በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጌታችንና
የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ወንጌላውያን ሁሉ ጽፈውታል፡፡ ከጥቃቅን ልዩነቶች በስተቀር የአራቱም ወንጌላውያን አጻጻፍ
እርስ በርስ የተስማማ ነው፡፡ ልዩነቱም ቢሆን አንዱ የገለጠውን ዝርዝር ነገር አንዱ ባለመጨመሩ እንጂ የሚለያይ ወይም የሚጋጭ ነገርን
በማካተቱ አይደለም፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በበኩላቸው የትንሣኤውን ነገር መሠረት አድርገው ያስተማሩት ትምህርት፣ የሰበኩት
ስብከት፣ እንዲሁም የተመስጧቸው ፍሬና የትርጓሜ ሐሳቦቻቸው እጅጉን የበዙ ሲሆን ከዚያ ውስጥ በዚህ ጽሑፍ አማካኝነት ጥቂቱን መርጠን
ለማየት እንሞክራለን፡፡ ለትምህርቱ እንዲመቸን በዋናነት የሉቃስን ወንጌል እንያዝና የተቀሩትን ምንባባት እንደ አስፈላጊነታቸው ከየወንጌላቱ
እንጨምራለን፡፡