Friday, May 20, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፬

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 12 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

አባ ዮሐንስ አፈወርቅ

ከዚህ በፊት እንደገለጽነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ገዳም እንዳይሔድ የዘገየው በእናቱ ተማጽኖ ነው፡፡ 372 .. ግን እናቱ ስላረፈች ይጓጓለት ወደነበረው ገዳም ሔደ፡፡ የገዳሙ ስም ሲልፕዮስ ይባላል፡፡ ሲልፕዮስ እጅግ ጫካ የተሞላበት የጽሞና ሥፍራ ነው፡፡
ጰላድዮስ እንደሚነግረን ቅዱስ ዮሐንስ ወደዚህ እንደ ደረሰ አንድን አባት አገኘ፤ አባ ሲሲኮስ ይባላሉ፡፡ አራት ዓመትንም ከእርሳቸው ጋር ቆየ፡፡ በዚህ አራት ዓመት ውስጥ ከእኒህ አባት በዓት አጠገብ የራሱ የኾነ በዓት ነበረው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ እንደዚሁም ከቀኑ አብዛኛውን ሰዓት በበዓቱ ያሳልፍ ነበር፡፡ አብዝቶ ይጸልያል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነባል፡፡ በተለይ በዚህ ገዳም የጽሞና ሕይወት በእጅጉ ይተገበር ነበር፡፡ የሚተኛው በሳር በተጎዘጎዘ መሬት ላይ ነበር፡፡ የሚለብሰው የፍየልና የግመል ቆዳ ነው፡፡ የሚበላው በቀን አንዴ ሲኾን ዳቦ በጨው ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህ ኹልጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የኾነው ሕይወት፡- “አዳም ከመበደሉ በፊት የነበረው ሕይወት ነውብሎ የማቴዎስ ወንጌልን ሲተረጉም 38ኛው ድርሳኑ ላይ ገልጾታል፡፡ አባ ሲሲኮስ ብዙ አምላካዊ ራዕዮችን እያዩ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የወደፊት ታላቅነቱን ዐይተዋል፡፡


ከዚህ የአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አሁንም ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሸጋገረ፡፡ መጀመሪያ ሲመጣ ካገኛቸው አባትም ተለየ፡፡ ለብቻው ወደ ሌላ በዓት ሔደ፡፡ ፈጽሞም ከሰው ተለየ፡፡ አይተኛም ማለት ይቻላል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠናል፡፡ ማጥናት ብቻ ሳይኾን በቃሉ ይይዛቸዋል፡፡ የሚበላው በጣም መናኛ ነገር ነው፡፡ከዚህም የተነሣይላል ጰላዲዮስከዚህም የተነሣ ጨጓራው ክፉኛ ታመመ፡፡ ከቅዝቃዜው የተነሣ ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ ወደ መኾን ደረሱ፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከባድ ራስ ምታትና የጨጓራ በሽታ ያመው እንደዚሁም ሰውነቱ ብርድን የማይችል የነበረው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ወደ ኦሎምፒያስ በጻፋቸው መልእክታቱ ላይ እነዚህን ሕመሞቹ በደንብ ጠቅሷቸዋል፡፡ አላነበባችሁትም? 
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ በጣም ከባድ የኾነ የትኅርምት ሕይወት የቆየው ለኹለት ዓመት ነው፤ እስከ 378 .. ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ምንም ማድረግ ስላልቻለ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ፡፡ ጰላዲዮስ ግን እንዲህ ይላል፡- “ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይኾን ዘንድ የእግዚአብሔር ሥራ በሕመሙ ምክንያት በዓቱን ትቶ ወደ አንጾኪያ እንዲመጣ አደረገው፡፡ምንም ወደ ከተማ ቢመለስም ግን ጤንነቱ በሚፈቅድለት መጠን የምንኩስና ሕይወቱን እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ይዞት ቀጥሏል፡፡ ወዲያው እንደተመለሰም የምንኩስና ሕይወትን ለሚያንቋሽሹ ሰዎች የጻፈው ድንቅ መጽሐፍ አለው፡፡ 
በዚህ ዓመት ላይ 364 .. አንሥቶ በሥልጣን ላይ የነበረውና 365 .. ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስን ያሳደደው ንጉሥ ቫሌንስ ስለ ሞተ ሊቀ ጳጳሱ ከተሰደደበት ከአርማንያ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ፡፡ እዚህ ላይ ግር እንዳይላችሁ! ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ ዮሐንስ አፈወርቅን ያጠመቀው ወደ አንጾኪያ በየጊዜው ይመላለስ ስለ ነበር ነው!
ያም ኾነ ይህ ከጳውሊኖስና ከጥቂት ተከታዮቹ በስተቀር ብዙው ሕዝብ ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስን እንደ ሕጋዊ ሊቀ ጳጳሳቸው ተቀበሉት፡፡ አሌክሳንድርያና ሮም ዕውቅናን የሰጡት ለጳውሊኖስ ስለ ነበረ ጳውሊኖስ ተጨነቀ፡፡ ነገር ግን ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ ቀርቦ ስላናገረው ተስማሙ፡፡ ጳውሊኖስ ማዕርጉ ሳይሻር እንደ ካህን ኾኖ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲያገለግል ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ ግን የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ ኾኖ እንዲያገለግል ተስማሙ፡፡

