በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ
ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 17 ቀን፣ 2008
ዓ.ም.)፡-
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ስግደት ለመላእክት ይገባልን?
መጽሐፍ ቅዱስ ለመላእክት መስገድ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ሰዎች ለእግዚአብሔር መላእክት ይሰግዱ ነበር፡፡ የሚከተሉትን በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡
† በለዓም ባልታዘዘው መንገድ ሲሔድ፣ መሔዱን እግዚአብሔር አልወደደምና የእግዚአብሔር መልአክ ሊከለክለው መጣና ከመንገዱ ቆመ፡፡ በለዓም መልአኩን ማየት ባይችልም የበለዓም አህያ ግን ከፊቷ የቆመውን መልአክ ዐይታ አልሔድም ብላ ቆመች፡፡ በለዓምም ሦስት ጊዜ ደበደባት፡፡ በመጨረሻም አህያይቱ በሰው አንደበት አናገረችው፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር የበለዓምን ዐይን ከፈተና መልአኩን ማየት ቻለ፡፡ ለመላእክት ስግደት ይገባልና ወዲያውም ሰገደለት፡፡ መልአኩም አልተቃወመውም፡፡ “እግዚአብሔርም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ ዐየ ሰገደም፤ በግንባሩም ወደቀ፡፡” ዘኁ. 22፡31፡፡
† በመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ ኢያሱ ለእግዚአብሔር መልአክ ሰግዷል፤ “እንዲህም ሆነ ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ ነበር፤ ኢያሱም ወደርሱ ቀርቦ ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህን?አለው፡፡ እርሱም አይደለሁም እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደና ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው አለው፡፡ የእግዚአብሔርም ሠራዊት አለቃ ኢያሱን አንተ የቆምህበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው፡፡ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፡፡” ኢያ. 5፡13-15፡፡
ኢያሱ በመጀመሪያ መልአኩን ሰይፍ ይዞ በሰው አምሳል ሲያየው አልሰገደለትም፡፡ ወይ ከእነርሱ ወይ ደግሞ ከጠላት ወገን ያለ ጦረኛ መስሎት ነበር፡፡ በኋላ ግን መልአክነቱ ሲገለጥለት ለመላእክት ስግደት እንደሚገባ በደንብ ያውቃልና ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለት፡፡ መልአኩም አልተቃወመም፡፡
† ነቢዩ ዳንኤልም መልአኩ ሲገለጥለት በፍርሐትና በመደንገጥ መሬት ላይ በመውደቅና በመደፋት ሲሰግድለት መልአኩ ዳስሶታል፡፡ ዳን. 8፡17-18፡፡
† ባለራእዩ ዮሐንስም በራእይ 19፡10 ላይ ለመልአኩ ሰግዷል፡፡ መልአኩ ምንም አንኳን እንዳይሰግድለት ቢነግረውም ዮሐንስ ግን በራእይ 22፡8 ላይ በድጋሚ ሰግዶለታል፡፡
ለአብነት ያህል እነዚህን አነሣን እንጂ ለመላእክት ስግደት እንደሚገባ የሚያስተምሩ ጥቅሶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ለመላእክት ሰግደዋል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግን አሁንም መልአኩ ዮሐንስን አትስገድልኝ ብሏል በማለት ለመላእክት ስግደት እንደማይገባ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ይህ ልክ አለመሆኑን እንደሚከተለው እናሳያለን፡፡
መልአኩ ዮሐንስን ለምን እንዳይሰግድለት ጠየቀው?
