Thursday, May 19, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፫


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 11 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከሊባንዮስ ሲማር የቆየውን የንግግር ክህሎት ትምህርት የጨረሰው 367 .. ላይ ነበር፡፡ ትምህርቱ የሚያልቅበት ወራት ራሱ ሰኔ አከባቢ ሲኾን ሐምሌ፣ ነሐሴና መስከረምም የዕረፍት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት 18 ዓመቱ ነበር፡፡ ዜና ሕይወቱን የጻፈው ጳላዲዮስ እንደተናገረው ቅዱስ ዮሐንስ ከጓደኞቹ ይልቅ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ዕውቀት ያለው ነበር፡፡ በትምህርቱ ብቻ ሳይኾን ወጣትነቱም ለብዙ ሰዎች አርአያ ነበር፡፡ 
ትምህርቱን ቢጨርስም ከእናቱ ጋር ነበር፡፡ ብዙ ጓደኞች ቢኖሩትም እንደ ባስልዮስ ግን የሚቀርበው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እድገታቸው በአንድ ሰፈር ነው፤ የተማሩት በአንድ ትምህርት ቤት ነው፤ ምግባራቸው የቀና ለብዙ ወጣቶችም አርአያ በመኾን የተመሰገኑ ናቸው፡፡ 
በኋላ ላይ ግን ከባስልዮስ ጋር ለጥቂት ጊዜያት ተለያዩ፡፡ የመለያየታቸው ምክንያትም ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ፍርድ ቤቶች እየሔደ እዚያ የሚሰጡትን ፍርዶች መስማት ያስደስተው ስለ ነበር ነው፤ የንግግር ክህሎት ከሊባንዮስ መማሩ ይህን እንዲወድ አድርጎታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልክ እንደ አብዛኛው የአንጾኪያ ሕዝብ ቲያትርን ይወድ ነበር፡፡ ጓደኛው ባስልዮስ ግን በእንደዚህ ዓይነት ነገር ብዙም ግድ አይሰጠውም ነበር፡፡ ባስልዮስ ይወደው የነበረው መጻሕፍትን ማንበብ ነው፡፡
ታሪክ ጸሐፊዎቹ ሶቅራጠስና ሶዞሜን እንደጻፉት፥ ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤቶች መሔዱ በኋላ የሕግ ጠበቃ ለመኾን በር ከፍቶለታል ይላሉ፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥም በሚያደርጋቸው ንግግሮች በሊባንዮስና በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ የከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካሪ፣ ሕግ አውጪ፣ አባቱ ሲያገለግልበት ከነበረው ከከፍተኛው ወታደራዊ ማዕርግ በላይ ወደ መኾን የሚያሸጋግረው ኾነ፡፡

ምንም እንኳን ቅዱስ ዮሐንስ ከላይ ወደ ገለጽናቸው ሹመቶች ይሸጋገራል ተብሎ ቢጠበቅም አስተሳሰቡ ኹሉ በአንድ ጊዜ ወደ ሌላ ነገር ተለወጠ፡፡ የመምህራኖቹ ትምህርት አስጠላው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት ፍቅር ተነደፈ፡፡ አስቀድሞ ጓደኛው ባስልዮስ በሔደበት መንገድ ለመጓዝ ወሰነ፡፡ በዚያ ሰዓት አነጋገርየፍልስፍና ኹሉ ጣሪያወደሚኾን ትምህርት - ይኸውም ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ ማንበብ - መጣ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስና ባስልዮስ ለምን ያህል ጊዜ ተለያይተው እንደ ነበረ ቁርጥ አድርገን መናገር ባይቻለንም መለያየታቸው የጥላቻ አልነበረምና ቅዱስ ዮሐንስ ድጋሜ በባስልዮስ ተማረከ፡፡ ባስልዮስም እጁን ዘርግቶ ጓደኛውንእንኳን ደኅና መጣህአለው፡፡ ባስልዮስ ከቅዱስ ዮሐንስ አስቀድሞ በሕሊናው ሲያመላልሰው የነበረው አንድ ዕቅድም አጫወተው፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን በጥልቀት ለማጥናት ከቤታቸው ወጥተው ወደ ገዳም መሔድ! ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ እጅግ ደስ ብሎት ተስማማ፡፡ ለመሔድ ወስነውም የሚያስፈልጋቸን ነገር ኹሉ አሰናዱ፡፡ ዝግጅታቸውን እንደ ጨረሱ ግን አንድ ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ፡፡ የዚህ ምክንያቱም አንቱዛ ነበረች፡፡ ወደ ገዳም ሊሔዱ እንደ ኾነ በሰማች ጊዜ አለቀሰች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ፡- “እናቴ ምን ኾንሽ?” አላት፡፡ አንቱዛም በእናትነት ድምጿ እንዲህ ስትል መለሰችለት፡- “ልጄ ወዳጄ! ለኹለተኛ ጊዜ ባልቴት አታድርገኝ፡፡ በሕይወት እስካለሁ ድረስም ከአጠገቤ አትራቅብኝ፡፡ቅዱስ ዮሐንስ እናቱን አሳዝኗት ሊሔድ ስላልወደደ ገዳማዊ ሕይወቱን ለጊዜውም ቢኾን አዘገየው፡፡ ምንም እንኳን እጅግ ወደጓጓለት ገዳማዊ ሕይወት ለጊዜው መሔድ ባይችልም ግን ቤቱን ወደ ገዳምነት ለወጠው፡፡ ራሱን ከውጪው ዓለም ለየ፡፡ ለቁመተ ሥጋ ያህል ብቻ እየቀመሰ፣ ለጥቂት ጊዜ ብቻም መሬት ላይ እየተኛ ቶሎ ቶሎ ለጸሎት ይነሣል፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ በየጊዜው ወደ አንጾኪያ የሚመጣውና በስደት በአርማንያ የሚኖረው ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ በሚያደርጋቸው ነገሮች በጣም ማረከው፡፡ መላጥዮስም ቅዱስ ዮሐንስን በተሰጥኦው፣ በመልካም ጠባዩና ሕይወቱ ስለ ወደደው ዘወትር ከእርሱ ጋር እንዲኾን ለመነው፡፡ ይህ የቅዱስ ዮሐንስና የሊቀ ጳጳሱ የመላጥዮስ ግንኙነትም በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ሌላ አዲስ ምዕራፍን ከፈተ፡፡ ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስ አጠመቀው! ከዚያ በኋላም ለሦስት ዓመት አስተማረው፡፡ከዚያን ጊዜ ጀምሮይላል ጰላድዮስ፡- “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፈጽሞ አልማለም፤ ማንንም አላማም፤ በሐሰት አልተናገረም፤ ማንንም አልተሳደበም፤ ጥቅም የሌለውን ነገር ታግሦ አልሰማም፡፡ይህ የኾነው እንግዲህ 368 .. ነው፡፡ አንዳንዶች 370 .. ነው ይላሉ፡፡ ይህን የሚሉበት ምክንያትም ቢያንስ የኹለት ዓመት የንዑሰ ክርስቲያን ትምህርትን ስለሚማር ነው የሚል ነው፡፡ ነገር ግን በዚያ ሰዓት ባሕል አንድ ሰው ቢያንስ የኹለት ዓመት የአመክሮ ጊዜ የሚሰጠው ከአሕዛብ የመጣ ከኾነ ነው፡፡ የክርስቲያን ቤተሰብ ልጅ ከኾነ ግን የአመክሮ ጊዜው ከተወለደበት ጊዜ አንሥቶ ነው፡፡ ያም ኾነ ይህ ቅዱስ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተጠመቀበት ዕለት ይታወቃልን?” ቢሉ አዎ! መቼ ነው? የበዓለ ትንሣኤ ዕለት ሌሊት! የፋሲካ እሑድ!
