Pages

Tuesday, April 8, 2014

ኒቆዲሞስ ዘረቡዕ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 30 ቀን 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 የሕልውናው መጀመሪያ ከመቼ ጊዜ ጀምሮ ነው የማይባል፣ ስለመጨረሻውም እስከመቼ ሁሉን አሳልፎ ይኖራል የማይባል፣ ከኪሩቤልና ከሱራፌል አንደበት ለእርሱ ምሥጋና ይሁን:: ለእርሱም መስቀልን በማመን እየተመኩ ራሳቸውንም በወንጌል ቀንበር እያስገዙ በቤተመቅደስ እና በመገናኛው ድንኳን ከሚሰበሰቡ ከምዕመናን ሥግደት የሚገባው የሰላም አምላክ ሰላሙን ይስጣችሁ:: (መጽሐፈ ምሥጢር)


 ይቤ እግዚአብሔር አቅውም ለክሙ ተክለ ሰላምእግዚአብሔር ይላል፡- በመካከላችሁ የሰላም ተክልን አቆማለሁ፤ የምላችሁን ብትሰሙኝ ለምድራችሁ የሰላሜን ብዛት እሰጣታለሁ መርዳት የምችል ማዳንም የምችል መማርም የምችል እኔ ነኝና::” ወገኖቼ በቅዱስ ያሬድ ሰላምታ ሰላም ብዬ የደራሲውን የተመረጡ የዕለቱን ጣዕመ ዜማ እነሆ!

 ነአኩተከ እግዚኦ አምላክነ ለደቂቀ አዳም ዘከፈልከነአቤቱ አምላካችን እናመሰግንሃለን:: ርስትህን ምሕረትህን ለአዳም ልጆች ያደልከን የፈጠርከው ከሰማይ እስከ ምድር ዳርቻ መላ፤ የእጆችህ ሥራዎች ትመግባቸዋለህ፤ በመድኃኒትህ አሳድረን፤ በጎህንም ሁልጊዜ ስጠንብሎ አምላኩን ከተማጸነ በኋላ እናቱን ከእንቅልፍ ሲነቃ ማመስገን ይጀምራል:: ጽዮን ቤተክርስቲያን እናቴ ሆይ ነይ:: ከአፌ የእውነትን ነገር እናገራለሁ፤ የሰማዕታት እናት የነገሥታት ከፍታ ነሽ::

 ተቀደሲ ወንሥኢ ኃይለ ቤተእግዚአብሔርተቀደሺ ኃይልን ያዢ (ውሰጂ)፤ እነሆ ንጉሥሽ መጥቷልና (ደርሷልና)፡፡ በኃይሉ የሚያበራልሽ ነው:: ይሕችን ቤት አስቀድሞ እግዚአብሔር አብ መሠረታት፤ ወልድም አነፃት፤ መንፈስ ቅዱስ ፈጸማት::… ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለምለዘለዓለም ይህች ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በእርሷ አድራለሁ:: የምስክር ድንኳን በእኛ ዘንድ ነበረች፤ ሁልጊዜም የመስቀልህም ሞገሥ ከእኛ ጋር ይኖራል::” ቅድስት ቤተክርስቲያን ሆይ ክብርሽና ኃይልሽ ለዓለም ሁሉ ይነገር:: አብ በሰሎሞን አድሮ መሠረተሽ፤ ወልድም በደሙ መሠረትነት አነጸሽ፤ መንፈስ ቅዱስም ከበዓለ በኋላ ፈጸመሽ:: ከእንግዲህ ያለመናወጥ ለዘለዓለም ትኖሪያለሽ፤ የሰማዩ ሥርዓት በአንቺ ተፈጽሟልና ሱራፌልና ኪሩቤል የማይዳስሱትን ሥጋ ወደመ እግዚአብሔር በውስጥሽ ይዘሻል:: ስለዚህም ሁልጊዜ አምላክሽ በአንቺ አድሮ ይኖራል::

  ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ እስከ እሁድ ባሉት ቀናቶች የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች በሙሉ ስለ ሆሳዕና በተለየ ይሰብካሉ:: ምክንያቱም መጪው ሳምንት ሕማማት ስለሆነ ሳምንቱን ወደዚህ ስቦ ሆሳዕናን ከረቡዕ እስከ እሁድ ይሰብካል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ይህን መሠረት አድርጋ የምትቀድሰውም ቅዳሴ ሆሳዕናን የሚያነሳውን ቅዳሴ ጎርጎርዮስን ብቻ ይሆናል:: ጽዮን ሆይ ደስ ይበልሽ፤ ወደ አንቺ የመጣውን ደስታ የእስራኤል ንጉሥ ተመልከቺ፤ ለአሕዛብ ሁሉ ብርሃንን የሚሠጥ ከአንቺ ተገኘ:: ደብረ ዘይት በደረሰ ጊዜ ሆሳዕና እያሉ ህፃናት የዘንባባ ዝንጣፊን ይዘው ንጉሥሽን አመሰገኑት:: ሆሳዕና እያሉ ብዙ ሕዝብ ተቀበሉት:: ዋጋው በእጁ ያለ እውነተኛው ብርሃንሽ መጥቷልና ጽዮን ሆይ ደስ ይበልሽ:: የአሕዛብ ነገሥታት ይሰግዱልሃል፤ እጅ መንሻንም ያመጡልሃል ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ብለው ያመሰግኑሃል::

