚሠዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ቢገዙ ይሻላቸው ነበር /አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 “ጌታችንም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ” /ቁ.15/፡፡ አስቀድመን እንደገለጥነው የእነዚህ አይሁዳውያን መሥዋዕት፣ በዓላት፣ ምናምቴን ጨምረው የሚያመጡት ቁርባን ደስ ስላላሰኘው ገለባብጦባቸዋል /ኢሳ.1፡11-15/፡፡ አንድ ነገር ግን ልብ በሉ! ጌታችን የገበያ ቦታውን ብቻ አልገለባበጠም፤ ይልቁንም መሥዋዕተ ኦሪቱም ጭምር እንጂ /Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 1.2:13-18/፡፡
“ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው” /ቁ.16/፡፡ ጌታችን ይህንን ሁሉ ሲያደርግ “የአባታችንን ቤት” ሳይሆን “የአባቴን ቤት” ሲል እንመለከተዋለን፡፡ ይኸውም አንዳንዶች እንደሚያናፍሱት የምንፍቅና ወሬ ሳይሆን እርሱ ዕሩይ ምስለ አብ በመለኰቱ (ከአባቱ ጋር የተካከለ መሆኑን) ያሳያል፡፡ “የአባቴን ቤት” የሚለውም አይሁድ አስቀድመው እግዚአብሔርን በአንድነቱ ብቻ ስለሚያውቁት ነው፡፡ አሁን ግን በባሕረ ዮርዳኖስ ግልጽ እንደሆነ በአንድነት በሦስትነት የሚመለክበት ቅዱስ ስፍራ ነው /ሉቃ.2፡49 St. Cyril of Jerusalem, Article 7:6/፡፡
 “ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ በመዝሙር 68፡10 ላይ እንደ ተጻፈ አሰቡ” /ቁ.17/።
ይህች ቅናት ጌታን እስከ መስቀል ድረስ ያደረሰች ቅናት ነች፡፡ ይህች ቅናት እርሱ ተዋርዶ እኛ የከበርንባት ቅናት ናት፡፡ ይህች ቅናት እርሱ ደሀ ሆኖ እኛ ባለጸጋ የሆንንባት ቅናት ናት፡፡ ወንድሞቼ! ዛሬ ይህች ቅናት ሁላችንም ልትበላን ያስፈልጋል! አኅቶቼ! ይህች ቅናት የአይሁድ ቅናት የመሰለች ክፉ ቅናት አይደለችም፡፡ ይህች ቅናት በውስጧ ተንኰል ያልተቀላቀለባት በንጹሕ ፍቅር የምትደረግ ቅናት ናት፡፡ ይህች ቅናት ዛሬ በተለይ አብዝታ ታስፈልገናለች፡፡ ፍቅር በቀዘቀዘበት ዘመን ይህች  ቅናት በቤታችን ታስፈልገናለች፤ መናፍቃን በበዙበት ዘመን ይህች ቅናት በቤተ ክርስቲያናችን ታስፈልገናለች፡፡
 ጌታ ዛሬም ይህች ቅናት ትበላዋለች፡፡ አማናዊው ቤተመቅደስ (ሰውነታችን) የነጋዴ ቤት፣ የክፋት ቤት፣ የሌቦች ቤት ሲሆን ጌታ ይህች ቅናት ትበላዋለች፡፡ ንጹሕ መሆን ሲገባን በተለያዩ ነገሮች ስንረክስ ዛሬም ያዝናል፡፡ ወደ ቤቱ እንመለስ፡፡ እግዚአብሔር ዛሬ በጅራፍ ሳይሆን በፍቅር ይጠራናል፡፡ እስክንከፍትለት ድረስም በበር ቆሟል፡፡ ወንድሞች እግዚአብሔርን “ማራናታ” እንበለው፡፡ ከዚያም ፈቃዳችንን ተመልክቶ እንዴት እንደሚያጠራን ራሱ ያውቅበታል፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ እኛን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!!

Sunday, May 20, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የአሥራ አንደኛው ሳምንት ጥናት!!!