ዲያቆን ዮሐንስ አፈወርቅ
ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ አብያተ ክርስቲያናትን ማጠናከር ጀመረ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም እንደ ጥንቱ የአናጉኒስጥስነት ተግባሩን ቀጠለ፡፡ ለኹለት ዓመትም በዚህ የማንበብ ማዕርግ ቆየ፡፡ 381 .. መጀመሪያ ላይ ግን ቅዱስ ዮሐንስን ዲያቆን አድርጎ ሾመው፡፡ 
ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ ጥር 381 .. ላይ ስላረፈ አሁንም ሌላ ችግር ተፈጠረ፡፡ በዚህ ጊዜ በመቅዶንዮስ ዙርያ ለመነጋገር ጉባኤ ተደርጎ ነበር፤ በቁስጥንጥንያ፡፡ የጉባኤው መሪ የነበረው መላጥዮስ ነው፡፡ ነገር ግን በድንገት ስላረፈ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ጉባኤውን መራው፡፡ አብረውም ስለ አንጾኪያ አነሡ፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ መንበሩን በጳውሊኖስ እንዲያዝ አሳብ ሲያቀርብ ሌሎች አበው ሊቃነ ጳጳሳት ግን አዲስ እንዲሾም ወሰኑ፡፡ በመኾኑም ፍላቪያን ተሾመ፡፡ ሮም ግን አሁንም ለፍላቪያን ዕውቅናን ነፈገችው፡፡
ምንም እንኳን ቅዱስ ዮሐንስ በሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ ዕረፍት በጣም ቢያዝንም ከአዲሱ ሊቀ ጳጳስ ከፍላቪያን ግን ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር የዲቁና አገልግሎቱን ቀጠለ፡፡ ሊቁ አገልግሎቱ ምን እንደ ነበረም የማቴዎስ ወንጌልን ሲተረጉም 82ኛው ድርሳኑ ላይ ጠቅሶታል፡፡ 
ከዚህም በተጨማሪ አንድ ዲያቆን ሊቀ ጳጳሱን መራዳት እንጂ መስበክ ስለማይፈቀድለት አገልግሎቶቹ ሕሙማንን መንከባከብ፣ እጓለ ማውታንን ማሳደግ፣ ድኾችን መርዳትና የመሳሰሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ዮሐንስ በእነዚህ ተግባራት ላይ ያገለግል ነበር፡፡ ምንም እንኳን በዓውደ ምሕረት ላይ ወጥቶ መስበክ ባይችልም ጣቶቹ ግን ከመጻፍ አልተቆጠቡም፡፡ ስለ ጋብቻ፣ ሰው ለምን በየጊዜው መከራ እንደሚደርስበት፣ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ ባቢላስ፣ ለአይሁድ እንዲሁም ለአረማውያን መልስ የሚኾኑ፣ ብቻ እዚህ እንዘርዝራቸው ቢባል የዚህ ጽሑፍ ዳራ የሚወስነን ብዙ መጻሕፍትን ጽፏል፡፡

