Saturday, April 30, 2016

የጌታችን ትንሣኤ



በዳዊት አብርሃም
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 22 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ወንጌላውያን ሁሉ ጽፈውታል፡፡ ከጥቃቅን ልዩነቶች በስተቀር የአራቱም ወንጌላውያን አጻጻፍ እርስ በርስ የተስማማ ነው፡፡ ልዩነቱም ቢሆን አንዱ የገለጠውን ዝርዝር ነገር አንዱ ባለመጨመሩ እንጂ የሚለያይ ወይም የሚጋጭ ነገርን በማካተቱ አይደለም፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በበኩላቸው የትንሣኤውን ነገር መሠረት አድርገው ያስተማሩት ትምህርት፣ የሰበኩት ስብከት፣ እንዲሁም የተመስጧቸው ፍሬና የትርጓሜ ሐሳቦቻቸው እጅጉን የበዙ ሲሆን ከዚያ ውስጥ በዚህ ጽሑፍ አማካኝነት ጥቂቱን መርጠን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ለትምህርቱ እንዲመቸን በዋናነት የሉቃስን ወንጌል እንያዝና የተቀሩትን ምንባባት እንደ አስፈላጊነታቸው ከየወንጌላቱ እንጨምራለን፡፡

‹‹ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ›› (ሉቃ. 24÷1)
‹‹ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን›› በሚል የተገለጠውን ዕለት አውግስጢኖስ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ‹‹የጌታ ቀን›› (ራእ 1፡10) ተብሎ የተጠራው የክርስቲያን ሰንበት እንደሆነ አስታውሶ ቀኑ የመጀመያው ብቻ ሳይሆን የመጨረሻውም መሆኑንና በዚህም ምክንያት በምስጢራዊ ፍቺ ዘላለማዊነትን የሚወክል ቀን መሆኑን ሲገልጥ ለመጀመሪያዋ ቀን መጀመሪያነቷን ሳያጠፋ “ስምንተኛዋ ቀን” የሚል ዐዲስ ፍቺን በመስጠት ነው፡፡ “የጌታ ቀን የሳምንቱ የመጀመሪያ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ነገር ግን ሁለተኛው ቀን ሲከተል የመጀመሪይው ቀን ኀላፊ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው ቀን ከስምንተኛው ቀን ጋር የተባበረባት ያቺ ቀን ግን ዘላለማዊነትን ትወክላለች፡፡ በዚያ በኀላፊው ቀን ከፈጣሪ ተለየን፤ በመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምክንያት ወደ መዋቲነት ተሸጋገርን፡፡ በዚህች የመጨረሻዋ ቀን ደግሞ እንደገና ወደ ሕይወት ተመለስን፤ የመጨረሻው ጠላታችን ሞት ተወግዶባታል፡፡ (1ኛቆሮ 15፡26) ከዚያ በኋላ ነው ይህ የሚያልፈው የማያልፍ፣ የሚጠፋውም የማይጠፋ፣ የሚሞተውም የማይሞት ወደ መሆን የተሸጋገረው (1ኛ ቆሮ 15፡53) የጠፋው ልጅ የቀድሞ ልብሱን ይለብሳል፤ በሰባቱ ቀን ዑደታት (ዓውደ ዕለት) የነበረውን ግዞቱን ጨርሶ ወደ ስምንተኛው የዕረፍት ዕለት መጥቷልና፡፡”
