(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ኒቆዲሞስ ማለት ድል አድራጊ፣ የሕዝብ አለቃ ማለት ነው፡፡ እውነትም ይህ ሰው አለቃ ነበር፡፡ አለቅነቱስ እንደ ምን ነው? ቢሉ በሦስተ ወገን ነው፡-
(ሀ) በሹመት፡-
የአይሁድ ሸንጎ - ማለትም የሳንሄድሪን - አባል ነበርና፡፡ ይህ እንግዲህ (ምንም እንኳን የሚያውክ ንጽጽር ቢኾንም) በእኛ ስናየው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የኾነ አንድ ሊቀ ጳጳስ እንደ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ዝቅ ብሎ ሊማር መጣ፡፡ ከማን? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ይበልጥ እንደነቃለን፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን ጓደኞቹ ትምህርትን የማይወዱ፣ እውነትን የሚጠሉ፣ ጌታችንን ለመግደል ዕለት ዕለት የሚመክሩ ቀናተኞች ቢኾኑም ኒቆዲሞስ ግን ከእነርሱ ተለይቶና ሹመቱ ሳያስታብየው በሥጋ ዕድሜ ከእርሱ ከሚያንስ ከጌታችን ዘንድ ሊማር ነውና የሚመጣው፡፡ እስኪ ትልቅ ጥምጣሙን አድርጎ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ሲማር በዓይነ ሕሊናችሁ ሳሉት! እንደ ምን ያለ ትሕትና ነው? እንዴት እውነትን የተጠማ ሰው ነው? “ቀን አይመቸኝምና ማታ አልሔድም፤ እንደዉም ጥሩ ምክንያት አገኘሁ” አላለም፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ተመሳስዬ ልኑር አላለም፡፡ ጌታችን የወደደውና ለትውልድ ኹሉ የተረፈ ምሥጢር - ስለ ጥምቀት - ያስተማረውም ስለዚሁ ግሩም ትሕትናውና ቅንዓቱ ነው፡፡ “ሥራህን ትተህ ለምን በቀን አትመጣም?” አላለውም፡፡ “አንተን ብቻ አላስተምርም” አላለውም፡፡ “ለምን ጓደኞቼ ያዩኛል ብለህ ፈራህ?” አላለውም፡፡ “ለምን እንደ ዕሩቅ ብእሲ ቈጥረህ መምህር ትለኛለህ?” አላለውም፤ በፍጹም፡፡ ሹመቱና እልቅናው ሳይታሰበው ዝቅ ብሎ ሊማር መጥቷልና፡፡ “አለቃ ስኾን እንዴት ለመማር - ያውም በጨለማ - እሔዳለሁ?” አላለምና፡፡ በመኾኑም ቸሩ ጌታችን እንደ ሳምራይቱ ሴት ለብቻውም ቢኾን የማታ ክፍለ ጊዜ አዘጋጀለት፡፡
(ለ) በዕውቀት፡-
እንዲህ ዓይነቱን ሰው ሊቃውንት፡- “ሞልቶ የሚያስጨምር” ይሉታል፡፡ ጎዶሎ ኾኖም የማያስጨምር አለና፡፡ ትምህርት የሚወደው የተማረ ሰው ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው፥ ኒቆዲሞስ ጌታችንን ለመግደል ሌት ተቀን ከሚያሴሩት ከፈሪሳውያን ወገን ነው፡፡ ነገር ግን ለትምህርት መጣ፤ ከተማረ አይሳደብምና፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተማረ ሰው ይወዱ ነበር ይባላል፡፡ ስለኾነም ብዙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጪ አገር እየሔደ እንዲማር ያደርጉ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ውጪ ሲላኩ እሳቸውን የማይወድ፣ እየዞረ ስማቸውን የሚያጠፋና የሚሳደብ አንድ ተማሪም ዕድሉን አግኝቶ ወደ ውጪ አገር ለመሔድ ተፍ ተፍ ይላል፡፡ ይህ ተማሪ ለአቡነ ቴዎፍሎስ በጎ ነገር የማያስብ መኾኑን የሚያውቁ ሰዎች ይቀርቧቸውና ስም እየጠቀሱ፡- “እንዴት እርሱን ወደ ውጪ አገር ልከው ያስተምሩታል” ይሏቸዋል፡፡ “እኮ እንዴት ለምንድን ነው የማይሔደው” በማለት ይጠይቃሉ፡፡ “እርሱኮ ለእርስዎ የማይተኛ እየዞረ ስምዎን የሚያጠፋ የሚሳደብ ነው” ይሏቸዋል፡፡ “የሚሳደበው እኮ ስላልተማረ ነው፡፡ ይሒድና ይማር፤ ከተማረ አይሳደብም” አሉ ይባላል፡፡ አውግስጢኖስ የተባለ ሊቅም፡- “እኔ በግሌ ቆሜ ከማስተማር ይልቅ ቁጭ ብሎ መማር ታላቅ የኾነ ሐሴት ይሰጠኛል” ብሏል፡፡ ኒቆዲሞስ ይህን ይመስላል፡፡ ምናልባትም’ኮ አብዛኞቹ ፈሪሳውያን ወንድሞቹ እንዳደረጉት ባይመጣና “ብመጣስ ምን አዲስ ነገር አገኛለሁ?” ቢል ኖሮ ዕውቀቱ ብሉይ መኾኑን ባላወቀ ነበር፡፡ እንዲሁ ዝም ብሎ ከሩቁ ኾኖ ጌታችን ላይ ቢፈርድ’ኮ ፍርጃው ስሕተት መኾኑ ባላወቀ ነበር ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ሰው ስላስጮኸው ብቻ እውነት መስሎን ስንት ጊዜ ፈርደን ይኾን? ኒቆዲሞስ ግን እንዲህ ይለናል፡- “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? “ /ዮሐ.7፡51/፡፡
(ሐ) በሀብት፡-
የአይሁድ ጽሑፎች የኒቆዲሞስ ሀብት መጠን ሲናገሩ “ለብዙ ዐሠርት ዓመታት የኢየሩሳሌምን ሕዝብ መመገብ የሚችል” ይሉታል፡፡ ግን ይማራል፡፡ ዛሬ ባለጸጎች እንደ ኒቆዲሞስ ቢማሩ ሀብታቸው የራሳቸው እንዳልኾነ በተረዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው፡- “ሀብት ከእግዚአብሔር በአደራ የሚረከቡት ንብረት” ነውና፤ እንዲጸድቁበት፡፡
እንግዲህ ተመልከቱ! በሰው ሰውኛ ኒቆዲሞስ ምንም የጎደለው ሰው አይደለም፡፡ ሹመት አለው፤ ዕውቀት አለው፤ ሀብትም አለው፡፡ በሹመታችን፣ በዕውቀታችን፣ በሀብታችን የምንመካ ሰዎች እስኪ ራሳችንን ከኒቆዲሞስ ጋር እንመዝነው፤ ያውም’ኮ በዚሁ ሰዓት ክርስቲያን አይደለም፤ ገና አይሁዳዊ ነው፡፡ አዎ! ይህ ኹሉ ያለ እግዚአብሔር ባዶ ነው፡፡ የማይሻረው ሹመት፣ የማይጠፋው ዕውቀት፣ ብል የማይበላው ሀብት ክርስትና ነው፤ ኦርቶዶክሳዊነት፡፡
No comments:
Post a Comment