Friday, January 22, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተረጐመው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ!


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
     በ388 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ተጀምሮ፥ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የተጠናቀቀው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የኦሪት ዘፍጥረት የትርጓሜ መጽሐፍ የመጀመሪያ ቅጹ በገበያ ላይ ዋለ፡፡ ይህ ከሐዋርያት ዘመን አንሥቶ በተመሠረተውና በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እንደ ታነፀ በሚነገረው ፓላዪያ (The Palaia) በተባለ በታላቁ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው ትምህርት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን እጅግ የጠለቀ ፍቅርና የሰው ልጅም ምን ያህል ክቡር ፍጥረት እንደ ኾነ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡

Saturday, January 9, 2016

ስግደት (ክፍል 1)


በዲ/ ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2008 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይል (ዘዳ.65) የሚወደድ የሆነውን አምላካችን እግዚአብሔርን ስናመልከው ሥጋችንንም፣ ነፍሳችንንም፣ መንፈሳችንንም አስተባብረን መሆን አለበት፡፡ መጻሕፍትን በማንበብ፣ ለብዎትን /ማስተዋልን/ በመጠቀም፣ ዕውቀትን ገንዘብ በማድረግ፣ ነቢብን /ንግግርን/ በማስገዛት፣ ሀልዎትን /መኖርን/ በመሠዋትና በመሳሰሉት እግዚአብሔርን ማምለክ ባሕርያተ ነፍስን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡ ጾም/ከሥጋ ፍላጎት መከልከል/ እና ስግደትን የመሳሰሉት ደግሞ በሥጋ እግዚአብሔርን የምናመልክባቸው፣ ሥጋችንን የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ (ይህ ማለት ግን ስግደት ለሥጋውያን ብቻ የተገባ ነው ማለት አይደለም፤መላእክቱ ሁሉ ስገዱለት”/መዝ.977/ እንዳለ መላእክትም የሚሰግዱ ናቸውና፡፡) ፍቅር፣ ቸርነት፣ ምኅረት፣ መመጽወት እና የመሳሰሉት የመንፈስ ሥራዎች ደግሞ ወደ ፍጹምነት የሚወስዱን የሥጋን ድካምና የነፍስን ሐልዮት የምንቀድስባቸው እንዲሁም መንፈሳችንን ለአምልኮተ እግዚአብሔር የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

Monday, December 28, 2015

ስለ በርለዓም ሰማዕት



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 18 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
    በርለዓም ሰማዕት በዲዮቅልጥያኖስ ጊዜ በአንጾኪያ የነበረ እጅግ ጥቡዕ ክርስቲያን ነው፡፡ መምለክያነ ጣዖት ለጣዖት ይሠዋ ዘንድ ባስገደዱት ጊዜ ያሳየው ጽናት እስከ ምን ድረስ እንደ ኾነ፣ የዲያብሎስ የማታለል ሥራ እንዴት በየጊዜው እንደሚቀያየር፣ ሊቁ ያስተምራቸው የነበሩት ምእመናንም ከዚህ ሰማዕት ምን ሊማሩ እንደሚገባቸው ሰማዕቱ ወዳረፈበት መቃብር ወስዶ ያስተማራቸው ነው፡፡ መታሰቢያዉም እ.ኤ.አ. ሕዳር 19 ነው፡፡
† † †

     (1) ዛሬ ንዑድ ክቡር የሚኾን በርለዓም ወደ ቅዱስ በዓሉ ጠርቶናል፡፡ ነገር ግን እንድናመሰግነው አይደለም፤ እንድንመስለው ነው እንጂ፡፡ ሲያመሰግን እንድንሰማውም አይደለም፤ የደረሰበትን ቅድስና ዐይተን እርሱን መስለን እዚያ የቅድስና ማዕርግ ላይ እንድንደርስ ነው እንጂ፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ወደ ሥልጣን ሲወጡ ሌሎች ሰዎች ልክ እንደ እነርሱ ታላላቅ ኾነው ማየትን በፍጹም አይወዱም፤ ቅንአት ውስጣቸውን ይተናነቃቸዋል፡፡ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ፍጹም ተቃራኒ ነው እንጂ፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት ክብራቸውን ከምንም በላይ ከፍ ብሎ የሚያዩት ደቀ መዛሙርቶቻቸው እነርሱን አብነት አድርገው ከእነርሱ በላይ የተሻሉ ኾነው ሲመለከቱአቸው ነው፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ሰማዕታትን ማመስገን ቢፈልግ እነርሱን ሊመስል ይገቧል፡፡ አንድ ሰው የእምነት አትሌቶችን ማሞገስ ቢፈልግ እነርሱን መስሎ ምግባር ትሩፋትን ሊሠራ ይገቧል፡፡ ይህ ነገርም እነርሱ ካገኙት ሹመት ሽልማት በላይ ሰማዕታቱን ደስ ያሰኛቸዋል፡፡ በእርግጥም ያገኙትን ሹመት ሽልማት ከምንም በላይ የሚያጣጥሙትና የተሰጣቸው ክብር ምን ያህል ታላቅ እንደ ኾነ የሚገነዘቡት እኛ እነርሱን መስለን የሔድን እንደ ኾነ ነው፡፡ ይህንንም በማስመልከት ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ የተናገረውን አድምጡ፤ እንዲህ ያለውን፡- “እናንተ በጌታችን ጸንታችሁ ብትቆሙ አሁን እኛ በሕይወት እንኖራለን” /1ኛ ተሰ.3፥8/፡፡ ከዚህ በፊትም ብፁዕ ሙሴ እንዲህ ብሏል፡- “አሁንም ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር ትላቸው እንደ ኾነ ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ” /ዘጸ.32፥32/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “እነርሱ ከተጎዱ የእኔ ክብር ምንም አይደለም፤ የምእመናን ሙላት ማለት የአካል መገናኘትም ነውና፡፡ ታዲያ ራስ የሕይወት አክሊልን አግኝቶ እግር ቢቀጣ ምን ጥቅም አለው?”

Thursday, December 17, 2015

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ (2)


በሥርጉተ ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 07 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ሰማዕትነቱ


ቅዱስ አግናጥዮስ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ በነበረበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከዓላውያን የሮማ ነገሥታት ከፍተኛ መከራና ስቃይ ይደርስባት ነበር:: በድምጥያኖስ ዘመነ መንግሥት ከነበረው የመከራ ማዕበል በጾም እና በጸሎት፣ በብዙ መንፈሳዊ ተጋድሎ፥ በተለይም ምእመናን መከራውን ተሰቅቀው ከሃይማኖት እንዳይወጡ ተግቶ በማስተማር እንደ መልካም ካፒቴን ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መርቶ አሻግሯል:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከትሕትናው የተነሣ ስለ ራሱ ሕይወት እውነተኛ የክርስቶስ ፍቅር ላይ ገና አልደረስኩም፤ እውነተኛ የደቀ መዝሙርነት ፍጽምና ላይ አልደረስኩም እያለ ያዝን ነበር:: በመሆኑም ሰማዕትነት የበለጠ ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርብ በማመን ለሰማዕትነት ክብር እንዲበቃ በእጅጉ ይመኝ ነበር::

FeedBurner FeedCount