ይህቺን ጌታ በትንሣኤው ያከበራትን የክርስቲያን ሰንበት ስምንተኛዋ ቀን እንዲሁም የመጀመሪያና ስምንተኛ፣ የመጀመሪያና የመጨረሻ ቀን እያሉ መጥራት በቀደምት ሊቃውንት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ሊቃውንቱ ይህን የሚሉበት ምክንያት በሥነ ፍጥረት ዕለተ ዕሑድ የመጀመሪያ የፍጥረት ቀን መሆኗን አዘክረው የቀድሞው ሥነ ፍጥረት በሐዲስ ተፈጥሮ ታድሶ ዳግም መወለዱን፣ በጌታችን ትንሣኤ ፍጥረት ሁሉ ዐዲስ ሆኖ መፈጠሩን ለመግለጽ ነው፡፡ እንዲሁም በሥነ ፍጥረት የሚታወቁት ዕለታት ሰባት ናቸው፡፡ እነዚህ ዕለታት እየተመላለሱ እስከ ዓለም ፍጻሜ ይኖራሉ፡፡ በዓለም ፍጻሜ ግን መመላለሳቸው ያበቃል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚከተለው ዘለዓለማዊነት ነው፡፡ ይህን ዘላለማዊ ሕይወት ያገኘነው ደግሞ በጌታችን ሲሆን ተስፋውን የጨበጥነው ደግሞ በትንሣኤው ነው፡፡ ስለሆነም የፍጥረት የመጀመሪያ ቀን የነበረችው ዕለተ እሑድ የጌታችን ትንሣኤም ስለተፈጸመባት ፍጥረታት ለሚያልፉባትና ዘላለማዊነት ለሚተካባት፣ ለምትመጣው ዐዲስ ዓለም ምሳሌ በመሆን ሁለት ትርጕም አግኝታለች፡፡ እንደ ሥነ ፍጥረት ቀንነቷ የመጀመሪያ ትባላለች፤ የዘላለማዊነት ምሳሌ እንደመሆኗ ደግሞ ከሰባቱ ቀናት ተነጥላ ስምንተኛዋ ለመባል በቅታለች፡፡ በግእዝ መጻሕፍትም “ሰሙን፣ ስምንተኛ” ተብላለች፡፡ የሰንበት ክብር በሰፊው በተዳሰሰበት ቅዳሴ አትናቴዎስ ‹‹ለለ ሰሙኑ ትነግሥ ወለለ ሰሙኑ ትሰፍን ወለለ ሰሙኑ ትትቄመር›› ተብሏል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ስምንተኛ በተባለች የመጀመሪያዋ ቀን ትንሣኤያችንንና ዘላለማዊ ሕይወታችንን ለማወጅ የሥጋውን ትንሣኤ በዚህች ክብርት ዕለት እንዲሆን ያደረገው፡፡ (ሮሜ 6፡9)
ቀኒቱ በማርቆስ ወንጌል ‹‹ሰንበትም ካለፈ በኋላ›› ተብላ ተገልጻለች፡፡ (16፡1) ይህንንም ቅዱስ አትናቴዎስ በትርጓሜ ሲያትት “በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰንበት በታላቅ ከበሬታ ትከበር ነበር፡፡ አሁን የበለጠ የምትከብር የጌታ ቀን የምትባል የክርስቲያን ሰንበት ናት፡፡ ቀዳሚት ሰንበት ሕጉን የምታስተምር ዕለት ሆና የተሰጠች ናት፡፡ ዋናው መምህር ሲመጣ ግን እርሱ ሕግጋትን ሁሉ ስለፈጸማቸው የእርሱን መምጣት ምሳሌ እየሆነ ሲሰብክ የቆየው ነገር ሁሉ ተለወጠ፡፡ ቀዳሚት ሰንበት በጨለማ ውስጥ የምታበራ የሻማ ብርሃንን ሆና ፀሓይ ከመውጣቷና ከመታየቷ በፊት ትታያለች፡፡” (ማር.16፡2 ሉቃ 24፡1)
ሴቶቹ ወደ መቃብሩ የመጡበትንም ሰዓት በተመለከተ ወንጌላዊ ማርቆስ “ፀሓይ ከወጣ በኋላ” ሲል ሌሎች ወንጌላውያን ግን “እጅግ ማለዳ” መሆኑን ገልጠዋል፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ገና ጨለማ ሳለ›› ብሏል፡፡ አውግስጢኖስ የወንጌሎችን መስማማት አብራርቶ በጻፈበት መጽሐፉ (The harmony of gospels) ላይ ይህን ነጥብ አንሥቶ እንደማይጣረስ ሲያብራራ እንዲህ ይላል፤ “ሁሉም ወንጌሎች የገለጡት ጊዜ ሰማያት በምሥራቅ በኩል በፀሓይ ወጋገን ማብራት የሚጀምሩበትን ነው፡፡ ይህም ፀሓይ ሙሉ በሙሉ ከመውጣቷ በፊት ያለውን ጊዜ ያመለክታል፡፡ በተለምዶ አነጋገራችን (customarily) ጎህ ሲቀድ የምንለው ጨለማው ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ በብርሃን ተበርዞ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ማርቆስ ፀሓይ ከወጣ በኋላ በሚል የገለጠው፣ ‹‹ገና ጨልሞም ሳለ›› ከሚለው ከቅዱስ ዮሐንስ ቃል ጋር የሚቃረን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቀኑ እየገፋ ሲመጣ የተራረፈው ጨለማ ከምትወጣው ፀሓይ በተመጣጣኝ መጠን ገና እያለፈ ስለሚሔድ ነው፡፡” 
     ሌላ ሊቅ ደግሞ የሰዓቲቱን ምስጢር እንደሚከተለው ይተረጕማል፡፡ “ገና ከጠዋቱ ከዚህ ቅዱስ ዕለት መጀመር አንሥቶ የትንሣኤው ክብር መነገር ጀመረ፡፡ ጌታ በሞት ላይ የተቀዳጀው ድል መነገር ጀመረ፡፡ እነዚህ ሴቶች አገልግሎታቸውን የጀመሩት ከቀኑ መፀነስ ጀምሮ ነውና፡፡ ይህን ነገር በምስጢር ስንተረጕመው መንፈሳዊው ጨለማ ወደ ንጋት ማደግ እንደ ጀመረ አብሣሪ ነው፡፡ የቀናት ፈጣሪ የሆነ እርሱ በሌሊቱ መጠናቀቂያ ላይ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ ስለዚህም ዐዲሱ ቀን በሞላው በዓል ለመሆን በቃ፤ በትንሣኤው ብርሃን ተጥለቅልቋልና፡፡”
የጌታችንን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ያሰቡት ቅዱሳት አንስት ማልደው ወደ መቃብሩ ደረሱ፡፡ ሴቶቹ ሽቱውን እንዳዘጋጁ ወንጌላዊው ሉቃስ ሲነግረን ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ “ገዙ” የሚል ቃልን ተጠቅሟል፡፡ ጌታችን ከሞተበት ሰዓት ጀምሮ ሽቱውን የማዘጋጀት ሥራ ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን በኦሪት ያከብሯት ዘንድ የታዘዘችው ዕለተ ሰንበት ስትገባ ሥራቸውን ያቆሙና የሰንበት ዕለት ስታበቃ ደግሞ የተቀረ ሥራቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ በነርሱ ዓቅም ሊዘጋጅ የማይችለውን ደግሞ ገዝተው በመጨመር ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡ በጠዋት ገና ጎህ ከመቅደዱ ቀደም ብለው መቃብሩ ላይ ከደረሱ ሌሊቱን ሲጓዙ አድረዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ነገር የሴቶቹን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡
ወደ መቃብሩ ሲቀርቡ ትልቅ ፈተና የሆነባቸው ወደ መቃብሩ ለመዝለቅ መዝጊያውን የመክፈቱ ነገር ነበርና ‹‹ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል?›› (ማር 16፡2) እያሉ መጨነቅ ጀመሩ፡፡ ጴጥሮስ ክርስቶሎገስ የተባለ ሊቅ ይህን ቃል መሠረት አድርጎ ሲሰብክ “ከመቃብሩ በራፍ ላይ ነው ወይንስ ከልቡናዎቻችሁ ላይ? ከመቃብሩ ላይ ወይንስ ከዓይኖቻችሁ ላይ? እናንተ ልቡናዎቻችሁ የተጠረቀሙ፣ ዐይኖቻችሁም የተዘጉ የተከፈተው መቃብር ውስጥ ያለውን ታላቅ ግርማ ማየት አትችሉም፡፡ ያንን ግርማ ለማየት የሽቱ ዘይቶቻችሁን አፍስሱ፤ በጌታ ሥጋ ላይ አይደለም፤ በራሳችሁ ዐይኖችና ልቡናዎች ላይ እንጂ፡፡ ያን ጊዜ በእምነት ብርሃንነት የእምነት ማነስ በጨለማ ውስጥ የደበቀውን ምስጢር ማየት ትችላላችሁ፡፡”
ጴጥሮስ ክርስቶሎጎስ የተባለው ይኸው ሊቅ የባለ ሽቱዎቹን ሴቶች ኹኔታ ከደቀመዛሙርቱ ኹኔታ ጋር እያነጻጸረ ሲሰብክ ደግሞ እንዲህ ብሏል፡፡ “ሴቶቹ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማክበር ቀዳሚዎች ናቸው፤ ደቀመዛሙርቱ ደግሞ ስለ ክርስቶስ መከራን ለመቀበል የመጀመሪያዎች ሆኑ፡፡ ሴቶቹ ሥጋውን ሽቱ ለመቀባት አዘጋጁ፤ ደቀመዛሙርቱ ደግሞ ለቅጣት መሣሪያዎች ሰውነታቸውን አዘጋጁ፡፡ ሴቶቹ ወደ መቃብር ገቡ፤ ደቀመዛሙርቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ እስር ቤት ሊገቡ ነው፡፡ ሴቶቹ ምስክርነታቸውን ለመግለጽ የተፋጠኑ ሆነዋል፤ ደቀመዛሙርቱም ስለርሱ የሰንሰለት እስራትን ለመቀበል የማይፈሩ ሆነዋል፡፡”
‹‹ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት›› አንድ ሊቅ የድንጋዩ መንከባለል በምስጢራዊ ፍቺ በሙሴ ሕግ ተጋርደው የነበሩት ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ግልጥ ሆነው የመሰጠታቸው ምሳሌ መሆኑን ይናገራል፤ የኦሪት ሕግ ለሙሴ የተሰጠው በድንጋይ ላይ ተጽፎ ነበርና፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ በዚያም ሁን እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው›› (ዘጸ 24፡12)
በማቴዎስ ወንጌል መሠረት መልአኩ ከሰማይ ወርዶ ድንጋዩን በማንከባለል ከበላዩ የተቀመጠ ሲሆን የማርቆስ ወንጌል ግን ሴቶቹ ወደ መቃብሩ ውስጥ ሲገቡ በጎልማሳ ወንድ አምሳል የተገለጠውን መልአክ እንዳገኙት ተጽፏል፡፡ ሉቃስ ደግሞ መላእክቱ ሁለት እንደነበሩ ጽፏል፡፡ አውግስጢኖስ እነዚህን አሳቦች ሲያስማማ “ማቴዎስ ሴቶቹ ወደ ውስጥ ሲገቡ ስላጋጠማቸው መልአክ ምንም አልጻፈም፤ በአንፃሩ ደግሞ ማርቆስ ወደ መቃብሩ ከመግባታቸው በፊት ከውጪ ያዩትንና የመቃብሩን ድንጋይ ስላንከባለለው የእግዚአብሔር መልአክ ምንም አልጻፈም፡፡ ይህም ስለሆነ አሳቡ የሚጋጭ አይደለም፡፡ ዝርዝር ጉዳዮችን አንደኛው ሲዘል ሌላኛው ይዞ መገኘቱ እንጂ” በሚል አብራርቷል፡፡
ይህን የምስራች ከተናገሩ መላእክት መካከል አንዱ በመቃብር ውስጥ በስተቀኝ ተቀምጦ በጎልማሳ ሰው አምሳል የታያቸው መሆኑን በተመለከተ ደግሞ ሌላ ሊቅ ሲገልጥ “የሙታን ትንሣኤ ሙሉ ሰው በመሆን የሚፈጸም መሆኑን ለማሳየት ነው” ይለናል፡፡ (ኤፌ.4፡13) ማለትም ተጨማሪ እድገት በማያስፈልግበት ወይም ያልተሟላና የቀረ እንከን በሌለበት እንዲሁም የጥንካሬና የአካል ፍጽምና ዘመን የሆነበት ዘመነ ውርዛዌ (ወጣትነት) ሙታን በፍጹም አካል የሚነሡበትን ኹኔታ የሚገልጥ ነው፡፡