ከሁሉ በፊት እስኪ ጥቅሱ ምን እንደሚል ልብ ብለን እናንብብ፤ ራእይ 19፡10 “ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ እርሱም እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ”
ራእይ 22፡8-9 “ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ፡፡ በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ፡፡ እርሱም እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ፡፡”
ሁለቱን ጥቅሶች ከመተንተናችን በፊት ‹መልአኩ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ” ሲል ሁለት ጊዜ ከልክሎታልና ለመላእክት ስግደት አይገባም› የሚሉ ወገኖች ጥያቄያቸው ስሕተት መሆኑን (አጠያየቁ ራሱ ማስተዋል የሌለበት መሆኑን) ለማመልከት ሦስት አመክንዮአዊ ነጥቦችን ላንሣ፡፡
1ኛ. ለመላእክት የሰገዱ ቅዱሳን ብዙ ሆነው ሳለ ዮሐንስን ብቻ መልአኩ እንዳይሰግድ ጠይቆታል፡፡ በቁጥር ደረጃ ስናየውም ለመላእክት ሰግደው ያልተከለከሉት ብዙ ናቸው፡፡ ከላይ ካነሣናቸው እንኳን በለዓም ፣ ኢያሱና ዳንኤል በመስገዳቸው ተባርከዋል፡፡ ሎጥም እንዲሁ (ዘፍ. 19)፡፡ ዮሐንስ መናፍቃኑ እንዳሰቡት መስገዱ ስሕተት ነው ቢባል እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ አትስገድ የተባለ አንድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ (መስገዱ ግን ስሕተት አለመሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው)፡፡ ሌሎቹ ግን መስገዳቸው አስባርኳቸዋል፡፡ ስለዚህ አንድ ቅን ሰው ይህን የሚጠይቀው ‹ሌሎቹ ቅዱሳን ሲሰግዱ ያልተከለከሉበት ዮሐንስ ግን የተከለከለበት ምክንያት ምን ይሆን› ብሎ ነው እንጂ እንዲሁ ‹ዮሐንስ አትስገድ ስለተባለ አልሰግድም› በማለት አይደለም፡፡ እንዲህማ ከሆነ እኛም ‹በለዓም አትስገድ ስላልተባለ እንሰግዳለን› ፣ ‹ኢያሱ ሰግዶ ስለተባረከ እንሰግዳለን› ፣ ‹ዳንኤል ሰግዶ ስለተዳሰሰ እንሰግዳለን› በማለት ብቻ ከእነርሱ ይልቅ በብዙ ምሳሌዎች የታጀበ መልስን መስጠት እንችል ነበር፡፡ ዓላማችን ግን እነርሱንም መመለስ ነውና ዮሐንስ አትስገድ የተባለበትም ምክንያት እነርሱ እንደሚያስቡት ለመላእክት ስግደት ስለማይገባ እንዳልሆነ እናሳያለን፡፡
2ኛ. መልአኩ ለእርሱ በተገለጠለት በፍጥሞ ደሴት ሳለ ራእዩን ሲመለከት በመንፈስ ቅዱስ በተቃኘ አገልግሎት ውስጥ ነበር፤ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ” (ራእይ 1፡10) ብሏልና፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ ለመላእክት ስግደት ሳይገባ ሰግዷል ካልን የሰገደው በስሕተት ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ‹በመንፈስ ነበርሁ› ብሎ ነበርና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ተሳስቶ አሰገደው ወደሚል ክህደት ይመራናል፡፡ በመንፈስ የሆነ ሰው ከማይሳሳተው ቅዱስ መንፈስ ጋር ነውና የሚሠራው ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ በመንፈስ የነበረው ዮሐንስም በመንፈስ በነበረበት ጊዜ የሠራው ሁሉ ልክ ነበር፡፡ መስገዱም ልክ ነበር፡፡ አንዳንድ የዋሕ ምእመናንና መምህራንም ይህንን ባለመረዳት ‹ዮሐንስ በስሕተት ለአምላክ የሚገባ የባሕሪይ ስግደትን ለመልአኩ ስለሰገደለት መልአኩ ገሰፀው› ብለው ይሳሳታሉ፡፡ ሆኖም ይህ አባባል ስሕተት ነው፡፡ ቅዱሱ ሐዋርያ ለክርስቶስ የሚገባን ስግደትና ለመልአክ የሚገባን ስግደት የሚያውቅ ጻድቅ ነው፡፡ መስገዱም ትክክል ነው፡፡
3ኛ. ቅዱስ ዮሐንስ ተሳስቶ ሰገደና መልአኩ ገሰፀው ብንል እንኳን መድገሙ ስለምንድን ነው ልንል ነው? ስሕተት የሆነ ከሆነ እንደ ሐዋርያነቱ ፈጥኖ ‹ስሕተቱን› በማረም ለሁለተኛ ጊዜ አለመስገድ ነበረበት፡፡ መልአኩ ያለውን አልቀበል ብሎ ከሆነም መልአኩ መቅጣት ነበረበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን መላእክት የተናገሩትን አልሰማ ያሏቸውን ቅዱሳን ሲቀጡ ዐሳይቶናል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ የመልአኩን ቃል ባለመስማቱ ካህኑ ዘካሪያስ ተቀጥቷል፡፡ “መልአኩም መልሶ እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም፡፡” (ሉቃ.1፡19-20)፡፡ ታዲያ ዮሐንስስ ተሳስቶ ከሆነ አትስገድ ተብሎ እንደገና ሲሰግድ ለምን አልተቀጣም? ነው ወይስ የእግዚአብሔር ፍርድ ከሰው ወደሰው ይለያያል?