ቀሲስ ዮሐንስ አፈወርቅ
386 .. ላይ ሊቀ ጳጳስ ፍላቪያን ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና ሾመው፡፡ በተሾመ ዕለትም ሊቀ ጳጳሱ ባለበት ነገ ሕዝቡ ምን ሊጠብቁ እንደሚገባቸው የሚያሳይ ድንቅ ስብከት ሰጠ፡፡ 
በዚህ ጊዜ የአንድ ቄስ ኃላፊነት በዋናነት መስበክና የንስሐ አባት ኾኖ ሕዝቡን መምከር ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ይህንን በአግባቡ የሚወጣ ትጉህ አባት ነው፡፡ 386 እስከ 397 .. ድረስም በአንጾኪያ የመጀመሪያው ሰባኪ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ከሊቀ ጳጳስ ፍላቪያን ጋር እየተዘዋወረ ሰብኳል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ይሰብከው የነበረው ግን ስለ አንጾኪያ ከተማ ስንነጋገር ነበረ ስላልነው ባለ ስድስት ማዕዝኑና ወርቃማው ቤተ ክርስቲያን ላይ ነው፡፡ በሐዋርያት እንደ ታነጸ በሚታመነው ፓለዪያ በሚባለው ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን ላይም ደጋግሞ ያስተምር ነበር፡፡ በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይኾን ቅዱሳን ሰማዕታት ዓፅማቸው ባረፈበት ቦታ ላይ በበዓለ ዕረፍታቸው ቀን እየሔደ ያስተምር ነበር፡፡ እንዲያውም ወደዚህ ቦታ የመጡትን ምእመናን ወደ ጦር ካምፕ እንደመጡ ይነግራቸው ነበር፡፡ በጦር ካምፕ ብዙ የጦር መሣሪያዎች እንዳሉ ኹሉ በእነዚህ የሰማዕታት መካነ መቃብርም መንፈሳዊ መሣሪያ እንዳለና ምእመናኑንም ይህንን ታጥቀው ወደ ጦር ሜዳ ማለትም ወደ መንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሔዱ ያስተምራቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ያስተምራቸው የነበሩ ትምህርቶችም መድረክ ላይ ኾኖ እንደሚያስተምራቸው ኾነው ወደ እኛ ደርሰዋል፡፡ ይህም የኾነበት ምክንያት መቅረጸ ድምጽ ስለ ነበረ ሳይኾን ታሪክ ጸሐፊው ሶቅራጠስ እንደ ተናገረው ሊቁ የሚናገረውን በቀጥታ በአጭር በአጭር እየጻፉ በኋላም እርሱ ራሱ የአርትዖት ሥራውን የሚሠራላቸው አጭር ጽሕፈት የሚጽፉ ኹለት ሰዎች (ስቴኖግራፈርስ) ስለ ነበሩ ነው፡፡
በጣም የሚያስደንቀው ደግሞ ሲያስተምር አይዘጋጅም፡፡ ማስታወሻ ወረቀት አይይዝም፤ መጽሐፍ ቅዱስን እንኳን በቃሉ ነው የሚያውቀው፡፡ ይህም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደ ኾነ በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል፡፡
ትምህርቱን የሚያስተምረው በበዓላት፣ እሑድ እሑድ ከቅዳሴ በኋላ፣ ዓርብና ቅዳሜ ነበር፡፡ ዐቢይ ጾም ሲኾን ግን በቅርቡ በታተመው በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ እንደ ገለጽሁት በየቀኑ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንድ ቄስ ለንኡሰ ክርስቲያን ትምህርትን የመስጠት ግዴታ ስለ ነበረበት ቅዱስ ዮሐንስም ይህን ያደርግ ነበር፡፡ እንዲያውም ለእነርሱ የሚኾን መጽሐፍም አዘጋጅቷል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አብዛኞቹን መጻሕፍቱ ያዘጋጃቸው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ እነዚህንና እነዚህን አዘጋጀ ለማለትና መጻሕፍቱ ስለ ምን እንደሚናገሩ ለመጻፍ በዚህች ቁንጽል ጽሑፍ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ ባይኾን እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ ወይ በመጽሐፍ መልክ አልያም ደግሞ በዚህ በመቅረዝ ድረ ገጽ እንመለስባቸዋለን፡፡ ምሳሌ ለመስጠት ያህል ግን በእንተ ሐወልታት፣ የማቴዎስ ወንጌል ማብራርያ፣ የዮሐንስ ወንጌል ማብራርያ፣ አብዛኞቹ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ማብራርያዎችና የመሳሰሉት ኹሉ በዚህ ወርቃማው ጊዜ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሐንስ አፈወርቅ ሊቀ ጳጳስ ዘቁስጥንጥንያ
ሕዳር መጨረሻ 397 .. ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አንድ አስቸኳይ መልእክት ተቀበለ፤ የአንጾኪያ ገዢ ከሚኾን ከአስተርዮስ የተላከ መልእክት ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መልእክቱን ተቀበለ፡፡ አነበበው፡፡ የሮማውያን በር ተብሎ በሚታወቀው በር በኩል ከዋናው አጥር ውጪ ባለው የሰማዕታት መካነ መቃብር ላይ ፈጥኖ እንዲመጣ የሚናገር ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደ ተባለው ወደ ተጠቀሰው ሥፍራ ሔደ፡፡ የጠበቀው ግን ሌላ ነገር ኾነበት፡፡ ከቤተ መንግሥት የተላኩ ወታደሮች 25 .. ያህል አርቀው ወሰዱት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ለምን ይህን እንደሚያደርጉ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ በዚህ ሰዓት ግን የአንጾኪያው ከተማ ገዢ አስተርዮስ እውነቱን ነገረው፡፡ ትእዛዙ የመጣው ከንጉሥ አርቃድዮስ እንደ ኾነ፣ እየወሰዱት ያሉት የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ወራሴ መንበር የነበረው የቁስጥንጥንያው ጳጳስ ኔክታርዮስ በዚሁ ዓመት መስከረም 26 ላይ ስላረፈ በእርሱ ቦታ ጵጵስናን ለመሾም እንደ ኾነ፣ እንዲህ በዘዴ እንዲወጣ ማድረጉም ምእመናን አባታችንን አንሰድም ብለው ተቃውሞ እንዳያስነሡ አስቦ እንደ ኾነ እውነቱን አሳወቀው፡፡
ከስድስት ቀናት የቀንና የሌሊት ጉዞ በኋላ ቁስጥንጥንያ ደረሱ፡፡ የካቲት 26 ቀን 398 .. ላይም ያለ ውዴታው፣ ምንም ሳይጠየቅ ብዙ ጳጳሳት ባሉበት በእስክንድርያው ፓትሪያርክ በቴዎፍሎስ እጅ ተሾመ፡፡

ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሾም ፈቃዱ አልነበረም፡፡ የንጉሡ ግዴታ ኾኖበት እንጂ የራሱ ዕጩ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ስለ ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ ወደ በኋላ እንመለስበታለን፡፡ አሁን ግን ወደ አዲሱ ፓትሪያርክ ወደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሐንስ አፈወርቅ ሊቀ ጳጳስ ዘቁስጥንጥንያ እንመለስ!

አዪ! ከዚህ በላይ ብቀጥል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ነገር እንዳላበዛባችሁ ዝንጋዔም እንዳላመጣናችሁ ስለ ፈራሁ ይህን ክፍል በዚህ እንቋጨው፡፡ አቤት! የዚህ ጽሑፍ ዳራ አናሳ ኾኖብኝ ግን ስንት ነገር ነው የዘለልኩት?!
በቀጣዩና በመጨረሻው ክፍል እንገናኝ!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount