Tuesday, April 26, 2016

ስግደት (ክፍል 4)

በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 18 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በሰሙነ ሕማማት የግዝት በዓል ቢሆን እንኳን ይሰገዳል!
የዘንድሮው የስቅለት በዓል 21 የሚውል በመሆኑና ዕለቱም የግዝት በዓል በመሆኑ ይሰገዳል ወይስ ይተዋል የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሡ ይስተዋላል፡፡ በዚህ በአራተኛ ክፍል ስግደትን በተመለከተ ጽሑፋችን ስግደትን ከሰሙነ ሕማማት ጋር አያይዘን እናነሣለን፡፡ በቀደሙት ክፍሎች መሠረታዊ የኦርቶዶክሳዊ ስግደት ይዘትንና ሥርዐትን የዳሰስን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ 
በሰሙነ ሕማማት የግዝት በዓል ቢሆን እንኳን ይሰገዳል፡፡ ለዚህ ምክንያቶችን ላስቀምጥ፡-

1. በቤተ ክርስቲያናችን የየትኛውም አይነትሥርዐት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ (8ቱን የሥርዐት መጻሕፍት ጨምሮ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመቀጠል የቤተክርስቲያን ጉባኤያትና የሊቃውንት አስተምህሮዎች በቤተክርስቲያን ሥርዐት ምንጭነት ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን በሥርዐት ምንጭነት የምንገለገልበት ፍትሐ ነገሥትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ከጉባኤያትና ከሊቃውንት አስተምህሮ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ከሠለስቱ ምዕት) ጀምሮ በመዘጋጀት እኛ ጋር የደረሰ ነው፡፡ ሆኖም መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕጎችን በሁለት ከፍሎ የሚዳስሰው ይኸው መጽሐፍ በተለይ በመንፈሳዊው ክፍሉ 22 ዋና ዋና መንፈሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሥርዐትን ሲደነግግ ‹‹ስግደትን›› ለብቻው በርእስነት አላነሣም፡፡ ሆኖም 19ኛው አንቀጽ ስለ እሑድና ስለ በዓላት ሲያነሣ ቁጥር 715 ላይ ‹‹በእሑድና በተከበሩት በዓላት ቀን ስግደት አይገባም እነዚህ የደስታ ቀኖች ናቸውና›› ይላል፡፡ ነገር ግን በዓላት ብሎ የጠቀሳቸውን በዚሁ አንቀጽ በቁጥር 724 ላይ ስናይ ስቅለትን ከመካከላቸው አናገኝም፡፡ አንቀጹ በዓላት ብሎ በጠቀሳቸው ልደት ጥምቀት ትንሣኤመስገድና መጾም በርግጥም አግባብ አይደለም፡፡ አንቀጽ 19 ስለ ስቅለት ያነሣው በቁጥር 730 ላይ ከሰሙነ ሕማማት ጋር ሥጋዊ ሥራን በወቅቱ መሥራት እንደማይገባ ለመግለጽ ሲል ብቻ ነው፡፡ (የተጠቀምሁት 1990.. በፓትርያርኩ ፈቃድ በትንሣኤ ዘጉባኤ የመጻሕፍት ማሳተሚያ ድርጅት የታተመውን ፍትሐ ነገሥት ነው፡፡)
ስለ ስግደት በስፋት (በአንጻራዊነት) የተነገረበት አንቀጽ ስለ ጸሎት የሚያትተው አንቀጽ 14 ነው፡፡ አንቀጹ ጸሎት ምን ምንን ማካተት እንዳለበት 6 ነጥቦችን ሲዘረዝር 6ኛነት ያነሣው ስግደትን ነው፡፡ (በጸሎት ውስጥ መደረግ ያለባቸው ሥርዐቶች፡- 1.መቆም 2.ወገብን በዝናር መታጠቅ 3.ወደ ምሥራቅ መዞር 4.በመስቀል አምሳል ማማተብ 5.በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የጸሎትን ቃላት ማንበብ 6.መስገድ ናቸው፡፡ /.. አን.14. .528-535) አንቀጽ 14 ቁጥር 536 እና 537 እንዲህ ይላሉ ‹‹የሚሰገድባቸው ጊዜያቶችና ቁጥሮች በቤተክርስቲያናችን ተጽፈዋል፡፡ የሚጸልይ ሰው በጸሎት ጊዜ ስግደትን ከሚያነሣ አንቀጽ ሲደርስ ለልዑል እግዚአብሔር ይስገድከአድንኖና ከአስተብርኮ በቀር እስከ ምድር መስገድን የሚተውባቸው የታወቁ ጊዜያቶች እነዚህ ናቸው፡፡ኒቅያ 20 በዕለተ እሑድና በበዓለ ሃምሳ ወራት ኒቅያ 32 በጌታችን በዓላትና በእመቤታችን በዓላት፣ ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ፤››፡፡ 
