Monday, May 7, 2012

አባታችን ተክለሃይማኖት ማለት እኒህ ናቸው=+=በታምራት ፍስሃ=+=

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን፡፡


            አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት የክርስቶስ ፍቅር ብልጫ ሆኖባቸዋልና ፡ ክርስትናቸውም የጣኦትን አምልኮ ተፀይፋለችና እኔ ክርስቲያን ነኝ በማለት የወንጌሉን የቃል ትምህርት በህይወት እየኖሩ አልጫ ለሆነው አለም ጨው ፡ በጨለማ ላለው ህዝብ ብርሃን ሆነው በኢትዮጵያ ከሰሜን እስከደቡብ ከምእራብ እስከ ምስራቅ ወንጌልን በቃልና በተግባር እያስተማሩ ዞሩ ፤ አለምን ንቀዋታልና ሃብትንና ስልጣንን ገፍተው ስለክርስቶስ በዱር በገደል በገዳም በዋሻ ይኖሩ ዘንድ ራሳቸውን ግድ አሉ፡፡ በነገስታት ቤት በቅምጥል ከመኖር ይልቅ ስለክርስትናው የነፃነትና የህይወት ምስክርነት በጣኦት አምላኪወች ፊት በሃዋርያት ድፍረት በሰወች ፡ በእንስሳትና በእፅዋት ላይ አድሮ ክርስቶስን ያስካደውን ፡ እግዚአብሄርን ያስረሳውን የዲያቢሎስ ሰራዊት በፅድቅ ታገሉት ፡ በወንጌሉ ሃይል ድል ነሱት ፡ በክርስቶስ ቃል አሳፈሩት ፡ በጨለማ ይንከላወስ ለነበረው ህዝብም ክርስቶስን ሰበኩላቸው ፡ በስላሴ ስም አጠመቋቸው ፡ የክርስቶስን ቅዱስ ስጋ ክቡር ደም አቀበሏቸው ፡ ዳግመኛም ቤተክርስቲያንን አሳንፀው ፡ ምእመናን መልሰው ወደጣኦት አምልኮ ወደሃጢአትም እንዳይመለሱ ፡ ካህናት አባቶችን እንዲጠብቋቸው  እያዘጋጁላቸው ለህዝቡ ሁሉ ሃዋርያ ሆነው ኖሩ፡፡

Saturday, May 5, 2012

በአቡነ ተክለሃይማኖት ገድል ላይ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች- (ለፕሮቴስታንቶችና ተሐድሶዎች የቀረበ)- ክፍል አንድ!=+=

አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሰማዕትነት ሞተው ቅዱስ ጳውሎስ “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራውም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ” ያለውን ለመፈጸም ይመኙ ነበር /ፊሊ.3፡11/፡፡ ነገር ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደዌ ዘእሴት (ዋጋን በሚያሰጥ የሆድ ሕመም) እንዲሞቱ ነው የፈቀደላቸው፡፡ በዚህ አሟሟታቸውም ከጌታችን መከራ መስቀል እንደሚያሳትፋቸው እንደ ሰማዕትነትም እንደሚቆጠርላቸው ነው የተነገራቸው፡፡ ይህ ደግሞ ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን አይደለም፡፡ ኢዮብን ስንመለከተው በደዌ ተልቶ ሸቶ ነበር፡፡ እንዲህ መሆኑ ግን ለጥቅሙ ነበር፡፡ ጳውሎስን ስናይ የጐድን ውጋት ነበረው /2ቆሮ.12፡7-10/፡፡ ነገር ግን ለጥቅሙ የተሰጠው ነበረ፡፡ ጢሞቲዎስን ስንመለከት የሆድ ሕመም ነበረው /1ጢሞ.3፡25/፡፡ ነገር ግን ለጥቅሙ ነበረ፡፡ ታድያ አቡነ ተክለሃይማኖት ዐስበ ሰማዕትነት (የሰማዕታትን ዋጋ) የሚያገኙበት ሕመም ያዛቸው ቢባል ምንድነው ብርቁ? አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በዐረፍተ ዘመናቸው መጨረሻ የያዛቸው ደዌ ዘዕሴት ነበረ ቢባል ምንድነው ድንቁ? የክርስቶስን መከራ የሚያሳትፍ እንጂ የክርስቶስን መከራ የሚተካ አልተባለም፡፡ እንግዲያውስ ወንድሞችና እኅቶች! ያልተባለውን ተባለ፣ ያልተፈጠረውን ተፈጠረ፣ ያልተጣፈውን ተጣፈ እያልን ውሸት ከመናገር ብንቆጠብስ?(ይቀጥላል!)