  (ከቻሉ በጸሎት ጀምረው በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት!)
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታችን ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ አሁን ግን እንዲህ የሚላት ምንም እንኳን ልጇ ወዳጇ ቢሆንም በአምላክነቱ ሰው የሚያዘው አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀን የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 22/፡፡ እመቤታችንም ይህንን ስለምታውቅ፡- “ልጄ ወዳጄ! አንተ ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ እንደሆንክ አውቃለሁ፤ ሁሉም በጊዜው ውብ አድርገህ የምትሠራ ኤልሻዳይ መሆንህንም አላጣውም፡፡ ልጄ ወዳጄ! አሁን የምለምንህ ወገኖቼን ከሐፍረት እንድትታደጋቸው እንጂ በአምላክነትህ ለማዘዝ አይደለም፤ ከባቴ አበሳ አምላክ መሆንህን አሳምሬ አውቃለሁና፡፡ ልጄ ሆይ! ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆነህ የመጣህ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እንደሆንክማ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ ቃል አውቃለሁ፤ በሕግ በአምልኮ ለሚቀርቡህ ግን ሰማዔ ጸሎት ነህና እባክህን ራራላቸው” ብላ በአራኅርኆ ማለደችው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም፡- “እናቴ ሆይ! አንቺ ሴት የምልሽ ኃይለ አርያማዊት እንዳልሆንሽ ለመግለጽ ነው፡፡ ይልቁንም አስቀድሞ በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ ተብሎ የተነገረልሽ የአዳም ልጅ መሆንሽን ለማስገንዘብ እንጂ ውኃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ” ብሎ መለሰላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ፡-  “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
“አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እኔህን ጋኖች ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው” /ቁ.6-7/። ወንጌላዊው “አይሁድ የማንጻት ልማድ የሚያደርጉባቸው የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ” የሚለን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ምክንያትን የሚፈልጉ ከሐድያን “ጠጁ አላለቀም ነበር፤ ቀርቶ የነበረውን አበርክቶ ሰጣቸው እንጂ” ብለው ምክንያት እንዳያገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም በኦሪቱ ሕግ መሠረት ጋኖቹ ለማንጻት የሚጠቀሙባቸው ጋኖች ከሆኑ ለመጠጥ የሚሆን ወይን ጠጅ ፈጽሞ አይቀዳባቸውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ቀጥሎም “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣ ግን አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ዶኪማስ ብሎ ጠራው። ሰው ሁሉ አስቀድሞ ሸሎውን፣ በርዳዳውን፣ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ ተራውን፣ መናኛውን ያጠጣል፡፡ አንተ ግን ሸሎውን፣ በርዳዳውን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው” /ቁ.8-10/። አንዳንድ ልበ ስሑታን “ሠርገኞቹ ሁሉም ሰክረው ስለ ነበር የወይኑን ጣዕም ሊያውቁ አይችሉም፤ ስለዚህ የጠጡት የተለወጠው መልካሙን ወይን ሳይሆን መናኛውን ነው” ብለው ለማጥላላት ይሞክራሉ፡፡ ወንጌላዊው ግን የእነዚህን ነቀፋ አስቀድሞ ስለሚያውቅ “መጀመርያ ሠርገኞቹ ሁሉ ቀመሱት” አላለንም፡፡ አስቀድሞ የቀመሰው ያልሰከረው ሊሰክርም የማይችለው አሳዳሪው ብቻ ነው፡፡ እንደውም ወንጌላዊው ትንሽ ቆየቶ፡- “ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወደ አደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ” በማለት ወይኑ በተአምራት የተለወጠ መሆኑን ነግሮናል /ምዕ.4፡46፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡  
 “ኢየሱስ በሦስት ዓመት ከሚያገርገው ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ቁ.11/። አስተውላችሁ ከሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወይን ለማድረግ ሲጸልይ ወይም ሲለምን አንመለከተውም፡፡ ይልቁንም ሠራተኞቹ ለአሳዳሪው እንዲሰጡት ነገራቸው እንጂ እስኪ ልቅመሰው እንኳን አላለም፡፡ እኛ እንደምናውቀው ተራ ወይን ሳይሆን እጅግ መልካም የሆነ ወይን እንደሰጣቸው ያውቃልና፡፡ በዚህም ጌትነቱን ገለጠ፤ ከአባቱ ጋር ያለውን መተካከል አሳየ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት፡፡
ወንድሞቼ ሆይ! ዛሬም እግዚአብሔር እንደ ውኃ ጣዕም ያጣው ሕይወታችንን ወደ መልካም ወይንነት ፍጹም ሊለውጠው ይፈልጋል፡፡ እንግዲያስ እንደ ውኃ የቀዘቀዘው፣ የደከመው ማንነታችን ወደ እርሱ እናቅርበውና ፈቃዳችንን ተመልክቶ ወደ ወይን ይቀይርልናል፡፡ ከዚያ በኋላ በቃና እንደሆነው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የደስታ ምክንያት እንሆናለን፡፡ ይህን ሁሉ እንድናደርግ እንደ ነነዌ ሰዎችም እንድንለወጥ እግዚአብሔር ይርዳን!!!

የዮሐንስ ወንጌል የ10ኛው ሳምንት ጥናት!!


“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ”/ቁ.3/፡፡ ሰርጉ የሆነው የይሁዳ ዕጣ ከምትሆን ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ነብዩ “የአሕዛብ ገሊላ” ባላት በቃና ነው /ኢሳ.9፡1/፡፡ ጌታ በዚያ መገኘቱ የአይሁድ ምኵራብ አማናዊውን ሙሽራ እንዳልተቀበለችው የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ግን በደስታ እንደተቀበለችው ያሳያል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ Commentary on the Gospel of John 2:1/፡፡ ይህም የሆነው ከተጠመቀ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ የመጀመርያው ቀን እንድርያስና ዮሐንስን የጠራበት ቀን ሲሆን ሁለተኛው ቀን ደግሞ ፊሊጶስና ናትናኤልን የጠራበት ቀን ነው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:2:1/፡፡ አንድም ጌታ የጾመው 40 ቀንና 40 ሌሊት እንደ አንድ ቀን ተቆጥሮ ነው፡፡
“እመቤታችንም ቤተ ዘመድ ናትና በዚያ ነበረች፡፡ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ” /ቁ.2/፡፡ “ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን እንግዲህ ሰው አይለየው” እንደ ተባለ ፈጣሪ በፍጥረት መጀመርያ በአዳምና በሔዋን የመሠረተውን የጥንቱን ሥርዓተ ጋብቻ በአዲሱ የምሕረት ኪዳን በኪዳነ መንፈስ ቅዱስም መጽናቱንና መቀደሱን ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው አንዴ ብቻ በተገኘበት በዚሁ ሠርግ አረጋግጦልናል /ቅዱስ ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ ክብር ይልቅ ስለ ሰዎች መልካምነት የሚገደው ነውና በዚያ ተገኘ፡፡ የባርያዎቹን መልክ ለመያዝ እንኳን ያላፈረ ጌታ በባሮቹ ሠርግ መገኘት አላሳፈረውም፤ እንኳንስ ከዚህ ቅዱስ ጋብቻ “ከኃጢአተኞች” ጋር እንኳን ሳያፍር ለመመገብ ተቀምጧል /ፊል.2፡7፣ማቴ.9፡13 ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 20፡1/፡፡
 ከዚያ በኋላ የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ እመቤታችንም “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” /ቁ.3/፡፡ ይህንንም ያደረገችው ልጇ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ስለምታውቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያች ቀን በፊት ሁሉንም በልቧ ትጠብቀው ነበር እንጂ “የአምላክ እናት ነኝ፤ እርሱም አምላክ ነው” እያለች ራሷን ከፍ ከፍ አታደርግም ነበር፡፡ በዚሁ ሰዓት ግን የሆነው ነገር አሳፋሪ ነውና ሁልንም ለሚችል ልጇ በቀስታ አናገረችው፡፡ ከራሷ ፍላጎት ይልቅ ስለ ምእመናን የምትጨነቅ እናት መሆኗንም ያመለክታል፡፡ ልመናዋም “ሊያደርግ ይችል ይሆናል” በሚልና ጥርጣሬ በተሞላበት አኳኋን ሳይሆን በእርግጠኝነት እንደሚያደርግላት በማመን ነበር፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱን ልብ ይፈልጋል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ/፡፡
ሌለው የምረዳው ነገር ደግሞ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ራሱን ለሕዝቡ መግለጥ ስለ ነበረበት ይህ ተአምር የአስተርእዮ አካልም እንደ ነበር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የተገለጠው የእርሱ አምላክነት ብቻ ሳይሆን የእናቱ እመ አምላክነትንም ጭምር ነበር፡፡
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታ ኢየሱስ ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ እዚህ ቦታ ግን ለእመቤታችን እንዲህ የሚላት በአምላክነቱ አገብሮ ተአዝዞ እንደሌለበት ለማጠየቅ ነው፤ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀትር የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና፡፡ ይህ ቢሆንም ግን “እመቤታችን ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ትላቸዋለች” /ቁ.5/፡፡ ልጇ ምን ያህል እንደሚያከብራት ደግሞም የጠየቀችውን እንደሚያደርግላት ታውቃለችና /ቅ.ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ይቆየን!!