እዚህ ልብ ልንለው የሚገባው የጌታችንና የእመቤታችን በዓላት የምንላቸው የትኞቹን እንደሆነ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ የጌታ በዓላትን ከላይ እንደጠቀስነው በአንቀጽ 19 ይዘረዝራቸዋል፡፡ እንግዲህ ከስቅለት በስተቀር በነዚህ በዓላት እንደማይሰገድ ከላይም ገልጸናል፡፡ ፍትሐ ነገሥቱ ከዘረዘራቸው ዐበይት በዓላት በተጨማሪ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ሌሎቹ የሥርዐት ምንጮች ከሆኑት ሊቃውንት የተማርናቸው 9 የጌታ ንዑሳን በዓላት አሉ፡፡ በነዚህ በዓላት ይሰገድ አይሰገድ ፍትሐ ነገሥቱ ያለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ በዓላት የጌታ በዓላትን በምናስብበት ወር በገባ 29ኛው ዕለት ውስጥ የተካተቱ ይመስላሉ፡፡ ወር በገባ 29ኛው (ዓመታዊው መጋቢት 29 ነው) ቀን ሁለት ዐበይት በዓላትን እንደምናስብ ልብ ማለትም ተገቢ ነው፡፡ አንዱ በዓለ ትስብእት /የጌት ጽንሰት/ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ትንሣኤው ነው፡፡ በዓለ ትስብእትን በታላቁ ጾም ውስጥ ለማክበር ስለማያመች፣ ስለ በዓሉ ታላቁን ጾምም ማቋረጥ ስለማይገባ በሥርዐተ ቤተክርስቲያን በታወቀ ምክንያት ወደ ታኅሣሥ 22 የተዛወረ ነው፡፡ ትንሣኤም ሁልጊዜ መጋቢት 29 እንዳይከበር፣ ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዝያ 29 ቀን ድረስ በኢይወርድና በኢይዐርግ ተወስኖ እንዲከበር ሥርዐተ ቤተክርስቲያን ያዛል፡፡ (በዓላት፣ / ብርሃኑ አድማስ ፤ፍት.ነገ. አን.19. . 728-731)፡፡ እንግዲህ 29 የማይሰገድበት የሚያደርጉት 1.በዕለቱ ትስብእቱን በማሰብ 2.ትንሣኤውን በማሰብ 3.ሌሎች የጌታ በዓላትን ጠቅልለን በማሰብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጾመ ኢየሱስ /ዐቢይ ጾም/ ደግሞ ከጾሞች ሁሉ ታላቅ ነውና በሌሎች ጾሞች የሚፈቀዱ በዚህ ጾም ግን የማይፈቀዱ ነገሮች (እንደ ሰርግ፣ የከበሮ አገልግሎት…) አሉት፡፡ ሰሙነ ሕማማት ደግሞ ከዚህም ይበልጥ ብዙ ነገሮች /ሥርዐተ ቅዳሴን ጨምሮ - ከዕለተ ሐሙስ በቀር/ የተገዘቱበት /የተከለከሉበት/ ወቅት ነው፡፡ አባቶቻችን ይህን ያውቁ ስለነበር በዓለ ትስብእትን በዐቢይ ጾም ወይም በሕማማት መኻል መጥቶ ጾሙን መሻርም ሆነ በዓሉን አለማክበር አግባብ ስላልሆነ ወደ ታኅሣሥ 22 ወሰዱት፡፡ ልብ በሉ ታኅሣሥ 22 ራሱ የጾም ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን ሕጉ እንደ ዐቢይ ጾም የማይጠብቅበት የነቢያት/የገና ጾም ነው በታኅሣሥ ያለው፡፡ ስለዚህ ሳንሰግድ ነገር ግን ከበሮ እየመታን በዓለ ትስብእትን እናከብራለን፡፡ ሌላው 29 ትንሣኤን አስበን ዕለቱ በሕማማት ቢሆን እንኳን አንሰግድም ካልን ከስቅለት በፊት ትንሣኤን የማክበር አመክንዮአዊ ስሕተት ውስጥ እንገባለን - ካለ ሕማም ካለ ሞት ትንሣኤ የለምና፡፡ የኛ በዓለ ትንሣኤ ደግሞ ከሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደነበሩት ክርስቲያኖች መጋቢት29 ጠብቆ ሰኞም ማክሰኞምየሚከበር ሳይሆን በሠለስቱ ምዕት ድንጋጌና በኒቂያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ከእሑድ ውጭ የማይከበር ነው፡፡ ሦስተኛው ንኡሳን የጌታ በዓላትን አስበን 29 ሕማማት ውስጥ ከሆነ አንሰግድም ካልን ስለ ወርኀዊ በዓል ዓመታዊውን ስለ ንዑሱ /ታናሹ/ ዐቢዩን /ታላቁን/ መሻር ይሆንብናል፡፡