 ተመሳሳይ ገጾች

 አባታችን ተክለሃይማኖት ማለት እኒህ ናቸው

አንዳንድ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች ከአንድ በላይ ሚስት ለምን አገቡ? እንዲህ በማድረጋቸውስ እግዚአብሔር ፈቅዶላቸዋል ማለት ይቻላልን?=+=

በብሉይ ኪዳን ከአንዲት ሚስተ በላይ አግብተዋል ከሚባሉት እነ አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ዳዊት እና ሰሎሞን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከአንድ በላይ አግብተዋል ማለት ግን እግዚአብሔር ፈቅዶላቸዋል በሥራቸውም ተደስቷል ማለት አይደለም፡፡ እያንዳንዳቸውን እያሳጠርን መመልከት እንችላለን፡- 1. አብርሃም፡- አብርሃም የደረሰባትና እስማኤልንም የወለደላት አጋር ሚስቱ ሳትሆን ገረዱ የነበረች ናት፡፡ ከእርሷ እንዲወልድ የተደረገው እንኳ ሚስቱ ሣራ ልጅ ስላልነበራት አስገድዳው እንጂ እርሱ ራሱ ሊደርስባት ፈልጎ አልያም ደግሞ እግዚአብሔር ይህን እንዲያደርግ ስለፈቀደለት አልነበረም፡፡ አብርሃም ይህን ያደረገው ዝሙት ለመፈጸም ወይም ሌላ ሚስት ለመጨመር ብሎ ሳይሆን የሚስቱን ቃል ሰምቶ ነው /ዘፍ.16፡3/፡፡ ሊቃውንት ሣራ አብርሃምን ለምን እንዳስገደደችው ሲያመሰጥሩት፡- እግዚአብሔር “ከጉልበትህ የሚወጣ ልጅ እንጂ ከአንተ ጋር ያለው ባርያ አይወርስህም” የሚል ቃል ገብቶለት ስለነበረ /ዘፍ.15፡4/ እርሷ ደግሞ ልጅ ስላልነበራትና እግዚአብሔር የገባውን ኪዳን ያስቀረ ስለመሰላት በሰውኛ ጥበብ ልጅ እንዲወልድ ማድረጓ ነበር ይላሉ፡፡ አብርሃም በመጨረሻ ያገባት ሚስት ኬጡራ ትባላለች /ዘፍ.25፡1/፡፡ ነገር ግን ኬጡራን ያገባት ሣራ እያለች ሳይሆን ከሞተች በኋላ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በመሐመዳውያን ዘንድ የምናየው ዓይነት አይደለም፡፡ 2. ያዕቆብ፡- በዘፍጥረት መጽሐፍ ያዕቆብ ራሔልንና ሊያን እንዳገባ እናነባለን፡፡ ነገር ግን ያዕቆብ ሊያን ያገባት በአጐቱ በላባ አታላይነነት እንጂ እርሱ ስለፈለገ ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ስለፈቀደለት አልነበረም /ዘፍ.29፡25/፡፡ 3. ዳዊት፡- መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ሚዛን ስለሆነ ዳዊት በቅድስና በተመላለሰባቸው ጊዜያት ከአንበሳ አፍ በጐችን ማስጣሉ፣ በአንዲት ጠጠር ሕዝበ እስራኤልንና እግዚአብሔርን የወቀሰ ጐልያድን መግደሉ፣ ሳውልን በይቅርታ ማሸነፉ፣ ሲሞት እንኳን “እሰይ እንኳን ሞተ” ሳይሆን ማልቀሱንና