መልአኩ በስተቀኝ በኩል መቀመጡንና የሚያንጸባርቅ ነጭ ልብስ መልበሱም ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡ ታላቁ ጎርጎርዮስ (Gregory the great) እንዲህ ይላል፡፡ “መልአኩ በቀኝ በኩል የተቀመጠ እንደነበርና ይህም ምን ትርጉም እንዳለው ልብ እንበል፤ ግራ በዚህ ዓለም የሚኖረንን ሕይወት ያመለክታል፤ ቀኝ ግን ዘላለማዊ ሕይወትን ያመለክታል፡፡ መድኀኒታችን የዚህን ዓለም ሕይወት ከሞት በመነሣት ስላሳለፈው ከኀላፊው ዓለም ወደ ዘላለማዊነት የመሸጋገርን ብስራት ለመናገር የመጣው መልአክ በቀኝ ተቀምጦ ታየ፡፡ ልብሱም ነጭ ነበር፤ ሊያበስር የመጣው የመዳናችንን ደስታ ስለሆነ፡፡”
መልአኩ ተቀምጦ ማብሰሩም የሚያሳየን አንድ ምስጢር አለ፡፡ መቀመጥ ድል ማድረግን ያሳያል፡፡ ቀድሞ ሥልጣን የነበረው ሞት ከሥልጣን መሻሩን፣ ጌታችን የሞትን ሥልጣን ሽሮ በሰማያዊት መንግሥቱ መቀመጡን ሊያሳይ መልአኩ ተቀምጦ ተናገረ፡፡ ተቀምጦ መናገር የነገሥታት ልማድ ነውና፡፡ በሉቃስ ወንጌል ደግሞ መላእክቱ ቆመው እንደ ነበር ተገልጧል፡፡ መቆም ደግሞ መሥዋዕት የሚያሳርጉ የካህናት ልማድ ነው፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ነውና ይህን ለመግለጽ መላእክት ቆመው ታዩ፡፡
‹‹ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም›› የሚለውን ንባብ መሠረት ያደረገ ሊቅ ከሕይወታችን ጋር አያይዞ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡፡ “በእኛም ሕይወት ውስጥ እንዲሁ ነው፡፡ በሞቱና በትንሣኤው ስናምን የተዘጋው መቃብር ይከፈትልናል፡፡ ወደ መቃብሩ ውስጥም እንገባለን፤ የጌታን ሥጋ ግን አናገኝም፡፡ ይልቁንም የትንሣኤውንና የሕያውነቱን ምስጢር የሚገልጡትን ትምህርቶች በማስታወስ እርሱ ሕያው አምላክ የመሆኑን እውነት ወደመረዳት እንሸጋገራለን፡፡ አይሁድና አረማውያን ግን ሞቱን ያቃለሉ እንደመሆናቸው ትንሣኤውንም ለማወቅ አይችሉም፡፡ እነርሱ የታሸገውን መቃብር የሚመስሉ ናቸው፤ ወደ መቃብሩ በመግባት የሞተው ሕያው መሆኑን ለማወቅ አይቻላቸውም፡፡ ሞትን ድል የነሳው፣ የሞትን ሥልጣን ያስወገደው እርሱ በመሬት ተቀብሮ እንደማይኖርና ሰማያዊ ስለሆነም ወደ ሰማይ የወጣ መሆኑን ለመገንዘብ አይችሉም፡፡”
‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ›› ግራ የተጋቡትንና የፈሩትን ሰዎች ለማረጋጋት የሚላኩት ቅዱሳን መላእክት ዛሬም ትንሣኤውን ለማብሰርና የፈሩትን ለማረጋጋት ተገልጠዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሲገልጽ “የጌታን መወለድ ለእረኞች ለማብሰር መላእክት ተገልጠው ነበር፡፡ አሁን ደግም ትንሣኤውን ይነግሩን ዘንድ መጡ፡፡ የሰማይ ሠራዊት በሥጋ የተገለጠውን በአምላክነቱ ያከብሩታል፡፡ በሥጋ በመገለጡ አምላክነቱ የቀረ አይደለምና አሁንም አምልኮታዊ አገልግሎታቸውን ይቀጥላሉ፡፡”