 ንልበስ ወልታ ዘብርሃን ፃኡየብርሃን ጋሻን እንያዝ፤ ውጡ ሕፃናትና ታዳጊዎች በታላቅ ምሥጋና እንደተቀበሉት ወልድን እንቀበለውእያለ ለምሥጋና ሊቁ ያነሳሳናል:: ሰኞና ማክሰኞ በዓራራይ ዜማ አሳልፈናል:: ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ አብዝተን ሆሳዕና መድኃኒት እንላለን::

 ዘየሐፅብ በወይን ልብሶ ወበደመ አስካል ዓፅፎበወይን ልብሱን የሚያጥብ ነው፤ የፍሬውንም ደም ለብሶ እርሱ ክርስቶስ እንደ ልብስ ብርሃንን የሚለብስ አይሁድ ከለሜዳ አለበሱት፤ ሰማይን እንደ ገበታ የሰቀለውን አይሁድ በእንጨት መስቀል ላይ ሰቀሉትዓይ ውእቱ ዝንቱ ዘአዕሩግ ይሰግዱ ሎቱይህ ታዳጊዎች የሚሰግዱለት፣ ሕፃናት ዘንባባ ዝንጣፊ አምጥተው የከበቡት ማነው? እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ናዝራዊ ነው:: ምሥጋና የሞላው ታላቅ ምክር ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ጽዮን ሆይ ንጉሥሽ ዋጋው ከእርሱ ጋር አለ::” ልብሱን በወይን የሚያጥብ እርሱ ነው:: ሆሳዕና መድኃኒት ዘለዓለማዊ መስዋዕት ሆኖ በዕለተ ዓርብ የሚፈስ ደሙን በሐሙስ ምሽት በወይን እናደርግ ዘንድ ሰጠን:: የሕፃናትን አፍ አስከፍቶ ምሥጋናን የሚቀበል ዛሬስ ሁሉን ካወቁ የእርሱ ከተባሉ ሰዎች ምሥጋናን ያጣው ስለምን ይሆን? ልበ ደንዳኖች አይሁድ ምሥጋናውን እንደከለከሉ ዛሬም እንዲሁ በሥራችን አይተው አሕዛብ እንዳያመሰግኑ ከልክለናልና ይቅር በለን::

 ንሥኡ ጸበርተ ወበቀልተ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱየእስራኤል ሥርዓቱ ነውና ዘንባባን ዝንጣፊን አምጡ፤ ሰማያዊ ሙሽራውንም በምሥጋና ተቀበሉ::” “ኢየሱስ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ላከ” እያለ ሊቁ ያዜማል:: “ሄዳችሁ ከፊታችሁ ካለችው መንደር ጌታቸው ይፈልጋቸዋልና አህያዋንና ውርንጭላዋን እንውሰድ በሏቸው:: እነርሱም አመጡለት ጨርቃቸውን አነጠፉ፤ በነቢይ እንደተነገረው ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ:: ጌታም ደስታሽ ዛሬ ተፈጸመ እኔ መጣሁልሽ ጽዮን ሆይ ደስ ይበልሽ አላት::

 እስመ እምጽዮን ይወጽእ ሕግከጽዮን ሕግ ይወጣልና፤ ቃለ እግዚአብሔር (ወልድም) ከኢየሩሳሌም፤ ጻድቅ ሰው ከእግዚአብሔር የሆነ እነሆ ንጉሥሽ መጣ (ደረሰ)::” ሕዝቡም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው አሉ:: እርሱ የሚያድን በመስቀሉ የሚታደግ ነው::

ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ዲበ ዕዋለ አድግ ነበረ ወለዕውራን ጸገዎሙበኪሩቤል ላይ የሚኖር በአህያ ላይ ተቀመጠ:: ለእውራን ብርሃንን ሰጣቸው፤ ሰላምንም አደረገ:: አኗኗሩ ከዓለም አስቀድሞ የሆነውን ሕዝብ ሁሉ ምሥጋናውን አዩ::” የጽዮን የቤተክርስቲያን ልጆች ከዛሬ ጀምሮ ሕፃናት በልጅነት አንደበታቸው መድኃኒታችን መድኃኒታችን እያሉ ያመሰግኑታል::

 እርሱምሥለ አብርሃም ተዓርከከአብርሃም ጋር ተፋቀረ፤ ከዮሐንስም ጋር ወደ ዮርዳኖስ ወረደ፡፡ ጌታ ሲሆን በእንጨት መስቀል ተሰቀለ፤ መድኃኒት ይሆነን ዘንድ ወረደ፤ ከደቀመዛሙርቱ ጋር የሆሳዕናን ዑደት አደረገ::” ጽዮን ዳግመኛ ደስ ይበልሽ፤ ንጉሥሽ የዋሕ ሆኖ በአህያ ተቀምጦ ፍጹም ትሕትናን ሰበከን:: እንዴት ያለ ክብርን የናቀ ንጉሥ ነው::

ቅድሜሁኒ ብርሃን ድኅሬሁኒ አሚን ማዕከሌሁኒ ሰላም ተቀበሉ ሕዝብበፊቱ ብርሃን፣ በኋላው ሃይማኖት፣ ማዕከሉ ሰላም ሆሳዕና በአርያም ለዳዊት ልጅ እያሉ ሕዝብ ተቀበሉት::” ጽዮን ደስ ይበልሽ፡፡

 ቦአ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በስብሐት ወብዙኅ ሰላምኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በምሥጋናና በብዙ ሰላም ገባ::” ይህንን ሰላሙን ያድለን::

No comments:

Post a Comment