(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 11
ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከሊባንዮስ ሲማር የቆየውን የንግግር ክህሎት ትምህርት የጨረሰው በ367 ዓ.ም. ላይ ነበር፡፡ ትምህርቱ የሚያልቅበት ወራት ራሱ ሰኔ አከባቢ ሲኾን ሐምሌ፣ ነሐሴና መስከረምም የዕረፍት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት 18 ዓመቱ ነበር፡፡ ዜና ሕይወቱን የጻፈው ጳላዲዮስ እንደተናገረው ቅዱስ ዮሐንስ ከጓደኞቹ ይልቅ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ዕውቀት ያለው ነበር፡፡ በትምህርቱ ብቻ ሳይኾን ወጣትነቱም ለብዙ ሰዎች አርአያ ነበር፡፡
ትምህርቱን ቢጨርስም ከእናቱ ጋር ነበር፡፡ ብዙ ጓደኞች ቢኖሩትም እንደ ባስልዮስ ግን የሚቀርበው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እድገታቸው በአንድ ሰፈር ነው፤ የተማሩት በአንድ ትምህርት ቤት ነው፤ ምግባራቸው የቀና ለብዙ ወጣቶችም አርአያ በመኾን የተመሰገኑ ናቸው፡፡
በኋላ ላይ ግን ከባስልዮስ ጋር ለጥቂት ጊዜያት ተለያዩ፡፡ የመለያየታቸው ምክንያትም ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ፍርድ ቤቶች እየሔደ እዚያ የሚሰጡትን ፍርዶች መስማት ያስደስተው ስለ ነበር ነው፤ የንግግር ክህሎት ከሊባንዮስ መማሩ ይህን እንዲወድ አድርጎታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልክ እንደ አብዛኛው የአንጾኪያ ሕዝብ ቲያትርን ይወድ ነበር፡፡ ጓደኛው ባስልዮስ ግን በእንደዚህ ዓይነት ነገር ብዙም ግድ አይሰጠውም ነበር፡፡ ባስልዮስ ይወደው የነበረው መጻሕፍትን ማንበብ ነው፡፡
ታሪክ ጸሐፊዎቹ ሶቅራጠስና ሶዞሜን እንደጻፉት፥ ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤቶች መሔዱ በኋላ የሕግ ጠበቃ ለመኾን በር ከፍቶለታል ይላሉ፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥም በሚያደርጋቸው ንግግሮች በሊባንዮስና በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ የከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካሪ፣ ሕግ አውጪ፣ አባቱ ሲያገለግልበት ከነበረው ከከፍተኛው ወታደራዊ ማዕርግ በላይ ወደ መኾን የሚያሸጋግረው ኾነ፡፡