የታሪክ ጸሐፊው ሶቅራጠስ እንደሚነግረን፥ ቅዱስ ዮሐንስ ከተጠመቀ ወዲህ ዓለምን ትቷል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ዘወትር ያጠና ነበር፡፡ በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሔደ ይጸልይ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ የነበሩት ኹለት ሰዎችን አሳምኗል፤ ቴዎድሮስንና ማክሲመስን፡፡ ስለ ማክሲመስ ብዙ የምናውቀው ነገር ባይኖርም ቴዎድሮስ ግን በኋላ የሜውፕሳስትያ ሊቀ ጳጳስ የኾነ ነው፡፡ ስለ ቴዎድሮስ በቅርቡ ሊቁ ራሱ የጻፈለትን ደብዳቤ በያዘው መጽሐፍ ላይ በሰፊው ወደ እናንተ እመለሳለሁ፡፡ አሁን ግን ወደዚህ እንመለስ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስና እነዚህ ኹለት ጓደኞቹ ከዲያድረስና ከካርተሪዮስ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተማሩ፡፡ እንዲህ እየተማሩ ሳሉ ጓደኝነታቸው ጠነከረ፡፡ አንድ ነገር ለማድረግም አብረው ወሰኑ፤ ላለማግባት! እስከ አሁን ድረስ እንግዲህ ቅዱስ ዮሐንስ የሚኖረው ከእናቱ ጋር ነው፡፡ ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስንም በብዙ ነገር ይረዷል፡፡ ምንም እንኳን ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር ወደ ገዳም ባይሔድም በየጊዜው እየተገናኙ ግን ያጠናሉ፤ ትርጉሙን ይማራሉ፤ የጸሎት መርሐ ግብራትን ያዘጋጃሉ፤ የምናኔ ሕይወትንም ይኖራሉ፡፡ ሊቁ በተለያየ መጻሕፍቱ ላይ፡- “የምናኔ ሕይወት ሲባል የግድ በገዳም ሔደው የሚኖሩት አይደለም፤ በዓለም እየኖሩም ከዓለም መለየት ይቻላልየሚለውም ከዚህ ተግባራዊ ሕይወቱ ተነሥቶ ነው፡፡ ይህ አኗኗር በሶርያውያኑ በእነ ቅዱስ አፍረሐት ሕይወትም የምናገኘው ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ጊዜ የጻፈው መጽሐፍ አለ፤ንጉሥና መነኮሴ ሲነጻጸሩየሚል፡፡ በዚህ መሳጭ መጽሐፉ እውነተኛ ንጉሥ መነኮሴ እንደ ኾነ ያትታል፡፡መነኮሴ ራሱን ይገዛል፤ ንጉሥ ግን ምንም ዓለምን ቢያስተዳድርም ፍላጎቱን ስለማይገዛ ባሪያ ነው፡፡ መነኮሴ የዚህ ዓለም ገዢ ከተባለው ከዲያብሎስና ከአጋንንት፣ ከመናፍቃን፣ ከከሐዲያን ጋር ዘወትር በጦርነት ነው፤ ድልም ያደርጋቸዋል፡፡ ንጉሥ ግን ከሥጋውያንና ከደማውያን ሰዎች ያውም ይበልጥ ሥልጣንን በመመኘት ነው፡፡ የመነኮሴ ጉባኤው ኹልጊዜ - በቀንም በሌሊትም - ከእግዚአብሔርና ከሠራዊቱ ጋር ነው፡፡ ንጉሥ ግን ቀን ቀን ከጦር አለቆቹ ጋር ሲሰበሰብ ይውላል፤ ሌሊትም ተኝቶ ያድራልእያለ ይቀጥላል!!! 

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ ጊዜ የጻፈው ሌላ መጽሐፍም አለ፤ወደ ቴዎድሮስ የተላከ መልእክትየሚል፡፡ ይህ ቴዎድሮስ ከላይ ስንጠቅሰው የነበረውና በኋላ የሜውፕሳስቲያ ጳጳስ ኾኖ የሚሾም ነው፡፡ ገዳማዊ ሕይወትን ትቶ ሔርሞን የተባለችን መልከ መልካም ሴት ለማግባት እንደዚሁም ገና ልጅ ስለ ነበር ይህ ሕይወት ከብዶት ሊተወው ስላሰበ ይህን እንዳያደርግ ሊቁ የጻፈለትና አሳምኖም የመለሰበት ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ሊቁ፡- “ማግባት ለአንተ ዝሙት ነውይሏል፡፡ ለምን? ቢባል ከላይ ስንጠቅሰው እንደ ነበረ አብረው ላለማግባት ወስነዋልና፡፡ በሌላ አገላለጽከክርስቶስ ጋር ቃል ኪዳን ካሰርክ በኋላ ከሴት ጋር ቃል ኪዳን ማሰር ለአንተ ዝሙት ነውሲለው ነው፡፡ መልሶታልም! አቤት መታደል፡፡ ደብዳቤ ጽፎ፣ በዚያ አሳምኖ፣ ማሳመን ብቻ ሳይኾን ሊቀ ጳጳስ እንዲኾን እስከማድረግ አደረሰው! ብዙ ነገር የሚያስብል ነው፤ ይልቅ ወደዚህ እንመለስ!
