Pages

Monday, September 15, 2014

የትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 5 ቀን፣ 2007 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 “ሃይማኖትማለት አምነ፣ አመነ ከሚል የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን መዝገበ ቃላታዊ ትርጓሜውምማመን፣ መታመንማለት ነው፡፡ በምሥጢራዊው ትርጕሙ ግንሃይማኖትማለት ፍጥረትን ኹሉ ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣ አንድ እግዚአብሔር እንዳለ፣ ለሚታየውም ለማይታየውም ፍጥረት ሠራዒውና መጋቢው ርሱ ብቻ እንደኾነ፣ ልዩ ሦስትነት እንዳለው፣ በዚኽ አለ በዚኽ የለም የማይባል ምሉዕ በኵለሄ እንደኾነ፣ማመን መታመን ማለት ነው፡፡


 “ማመንማለትም ይኾንልኛል ይደረግልኛል ብሎ መቀበል፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ተስፋ ማድረግ፤ አለመጠራጠር ማለት ሲኾን፤መታመንማለት ደግሞ ያመኑትን እውነት በሰው ፊት በአንደበት መመስከርና በተግባራዊ ሕይወት መግለጥ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይኽን በተመለከተ፡- “ይኽም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ኾነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልናብሎ አስተምሯል /ሮሜ.108-10/፡፡ ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ፡- “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትኹ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻልበማለት ከኹሉ አስቀድሞ እምነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳና፤ ቀጥሎምማንም ግን በዚኽ መሠረት ላይ በወርቅ ቢኾን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤በማለት ምግባር ትሩፋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል /1 ቆሮ.31012/ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት 9ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “እምነት መሠረት ናት፤ ሌሎች ግን ሕንፃና ግንብ ናቸውበማለት ምግባርና ትሩፋት ከመሥራት በፊት እምነት እንደሚቀድም አስተምሯል /.80-81/፡፡
 ስለዚኽትምህርተ ሃይማኖትስንል ስለዚኹ ስለምናምነው አምላክ የምንማማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው ማለት ነው፡፡ስለምናምነው አምላክ የምንማማርበት የትምህርት ዘርፍ ነውሲባል ግን በፍልስፍናና በዚኽ ዓለም እንደምናደርገው በምርምርና በሙከራ እንደርስበታለን ለማለት ሳይኾን እግዚአብሔር ራሱ በተለያየ መንገድ የገለጠውንና እንድናውቀው የፈቀደውን ብቻ እንማማራለን ለማለት ነው፡፡ በዚኹ ዙርያ ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔር ስንማማር በስፋት እንመለስበታለን፡፡
በፍልስፍናው ዓለም ፍልስፍናን ለመማር የራሱ የኾነ ቅድመ ኹኔታ (Axiom) እንዳለ ኹሉ በትምህርተ ሃይማኖትም ስለ ፈጣሪ ለማወቅወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል ተብሎ እንደተጻፈ አስቀድሞ እምነት ያስፈልጋል /ዕብ.116/፡፡ እምነት ማለትም ለመለኮታዊው መገለጥ የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡ በትምህርተ ሃይማኖት የመዠመሪያው ቅድመ ኹኔታ ይኽ እምነት ነው፡፡ እምነት ሳይኖረን ትምህርተ ሃይማኖትን መማር አይቻለንም፤ ትምህርተ ሃይማኖት የአዕምሮ ጨዋታ አይደለምና፡፡ ትምህርተ ሃይማኖትን ስናጠና ኹል ጊዜ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ እምነት ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ስጦታ ቢኾንም ፈቃዳችንን ይጠይቃል፡፡ ይኽ አካሔድም በቤተ ክርስቲያን ቋንቋፍኖተ አሚንይባላል፡፡  
 ቀጥሎ የሚመጣው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስእኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንኾንኽ አምነናል፤ ዐውቀናልምእንዳለው ዕውቀት ነው /ዮሐ.669/፡፡ ኾኖም አኹንም ጥንቃቄ ያስፈልገናል፡፡ ይኸውም ይኽ ስለ ፈጣሪ የምናውቀው እውነት መጨረሻ የለውም፡፡ ለምን? እግዚአብሔር ወሰን የለውምና /ኤር.2323/፡፡ ተጠንቶ የሚያልቀው ውስንነት ስላለው አካል (ፍጡር) ብቻ ነው፤ ያውም አብዛኛው አያልቅም፡፡ ስለኾነም ስለ እግዚአብሔር የምንማረው ኹሉ በጥቂት ቃላት ብቻ ታጥሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ይኽ አነጋገር በኦሬንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት አነጋገር “Apophatism - አፖፋቲዝምይባላል፡፡ በኢ////. “አንድም አንድምታእያልን የምናውቀው ነው፡፡
ታድያ መማራችን ምን ፋይዳ አለው?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡
1) የተገለጠውን እውነት ለመረዳት ይጠቅማል፤
2) የቀደመችውን አንዲቷን መንገድ መያዝ ስለሚያስፈልግ እውነትን ከሐሰት ለመለየት ይረዳናል፤
 ምንም እንኳን ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ቢኾንም፥ ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሰዎች ፈልገው የማያገኙት ቢኾንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስና በሥነ ፍጥረት የተገለጠውን ግልጽ ትምህርት መማርን ግን አያወግዝም፡፡ ኹል ጊዜ እውነትን ለማወቅ ከመጠየቅ ዕረፍት የሌለው የሰው ልጅ አዕምሮንም በአመክንዮ (By Reason) ማስረዳትን እንዲኹ አያወግዝም፡፡ ይልቁንም አመክንዮን በትክክለኛው መንገድ እንድንጠቀምበት ያግዛል እንጂ፡፡
ተመስጦ

ቸርና ሰው ወዳጅ የኾንከው እግዚአብሔር ሆይ! ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣኸን አንተ ነኽ፡፡ ምን እንደሚያስፈልገን ዐውቀኅ የሚጠቅመንን ብቻ የምትሰጠን አንተ ነኽ፡፡ ይኽም የምታደርገው ስለ ፍቅርኅ እንጂ ከእኛ መልካም ነገር አግኝተኅ አይደለም፡፡ ቅዱስ ሆይ! እንኪያስ እኛም ፍቅርኅ ይገባን ዘንድ ልቡናችንን በብርሃንኅ አብራልን፡፡ አምነንና ታምነን እንጸና ዘንድ ርዳን፡፡ በፍኖተ አዕምሮ ሳይኾን በፍኖተ አሚን ተጕዘን እናንተ የአባቴ ብሩካን፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ዠምሮ የተዘጋጀላችኁን መንግሥት ውረሱብለኅ በቀኝ ከምታቆማቸው ቅዱሳን ጋር እንቈጠር ዘንድ ቸርነትኅ ትርዳን፡፡ አሜን፤ ይኹንልን፤ ይደረግልን፡፡

No comments:

Post a Comment