Saturday, June 2, 2012

ርደተ መንፈስ ቅዱስ - በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ!!


  መንፈሳዊ ጸጋቹ በዛሬው ዕለት በእኛ ላይ በምላት ወርዷልና መንፈስ ቅዱስን በመንፈሳዊ ጣዕመ ዝማሬ ከፍ ከፍ እናድርገው፡፡ ምንም እንኳን ያገኘነውን የጸጋ ታላቅነት ለመግለጽ የእኛ ቃላት በጣም ደካሞች ቢሆኑም እንደ አቅማችን ኃይሉንና ሥራውን ከማመስገን አንከልከል፡፡
  
 እያከበርን ያለነው የጴንጤ ቆስጤ በዐል ነው፤ የርደተ መንፈስ ቅዱስ ቀን፣ ተስፋ ፍጻሜ ያገኘበት ቀን፣ መጠበቅንና የመዳንን ናፍቆት ያበቃበት ቀን፣ ጸሎተ ሐዋርያት መልስ ያገኘበት ቀን፣ ዐስበ ትዕግሥትን ያየንበት ቀን፡፡ የዛሬው ዕለት በዔቦር ዘመን ቋንቋን የደበላለቀ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የእሳት ላንቃዎችን ሲያሳይ የተመለከትንበት ነው /ዘፍ.10፡25/፡፡ በዔቦር ዘመን አስወቃሹንና አሳፋሪውን የሰው ልጅ ፈቃድ ለመግታት ቋንቋቸውን የደበላለቀ መንፈስ ቅዱስ ዛሬ ግን ደቀመዛሙርቱ ሁሉም በአንድ ቤት ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ንፋስ መጥቶ ቤቱን ሲሞላው፤ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖችም ሲያሳያቸው፤ በፈቃዱም የሰባኪነትን ልሳን ሲሰጣቸው አየን፡፡
  
 ይህ ቅዱስ መንፈስ በሥነ ፍጥረት መጀመርያ በውኃ ላይ ሲሰፍ አየነው፤ በኋላ በዘመነ ሐዲስም በጌታችን ራስ ላይ ሲያርፍ አየነው፡፡
  
 ይህ በርግብ አምሳል በጥፋት ውኃ ላይ በርሮ የንፍር ውኃ መጉደሉን ለኖኅ ያበሰረ መንፈስ ቅዱስ በኋላም በርግብ አምሳል በዮርዳኖስ ውኆች ላይ በመታየት ሲጠመቅ የነበረውን በግ ለዓለም ሁሉ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ መሆኑን ሲገልጥ ሲመሰክር አየነው፡፡
   

Friday, June 1, 2012

ጾመ ሐዋርያት- በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ


በየአመቱ በዕለተ ሰኑይ ብቻ (ሰኞ ቀን ብቻ) የሚጀምሩ ሦስት አጽዋማት አሉ፡፡ እነርሱም ዓቢይ ጾም፣ ጾመ ነነዌ እና ጾመ ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነዚህ አጽዋማት ምን ጊዜም ቅበላቸው እሁድ ሲሆን የሚገቡት ደግሞ ሰኞ ቀን ነው፡፡ በየትኛውም አመት ይህን ዕለት አይለቁም፡፡

ስለዚህ 2004 ጾም ሐዋርያት ግንቦት 27 የፊታችን ሰኞ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በየግላችንም ያጋጠሙንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ውጊያዎች በማሰብ ድል የምናደርግበትን ኃይል ፈጣሪያችን ይሰጠን ጾሙን ከወትሮው በበለጠ ጥንቃቄ ልንጾመው ይገባናል፡፡

የጾሙን ታላቅነት ተረድተን እንድንጾመው የትመጣውን፣ ትንቢቱን፣ ምሳሌውንና ምሥጢሩን መረዳት አጋዥ ስለሚሆነን አስቀድመን ስለጾሙ እንማር ዘንድ በአጭሩ አቅርቤዋለሁ! የምችለውን ያህል እጽፍ ዘንድ ብርታቱንና ጥበቡን የሰጠኝ አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ክብር ምስጋና ይድረሰው! አሜን!