ጰላዲዮስ እንደሚነግረን ቅዱስ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ መላጥዮስን እየረዳው ሦስት ዓመት ቆይቷል፡፡ ይህም ማለት እስከ 371 .. መኾኑ ነው፡፡ በዚህ ጊዜም ቅዱስ ዮሐንስ አናጉንስጢስ ኾኖ ተሾመ፡፡ የአንባቢነት ማዕርግ ማለት ነው፡፡ እንደ አናጉኒስጥስነቱም የብሉይ ኪዳን እንዲሁም መልእክታትን በአጠቃላይ ያነብ ነበር፡፡ ካህናትንም መጻሕፍትን በማቅረብ ይራዳቸው ነበር፡፡ 
በዚህ ወቅት ላይ ኹለት አስደናቂ ነገሮች ተከሰቱ፡፡ አንደኛው ክስተት ለሚቀጥለው አንድ ዓመት ተጽዕኖ ያደረገበት ሲኾን ኹለተኛው ግን እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ የዘለቀው ነው፡፡ አንደኛው ምን ነበረ ያልን እንደ ኾነም፡- ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ከጓደኛው ጋር ኾኖ በኦሮንቶስ ወንዝ ዳርቻ ወደ ቅዱሳን ሰማዕታት መካነ መቃብር እየሔደ ነበር፡፡ ድንገትም ጓደኛው ወደ ወንዙ ሲመለከት ውኃው ላይ የተንሳፈፈ አንድ ነጭ ነገርን ያያል፡፡ የተጠቀለለ ጨርቅ ይመስላል፡፡ ሊያወጡት ፈልገው ሲመለከቱት ግን መጽሐፍ ነው፡፡ አወጡት፡፡ ገልጠው ሲያዩት ያስፈራል፡፡ የጥንቆላ መጽሐፍ ነበር፡፡ ያስፈራቸው መጽሐፉ አልነበረም፡፡ በዚያ ሰዓት እንደዚህ ዓይነት የጥንቆላ መጻሕፍት የአገሪቱ ንጉሥ መቼ እንደሚሞት፣ የሚተካው ማን እንደ ኾነና ስለ ሌሎችም ነገሮች አብሮ ስለሚናገር እንደዚህ ዓይነት ይዘት ያለው መጽሐፍን የጻፈ ወይም ይዞ የተገኘ ወዲያው ይገደል ስለ ነበር ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉና የሚከታተሉ ወታደሮችም በየቦታው ይሰማሩ ነበር፡፡ እናም ይህን መጽሐፍ ከውኃው አውጥተው ማየት እንደ ጀመሩ አንድ ሰው ወደ እነርሱ እየተጠጋ መጣ፡፡ በፍርሐት ተናጡ፡፡ ሰውዬው ሳያያቸውም መልሰው ወደ ወንዙ ጣሉት፡፡ ከሞትም ተረፉ! “እንዲህ መትረፌይላል ቅዱስ ዮሐንስ በኋላ በቁስጥንጥንያ ሲያስተምር፡- “እንዲህ መትረፌ የእግዚአብሔር ቸርነት ነበር፡፡እንኳንም ተረፈልን ቅዱስ አባታችን! ይኼን ኹሉ መጻሕፍት መቼ እናገኘው ነበርና?! 
እሺ - ወደ ኹለተኛው እንሒድ! ቅዱስ ዮሐንስና ጓደኛው ባስልዮስ አንድ ነገር እየተወራ እንደ ኾነ በጭምጨምታ ሰሙ፤ ሕዝቡና ካህናቱ ቀሳውስት አድርገው ሊሾሟቸው እንዳሰቡ! የሚገርመው ደግሞ ኹለቱም ገና ሠላሳ ዓመት እንኳን አልሞላቸውም፡፡ የቅድስና ሕይወታቸውና የተማሩ መኾናቸው ግን ሕዝቡንና ካህናቱን ማረካቸው፡፡ መስፈርታቸውን ተመልከቱ! ከዚህ በላይ ምንም አልልም፡፡ 
ኹለቱም ወጣቶች ይህን እንደ ሰሙ ተጨነቁ፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስእኔ እንኳን በፍጹም ለዚህ የተገባሁ አይደለሁም፡፡ ባስልዮስ ግን ጥንቱም ከእኔ አስቀድሞ መጻሕፍትን ማንበብ የሚወድና አርአያዬ ነውና ለዚህ የሚመጥን ሰው ነውብሎ አሰበ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ያስብ እንጂ ከባስልዮስ ጋር የተስማሙት ግን ወይ ኹለቱም አብረው እምቢ እንዲሉ ካልኾነ ደግሞ ኹለቱም እንዲሾሙ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በልቡ ባስልዮስ እንዲሾም አስቦ ስለነበር እሺ አለ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ሲመጣ ግን ቅዱስ ዮሐንስእኔ ለዚህ ኃላፊነት አልበቃምብሎ ተደበቀ፡፡ ባስልዮስ ብቻውንም ክህነቱን ተቀበለ፡፡
ባስልዮስ በዚህ ምክንያት በጣም አዘነበት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን ወንድሙን ለማታለል አስቦ ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲል እንዲህ እንዳደረገ አስረዳው፡፡ ከዚህ የተነሣምበእንተ ክህነትየተሰኘ እጅግ አስደናቂ ስድስት ተከታታይ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ እነዚህ ጣፋጭ የኾኑ መጻሕፍቱም የክህነት ኃላፊነት ጥቅምና ትልቅነት፣ ፈተናዎቹና ከባድነቱ፣ የካህናት ዋና መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ መኾኑንና መጻሕፍትን ያልተማረና ክብደቱን ያልተረዳ ሰውም ክህነትን ሊቀበል እንደማይገባው፣ በአጠቃላይ ወደ ክህነት የሚገቡ ሰዎች ማወቅ የሚገባቸውን ነገር የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
ቀጣዩ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወት ወዴት ይወስደን ይኾን? ይከታተሉ!!!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount