(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 10 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች ሆይ! በክፍል አንድ ትምህርታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ተወለደባት ከተማ ስለ አንጾኪያ ጥቂት ተነጋግረናል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ወደ ሊቁ ልደትና እድገት እንቀጥል፤ መልካም ንባብ!
ከአንደበተ ርቱዕነቱ የተነሣ አፈወርቅ የተባለው ይህ ቅዱስ የተወለደው በ347 ዓ.ም. ነው፡፡ 50 ዓመት የሚኾን ዕድሜውን የሚያሳልፈውም በዚህች በአንጾኪያ ከተማ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዕድሜ በ330 ዓ.ም. ገደማ ከተወለዱት ከቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያና ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደዚሁም በ335 ዓ.ም. ከተወለደው ከቅዱስ ባስልዮስ ታናሽ ወንድም ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በዕድሜ ያንሳል፡፡ ከአባ ሆሮኒመስ ደግሞ ተቀራራቢ ዕድሜ አላቸው፡፡ በኋላ ከመንበሩ እንዲጋዝ ከሚያደርገው ከአሌክሳንድርያው ፓትሪያርክ ከቴዎፍሎስም ጋር ልደታቸው ተቀራራቢ ነው፤ ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ የሚወለደው በ345 ዓ.ም. ላይ ነውና፡፡
አባቱ ሱኩንዶስ ሲባል እናቱ ደግሞ አንቱዛ ትባላለች፡፡ ሱኩንዶስ የሚለው ስም በላቲን እንደ መኾኑ አባቱ የሮም ተወላጅ ኾኖ በአንጾክያ ይኖር እንደ ነበር ያመለክታል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አክስት ማለትም የሱኩንዶስ እኅት የምትኾን “ሳባንያና” ም ስሟ የላቲን መኾኑ ይህን ያጠናክራል፡፡ ሳባንያና እጅግ መንፈሳዊት ሴት እንደ ነበረች የሊቁን ዜና ሕይወት የጻፈው ጰላድዮስ መስክሯል፡፡ ሊቁ ታላቅ እኅት የነበረችው ስትኾን ስሟ ማን እንደሚባል ግን እስከ አሁን ባለው መረጃ እኛ ጋር አልደረሰም፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከባለጸጋ ቤተሰብ እንደ ነበረ ማወቅ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እናቱ አንቱዛ - በኋላ እንደምንመለከተው - ልጇን የምታስተምርበት ትምህርት ቤት በዚያ ሰዓት እጅግ የታወቀ ትምህርት ቤት ነውና፡፡ ምንም እንኳን ስለ አባቱ ብዙ መናገር ባንችልም እናቱ ግን እጅግ ብርቱ ክርስቲያን እንደ ነበረች ሊቁ ራሱ “በእንተ ክህነት” በተባለ መጽሐፉ ላይ ተናግሯል፡፡ እናቱ እንደዚህ ብርቱ ክርስቲያን ብትኾንም ግን እስኪያድግ ድረስ አልተጠመቀም ነበር፡፡ ይህም የኾነበት ምክንያት በዚያን ጊዜ የነበሩ ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ ኃጢአት እንዳይሠሩ ይፈሩ ስለ ነበርና የሕዝቡ ልማድ ኾኖ ስለ ነበር ነው፡፡
የሊቁ አባት ያረፈው አንቱዛ 20 ዓመት ሲኾናት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በክርስቲያኑ ብቻ ሳይኾን በሌላውም ሕዝብ በነበረው ልማድ ግን አንቱዛ ድጋሜ ሳታገባ ቀርታለች፡፡ በመኾኑም ሊቁንም ኾነ ታላቅ እኅቱን በኃላፊነት ያሳደገቻቸው እርሷ ብቻዋን ነች፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ! አንቱዛ ገና ወጣት ነች፡፡ የልጆቿ አባት ያረፈው ሕፃናቱ ገና ልጆች ሳሉ ነው፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን የመሰለ ልጅ እንዴት ብታሳድገው ነው እንደዚህ ዓይነት ቅዱስ የኾነው? እርሷስ ምን ያህል ጠንካራ እምነት ያላት ሴት ብትኾን ነው?
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የሕፃንነት ዕድሜውን ያሳለፈው ከተንከባካቢዎቹ፣ ከእናቱ ሠራተኞች፣ በተለይ ደግሞ ከእናቱ ጋር ነው፡፡ በኋላ ወደ ገዳም አብሮት የሚሔደው ባስልዮስ የተባለ የሕፃንነት ጓደኛም ነበረው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ትምህርት ቤት መሔድ ሲጀምር ይማረው የነበረው ትምህርት ከ4ኛው ቅ.ል.ክ. አንሥቶ በግሪኮ-ሮማን ግዛት ይታወቅ በነበረው ሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ሕፃን በሰባት ዓመቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ይጀምርና የሚማሩትም ቀለል ያለ የንባብ፣ የመጻፍና የሒሳብ ትምህርት ነው፡፡ ከዐሥር እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት ሲኾናቸው ደግሞ የሰዋስው ትምህርት ይማራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ሕጻን የጥንት የግሪክ ጽሑፎችን በተለይም የሆሜር፣ የዩሪፒደስ፣ የማናንደር እንዲሁም የዲሞስተነስ ጽሑፎችን መሠረት አድርገው ሰዋስውን ይማራል፡፡ ከዚህም አብሮ የታሪክ፣ የሚቶሎጂ እንዲሁም የሞራል ትምህርቶችን ይማራል፤ በቃላቸውም ይይዛል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ትምህርት ለክርስቲያኖች የሚስማማ ትምህርት ባይኾንም - ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ምንም ይዘት የለውምና - አንቱዛ ግን ልጇን ቅዱስ ዮሐንስን ወደዚህ ትምህርት ቤት ከመላክ ውጪ አማራጭ አልነበራትም፡፡
ይህን ኹለት ደረጃ ካለፉ በኋላ ታዳጊዎቹ የሚማሩት የንግግር ክህሎት ትምህርትን ነው፤ ይኸውም በአንዳንድ ምክንያት ካልዘገየ በስተቀር በ14 ወይም በ15 ዓመታቸው መኾኑ ነው፡፡ እናም በዚህ ጊዜ ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ እንዴት የተለያየ ዓይነት ይዘት ያለውን ንግግር እንደሚያደርጉ ይማራሉ፡፡ ለቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የንግግር ችሎታ አርአያ የነበረው መምህርም ሊባንዮስ ነው፡፡ የፍልስፍና ትምህርት ደግሞ ከአንድራጋትዮስ ተምሯል፡፡ ሊባንዮስ እጅግ የተማረ ሰው ሲኾን በዚያ ሰዓት ስለ ነበረው የከተማይቱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ምን እንደሚመስል በጥልቀት የሚያውቅና የጻፈ ሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን ከተማሪዎቹ መካከል ክርስቲያኖች የነበሩ ቢኾንም፣ ምንም እንኳን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እናት አንቱዛን ጨምሮ ብዙ ክርስቲያኖችን ቢያደንቅም ክርስትናን ግን በጥርጣሬ የሚያየው ሃይማኖት ነበር፡፡
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተለያዩ ድርሳናት እንደምናገኘው ሊቁ ለእነ ሆሜር ጽሑፍ እንዲሁም ሊባንዮስን ለመሰሉ ምሁራን ከፍ ያለ አድናቆት ነበረው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከላይ እንዳየነው የሕፃንነት ዕድሜው በጽሑፋቸውና በትምህርታቸው ስለሚቀረጽ ነው፡፡ በተለይ ሊባንዮስ ለሆሜር፣ ለፕሌቶና ለዲሞስተነስ ጽሑፎች ከፍተኛ ፍቅር ስለ ነበረው ሊቁም እነዚህን መጻሕፍት በጣም ይወዳቸዋል፤ አንብቧቸዋልም፡፡ ለዚህም ነው ሊባንዮስ ሊሞት ሲል “ማን ቢተካህ ትወዳለህ?” ተብሎ ሲጠየቅ፡- “ክርስቲያኖች ከእኛ ሰርቀው ባይወስዱት ኖሮ ዮሐንስ ቢተካኝ እወድ ነበር” ያለው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተወለደ አንሥቶ እስከ 362 ዓ.ም. ድረስ አንጾኪያ አንጻራዊ ሰላም ነበራት፡፡ በ362 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ የመጣው ንጉሥ (ጁሊያን) ግን በሐሰተኛ መረጃ ክርስትናን ከመጥላቱ የተነሣ ክርስቲያኖች በትልልቆቹ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው መማር እንዳይችሉ የሚያደርግ አዋጅ አወጀ፡፡ ይኸውም የተማሩ ክርስቲያኖች እንዳይኖሩ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በከተማይቱ በነበረው የአፖሎ ጣዖት ቤት አምላኪዎች የቅዱስ ባቢላስ ቅዱስ ሥፍራ እንዲፈርስና ከከተማይቱ ውጪ እንዲኾን አድርጓል፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን ተዘግተው የነበሩ አብያተ ጣዖታት አስከፍቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንግዲህ በዚህ የልጅነት ዕድሜው ይህን እየተመለከተ ነበር ያደገው፡፡
ከዚህ በላፈ ደግሞ በዚህ ሰዓት የአንጾኪያ ክርስቲያኖች የውስጥ ጭንቀት ነበረባቸው፡፡ ይኸውም በአርዮስና በኋላም በመቅዶንዮስ አማካኝነት ከተነሡ ኑፋቄዎች መነሻነት ነው፡፡ ምንም እንኳን የአርዮስ ኑፋቄ በ325 ዓ.ም. ላይ ውሳኔ ያገኘ ቢኾንም በ331 ዓ.ም. ላይ የአንጾክያ ሊቀ ጳጳስ የነበረውን ኦርቶዶክሳዊ አባት ኤዎስጣጤዎስን አርዮሳውያኑ መሪዎች በሰበብ በአስባቡ ከመንበሩ ስላሳደዱት ክርስቲያኖቹ ራሳቸው በኹለት ቡድን ተከፍለዋል፡፡ አንደኛው ቡድን አዲስ የሚሾሙትን ጳጳሳት ሳይቀበል በቄስ ጳውሊኖስ መሪነት ኤዎስጣጤዎስን ይጠብቁ የነበረ ሲኾን ሌላኛውና ብዙሃኑን ያካተተው ቡድን ደግሞ ጠንካራ ግንኙነት ባይኖራቸውም ለተወሰኑ ዓመታት ከሚሾሙት ጳጳሳት ጋር ይኖር ነበር፡፡ በ350ዎቹን በ360ዎቹ ላይ ግን ኤይቲዮስና አውኖምዮስ የተባሉ አርዮሳውያን የአርዮስን ምንፍቅና እንደ አዲስ ስላነሡት ከሚሾሙት ጳጳሳት ጋር ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች ግንኙነታቸውን ሙሉ ለሙሉ አቋርጠው በዲያድርስና በፍላቪያን መመራት ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከየትኛው ቡድን ጋር ነበር ያልን እንደ ኾነም በዚህ በዲያድርስና በፍላቪያን ከሚመሩት ጋር ነው፡፡
ከላይ የጠቀስነውና ተሰድዶ የነበረው ኤዎስጣጤዎስ ካረፈ በኋላም በኹሉም ስምምነት ቅንና ንጹህ የኾነ መላጥዮስ የአንጾክያ ሊቀ ጳጳስ ኾኖ ተሸሟል፡፡ ነገር ግን አሁንም በዚያ ሰዓት የነበረው አርዮሳዊ ንጉሥ ቁንስጣ ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ አሳደደው፡፡ ይህ አርዮሳዊው ንጉሥ ግን ታኅሳስ 3 ቀን 361 ዓ.ም. ላይ በድንገት ሞተ፡፡
ቁንስጣን የተካው ንጉሥ ጁሊያን ነው፡፡ ጁሊያን ደግሞ ከላይ እንደገለጽነው የሚወደው አምልኮተ ጣዖትን ስለ ኾነ ለክርስቲያኖችም ኾነ ለአርዮሳውያን ወይም ለሌሎቹ የሃይማኖት ቡድኖች እኩል ነበር፡፡ ለዚህም ነው መላጥዮስ ከተሰደደበት እንዲመለስ ያደረገው፡፡
ነገር ግን በዚህ ጊዜ አንድ አስቸጋሪ ኹኔታ ተከስቶ ነበር፡፡ መላጥዮስ ወደ አንጾክያ ከመመለሱ በፊት ከላይ ስንጠቅሳቸው የነበሩት ኤውጣጥዮሳውያን መሪያቸው ቄስ ጳውሊኖስ የካግሊያሪው ሉሲፈር እየተባለ በሚጠራ ጳጳስ የአንጾኪያ ጳጳስ ኾኖ ተሾሞ ነበርና፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ! በአንዲቷ አንጾኪያ አሁን “ኹለት ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት” ተሾሙ ማለት ነው፡፡ እናም ልዩነቱ እየባሰበት ሔደ፡፡ የአርዮሳውያን ሳያንስ አሁን ሌላ ችግር ተጨመረበት፡፡ በጎነቱ ግን በጳውሊኖስ የሚመሩትም ኾነ በመላጥዮስ የሚመሩት በአርዮሳውያን ላይ አንድ ዓይነት አቋም የነበራቸው መኾኑ ነው፡፡
ልዩነቱ እንዲከር ያደረገው ግን የአሌክሳንድርያ ቤተ ክርስቲያንም ኾነች የሮም ቤተ ክርስቲያን ከመላጥዮስ ይልቅ ለጳውሊኖስ ሕጋዊ ዕውቅናን መስጠታቸው ነበር፡፡ ይህ አሳዛኝ ልዩነት እንግዲህ በኋላ በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ብቻ ሳይኾን በሶሪያ ቤተ ክርስቲያን ላይም ትልቅ ተጽዕኖ ነበረው፡፡
No comments:
Post a Comment