ማዘኑን፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ዛሬ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ምግብ የሆነውን መዝሙር መዘመሩ ቢጽፍልንም ከዚያ በኋላ ያደረገውን ኃጢአትም አያስቀርብንም፡፡ እናም ዳዊት ወደ ንግሥና ከወጣ በኋላ የሰውነት ድካም ታይቶበታል፡፡ ከአንድ ኃጢአት ወደ ሌላ ኃጢአት ሲሸጋገርም እንመለከታለን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ስንፍና ሕሊናንና አስተሳሰብን ያደነዝዛል፤ የማይወዱትንም ኃጢአት እንዲያደርጉ በርን ይከፍታል” እንዳለው ዳዊት በዚያን ጊዜ ከአሞናውያን ጋር በነበረው ጦርነት ሠራዊቱን አዝምቶ መጸለይ ሲገባው እርሱ በስንፈና አልጋ ተኝቶ ነበር፡፡ መተኛቱም ሳያንሰው ከእንቅልፉ ሲነቃ በሰገነቱ ሲመላለስ አንዲት መልከመልካም ሴትን ቢመለከት በዝሙት ጾር ተነድፏል፡፡ መነደፍ ብቻም ሳይሆን ደረሰባት፡፡ እናም አረገዘች፡፡ በኋላም ይህን ኃጢአቱ ለመሸፈን ብሎ ባሏን ጠርቶ ከእርሷ ጋር እንዲተኛና ከባሏ እንደጸነሰች ማስመሰል ፈልጐ ነበር፡፡ ኦርዮ ግን ወደ ሚስቱ ወደ ቤርሳቤህ አልሄደም፡፡ ለኦርዮ ወደ ቤቱ ሄዶ ከሚስቱም ጋር መተኛት ማለት እግዚአብሔርን (ታቦተ ጽዮንን)፣ ሕዝቡን (እስራኤልን)፣ ነገደ ይሁዳን፣ አለቃው ኢዮአብን እና በጦር ሜዳ ያሉትን ጓደኞቹን ሁሉ እንደ መሳደብ ነበረ፡፡ ዳግመኛ በመላ ፍትወቱ እንዲነሣሣበት ፈልጐ ቢያሰክረውም ኦርዮ በጌታው ምንጣፍ ከባሮቹ ጋር ተኛ እንጂ ወደ ሚስቱ አልሄደም፡፡ ከዚህ በኋላ ዳዊት ያሰበው ሁሉ እንዳልተፈጸመለት ባየ ጊዜ ኦርዮን ማስገደል መርጧል፡፡ እናም አስገደለው፡፡ መጽሐፍ ዳዊት ያደረገው ሁሉ ማለትም ከቤርሳቤህ ጋር መድረሱ፣ ይባስ ብሎም አንዱን ባሏ ኦርዮን ማስገደሉ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ” ይላል /2ሳሙ.11፡27/፡፡ ምንም እንኳን ዳዊት መንፈሳዊ ልምምዶችን የተለማመደ፣ ሕግ አዋቂ፣ በሕዝብ ላይ የሚፈርድ ንጉሥ፣ የእግዚአብሔርም ነብይ ቢሆንም ከዚህ ኃጢአቱ ሊመለስ ባለመቻሉ ሌላ ነብይ አስፈልጐታል፡፡ ስለዚህም ነብዩ ናታን በጥበብ ገስጾታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ዳዊት ያለ ምንም ማመካኘት ኦርዮን ወይም ቤርሳቤህን ሳይሆን “እግዚአብሔርን በድያለሁ” በማለት ንስሐ ገብቷል /2ነገ.12፡13/፡፡ እንዲህ በማድረጉም “እግዚአብሔር… ኃጢአትህን አርቆልሃል” ተባለ፡፡ ስለዚህ ዳዊት በግልጽ ቋንቋ አመነዘረ እንጂ ሌላ ሴት አገባ አይባልም፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንት “የዳዊት ቅድስና ከንስሐ እንጂ ካለመበደል የተገኘ አይደለም” የሚሉት፡፡ 4. ልጁ ሰሎሞንም ቢሆን ብዙ ሚስቶችን ቢያገባም