(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ኒቆዲሞስ ማለት ድል አድራጊ፣ የሕዝብ አለቃ ማለት ነው፡፡ እውነትም ይህ ሰው አለቃ ነበር፡፡ አለቅነቱስ እንደ ምን ነው? ቢሉ በሦስተ ወገን ነው፡-
(ሀ) በሹመት፡-
የአይሁድ ሸንጎ - ማለትም የሳንሄድሪን - አባል ነበርና፡፡ ይህ እንግዲህ (ምንም እንኳን የሚያውክ ንጽጽር ቢኾንም) በእኛ ስናየው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የኾነ አንድ ሊቀ ጳጳስ እንደ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ዝቅ ብሎ ሊማር መጣ፡፡ ከማን? ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ይበልጥ እንደነቃለን፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳን ጓደኞቹ ትምህርትን የማይወዱ፣ እውነትን የሚጠሉ፣ ጌታችንን ለመግደል ዕለት ዕለት የሚመክሩ ቀናተኞች ቢኾኑም ኒቆዲሞስ ግን ከእነርሱ ተለይቶና ሹመቱ ሳያስታብየው በሥጋ ዕድሜ ከእርሱ ከሚያንስ ከጌታችን ዘንድ ሊማር ነውና የሚመጣው፡፡ እስኪ ትልቅ ጥምጣሙን አድርጎ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ሲማር በዓይነ ሕሊናችሁ ሳሉት! እንደ ምን ያለ ትሕትና ነው? እንዴት እውነትን የተጠማ ሰው ነው? “ቀን አይመቸኝምና ማታ አልሔድም፤ እንደዉም ጥሩ ምክንያት አገኘሁ” አላለም፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ተመሳስዬ ልኑር አላለም፡፡ ጌታችን የወደደውና ለትውልድ ኹሉ የተረፈ ምሥጢር - ስለ ጥምቀት - ያስተማረውም ስለዚሁ ግሩም ትሕትናውና ቅንዓቱ ነው፡፡ “ሥራህን ትተህ ለምን በቀን አትመጣም?” አላለውም፡፡ “አንተን ብቻ አላስተምርም” አላለውም፡፡ “ለምን ጓደኞቼ ያዩኛል ብለህ ፈራህ?” አላለውም፡፡ “ለምን እንደ ዕሩቅ ብእሲ ቈጥረህ መምህር ትለኛለህ?” አላለውም፤ በፍጹም፡፡ ሹመቱና እልቅናው ሳይታሰበው ዝቅ ብሎ ሊማር መጥቷልና፡፡ “አለቃ ስኾን እንዴት ለመማር - ያውም በጨለማ - እሔዳለሁ?” አላለምና፡፡ በመኾኑም ቸሩ ጌታችን እንደ ሳምራይቱ ሴት ለብቻውም ቢኾን የማታ ክፍለ ጊዜ አዘጋጀለት፡፡