(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 9 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች ሆይ! ግንቦት 12 የተወዳጁ አባታችን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት እንደ መኾኑ ስለ ሊቁ ከዚህ በፊት ከምናውቀው በተጨማሪ አንዳንድ ነገሮችን እንድንነጋገር ወድጃለሁ፡፡
በዚሁ የመጀመሪያ ክፍልም ስለ ተወለደባትና ስላደገባት ከተማ ስለ አንጾኪያ የተወሰኑ ነጥቦችን እንነጋገራለን፡፡ መልካም ንባብ!
በአራተኛ መ.ክ.ዘ. አጋማሽ ላይ በሮማ ክፍለ ግዛት እጅግ በጣም ከሚታወቁት ከተሞች አንዷ አንጾኪያ ነች፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት አንጣክያ ተብላ በምትታወቀው የደቡብ ቱርክ ውስጥ የምትገኝ የሶሪያ ልሳነ ምድር ነች፡፡
ይህቺ ከተማ በ300 ቅ.ል.ክ. የታላቁ እስክንድር ጀኔሮችሎች አንዱ በሚኾን በሴሉከስ ቀዳማዊ ኒካቶር በደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኝ ባሕሩ በሚፈስ ኦሮንቶስ በተባለ ወንዝ ዳር የተመሠረተች ናት፡፡ አጥሯ ግንብ ሲኾን 10 ኪሎ ሜትር ያህል ይረዝማል፡፡ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 508 ሜትር ከፍታ ያለውና በደን የተሸፈነ ተራራ አላት፡፡ ዋናው መንገዷ በእብነ በረድ የተነጠፈ፣ በኹለቱም አቅጣጫ ኹለት ፎቅ ባላቸው ሕንፃዎች የደመቀ፣ ሌሊት ሌሊት በዘይት በሚሠሩ መብራቶች ያሸበረቀ ነው፡፡ ከተማይቱ እጅግ አስደናቂ በኾኑ ሕንፃዎች የተዋበች፣ በቂ የሚባል የውኃ ተደራሽነት ያላት፣ 18 የሚኾኑ የመዋኛ ሥፍራዎችና ቲአትር ቤቶች እንዲሁም የሰረገላ እሽቅድድም ቦታዎች የሚገኙባት ናት፡፡ ከከተማይቱ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 8 ኪሎ ሜትር ላይ ነፋሻማ ቦታ ላይ የተሠሩ ቪላ ቤቶች፣ አሁንም በጥቅም ላይ ያሉ ፏፏቴዎች፣ አፖሎ የተባለ ጣዖት ቤትና የኦሎምፒክ ውድድር በየጊዜው የሚካሔድበት ሥፍራ የሚገኙባት ከተማ ነች፡፡
ኤስያንና ሜድትራንያንን በሚያገናኝ መስመር የምትገኝ የንግድ ዋና ማእከል እንደ መኾኗ፣ ሴሉኪያ በተባለ ወደብ አጠገብ እንደ መገኘቷ፣ ሰፋፊ እርሻዎች በሚካሔዱበት አከባቢ እንደ መከተሟ አንጾኪያ እጅግ ሀብታም ከተማ እንድትኾን አድርጓታል፡፡ በውስጧ ሳንቲምና የጦር መሣሪያ ዕቃዎች የይመረቱባታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከተማይቱ ባሏት ትምህርት ቤቶችና እጅግ የተማሩ ሰዎች የታወቀች ነች፡፡ የሮማው ምሥራቃዊ ክፍለ ግዛት የጦር ማእከልም ነች፡፡
በጥንቱ መመዘኛ ስትታይ አንጾኪያ በጣም ትልቅ ከተማ ነች፡፡ ምንም እንኳን ከሮም ብታንስም ከቁስጥንጥንያና ከአሌክሳንድርያ ከተሞች ግን የምትወዳደር ነች፡፡ በከተማዋ ይኖር የነበረው የሕዝብ ብዛት እስከ ሦስት መቶ ሺሕ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ምንም እንኳን የተለያየ ሕዝብ ይኖርባት የነበረ ቢኾንም አብዛኛው ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ ግን ግሪክኛ ነው፡፡ ከከተማይቱ ዙርያ ይኖሩ የነበሩ ገበሬዎች ግን የሶሪያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ሕዝቧ መካከል አንድ ዐሥረኛው ድኻ ነው፡፡ ከሕዝቡ የሚበዛውም ክርስቲያን ነው፡፡ ከክርስቲያኖች በተጨማሪም ግን አሕዛብ ነበሩ፤ አይሁድም ነበሩ፡፡
አንጾኪያውያን በክርስትናቸው እጅግ ይኮሩ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያታቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ ክርስቲያኖች የተባሉት እነርሱ እንደ ኾኑ በማሰብ፣ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ከተማቸው መጥተው ስላስተማሩ፣ ጉባኤ ኒቅያ በስድስተኛው ቀኖና ላይ አንጾኪያን ልክ እንደ ሮምና አሌክሳንድርያ እኩል ሥፍራ ስላገኘችና በሌሎችም ምክንያቶች ነው፡፡
በአንጾኪያ የነበረው ትልቁ ቤተ ክርስቲያን ባለ ስድስት ማዕዘን ሲኾን በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በ327 ዓ.ም. ተጀምሮ በልጁ አልቆ በጥር 6 341 ዓ.ም. ላይ አገልግሎት የጀመረ ነው፡፡ ይህ እጅግ አስደናቂ የኾነው ቤ/ክ. የተሠራው በቤተ መንግሥቱ አጠገብ ነበር፡፡ ከዚህ ትልቅ ቤ/ክ. በተጨማሪ በከተማይቱ ሦስትና አራት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ ከእነዚህ በጣም የምትታወቀው ፓለዪያ የተባለችዋ ነች፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የሰማዕታት ዓፅም ያረፉባቸው ቅዱሳን መካናት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በቅዱስ ባቢላስ፣ በመቃብያን የተሰየሙና እነዚህ ሰማዕታት ያረፉባቸው ናቸው፡፡
የአንጾኪያ ሕዝብ በጣም ይወደው የነበረው የመዝናኛ ዓይነት የፈረስ ግልቢያና ቲያትር ሲኾን ከከተማይቱ ውጪ ወደሚገኙ ፏፏቴዎች በመሔድም ይዝናኑ ነበር፡፡
ከዚሁ በተቃራኒ ደግሞ በአንጾኪያ ዙርያ ያሉ ተራራዎች በባሕታውያንና በመነኮሳት የተሞሉ በዓቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ባሕታውያንና መነኮሳት ለአንዳንድ ጉዳይ ካልኾነ በስተቀር ወደ ከተማይቱ አይወጡም ነበር፡፡ ከወጡ ግን ሕዝቡ በአጠቃላይ - ክርስቲያኑም ክርስቲያን ያልኾነውም - የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሳይቀሩ እጅግ በጣም ያከብሯቸው ነበር፡፡ በመኾኑም ከእነዚህ ገዳማውያን አባቶች በረከት ለመቀበል፣ ለምክር ሕዝቡ ወደ በዓቶቻቸው በየጊዜው ይሔድ ነበር፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንግዲህ የሚወለደው በዚህች እጅግ ውስብስብና ደማቅ ከተማ ነው!
kale hiwote Yasemalene
ReplyDelete