ሐሳባችንን የሚያጠናክርልን ሌላኛው መረጃ ደግሞ ፍትሐ ነገሥት ስለ ቀዳም ሥዑር የገለጸበት ክፍል ነው፡፡ በሰንበት እንዳይጾምና እንዳይሰገድ ፍትሐ ነገሥቱ በአንቀጽ 14 ማዘዙን ቀደም ሲል አይተናል፡፡ ነገር ግን ከሰንበቶች አንዷ በምትሆነው ከትንሣኤ በፊት ባለችው ቅዳሜ እንዲጾም መልሶ ያዛል /አንቀጽ 19 ቁጥር 577/፡፡ ይህም የጌታን ሕማማቱንና ሞቱን በማሰብ ነው፡፡ ይህም ስለ ሕማማቱ የሚሠራ ሥርዐት ከሌላ ሥርዐት ንዑስ /ታናሽ - የሚያንስ/ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ደግሞ ሕማማቱን በሐዘን በጾም በስግደት የጌታን መከራ በማሰብ እንዲከበር ያዛልና በሌላ ንዑስ ሥርዐት የሚሻር አይደለም፡፡ በሰንበት አትጹም የሚለው ትዕዛዝ በሕማማት ጹም ለሚለው የተገዛ ሆነ፡፡ ይህች ቅዳሜምቀዳም ሥዑር - የተሻረችው ቅዳሜተባለች፡፡ የግዝት ዕለታትም በሕማማት ከዋሉሥዑር ዕለታትይሆናሉ ማለት ነው፡፡
2. እንዲህ አይነት ግራ መጋባት ሲፈጠር መጻሕፍትን ከማየት ባሻገር በጊዜያችን የሚገኙ ሊቃውንት ምን እንደሚሉ መስማት ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትም ግዴታም ነውና ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በጊዜያችን የተገኙ የሥርዐተ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ምን እንዳሉ እንመልከት፡፡ ሚያዝያ 2004 .. ላይ የሰምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስምዐ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት) በሚል ርእስ ሰሙነ ሕማማትን ብቻ የተመለከቱ ጉዳዮችን ለንባብ አብቅተው ነበር፡፡ ከአርእስተ ጉዳዮቹ አንዱየግዝት በዓላት በሰሙነ ሕማማት ቢውሉ ይሰገዳልን?› በሚል ሁለት ሊቃውንት የተጠየቁበት ክፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና የዕቅድ መምሪያ ምክትል ኃላፊ እንደሆኑ የተገለጸው ሊቀ ትጉሃን ኃይለጊዮርጊስ ዳኘ ለጥያቄው የሚከተለውን ምላሽ በተለይ ስቅለት ላይ አተኩረው ሰጥተዋል፡፡
‹‹የሰሙነ ሕማማት ቀናት የጌታችንን መከራና ሥቃይ የምናስብበት፣ የሐዘን የመከራ ጊዜያት ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ስቅለት ከጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ በመሆኑ በዓሉ ራሱ የሚከበረው በስግደት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ በዓሉ የጌታን መከራና ሥቃይ መንገላታቱን የምናስታውስበት በመሆኑ በዓሉ የሚከበረው በስግደት በጾምና በጸሎት በንባብና በትምህርት ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን በዓል የሚሽር ምንም አይነት የግዝት በዓል የለም፡፡ የግዝት በዓላት በየወሩ በውዳሴና በቅዳሴ የምናከብራቸው ወርኃዊ በዓላት ይኼንን በዓመት አንድ ቀን የሚመጣን ልዩና ዐቢይ በዓል ይሽሩታል የሚል ትምህርት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አላስተማሩንም፡፡›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በሞት የተለዩንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የነበሩት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬም የሚከተለውን ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹…በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት፣ ክህነት መስጠት፣ ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም፤ የቤተክርስቲያን ቀኖና ሕማማቱ በሐዘን፣ አብዝቶ በመጾም፣ ስለመከራው በማሰብ፣ በስግደት እንዲከበሩ የሚያሳስብ መመሪያ የተላለፈበትን በዓል በወር የሚከበሩ የግዝት በዓላት አይሽሩትም፡፡ የሰሙነ ሕማማት በዓል ልዩና የስቅለቱን፣ የመከራውን፣ የሕማሙን ነገር የምናስብበት በመሆኑ መከበር የሚገባው በስግደት ነው፡፡ የሊቃውንቱም ትምህርት ይኸው ነው፡፡›› (ስምዐ ተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 2004.. ገጽ 24-25) ስለዚህ የዘንድሮው ስቅለት 21 በመሆኑ ምንም አይነት ለውጥ አይደረግም፡፡ በዓሉ እንደ ቀድሞው በስግደት ይከበራል፡፡

