በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይል (ዘዳ.6፡5) የሚወደድ የሆነውን አምላካችን እግዚአብሔርን ስናመልከው ሥጋችንንም፣ ነፍሳችንንም፣ መንፈሳችንንም አስተባብረን መሆን አለበት፡፡ መጻሕፍትን በማንበብ፣ ለብዎትን /ማስተዋልን/ በመጠቀም፣ ዕውቀትን ገንዘብ በማድረግ፣ ነቢብን /ንግግርን/ በማስገዛት፣ ሀልዎትን /መኖርን/ በመሠዋትና በመሳሰሉት እግዚአብሔርን ማምለክ ባሕርያተ ነፍስን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡ ጾም/ከሥጋ ፍላጎት መከልከል/ እና ስግደትን የመሳሰሉት ደግሞ በሥጋ እግዚአብሔርን የምናመልክባቸው፣ ሥጋችንን የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ (ይህ ማለት ግን ስግደት ለሥጋውያን ብቻ የተገባ ነው ማለት አይደለም፤ “መላእክቱ ሁሉ ስገዱለት”/መዝ.97፡7/ እንዳለ መላእክትም የሚሰግዱ ናቸውና፡፡) ፍቅር፣ ቸርነት፣ ምኅረት፣ መመጽወት እና የመሳሰሉት የመንፈስ ሥራዎች ደግሞ ወደ ፍጹምነት የሚወስዱን የሥጋን ድካምና የነፍስን ሐልዮት የምንቀድስባቸው እንዲሁም መንፈሳችንን ለአምልኮተ እግዚአብሔር የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