ቅዱስ ቄርሎስ ደግሞ “ሴቶቹ ጌታን ፈልገው ወደ መቃብር ቢገቡም በዚያ አላገኙትም፤ ምክንያቱም እርሱ ሕይወት ነውና” ካለ በኋላ ቀጥሎም “ሴቶቹ ወደ መቃብሩ ሲቀርቡ የጌታን ሥጋ አላገኙም፤ በዚህም ግራ ተጋቡ፡፡ ከዚያስ ምን ተከተለ? ስለ ፍቅራቸውና ለጌታ ስለ መቅናታቸው መልካሙን የምስራች የሚነግሯቸው መላእክት ይገለጡላቸው ዘንድ የተገቡ ሆኑ፡፡ ‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ? በዚህ የለም ተነሥቷል› ሲሉም ነገሯቸው፡፡”
     ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም፡፡›› አውግስጢኖስ ይህን ኀይለ ቃል ሲያብራራ “የእግዚአብሔር ቃል ለዘወትር ሕያው ነው፤ በባሕርዩም ሕይወት ነው፡፡ በትሕትና ራሱን ዝቅ ሲያደርግና ራሱን ባዶ ሲያደርግ እንደ እኛ እንደ ባርያዎቹ ለመሆን ራሱን አቀረበ፤ እንደ እኛ ሞትን ቀመሰ፡፡ የእርሱ መሞት ግን የራሱ የ“ሞት” መሞት መሆኑ ታውቋል፡፡ ምክንያቱም እርሱ ጌታችን ከሞት ተለይቶ በማይሞት ሰውነት ተነሥቷልና፡፡ እንግዲህ ማንም ከሙታን መካከል ሕያው የሆነውን እርሱን አይፈልግ፡፡ እርሱ በሞትና በመቃብር ውስጥ “በዚህ የለም” ከተባለ እንግዲህ ወዴት ነው ያለው? ግልጥ ነው፤ በሰማያት በመለኮታዊ ክብሩ ነው፡፡”
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ስለ ትንሣኤው ኹኔታ ሲናገር “ጌታችን ሲነሣ ልብሶቹን በመቃብር ውስጥ ትቶ ከሆነ የተነሣው (በእርግጥም ነውና)÷ ይህ ነገር የሚገልጠው አዳም ከመውደቁ በፊት በነበረበት ኹኔታ ልብስ ሳያስፈልገው ወደ ገነት እንደሚገባ ነው፡፡ ወደ ገነት ለመግባት አስቀድሞ ልብሶቹን በማውለቅ ዕርቃኑን ሊሆን ይገባዋል፡፡ ‹‹አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ አይተፋፈሩም ነበር›› (ዘፍ 2፡25) እንደተባለው፡፡ በሌላ አተረጓጎም ደግሞ ብናየው ልብሶቹን በዚያ የተዋቸው የምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ሁኔታ እንዴት እንደሚሆን ለመግለጥ ነው፡፡ እርሱ ከሙታን ሲነሣ ያለልብስ እንደ ነበር እኛም ከሙታን ስንነሣ ሥራችንን ይዘን እንጂ ልብሳችንን ይዘን አይደለም፡፡”
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደመሠከሩት ጌታችን ሲነሣ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ አላለም፡፡ ሞትን ድል ነሥቶ የወጣው በተዘጋ መቃብር ውስጥ ነው፡፡ ይህንንም አንድ የሰባተኛው ክፍለ ዘመን ሊቅ ሲገልጠው “መልአኩ ድንጋዩን ያንከባለለው ከሞት የተነሣው ጌታ እንዲወጣ ለማድረግ ሳይሆን ሰዎች በእውነት ቀደም ብሎ እንደ ተነሣ አይተው ለማመን እንዲችሉ ማስረጃ ይሆናቸው ዘንድ ነው፡፡ የድንግል ማኅፀን ኅቱም እንደሆነ መቃብሩም ዝግ ነበር፡፡ ወደ ዓለም በኅቱም ማኅፀን እንደገባ ከዓለምም ሲወጣ በኅቱም መቃብር አማካኝነት ነው፡፡” ጌታችን ከኅቱም መቃብር የመነሣቱን ነገር የማቴዎስ ወንጌል ይበልጥ ግልጥ ያደርገዋል፡፡ እንዲህ በማለት፡- ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመ›› (ማቴ 28፡2)፡፡