በስሕተት ደረጃ ካየነው እኮ ከዘካሪያስ ይልቅ አትስገድ ተብሎ መስገድ ይብሳል፡፡ እንዲያውም በመለኮቱ የሚመጡበትን የማይወደውን እግዚአብሔርን ማስቆጣትና የእርሱን ስግደት ለሌላ መስጠት ነው፡፡ የዘካሪያስ ግን ይህ ይሆንልሃል ብቻ ነው የተባለው፡፡ እርሱም ቢሆን እንዴት ይሆናል አርጅቻለሁ እኮ ብሎ በመጠራጠር ተከራከረ እንጂ አይሆንም አላለም፡፡ ዮሐንስ ግን ስግደቱ እኮ ላንተ ይገባል ብሎ ሳይከራከር ደግሞ ሰገደ፡፡ ታዲያ ተሳስቶ ቢሆን የዮሐንስ የበለጠ ድፍረት አይደለምን? ነገር ግን መስገዱ ልክ ስለነበር መልአኩም እንዳይሰግድለት ጠየቀው እንጂ አላገደውም፡፡
ታዲያ መልአኩ ከሌሎች ለይቶ ዮሐንስን ለምን እንዳይሰግድ ጠየቀው?
ሌሎች ቅዱሳን ለመላእክት ሲሰግዱ ያልተከለከሉት ዮሐንስ ግን እንዳይሰግድ የተጠየቀው ስለ ክብሩ ነው፡፡ ዮሐንስ ከሌሎቹ ለመላእክት ከሰገዱት ቅዱሳን ይልቅ የከበረና ከመላእክት ጋር የተካከለ እንዲያውም የበለጠ ነው፡፡ ስለዚህ ‹የምትተካከለኝ ወይም የምትበልጠኝ ሆነህ ለኔ መስገድ አይገባህም› ሲል ስለ ትሕትና መልአኩ ዮሐንስን ‹እንዳታደርገው ተጠንቀቅ› አለው፡፡ ይህንን የዮሐንስን ክቡርነት በሚከተለው መልኩ እንዘረዝራለን፡፡
1ኛ. ዮሐንስ አልሞተም
ሰውን ከመላእክት የሚያሣንሰው አንዱ ምክንያት ሞቱ ነው፡፡ ሰው ሞት ያለበት በመሆኑ ሞት ከሌለባቸው መላእክት ይልቅ ያንሣል፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ስለኛ ኃጢአት በመሞቱ ከመላእክት በጥቂት እንዳነሰ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ “...ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን፡፡” ዕብ. 2፡9፡፡ ‹አንሶ› የሚለው ቃል በፈቃዱ ያደረገውን ትሕትናውን እንጂ ማነሱን አይገልፅም፤ መላእክት እንኳን የማይቀምሱትን ሞት እርሱ ግን ስለኛ ሳይጠየፍ ራሱን አዋርዶ ቀመሰ ለማለት ነው፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ ሞትን ያላየ በመሆኑ ከመላእክት ጋር የተካከለ ነው፡፡ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ከሐዋርያት ጋር ሳለ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፤ “ኢየሱስም፣ እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው፡፡ ስለዚህ ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አለው እንጂ አይሞትም አላለውም፡፡” ዮሐ.21፡22-23፡፡
ሞትን ሳይቀምሱ ያረጉ እንደ ኤሊያስና ሄኖክ ያሉ ቅዱሳን እንኳን ክርስቶስ ድጋሚ ከመምጣቱ በፊት ሞትን የሚቀምሱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሞትን የማይቀምስ ከሰዎች ማንም ባይኖርም እንደ ዮሐንስ የተሠወሩ ግን አሉ፡፡ የተጠቀሰው የወንጌል ክፍልን አባቶች ሲተረጉሙ ዮሐንስ ሞትን የማይቀምስ መሆኑን ሳይሆን እንዳልሞተ ገልፀዋል፡፡ (የወንጌል ትርጓሜ)፡፡ ጌታም ‹እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ› አለ እንጂ ጭራሽ እንዳይሞት አላለም፡፡ ይህንን ግን ሐዋርያቱ በጊዜው ሲተረጉሙት ‹ያ ደቀመዝሙር አይሞትም› ማለታቸው ስሕተት ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ ጥቅሱ ዮሐንስ እንዳልሞተ የሚጠቁም ነው፤ ጌታ ራሱ እስኪመጣ ድረስ ሞትን እንዳይቀምስ እንደሚያደርገው ተናግሩአልና፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ ባለመሞቱ ከመላእክት እንዳያንስ አድርጎታል፡፡