መጽሐፍ ቅዱስ “እንዲህ በማድረጉ እግዚአብሔርን አሳዘነው” እንጂ “አስደሰተው” ብሎ አልመዘገበልንም፡፡ እንዲያውም እንዲህ በማድረጉ ዕድሜው አጥሯል፤ መንግሥቱ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ይህን ታሪክ በ1ነገ.11 ሙሉውን ማንበብ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ከአንዲት በላይ ሚስት ማግባት ከሕገ እግዚአብሔርና ከስነ ተፈጥሮ አንጻር ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያቱም ከሕገ እግዚአብሔር አንጻር ስናየው አንድ ወንድና አንዲት ሴት አድርጐ ፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ መተባበር እንዳለባቸውም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህ ፈቃዱም ትዕዛዙም ባይሆን ኖሮ ወይም ደግሞ አንዱ ወንድ ከአንዲት ሚስት በላይ ማግባት ተፈቅዶለት ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአንድ አዳም ብዙ ሴቶችን በፈጠረለት ነበር፡፡ ወይም በግልባጩ አንዲት ሴት ከአንድ ወንድ በላይ ማግባት ተፈቅዶላት ቢሆን ኖሮ ብዙ ወንዶችን ፈጥሮ ከአንዲቷ ሴት ጋር ባጣመራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ አላደረገም፡፡ ስለዚህ ከአንድ ሚሰት በላይ ማግባት ይህን ሕገ እግዚአብሔር የሚጻረር ነው፡፡ ከሕገ ተፈጥሮ አንጻር ስናየው ደግሞ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው፡፡ የአንድ አዳም አካል የአንዲት ሔዋን አካል ነው፡፡ ይህ የአንድ አዳም አንድ አካል ከአንድ በላይ ሚስት አገባ ማለት ግን ከአንድ በላይ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሕገ ተፈጥሮን የሚጻረር ነው፡፡ ስለዚህ ከአንዲት በላይ ሚስት ማግባት በመሐመድ የተሰበከ የሰይጣን ትምህርት እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመርያው ያዘዘው ትእዛዝ ወይም በተፈጥሮ የሰጠው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እንድናገባ የፈቀደልን አንዲት ሚስትን ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ አንድ ነው፤ ሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ብቻ ናት፡፡ በክርስቶስ የተመሰለው ባልም ልትኖሮው የሚገባት አንዲት ሚስት ብቻ ናት /ኤፌ.5፡23/፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!!