ጾመ ሐዋርያት በራሳቸው በሐዋርያት የተጀመረ ጾም እንደመሆኑ መጠን በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከዛሬ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲጾም የኖረ ጾም ነው፡፡ ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የአዋልድ መጻሕፍትና የታሪክ በርካታ ምስክሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ጾሙን እንደ እንግዳ ነገር መቁጠርና ዘመን አመጣሽ አድርጎ ማየት የራስን አላዋቂነት ያሳያል፡፡ ይህን ማለት ያስፈለገው ጥቂቶች ጾሙን ድሮ ያልነበረና ዘመን አመጣሽ አድርገው ስለሚናገሩ ነው፡፡

      ጾመ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ዕድሜያቸው ለጾም የደረሱ ምእመናን በሙሉ እንዲጾሙአቸው ካወጀቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንደበት ቀን የተቀጠረለት፣ ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌ የተመሰለለት ጾም መሆኑ ከአጽዋማት ሁሉ ለየት ያደርገዋል፡፡

  ጌታችን ስለዚህ ጾም ትንቢተ በመናገር፣ ምሳሌ በመመሰል ሰፊ ትምህርት የሰጠው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ደቀ መዛሙርትህ የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ እርሱም ሲመልስ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል በዚያ ጊዜም ይጦማሉ፡፡ በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል የወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡ አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡›› (ማቴ9.14-17)

በመቀጠል እስከ መጨረሻ የምንመለከተው ከላይ የሰፈረውን የማቴዎስ ወንጌል አጭር ገጸ ንባብ ሐሳብ በመሆኑ መለስ እያሉ ታሪኩን ማንበብ ወይም በልብ ከመዘገቡ በኋላ ቀጣዩን ክፍል ማንበብ ምሥጢሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡

Wednesday, May 30, 2012

አብ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋል- የዮሐንስ ወንጌል የ25ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡18-28)=+=


     ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እነርሱ መዳን ብሎ ወደ ቤታቸው ቢመጣም፣ በኃይልና በሥልጣን የሚያደርገውን ሁሉ ሲያደርግ ቢመለከቱትም መጻሕፍትን ከመመርመር ይልቅ፣ ትንቢተ ነብያትን ከማገናዘብ ይልቅ አይሁድ የራሳቸውን ወግ በመጥቀስ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ የሚናገረውን እንኳን ባያምኑ የሚያደርገውን አይተው ወደ እርሱ እንዲመጡ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ይባስኑ ውስጣቸው በቅናት ይቆስል ነበር፡፡ ስለዚህም “ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚያስተካክል ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም” ለማለት ደፈሩ /ቁ.18/፡፡ ጌታችን ግን አንዳንድ ልበ ስሑታን እንደሚሉት “ስለምን ልትገደሉኝ ትፈልጋላችሁ? እኔ ከአብ ጋር የተካከልኩ አይደለሁም” ወይም “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም አገለግላለሁ” ሳይሆን “አባቴ እስከ ዛሬ (ቅዳሜ ቅዳሜ) ይሠራል (አንዳንድ ድውይ ይፈውሳል) እኔም እንዲሁ እሠራለሁ (መጻጉዕን ፈወስኩ)” ይላቸዋል /ቁ.17/፡፡ ወንጌላዊው እዚህ ጋር የአይሁዳውያኑ አባባል ትክክል ስለነበረ በሌላ ቦታ /ዮሐ.2፡19/ እንደሚያደርገው ማስተካከያ አላደረገበትም፤ ከዚህ በፊት እንዳደረገውም “አይሁድ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እንዳስተካከለ ቢያስቡም ክርስቶስ ግን እንዲህ ማለቱ ነበር” አይልም /Saint John Chrysostom Homilies on St. John, Hom 38./፡፡