እኔም ስግደትን የተመለከቱ ጽሑፌቼን በዚህ በመጨረስ ክፍል አበቃሁ፡፡
በሥርዐትና በጥንቃቄ የምናመልከው አምላካችን ከሥርዐት እንዳንወጣ ይጠብቀን፤
ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም

4 comments:

  1. amen wendmachn edme tena ystih fetari ketlew ayzoh end ante yalu memahran ayasatan amlakachn

    ReplyDelete
  2. እግዚአብሔር ይስጥልን በጣም ጠቃሚ መረጃ ነው የሰጠኸን እናመሰግናለን

    ReplyDelete
  3. በጣዕም ኣመሰግናለሁኝ፡ግን ኣንድ ጥያቄ ኣለኝ፡
    እርሱ ድግሞ፡ሶስይ ዓይነት መልስ ሰማሁት፡
    1፥ኣንድ ከኢትዮጵያ ቆሞስ ኣይሰገድም ኣሉ፡
    2፥መምህር ዘበነ ለማ፡በኣስተብርኮ እንጂ፡ምሉ በምሉ ፊትህን መሬት ኣይደረስም ኣሉ፡
    3፥እርስዎ ደግሞ፡ምሉ በምሉ ይሰገዳል ኣልክ።
    ስለዚ የንየ ጥያቄ፡
    *እርስ በርሳችሁ ተስማምታትችሁ ልምን ኣስቀድሞ ኣንድ ዕይነት መልስ ያልሰጥታችሁን ነው?
    ኣመሰግናለሁኝ፡መልካም በዓል ለሁላችን፡

    ReplyDelete
  4. በጣም አስተማሪ እና ህይወት የሚሰጥ ትምህርት ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን !
    ናይ አገልግሎትኩም ዘመን ይባርክ .

    ReplyDelete

FeedBurner FeedCount