የዮሐንስ ወንጌል የ9ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.1፡44-ፍጻሜ)!!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምለካ አሜን!!
“በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና ተከተለኝ አለው” /ቁ.44/፡፡
 ጌታ በወርቃማው ስብከቱ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “የሚፈልግ እርሱ ያገኛል” /ማቴ.7፡8/፡፡ እውነት ነው! ፊልጶስ የተዘጋጀና እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ስለ ነበረው እነ እንድርያስ ከመጥምቁ እንደተማሩት ከማንም ሳይማር ጌታ “ተከተለኝ” ስላለው ብቻ ተከትሎታል፡፡ ቀጥለን እንደምንመለከተውም ሲያነበው የነበረው ትንቢት ሲፈጸምለት ስላየ በጣምኑ ተደስቷል፡፡ በእርግጥም ጌታ ይህንኑ ልቡን አይቶ ተከተለኝ ብሎታል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily on John 20፡1/፡፡
ይህ ፊልጶስ አስቀድመው ዮሐንስ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” ሲል ሰምተው ከተከተሉተ ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ (የዓሣ ከተማ) ነበረ /ቁ.45/። ፊሊጶስ እንደ ናትናኤል ባይሆንም ከነብያትና ከሙሴ መጻሕፍት በትንሽ በትንሹ ያነብ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በኦሪት የጻፈለትን ነቢያትም ስለ እርሱ ትንቢት የተናገሩለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል” የሚለው፡፡ እዚህ ጋር ናትናኤልም የሕግና የነብያትን መጻሕፍት ያውቅ እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ናትናኤል ግን መልሶ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” ብሎታል /ቁ.47/፡፡ ለምን እንዲህ አለው? ስንልም ገሊላ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖር ማኅበረሰብ የሚኖርባት፣ ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ብዙም ግድ የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አከባቢ እንደሆነች እንመለከታለን፡፡ ስለዚህም በሌሎቹ የአይሁድ ሕዝብ ዘንድ የተናቁ ነበሩ፡፡ አይሁድ ለኒቆዲሞስ “ነብይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ” ማለታቸውም ይህንኑ ሐሳብ ያጠናክራል /ዮሐ.7፡52/፡፡ ፊልጶስ ናትናኤል ከሚለው ሐሳብ ተቃራኒ የሆነ ነገር ተደርጐ ስላየና ተከራክሮ ማስረዳት ባይቻለው “የእኔ ንግግር ካላሳመነህ ጌታ ራሱ ያሳምንህ ዘንድ መጥተህ እይና ተረዳ” አለው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:1:46/።
 ናትናኤልም አሁን የፊሊጶስን ንግግር ለማረጋገጥ መጣ፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፡- ክዳት ተንኰል የሌለበት በእውነት እስራኤላዊ እነሆ አለ” /ቁ.48/፡፡ የሚገርም ነው! ናትናኤል “ከገሊላ መልካም ነገር ይወጣልን?” በማለቱ እንደሰው አስተሳሰብ መወቀስ ሲገባው ተመሰገነ፤ በውዳሴ ከንቱ ሳይሆን በአውነት በጌታ አንደበት ተወደሰ፡፡ እንዴትስ አልተወቀሰም ስንልም የናትናኤል ንግግር ከተንኰል የመነጨ ሳይሆን የፊሊጶስ ንግግር ከነብያቱ ትንቢት ጋር የተጋጨ መስሎት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ናትናኤል ከመጻሕፍት ሲያነብ ያገኘውና የተረዳው ክርስቶስ ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም እንጂ ከናዝሬት እንደማይመጣ ነውና /ሚክ.5፡2/፡፡ ስለዚህ ናትናኤል እንደዚያ ማለቱና ክርስቶስም “ተንኰል የሌለበት ማለቱ” ትክክል ነበር፡፡ መጻሕፍትን አንዳንዶች እንደሚያደርጉት በራሱ ፈቃድ ለመተርጐም አለመሞከሩ ደግሞ የበለጠ ቅንነቱን ያሳያል /ቅ.ኤፍሬም ሶርያዊ Commentary on Tatian’s Diatessaron 4:14/፡፡
 የናትናኤል ቅንነት የበለጠ ግልጽ የሚሆነው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጌታ “ተንኰል የሌለበት” ሲለው “ከወዴት ታውቀኛለህ?” ማለቱም ጭምር እንጂ። “ኢየሱስም መልሶ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው” በማለት የበለጠ ያምን ዘንድ የነበረበትን ቦታ ብቻ ሳይሆን ጊዜውም ጭምር ነገረው /ቁ.49፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ በምሥጢራዊ አነጋገር ግን “አባትህ አዳምና እናትህ ሔዋን በወደቁበት ዕጸ በለስ ስር ወድቀህ በኃጢአት ተጐሳቁለህ ሳለህ በመለኰታዊ ባሕርዬ አውቃሃለሁ፤ አይቻሃለሁ” ማለቱ ነበር /ቅ.አምብሮስ/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ ከዚሁ የበለስ ግልድም አላቅቆ ጸጋውን ያለብሰን ዘንድ እኛን የጠፋነውን ለመፈለግ መጥቷል /አውግስጢኖስ/፡፡
 ከዚህ በኋላ ክርስቶስ የልቡን ስለነገረው ምንም ሳይጠራጠር እምነት ጨመረና “መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ፡፡ በዚህ ሰዓት ፊልጶስ እንደነገረው ከማመን፣ ከመረዳት፣ ከመደነቅ፤ በሐሴት ከሞመላትና ለክርስቶስ እጅ ከመስጠት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረውም /ቁ.50/፡፡ “ኢየሱስም መልሶ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? በል በዚህ ብቻ አትደነቅ! ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ /ቁ.51/። እኔ ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) ስላይደለሁ ገና ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት እኔን ለማገልገል ሲወጡና ሲወርዱ ታያለህ” በማለት አባቱ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያየውን ራዕይ መፈጸሙን ይነግረው ነበር /ቁ.52/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ እንደተናገረው ናትናኤል መላእክት ክርስቶስ ፈታኙን ድል ሲያደርግ /ማቴ.4፡11/፤ ሲሰቀል፣ ከሙታን ተለይቶ ሲነሣ፣ ሲያርግ መላእክት ሲያገለግሉት አይቷል፡፡ ናትናኤል ባያይም ይህ ክስተት በቤተልሔም ግርግምም “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰበእ ሃሌ ሉያ” ሲሉ ተመልክተናል፡፡
አስተውላችሁ ከሆነ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ከነገረው በኋላ ናትናኤል አንዲትም ቃል መልሶ አልተነፈሰም /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ላላመኑት እንደ ናትናኤል “ረቢ አማን አንተ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር- መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚል ቀና ልብ ይስጥልን፤ እኛንም በተዋሕዶ ያጽናን አሜን!!!!!!