   ከዚህ በኋላ ስለ ሰው ልጆች መዳን አብዝቶ የሚሻ ጌታችን እንዲህ ይላቸዋል፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” /ቁ.19/፡፡ ምን ማለት ይሆን? እውነት “ነፍሴን ላኖራትም ላነሣትም ሥልጣን አለኝ” ያለው ጌታ ምንም ሊያደርግ አይችልምን? /ዮሐ.10፡18/፡፡ ወንድሞቼ ይህን በጥንቃቄ ልናስተውለው ይገባል፡፡ ይህ መለኰታዊ ቃል አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሳይሆን እንዲህ ማለቱ ነው፡- “እኔ ከራሴ ብቻ አንቅቼ ምንም ምን ሥራ አልሠራም፤ ከአብ በሕልውና ያየሁትን በህልውና ያገኘሁትም እሠራለሁ እንጂ፡፡ የአብ ፈቃድ የእኔ ፈቃድ ናት፤ የአብና የእኔ ፈቃድ እርስ በእርሷ የምትለያይ አይደለችም፡፡ እስከ ዛሬ አብ የወደደውን ሲያደርግ እንደነበረ እኔም እንዲሁ (በተመሳሳይ ሥልጣን በተመሳሳይ ዕሪና) የወደድኩትን አደርጋለሁ፡፡ አብ ይፈውስ እንደነበረ እኔም እፈውሳለሁ፡፡ ስለዚህ አብ አባቴ ነው ስላልኳችሁ አትደነቁ፤ ከአባቴ ጋር የተካከልኩ ነኝ ስላልኳችሁ አትበሳጩ፡፡ እናንተን ለማዳን ብዬ ምንም ከአባቴ ጋር ያለኝን መተካከል እንደመቀማት ሳልቆጥረው የእናንተ የባርያቼን መልክ ብይዝም አብ የሚያደርገውን ሁሉ እኔ ደግሞ ይህን እንዲሁ አደርጋለሁና /ፊል.2፡6/፤ የአብ የሆነ ሁሉ የእኔ ነውና፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአብ ነውና /ዮሐ.17፡10/፡፡ የሆነው ሁሉ በእኔ የሆነው አብ መፍጠር የማይችል ሆኖ ሳይሆን በሥላሴ ዘንድ የፈቃድ ልዩነት ስለሌለ ነው” /ዮሐ.1፡3 Saint AmbroseOf the Holy Spirit Book 2:8:69/። በእርግጥም ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣው አብ ምንም አላደረገም አይባልም /ዮሐ.11፡42/፤ ክርስቶስ የዓይነ ሥውሩን ብርሃን ሲመልስለት መንፈስ ቅዱስ ምንም አላደረገም አይባልም /ዮሐ.9፡3/፡፡ የሥላሴ ሥራ በአንድነት በአንድ ፈቃድ የሚደረግ እንጂ በተናጠል የሚደረግ አይደለምና /Saint Augustine. Sermon on N.T. Lessons, 76:9/፡፡

Sunday, May 27, 2012

ታላቅ መሆንን ስትፈልጉ ታላቅ መሆንን አትፈልጉ ከዚያም ታላቅ ትሆናላችሁ


ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያሰተምር እንዲህ አለ፡- “ማንም ከእናንተ ታላቅ መሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን… ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባርያ ይሁን… ታላቅ መሆንን ማሰብ የክፉዎች ሐሳብ ነው… የመጀመርያነትን ስፍራ መፈለግ የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው… ታላቅነትን መፈለግ ታናሽነት ነው፡፡
   ስለዚህ ይህን ልቡና ከእናንተ ገርዛችሁ ጣሉት… በእናንተ በክርስቲያኖች ዘንድ እንዲህ አይደለም… በአሕዛብ ዘንድ የመጀመርያነትን ስፍራ የሚይዙ በሌሎች ዘንድ አለቆች እንዲሆኑ ነው… በእኔ ዘንድ ግን የመጨረሻውን ስፍራ የሚይዝ እርሱ የመጀመርያ ነው፡፡
   ይህን ከእኔ መማር ትችላላችሁ… እኔ ምንም የነገሥታት ንጉሥ የአለቆችም አለቃ ብሆንም በፈቃዴ የባርያዎቼን የእናንተን መልክ እይዝ ዘንድ አልተጠየፍኩም… በሰዎች ዘንድ የተገፋሁ ሆንኩ… ተተፋብኝ… ተገረፍኩኝ… ይህም ሳይበቃኝ በመስቀል ሞት ሞትኩኝ፡፡ ነገር ግን ላገለግል ስለ ብዙዎችም ነፍሴን ቤዛ ልሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉኝ አልመጣሁም፡፡ ቤዛነቴም ለወዳጆቼ ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉኝም ለሚወግሩኝም ለሚያሰቃዩኝም ጭምር ነው፡፡ የእናንተ አገልጋይነት ግን ለእናንተ ለራሳችሁ እንጂ ለሌሎች ቤዛነት የሚሆን አይደለም፡፡
  እንዲህ አድርጌ ስነግራችሁ ክብራችሁ ዝቅ ዝቅ ያለ መስሎ አይታያችሁ… ምንም ያህል ዝቅ ዝቅ ብትሉም እኔ የተዋረድኩትን ያህል አትዋረዱም… እኔ ይኼን ያህል ከመጨረሻው የክብር ጠርዝ ወደ መጨረሻው የውርደት ጠርዝ ብወርድም ለብዙዎች መነሣት ሆንኩኝ… ክብሬ ከመቃብር በላይ ሆነ… ክብሬ በዓለም ላይ ከአጥብያ ኮከብ በላይ ደመቀ፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመወለዴ በፊት መታወቄ በመላእክት ዘንድ ብቻ ነበር… አሁን ሰው ከሆንኩኝ በኋላ ግን ክብሬ በመላእክት ብቻ ሳይሆን በሰው ዘንድም የታወቀ ነው፡፡

FeedBurner FeedCount