2ኛ. አላገባም
መላእክት አያገቡም፤ አይራቡም፡፡ አንዱ ሲሞት አንዱን እያለች ሰባት ወንድማማቾችን ያገባችው ሴት በሰማይ ቤት የትኛውን እንደምታገባ አይሁድ ጌታን ሲጠይቁት ጌታም “መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ፡፡ በትንሣኤ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም፡፡” አላቸው፡፡ ማቴ.22፡29-30፡፡ ከትንሣኤ በኋላ ሰዎች እንደማያገቡ ለማሳየት የመላእክትን አለመጋባት በምሳሌነት አምጥቷል፡፡ ስለዚህ መላእክት አያገቡም፤ አይጋቡምም፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም ባለማግባትና ንጽሁን በመጠበቅ ምድራዊ መልአክ ሆኗል፡፡ ባለማግባት መላእክትን አክሏል፡፡
3ኛ. እንደ መላእክት ዓለመ መላእክትን ዐይቷል፡፡
4ኛ. ክህነት ያለው መሆኑ
ከመላእክት የሚያስበልጠው ክህነትም አለው፡፡ መላእክት ክህነት የላቸውም፡፡ የክህነት ጸጋ ለሰው ብቻ የተሰጠች ናት፡፡ ስለዚህ ክህነት ያለው በመሆኑ ዮሐንስ ከመልአኩ በልጧል፡፡
ይህንን የተረዳው መልአክም የሚበልጠው ቅዱስ ሰው ሲሰግድለት ‹አይገባም› እንደማለት ከለከለው፡፡ ትላንት ‹በግዜር› ተብሏልና ዛሬ ‹ኖር› አልልም እንደማይባለው ሁሉ ‹ከዚህ ቀደም አትስገድልኝ ሲል አክብሮኛልና በቃ አልሰግድም› ያላለው ዮሐንስ ለእግዚአብሔር መልአክ በመስገድ እግዚአብሔርን አከበረው፡፡ (አባባሏን ከመምህር ኅብረት የሺጥላ የተዋስኳት ነች) መልአኩም የጌታን ወዳጅ የዮሐንስን ክብር ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን አከበረው፡፡
ልብ በሉ መልአኩ ዮሐንስ ሲሰግድለት “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ” (ራእ. 19፡10) ነው ያለው፡፡ መልአኩ ራሱ እንደ ዮሐንስና ክብራቸው እንደ መላእክት ከሆኑት ከወንድሞቹ ከሐዋርያት ጋር አብሮ ባሪያ እንደሆነ ተናገረ፡፡ አያሱ ለመልአኩ በሰገደ ጊዜ ግን መልአኩ ጌታ ኢያሱ ደግሞ ባሪያ ነበሩ፤ “በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደና ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው አለው፡፡” (ኢያ. 5፡14)፡፡ በዮሐንስ ጊዜ ግን ዮሐንስ ባሪያ መልአኩ ጌታ አልሆኑም፡፡ ይልቁንስ መልአኩ እንደመሰከረው ሁለቱም የእግዚአብሔር ባሪያዎች ተባሉ እንጂ፡፡ ስለዚህ የዮሐንስ ባርነት ደረጃው ከፍ ብሎ የመልአኩ ባርነት ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የበታቼ እንደሆነ ሰው አትስገድልኝ፤ ይልቁንስ ለእግዚአብሔር ስገድ አለው፡፡
ዮሐንስ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሰግድለትም መልአኩ ተመሳሳይ ነገርን ነው ያለው፤ “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ፡፡” አሁንም ደግሞ ከእርሱ ጋር ባሪያ እንደሆነ ነው የተናገረው፡፡ ስለዚህ መልአኩ ስለ ዮሐንስ ክብርና ልዕልና አትስገድልኝ ሲል ጠየቀው እንጂ ለመላእክት ስግደት እንደማይገባ አላስተማረም፡፡ መላእክት ስግደት እንደሚገባቸው ጠንቅቆ የሚያውቀው ዮሐንስም በመስገድ ይህን አረጋግጧል፡፡
(በሦስት ክፍል እንደሚጠናቀቅ የጠቆምኩ ቢሆንም ጽሑፉ በመርዘሙና አራተኛ ክፍል አስፈላጊ በመሆኑ ሰሙነ ሕማማትንና ስግደትን በአራተኛው ክፍል እንዳቀርብ እንደሆንኩ ከይቅርታ ጋር አሳውቃለሁ)
ቃለ ህይውት ያሰማልን ።
ReplyDeleteየዚህ መፅሐፍ ቃል ከሚጠብቁትም ጋር አብሬ ባሬያ ነኝ የምትለዋን ቃል ፅሑፍ ሙሉውን ሽባ ያደርግብሃል።
ReplyDelete