Saturday, May 19, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የ8ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.1፡35-42)!!

“በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስን ሲሄድ አይቶት፡- እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ።” /ቁ.35-36/
 የሰው ልጅ በባሕርይው ሐዋርያው፡- “ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ አይታክተኝም፤ እናንተን ያበረታችኋልና” እንዳለው ተደጋግሞ ካልተነገረው በቀር ተሎ አይገባውም /ፊል.3፡1/፡፡ ለዚህም ነው መጥምቁ ከዚህ በፊት የተናገረውን ቃል መልሶ የሚነግራቸው፡፡ ሲነግራቸውም መንደሩ እየዞረ ሳይሆን ሁሉም ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ እንዲመጡ በማድረግ ነበረ፡፡ “ለምን እንዲህ አደረገ?” ብለን ስንጠይቅም አንደኛ ሌሎች እርሱን የሚመስሉ ሐሰተኞች ዮሐንሶች በተነሡ ነበር፤ ሁለተኛ ሕዝቡ ሁሉም በተሰበሰበበት ሁኔታ “እነሆ የነገርኳችሁ በግ” ቢላቸው የበለጠ ታማኝነትን ያገኛል፤ ሦስተኛ ምስክነቱ እውነት እንደሆነ (ከዝምድናው የተነሣ እንዳልሆነ) አብም መንፈስ ቅዱስም ሲያረጋግጡት ሕዝቡ የበለጠ ያምናል፤ አራተኛ አይሁድ ክርስቶስ ሕግ አፍራሽ ነው ብለው ላለማመናቸው ምክንያት እንዲያጡ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ነበረበት፡፡ ነብያትን መታዘዝ ጽድቅ ነውና፡፡ ስለዚህ ሚዜው ሙሽራይቱን ከሙሽራው ጋር ለማገናኘት አሁንም ከወንዙ ዳር ቆሞ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ በግ” እያለ ይጮኽ ነበር /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐ. ወንጌል ትርጓሜ ድርሳን 18፣ ድርሳን በእንተ ጥምቀት/፡፡
  ከዚህ በኋላ ሁሉም ሳይሆኑ “ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ዮሐንስ ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።” /ቁ.37/ እውነት ነው! ፀሐይ ከወጣች በኋላስ የሻማ ጥቅሙ ምንድነው? የዮሐንስ ጥምቀትስ የክርስቶስ ጥምቀት ከመጣች በኋላ ምን ረብሕ አላት? /ቅ.ኤፍሬም ሶርያዊ Commentary on Tatians Diatessaron 4:17/፡፡
ክርስቶስም ሲከተሉት አይቶ በልባቸው ምን እንደሚፈልጉ ስለማያውቅ ሳይሆን ፈቃደኝነታቸውን ለመጠየቅ “ምን ትሻላችሁ?” አላቸው /ቁ.38/፡፡   እነርሱም “ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?”  በማለት የሚፈልጉት እንዲያስተምራቸው እንደሆነና ወዴት እንደሚኖር በግልጽ ነገሩት፡፡ እርሱም “መጥታችሁ እዩ” አላቸው። መጥተውም ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች ማረፍያ ጐጆ እንዳላቸው ክርስቶስ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት እንደ ሌለው አዩ፤ በዚያም ቀን እስከ አሥር ሰዓት ድረስ በእርሱ ዘንድ ሲማሩ ዋሉ /ቁ.39፣ ሉቃ.9፡58/፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ሆነው ሄደውም እስራኤል ዘነፍስ ተባሉ /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:1:38/፡፡
 “ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ” /ቁ.40/፡፡ ምንም እንኳን ስሙ የተጠቀሰው እንድርያስ ብቻ ቢሆንም ሁለተኛው ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ራሱ ነበር፡፡ “እንዴት ይታወቃል?” ቢሉ ወንጌሉን ሲጽፍ የተለያየ ቦታ ስለ እርሱ የሚነገሩትን “ጌታ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር” ይላል እንጂ በሙሉ ስለ ትሕትና ብሎ ስሙን አይጠቅስምና /ዮሐ.19፡26፣ ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ ዝኒ ከማሁ/፡፡
“እንድርያስም አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና፡- መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው። ወደ ኢየሱስም አመጣው” /ቁ.41/፡፡ የሚገርም ነበር! ሰብአ ሰገል “የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” ብለው ጠይቀው ለራሳቸው አግኝተውት ስለሄዱ አሁን እንድርያስ ሲያገኘው በጣም ነበር የተደሰተው፡፡ ምክንያቱም መጥምቁ የሚጠበቀው መሲሕ እርሱ መሆኑን ነግሮዋቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስ ሲመሰክር አይተዋል፡፡ ክርስቶስም እርሱ ማን እንደሆነ ነግሮታል፡፡ እንድርያስ ያልተማሩና የተናቁ የገሊላ ሰዎች በመሆናቸው መሲሑን ሲያገኘው በጣም ተደስቷል፡፡ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን ወጣለት” የሚለው የነብዩ ቃል ሲፈጸምለት በዓይኑ አይቷል /ኢሳ.9፡1/፤ “ምናምንቴዎችን መረጠ” የሚለው ቃል ሲፈጸምለት የማይደሰትስ ማን ነው? /1ቆሮ.1፡27፣ ኤፍሬም ሶርያዊ ዝኒ ከማሁ/፡፡ የሚደንቀው ደግሞ እንድርያስ እዚያ ተቀምጦ አልቀረም፤ ወንድሙን ይጠራ ዘንድ ተፋጠነ እንጂ፡፡ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ተምሮና አምኖ “መሲሕን አግኝተናል” እያለ ወንድሙን ለመስበክ ተቻኮለ፡፡ በጣም በጉጉት ሲጠብቀው እንደነበረም ያመለክታል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 19/፡፡
 “ኢየሱስም ስምዖንን ተመልክቶ። አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ፤ አንተ ኬፋ ትባላለህ አለው፤ ትርጓሜው ጴጥሮስ ማለት ነው” /ቁ.42/፡፡ ጴጥሮስ ለመጀመርያ ጊዜ ስሙ የሚቀየረው በዚሁ ሰዓት ነው፡፡ ጴጥሮስ ማለት ዐለት ማለት ነው፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን መሠረት ጽኑ እና የማይነዋወጥ መሆኑን ያመለክታል /ማቴ.7፡24፣ ማቴ.16፡18፣ አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ 7፡14/፡፡
 “ክርስቶስ ለአንዳንዶቹ ሐዋርያት ስማቸውን የሚቀይርላቸው ለምንድነው?” ብለን ስንጠይቅም በብሉይ ኪዳንም አብራምን አብራሃም፣ ሦራን ሣራ፣ ያዕቆብን እስራኤል ያለ አምላክ እርሱ እንደሆነ እንገነዘብ ዘንድ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ሳንወደው ለወደደን ከዲያብሎስ መንጋጋ አላቅቆም ወዳጆቹን ላደረገን ለእግዚአብሔር ዛሬም ዘወትርም ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን!!

የእግዚአብሔር በግ (የዮሐንስ ወንጌል የ7ኛው ሳምንት ጥናት)!!

“በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” ዮሐ.1፡29
 የሚገርም ምስክርነት ነው፡፡ ጌታስ “በሰው ፊት የሚያምንብኝን ሁሉ እኔም በእግዚአብሔር መላእክት ፊት አምነዋለሁ” አይደል ያለው /ሉቃ.12፡8/፡፡ መጥምቁ ምስክርነቱን ለአይሁድ ሁሉ ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያአትት ወያሴስል ኃጢአተ ዓለም- የሰውን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር መሥዋዕቱ እነሆ!” ይላቸው ነበር /John Chrysostom, Homily on the Gospel of John, 17/፡፡ አዎ! ዮሐንስ ከእንግዲህ ወዲህ ዝግጅቱን ጨርሷል፡፡ ያ ለስድስት ወራት ሲያዘጋጀው የነበረና ለዓለም ሁሉ የሚሠዋው ንጹሑ በግ መጥቷልና /2ቆሮ.5፡14፣ ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ Commentary on the Gospel of John 2:1/፡፡ ይህ ንጹሕ በግ እንደ ብሉይ ኪዳኑ ዓይነት በግ አይደለም፤ ይህ በግ ነብዩ “እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ በግ ጠቦት ሆንሁ” ያለው ነው /ኤር.11፡29፣ አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 6/፡፡ ይህ በግ ኢሳይያስ “በሸላቾቹ ፊት ዝም አለ” ያለለት በግ ነው /ኢሳ.53፡7፣ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ Proof of the Gospels 1:10/፡፡ ይህ በግ በዕጸ ሳቤቅ (በእመቤታችን) ተይዞ የተገኘውና በይስሐቅ ፈንታ የተሠዋው በግ ነው /ዘፍ.22፡13፣ አውግስጢኖስ Sermon 19:3/፡፡ ይህ በግ በምድረ ግብጽ ሞተ በኩር በመጣ ጊዜ በእስራኤላውያን በኩራት ፈንታ የተሠዋው በግ ነው /ዘጸ.12፡21-30/፤ ይህ በግ አቤል ለእግዚአብሔር ያቀረበው ንጹሑ በግ ነው /ዘፍ.4፡4፣ አምብሮስ/፡፡
 መጥምቁ በዚያ ለነበሩ አይሁድ ይህን ሁሉ የሚመሰክርላቸው በመጻሕፍቶቻቸው የተነገረውን ትንቢት ሁሉ መፈጸሙን አውቀው በክርስቶስ እንዲያምኑ ነው /ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 የሚደንቅ ነው! ይስሐቅ ከርብቃ ጋር /ዘፍ.24/፣ ያዕቆብ ከራሄል ጋር /ዘፍ.29/፣ ሙሴም ከሲፓራ ጋር ለመጋባት በውኃ ጉድጓድ እንደተገናኙ ሁሉ /ዘጸ.2፡15-21/ ክርስቶስም ከሙሽራው ከቤተ ክርስቲያን ጋር በዮርዳኖስ ወንዝ ተጋብቷል /ኤፌ.5፡32፣ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ Commentary on Tatians Diatessaron 3:17/፡፡
 መጥምቁ ምስክርነቱን ይቀጥልና “አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።” ይላቸዋል /ቁ.30/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “የዓለምን ኃጢአት ያስወግዳል ያልኳችሁ በግ፣ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል ያልኳችሁ ሰው እርሱ ነው፡፡ እርሱ አወጣጡ ከዘላለም የሆነ አምላክ ነው፤ እኔ ግን አይደለሁም፡፡” አሁንም ይቀጥልና “እኔም አላውቀውም ነበር” ይላል/ቁ.31/፡፡ “ታድያ ካለወቅከው እንዴት ትመሰክራለህ? ካላችሁኝም ‘አላውቀውም ነበር’ አልኳችሁ እንጂ ‘አላውቀውም’ አላልኩም ብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ ‘አወጣጡ ከዘላለም ከሆነ ታድያ አሁን ካንተ ዘንድ ለመጠመቅ ምን አተጋው?’ ካላችሁኝም እንዲህ እላችኋለሁ ‘ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ’ ብዬ እመሰክራችኋለሁ፡፡ እርሱስ እንደ እኔና እንደናንተ ጥምቀት የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ‘ቅድም አላውቀውም ነበር ብለኸን ነበር፡፡ አሁን እንዴት አወቅከው?’ ካላችሁኝ ‘መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፡- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ’ እላችኋለሁ” /ቁ.32-33/፡፡  መጥምቁ እየደጋገመ “አላውቀውም ነበር” የሚለን ስለ ክርስቶስ የሚሰብከው ሁሉ “ተዛምዶተ ሥጋ ኑሮት ነው፤ ማማለጃ ተቀብሎ ነው፤ አብሮ አደግ ሁኖ ነው” ብሎ ማንም እንዳያስብ ነው፡፡ በበረሀ የማደጉ አንዱ ምሥጢርም ይኸው ነበር /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 የመንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረድ ሌላ የሚያስገነዝበን ምሥጢር አለው፡፡ ይኸውም እንዲህ ነው፡- መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ሰው በእግዚአብሔር መልክ እና ምሳሌ  ተፈጥሯል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከአፈር ካበጃጀው በኋላ እፍ ሲልበት መልኩን ሥሎበታል፡፡ ሲበድል ግን ይህ መልኩ ተበላሽቷል፤ የጸጋ ልብሱ ቆሽሾአል፡፡ የተሰጠው መንፈስ ቅዱስ እየራቀው ሄደ፡፡ ፈጣሪውንም እየረሳ ሄደ፡፡ መፍቀሬ ሰብእ እግዚአብሔር ግን የተበተነውን መንጋ መሰብሰብ ወደደ፡፡ የሰው ልጅ በመጀመርያው አዳም ያጣውን ጽድቅም በሁለተኛው አዳም መታዘዝ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብእ አደረገው /2ቆሮ.5፡21/፡፡ መንፈስን የሚያድል ክርስቶስም ከእኛ ርቆ የነበረውን ቅዱስ መንፈስ በእኛ ተገብቶ ተቀበለው፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት የራቀው መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ንጽሕና ወደ እኛ ተመለሰ /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ፣ ዝኒ ከማሁ/፡፡ በኖኅ ጊዜ እንደተደረገውም ያ መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም ሲያውጅ ተመልክተናል /ቅ.ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም፣ Catechetical Lecture 17:9/፡፡
 ከእናንተ መካከል “አይሁድ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ሲወርድ እየተመለከቱ እንዴት በክርስቶስ አላመኑም?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስለታለሁ፡- “ነገረ እግዚአብሔር በዓይነ ሥጋ ብቻ በማየት አይገባም፤ ይልቁንም በዓይነ ልቡና አይቶ ማስተዋልን ይጠይቃል እንጂ” /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
መጥምቁ ንግግሩን እንዲህ ብሎ ይጨርሳል፡- “እኔም አይቻለሁ-  ከመ ዝንቱ ውእቱ ወልዱ ለእግዚአብሔር- እርሱ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ” /ቁ.34/፡፡
እውነት ነው!! ሁላችንም ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እንደሆነ፤ በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን አምላክ እንደሆነ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዳለው፤ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ እንደሆነች ልንመሰክር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁሉ በአፍም በመጣፍም እንዲሁም በምግባር እንገልጠው ዘንድ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!

የዮሐንስ መጥምቅ ምስክርነት (የዮሐንስ ወንጌል የስድስተኛው ሳምንት ጥናት)!!

“አይሁድም አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው” /ቁ.19/፡፡  ቅናት ክፉ ነገር ነው፡፡ ክፋትነቱም ለአድራጊው እንጂ ለሚደረግበት ሰው አይደለም፡፡ ሐዋርያውስ፡-“ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?” አይደል ያለው /1ቆሮ.6፡7/? ወንጌላዊው እነዚህ አይሁድ ከየት እንደመጡ የሚነግረን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከዋናው ቤተ መቅደስ የመጡ እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ለመናገር እንጂ፡፡ ዮሐንስ ማን መሆኑን እማ “ይህ ሕጻን ምን ይሆን” እያሉ ሲደነቁ ነበርና /ሉቃ.1፡66፣ St. John Chrysostom homily on the Gospel of John, homily 16/፡፡ ተራው ሕዝብ ግን መጥምቁ በሚናገረው ሁሉ በጣም ስለሚማረኩ በቀላሉ የሚለውን ሁሉ ያምኑት ነበር፡፡ ስለዚህም ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ዕድል ነበረው፤ “አዎ መሲሑ ነኝ” ቢላቸው እንኳን ባላንገራገሩ ነበር፤ አላደረገውም እንጂ /Augustin sermon 289:4/፡፡ ካህናቱና ሌዋውያኑ ግን አይቀበሉትም፡፡ በእውነትም የእፉኝት ልጆች ናቸው፡፡ ወደ ወንዙ እየመጡ ሲጠመቁ የነበሩ ሰዎች አሁን ከሕዝቡ የሚቀበሉትን ከበሬታ ስለቀነሰባቸው “ማን ነህ” ይሉት ጀመር፡፡ ብጹዕ ዮሐንስ ግን ተራው ሕዝብ “መሲሑ ሊሆን ይችላል” የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤአቸው ለማቅናት ሳይክድ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ይላቸው ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የእነዚህ ክፉ እረኞች ምክንያታዊነትም ከንቱ ለማድረግ ወንጌላዊው “ዮሐንስ መሰከረ” እያለ ሦስት ጊዜ ይነግረናል /ቁ.8፣ 15፣ 20/፡፡
 ከዚያ በኋላ ወደ ሌላ ጥያቄ ያመሩና፡- “እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ይሉታል /ቁ.20/፡፡ ምክንያቱም ከመሲሑ በመቀጠል በጉጉት የሚጠብቁት ኤልያስ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ኤልያስ የዳግም ምጽዓት አዋጅ ነጋሪ በመሆን ከዮሐንስ ጋር ቢመሳሰልም “እኔ ኤልያስ አይደለሁም” ይላቸው ነበር /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡
 ምናልባት ከእናንተ መካከል ጌታ፡- “`ኤልያስስ መጥቷል` ካለው ጋር አይጋጭምን?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል /ማቴ.17፡10/፡፡ በፍጹም! ምክንያቱም ቅዱስ ገብርኤል ይህንን ሐሳብ ግልጽ ሲያደርግልን “እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ… በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል” ብሎናል /ሉቃ.1፡17/፡፡ ይህም ማለት “ዮሐንስ በኤልያስ መንፈስ መጣ እንጂ በቁሙ ኤልያስ አይደለም” ማለት ነው፡፡ እውነት ነው! ኤልያስ የዳግም ምጽዓት አዋጅ ነጋሪ እንደሆነ ሁሉ በኤልያስ መንፈስ የመጣው ዮሐንስም ለመጀመርያው ምጽዓት አዋጅ ነጋሪ ነበርና /Gregory the Great, Forty Homelies, 4/፡፡
  አሁንም ይቀጥሉና፡- “ታድያ ኤልያስ ካልሆንክ በኦሪት ዘዳግም ሙሴ ይመጣል ያለው ነብዩ ነህን?” ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ይጠቁታል /ዘዳ.18፡15፣ Origen: commentary on the Gospel of John/፡፡ እርሱ ግን “ነብይ አይደለሁም” ሳይሆን “እናንተ የምትሉት ነብይ አይደለሁም” ይላቸው ነበር /ማቴ.11፡9፣ ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 የሚገርመው ግን እነርሱም ጥያቂያቸውን ሳይሰለቹ ይጠይቁታል እርሱም ሳይሰለች ይመልስላቸዋል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ “እንኪያስ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት” /ቁ.22/፡፡ እርሱም በሕዝቡ ልቡና ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤና በእነዚያ ያለውን ተንኰል ከንቱ ካደረገ በኋላ እነርሱ ከሚቀበሉት መጽሐፍ እየጠቀሰ፡- “እኔ በበረሀ የሚጮህ ድምጽ ነኝ፤ ከእኔ በፊት የነበረውና አሁን ሥጋ ለብሶ በመካከላችሁ የቆመው ቃል ግን የምትጠብቁት መሲሕ ነው” እያለ የነቢዩ ኢሳይያስን የትንቢት ፍጻሜ ይነግራቸው ነበር /ቁ.23፣ ኢሳ.40፡3፣ ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒ ከማሁ 6/፡፡ እንዲህ እያደረገም ልቡናቸውን የንስሐ ፍሬ አፍርቶ ለጌታ እንዲያዘጋጁ አጥብቆ ያስተምራቸው ነበር፤ ሁሉም እንዲሰሙትም ጮክ ብሎ ይናገር ነበር፤ ከእግዚአብሔር ጸጋ ተራቁታ የነበረችው ነፍስ ከአምላኳ ጋር እንድትገናኝ ያዘጋጅ ነበር /አርጌንስ ዝኒ ከማሁ 6፡100/፡፡
 “የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት” /ቁ.24/፡፡ አስቀድመን ቅናት ያልነው እንግዲህ ይኸው ነው፡፡ ምክንያቱም መጥምቁ ማንነቱን በትክክል እየነገራቸው እንኳን ይሰናከሉበት ነበርና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡ ዮሐንስ ግን የእርሱ ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ለምትመጣው ፍጽምት ጥምቀት የማዘጋጀት አገልግሎት እንደሆነች “እኔ በውኃ የንስሐ ጥምቀት አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት ልጅነትን በምታሰጥ ጥምቀትም የሚያጠምቅ በመካከላችሁ ቆሞአል” እያለ ይነግራቸው ነበር /St. Cyril of Alexandria Commentary on the Gospel of John 1:10/፡፡ በእርግጥም የዮሐንስ ጥምቀት ለንስሐ የምታዘጋጅ እንጂ መንፈስ ቅዱስን የምታሰጥ አልነበረችም /ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒከማሁ 4 /፡፡
 እነዚህ ክፉዎች ይዘውት ለመጡት ተንኰልና በሕዝቡ ልብ የነበረውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመቃወምና በጣቱ እያመለከተ፡- “እነሆ እናንተ በመለኰቱ አይታችሁት የማታውቁ አሁን ሥጋ ለብሶ በእናንተ መካከል አለ፤ እርሱ በመጀመርያ ቃል የነበረ ነው፤ አሁን ግን በምልዓት ያልተለየውን ዓለም ሥጋ ለብሶ ጎብኝቶታል፤ እርሱ ከእኔ ይበልጣል፤ እኔ ግን የጫማውን ጠፍር እንኳን መፍታት የማይገባኝ ወራዳ ነኝ፤ ዮሐንስ ይበልጣል የሚለው የተሳሳተ ግንዛብያችሁ አስወግዱና ከእኔ ይልቅ ወደ እርሱ ዘወር በሉ፤ እኔ ሚዜ ነኝ እርሱ ግን ሙሽራ ነው” እያለ ለሁሉም ይመልስላቸው ነበር /Apolinaris of Laodicea, Fragments on John 5/፡፡ በጥንት ጊዜ፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ /ሩት.4፡7/፡፡ ሙሽራይቱ (ቤተ ክርስቲያን) ያለችው ደግሞ እርሱ ክርስቶስ እንጂ ዮሐንስ አይደለም፡፡ ስለዚህ መጥምቁ “እንኳንስ ሙሽራ ልሆን ቀርቶ እርሱ የረገጣትን ኮቴ እንኳን ልረግጥ አይገባኝም” ማለቱ ተገቢ ነበር /ታላቁ ጐርጐርዮስ ዝኒከማሁ 4/፡፡
 ይህ ሁሉ በሰዋራ ቦታ ሳይሆን ሕዝቡ በተሰበሰበበት ዮሐንስም ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ እና በቤተ ራባ ሆነ /ቁ.28፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ወንድሞቼ! ሴቶች ከወለዷቸው ሁሉ ከእርሱ የሚበልጥ የሌለ ዮሐንስ የጌታን የጫማ ማዘብያ መንካት አይገባኝም ካለ እኛማ ምን ያህል ያልተገባን እንሆን ይሆን? ዓለም ለእርሱ ያልተገባችው ይልቁንም ዕድሜውም በሙሉ እግዚአብሔርን በማገልገል አንገቱ የተሰየፈው ዮሐንስ እንዲህ ካለ በኃጢአት የጨቀየን እኛማ ምን እንል ይሆን? ትሕትናው እንዴት ከፍ ከፍ እንዳደረገችው ታስተውሉ ዘንድ እማልዳችኋለሁ! እርሱ የጫማውን ማዘብያ እንኳን “አልነካም” ቢልም ሰውን አፍቃሪ ጌታ ግን “እንኳንስ ጫማዬ ገና እኔን ታጠምቀኛለህ” ብሎታል፤ “አጥምቆታልም”፤ ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ ራቅ” ቢለውም ሰው ወዳጁ ጌታ ግን “ገና ቤተ ክርስቲያኔን በአንተ ላይ እመሠርታታለሁ” ብሎታል፡፡ እውነት ነው! ትዕቢት ቅዱሳን መላእክትን ርኩሳን መላእክትን ታደርጋለች፤ ትሕትና ግን ወደ ሕይወት ዛፍ የምታስወጣ መሰላል ነች፡፡ ምንም ያህል ጾመኞች፣ ጸሎትን የምናዘወትር፣ ሌላም ሁሉ ብናደርግ ትሕትና ግን ከሌለን የትሕትና ጌታ ከእኛ ጋር የለም፡፡ በሰው ዘንድ ከፍ ከፍ ያለ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የረከሰ ነውና /ሉቃ.16፡15/፡፡ አቤቱ እንደ ቸርነትህ ነው እንጂ እንደ በደላችን አይሁን፡፡ አሜን!!  

Friday, May 18, 2012

THE MOST VERSATILE ETHIOPIAN SCHOLAR & SAINT- St. YARED=+=



IN THE NAME OF THE FATHER, THE SON, AND OF THE HOLY SPIRIT ONE GOD AMEN!

Selam=+= (To mean Peace be to you in Ethiopic!)

Here is the second part of what I have promised you in the last time.
St. Yared; the great Ethiopian scholar, was born in Axum (One of the Ancient Cities in the world in Northern Part of Ethiopia and where the Arc of the Covenant lies) in 505 AD (This is Ethiopic calendar. I will present in the future). His father was called Isaac and his mother Christina.

His father died when he was 7. His mother then gave to the then Scholar and his uncle; Gedewon, in the courtyard of Axum Zion church to adopt her son and to take over the responsibility regarding his education. But; St. Yared was not intelligent enough in the beginning to compete with the other children, and His uncle was so impatient with him and he gave him several lashes for his inability not to compete with his peers.
Realizing that he was not going to be successful with his education, Yared left school and went to Medebay, a town where his another uncle resided. On his way to Medebay, not far from Aksum, he was forced to seek shelter under a tree from a heavy rain, in a place called Maikrah. While he was standing by leaning to the tree, he was immersed in thoughts about his poor performance in his education and his inability to compete with his peers. Suddenly, he noticed an ant, which tried to climb the tree with a load of a seed. The ant carrying a piece of food item made six attempts to climb the tree without success. However, at the seventh trial, the ant was able to successfully climb the tree and unloaded the food item at its destination. Yared watched the whole incident very closely and attentively; he was touched by the determined acts of the ant. He then thought about the accomplishment of this little creature and then pondered why he lacked patience to succeed in his own schooling.

He got a valuable lesson from the ant. In fact, he cried hard and then underwent self-criticism. The ant became his source of inspiration and he decided to return back to school. He realized the advice he received from his uncle was a useful advice to guide him in life. He begged Aba Gedeon to forgive him for his past carelessness. He also asked him to give him one more chance. He wants all the lessons and he is ready to learn.

His teacher, Aba Gedewon then began to teach him the Book of David. Yared not only was taking the lessons, but every day he would stop at Aksum Zion church to pray and to beg his God to show him the light. His prayer was answered and he turned out to be a good student. Within a short period of time, he showed a remarkable progress and his friends noticed the change in him. They were impressed and started to admire him. He completed the Old and New Testaments lessons at a much faster pace. He also finished the rest of lessons ahead of schedule and graduated to become a Deacon. He was fluent in Hebrew and Greek, apart from Ge’ez. After that he become a Deacon & served at Axum Zion Church where he late on become a married priest who succeeded to the position of his uncle. He was the first Ethiopian Scholar to compose a hymn. But his hymn was not a result of learning only; but a matter of inspiration. As a matter of inspiration, he was made to enjoy the company of, and listening to the singing of angels (which revealed themselves in the form of three birds!) and then he was taken up in spirit to the heavenly Jerusalem where he could learn the song of the Twenty Four Priests to heaven. When he returned to himself, he went into the church of Axum at the 3rd hour of the day & he began to cry out with a loud voice saying “hale luya laab, hale luya lewold, hale luya wolemenfes qidus qidameha letsion semaye sarere wedagem arayo lemusse zekeme yegeber gibra ledebtera which is to mean Hallelujah to the Father, Hallelujah to the Son, Hallelujah to the Holy Spirit.’’ This was later labeled Mahlete Aryam (The Highest).

His hymn has three modes: Geez, Araray, and Ezil. These three modes are well characterized in a way, which can be used on fast days, ordinary days, and on great festivals.
His literature has unique mystery in his hymnary (In Ethiopic Digwa). He arranged hymns for each season of the year; for summer, winter, spring, and Autumn, and for festivals and Sabbaths, and for the days of St. Mary, Angels, the Prophets, the Martyrs, the Apostles and the Righteous.

St. Yared preached the Gospel throughout Ethiopia. He also composed a song to the Ethiopian Anaphora. There are five hymn books composed by St. Yared. They are: Digwa, Tsome Digwa, Mieraf, Zimare,Mewasiet, and The Chant of the Liturgy.He used to elaborate his hymn in musical notation which in many ways is connected with its religious meaning (symbol). It consists of Biblical signs and letters as well as musical dots placed above the relevant syllables. They indicate the raising or lowering of the voice as well as other modes of pronunciation.

These Signs (Milikt in Ethiopic) serve to instruct the singer in how to instruct the single note and how to interpret the melody (Note that Mozart was not yet born).
The signs are 8. (It is difficult for me to put them here in sign as am not good in drawing! But; you can easily Google it.)

In general the works of Yared would consolidate almost the Theological, Ethical, Musical and Philospphical world of human thought (Qine- to mean Poet in Ethiopic).

St. Yared is the most venerated Holy Father canonized by the church and a great Theologian who could help the Christian Faith to be deeply rooted in the country. The bad news is his writings are not yet translated to other international languages.

The feast of St. Yared is tomorrow, Ginbot 11 E.C. (which is 19th of May in. G.C.).

May the blessings and Intercession of St. Yared be with us and all Christians. Amen!!
(To be continued in other Ethiopic articles)

FeedBurner FeedCount