‹‹የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ፡፡›› ይህን ኀይለ ቃል መሠረት ያደረገ አንድ መተርጕም ደግሞ “የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ፤ የምናምንበትን እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ያደርገን ዘንድ፡፡ በኀጢአተኞች እጅ ተያዘ፤ በኀጢአት ከመያዝና ከርኩሳን መናፍስት እስራት ነፃ ያወጣን ዘንድ፡፡ ደግሞም ተሰቅሎ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሣ፤ እኛም መከራ ከመቀበል ትሩፋት ተሳታፊ እንድንሆን፣ የትንሣኤ ሙታን ተስፋም ይኖረን ዘንድ” ሲል አስተምሯል፡፡


‹‹ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም።›› ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ቃል መሠረት አድርጎ ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ስለ ትንሣኤው ያስተማረውን አላስታወሱም፤ እንዲያውም ስለ ትንሣኤ ምንም ነገር አላወቁም ይላል፡፡ “ስለ ትንሣኤ ምንም የተረዱት ነገር እንደ ሌለ አስተዋለችሁን? ወንጌላዊው ይህን በግልጥ ነው ያስቀመጠው፡፡ ስለ ትንሣኤው ማስተዋል ካላመቻላቸው በተጨማሪ ስለሌሎች ነገሮችም ጥልቅ ግንዛቤው አልነበራቸውም፡፡ ይኸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት፣ እነርሱም ለመንግሥቱ የተመረጡ የመጀመሪያ ፍሬዎች ስለ መሆናቸው፣ ስለ እርገቱና ስለመሰለው ሁሉ አላወቁም፡፡ ገና ምድራውያን ናቸው፤ የሰማዩን ለማወቅ የሚረዳ መንፈሳዊ ክንፍ አብቅለው መብረር አልጀመሩም፡፡ የእነርሱ ግንዛቤ የነበረው ይህ ብቻ ነው፡፡ ይጠብቁ የነበረው መንግሥቱ ምድራዊ ሆኖ በፍጥነት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ ነው፡፡ ስለ ሰማያዊው መንግሥት መረዳቱ አልነበራቸውም፡፡ የደቀ መዛሙርቱ አመለካከት እንደዚህ እንደነበር ሌላው ወንጌላዊ ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡ በሰብአዊው መንግሥት ውስጥ እንገባለን ብለው ነበር የሚጠብቁት እንጂ ወደ መስቀል መከራና ወደ ሞት እንገባን የሚል ሐሳብ አልነበራቸውም፡፡ እልፍ ጊዜ ሲናገረው ያደመጡ ቢሆንም መረዳቱ ግን አልነበራቸውም፡፡”
የትንሣኤውን ዜና ሴቶች መናገራቸውን በተመለተ አውግስጢኖስ “ወደ መቃብሩ የመጡት ሴቶች በመቃብሩ ውስጥ ምንም አላገኙም፡፡ በጠበቁት ነገር ፈንታ መላእክት የመነሣቱን የምስራች ነገሯቸው፡፡ ሴቶቹ ይህን ዜና ለወንዶቹ ነገሯቸው፡፡ ከዚያስ የተጻፈው ምን ይላል? ወንዶቹ ‹‹ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም›› የሰው ኹኔታ እንዴት አሳዛኝ ነው! ሔዋን ከእባብ ጋር ተቀራርባ የሰማችውን ነገር እንዳለ ተቀበለችው፤ ሐሰተኛዋ ሴትም በመታመኗ ምክንያት እኛ ሁላችን ሞትን፡፡ ሕይወት የሚሆነውን እውነተኛ ዜና ባመጡ ጊዜ ግን ሴቶቹ አልታመኑም፡፡ ሴቶች ሊታመኑ ካልቻሉ አዳም ሔዋንን