Pages

Friday, May 4, 2012

ተሐድሶ በ… ያስፈልጋል፤ ሃይማኖት ግን አይታደስም =+= በአባ ሳሙኤል፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ=+=!!

ዶግማ የሚለው ቃል “ዶኪን” ከሚል የግሪክ ግሥ (አንቀጽ) የተገኘ ነው፡፡ በጥንቱ ግሪክኛ ቋንቋ “ዶኪን ሚ” የሚለው አገላለጽ ወደ አማርኛ አገላለጽ ሲቀየር ወስኛለሁ፤ እርግጠኛ ነኝ፤ ጽኑዕ እምነቴ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዶግማ ማለት እርግጠኛ የሆነ ነገር፣ የተወሰነ ነገር፣ የታመነ ነገር ማለት ነው፡፡ ይህን እውነተኛ (የታመነ) ነገር፣ የተረጋገጠ ነገር፣ የተወሰነ ነገር ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን አተረጓጐም ዶግማ ሲባል የሃይማኖት አባቶች የማይቀየር፣ የማይሻሻል፣ የማይለወጥ፣ የማያረጅ ብለው ይፈቱታል፡፡ አዎ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት አይሻሻልም፤ አይታደስም ብላ የምታስተምረው፡፡ ተሐድሶ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በአስተዳደር፣ በልማት፣… ወዘተ ያስፈልጋል፤ ሃይማኖት ግን አይታደስም፡፡ ስለሆነም “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም” የሚለውን ማስተዋል ይገባል /ማቴ.24፡35/፡፡ ማለትም ራሱ ጌታ የተናገረውን የቃሉን ጽኑነት፣ ተአማኒነት፣ እርግጠኝነት፣ ልክነት በትክክል ያረጋግጣል፡፡ ዶግማ የሚለው ቃሉ የተመረጠውም ከላይ እንደተገለጠው እርግጠኛነትን የሚያመለክት ቃል ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡… በኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት አተረጓጐም መሠረት ዶግማ የምንለው፡-  ሃይማኖታዊ የሆነ እውነታ፤  በመለኰት መገለጥ የተመሠረተ (የተገኘ) እና  ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ትምህርት ነው፡፡… አንድ ሰው መናፍቅ ሆነ የሚባለው ዶግማን ከእምነቱ ሕግና ሥርዓት ውጭ እናሻሻል፣ እናድስ በሚል አመለካከት ከትክክለኛው አባባልና አነጋገር እንዲሁም አስተሳሰብ ወጥቶ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ አዛብቶ ሳይተረጕም እንዲያውም ወደ ሃይማኖት ፈጽሞ ሳይገባ በውጭ ሆኖ የሚለፈልፍ ሰው ግን ሃይማኖት አልባ፣ ከሐዲ ወይም አስተያየት ሰጪ ነው፡፡ እየተደረገና እየተባለ ካለው ሁሉ በሃይማኖት ጸንተን እግዚአብሔር በምሕረቱ በቸርነቱ ስለጐበኘን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ስውርና አሳፋሪ የሆነውን ነገር አስወግደን በተንኰልም አንሠራም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከውሸት ጋር አንቀይጥም፤ ይልቅስ እውነቱን በይፋ እናሳያለን፡፡ ራሳችንንም በሰው ኅሊና ግልጥ እያደረግን በእግዚአብሔር ፊት እንኖራለን፡፡ ያበሠርነው የምሥራች ቃል ምናልባት የተሠወረ ቢሆንም የተሠወረባቸው ለሚጠፉት ነው፡፡ እነርሱም የማያምኑበት ምክንያት ለጊዜው የዚህ ዓለም አምላክ/ገዢ የሆነው ሰይጣን ልቡናቸውን ስላሳወረው ነው፡፡ በየአቅጣጫው መከራ ይደርስብናል፤ ግን አንሸነፍም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግራ ይገባናል፤ ግን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ጠላቶች ያሳድዱናል፤ ነገር ግን ወዳጆች አጥተን አናውቅም፡፡ ተመተን እንወድቃለን፤ ግን አንሞትም፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በእኛ ሰውነት እንዲገለጥ ዘወትር የመድኃኒታችን የኢየሱስን ሞት በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡ የእርሱ ሕይወት በሚሞተው ሰውነታችን እንዲገለጥ “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” ተብሎ እንደተጻፈ እኛም ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤ እንጽፋለንም /2ቆሮ.4፡1/፡፡… ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!! (ምንጭ፡- ፈለገ አሚን ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ገጽ 1-5)!

 ተመሳሳይ ገጾች

በአቡነ ተክለሃይማኖት ገድል ላይ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች-

አንድ ፕሮቴስታንት ለጠየቀኝ የተለያዩ ጥያቄዎች

No comments:

Post a Comment