Friday, May 4, 2012

ተሐድሶ በ… ያስፈልጋል፤ ሃይማኖት ግን አይታደስም =+= በአባ ሳሙኤል፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ=+=!!

ዶግማ የሚለው ቃል “ዶኪን” ከሚል የግሪክ ግሥ (አንቀጽ) የተገኘ ነው፡፡ በጥንቱ ግሪክኛ ቋንቋ “ዶኪን ሚ” የሚለው አገላለጽ ወደ አማርኛ አገላለጽ ሲቀየር ወስኛለሁ፤ እርግጠኛ ነኝ፤ ጽኑዕ እምነቴ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዶግማ ማለት እርግጠኛ የሆነ ነገር፣ የተወሰነ ነገር፣ የታመነ ነገር ማለት ነው፡፡ ይህን እውነተኛ (የታመነ) ነገር፣ የተረጋገጠ ነገር፣ የተወሰነ ነገር ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን አተረጓጐም ዶግማ ሲባል የሃይማኖት አባቶች የማይቀየር፣ የማይሻሻል፣ የማይለወጥ፣ የማያረጅ ብለው ይፈቱታል፡፡ አዎ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖት አይሻሻልም፤ አይታደስም ብላ የምታስተምረው፡፡ ተሐድሶ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በአስተዳደር፣ በልማት፣… ወዘተ ያስፈልጋል፤ ሃይማኖት ግን አይታደስም፡፡ ስለሆነም “ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም” የሚለውን ማስተዋል ይገባል /ማቴ.24፡35/፡፡ ማለትም ራሱ ጌታ የተናገረውን የቃሉን ጽኑነት፣ ተአማኒነት፣ እርግጠኝነት፣ ልክነት በትክክል ያረጋግጣል፡፡ ዶግማ የሚለው ቃሉ የተመረጠውም ከላይ እንደተገለጠው እርግጠኛነትን የሚያመለክት ቃል ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡… በኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት አተረጓጐም መሠረት ዶግማ የምንለው፡-  ሃይማኖታዊ የሆነ እውነታ፤  በመለኰት መገለጥ የተመሠረተ (የተገኘ) እና  ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ትምህርት ነው፡፡… አንድ ሰው መናፍቅ ሆነ የሚባለው ዶግማን ከእምነቱ ሕግና ሥርዓት ውጭ እናሻሻል፣ እናድስ በሚል አመለካከት ከትክክለኛው አባባልና አነጋገር እንዲሁም አስተሳሰብ ወጥቶ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ አዛብቶ ሳይተረጕም እንዲያውም ወደ ሃይማኖት ፈጽሞ ሳይገባ በውጭ ሆኖ የሚለፈልፍ ሰው ግን ሃይማኖት አልባ፣ ከሐዲ ወይም አስተያየት ሰጪ ነው፡፡ እየተደረገና እየተባለ ካለው ሁሉ በሃይማኖት ጸንተን እግዚአብሔር በምሕረቱ በቸርነቱ ስለጐበኘን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ስውርና አሳፋሪ የሆነውን ነገር አስወግደን በተንኰልም አንሠራም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከውሸት ጋር አንቀይጥም፤ ይልቅስ እውነቱን በይፋ እናሳያለን፡፡ ራሳችንንም በሰው ኅሊና ግልጥ እያደረግን በእግዚአብሔር ፊት እንኖራለን፡፡ ያበሠርነው የምሥራች ቃል ምናልባት የተሠወረ ቢሆንም የተሠወረባቸው ለሚጠፉት ነው፡፡ እነርሱም የማያምኑበት ምክንያት ለጊዜው የዚህ ዓለም አምላክ/ገዢ የሆነው ሰይጣን ልቡናቸውን ስላሳወረው ነው፡፡ በየአቅጣጫው መከራ ይደርስብናል፤ ግን አንሸነፍም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግራ ይገባናል፤ ግን ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ጠላቶች ያሳድዱናል፤ ነገር ግን ወዳጆች አጥተን አናውቅም፡፡ ተመተን እንወድቃለን፤ ግን አንሞትም፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በእኛ ሰውነት እንዲገለጥ ዘወትር የመድኃኒታችን የኢየሱስን ሞት በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡ የእርሱ ሕይወት በሚሞተው ሰውነታችን እንዲገለጥ “አመንሁ፤ ስለዚህም ተናገርሁ” ተብሎ እንደተጻፈ እኛም ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤ እንጽፋለንም /2ቆሮ.4፡1/፡፡… ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!! (ምንጭ፡- ፈለገ አሚን ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ገጽ 1-5)!

 ተመሳሳይ ገጾች

በአቡነ ተክለሃይማኖት ገድል ላይ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች-

አንድ ፕሮቴስታንት ለጠየቀኝ የተለያዩ ጥያቄዎች

FeedBurner FeedCount