ለምን አመናት? ሴቶች ሊታመኑ ከተገባቸው ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ቅዱሳት ሴቶቹን ለምን አላመኗቸውም? ጌታችን ግን ይህን ያደረገው ሊያስተምረን ነው፡፡ ለትምህርታችን ብሎ የትንሣኤውን ምስራች ለመጀመሪያ ጊዜ ለሴቶች ገልጦ እንዲገልጡት አደረጋቸው፡፡ የሰው ልጅ የወደቀው በሴት ምክንያት ነበርና አሁንም ትንሣኤው በሴት በኩል እንዲታወጅ አደረገ፡፡ ድንግል ክርስቶስን ወለደች፤ ሴቶችም ትንሣኤውን ቀድመው አወጁ፡፡ በሴት በኩል ሞት ሆነ፤ በሴት በኩልም ሕይወት ሆነ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን አላመኑም፤ እውነትን የሚናገሩት ሴቶች እየቃዡ እንደሆነ አሰቡ እንጂ፡፡”
አውግስጢኖስ ሲቀጥልም እንዲህ ይላል፡- “ይህን ተስፋ፣ ይህን ስጦታ፣ ይህን ቃል ኪዳን፣ ይህን የበዛ የተትረፈረ ጸጋ ክርስቶስ ሲሞት ደቀ መዛሙርቱ ጨርሰው ረሱት፤ ከመንፈሳቸው ተሰወረባቸው፡፡ እርሱ ሲሞት ከተስፋ ተለዩ፡፡ በዚህ ቦታ የምናየው ደግሞ የትንሣኤውን ዜና ለማመን ሲቸገሩ ነው፡፡ ሴቶቹ የተናገሩት እውነት ነው፡፡ እውነት ግን እንደቅዠት ተቆጠረ፡፡ የትንሣኤው ዜና የተዘገበው ዛሬ ቢሆን እንዲህ ዓይነት ምላሽ አያገኝም ነበር? ያንን ዜና ላለመስማት ጆሮውን የማይዘጋ ማን ይኖራል? ደቀ መዛሙርቱ የሆኑት እንዲያ ነው፡፡ ዛሬ ግልገሎቹን የሚያንቀጠቅጠው ያለማመን በሽታ በኮርማዎቹ ላይ ጥንት የነበረ ነው፡፡”
ሌላ ሊቅ ደግሞ “የደቀ መዛሙርቱ ጥርጥር ለእኛ የእምነት መሠረት ሆኗል” ይላል፡፡ “ጥርጥራቸውና ፍርሐታቸው እንዲሁም ለማመን መዘግየታቸው ለእኛ ማመን መሠረት ባይሆን ኖሮ÷ የእውነት መንፈስ ይህን ዓይነቱን ማቅማማትና ጥርጥር በወንጌል መምህራን ልቡና ውስጥ እንዲኖር አይፈቅድም ነበር፡፡ በደቀ መዛሙርቱ የተገለጠው አለማመንና አደጋ ውስጥ የመሆን ስሜት የእኛን አለማመንና አደጋ ውስጥ መሆን አመልካች ነው፡፡ (እነርሱ በእኛ ተገብተው) በመጠራጠራቸው በምድራዊ ጥበብና በሥጋዊ ድካም ውስጥ ሆነን ትንሣኤውን ለማመን እንደምንቸገር ይገልጣል፡፡ የእነርሱ ተጠራጥረው ነገሩን አይተው ለማጣራት በመፈለግ ወደ መቃብሩ መጓዛቸውና አይተው ማረጋገጣቸው ዛሬ ለእኛ እምነት መሠረት ሆነ፤ የእነርሱ መዳሰስ ለእኛ ጥንካሬን ሆነን፡፡ የመለኮታዊውን ዕቅድና አሠራር እንዲሁም ለማመናችን አስፈላጊ የነበረውን የደቀ መዛሙርቱን [ለማመን] መዘግየት እናመስግን፡፡ እነርሱ “ተጠራጠሩ” ስለዚህም እኛ መጠራጠር አይኖርብንም፡፡ ለእኛ መጠራጠር እነርሱ አስቀድመው ምላሽ ሰጡት፡፡” (2ኛ ዮሐ 1፡1-3 ሉቃ 24፡25) ይህ ሊቅ እንደ ገለጠው ለጊዜው ለደቀ መዛሙርቱ ፈታኝ የነበረው ኹኔታ ለዛሬው እምነታችን የሚኖረውን ጠቀሜታ ልብ ብለን በትንሣኤው ብርሃን እምነታችንን እንድናጠነክር የትንሣኤው አምላክ ይርዳን፡፡ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

1 comment:

  1. አሜን አሜን። ቃለ ህይወት ያሰማልን ።

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount