(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 12 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
አባ ዮሐንስ አፈወርቅ
ከዚህ በፊት እንደገለጽነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ገዳም እንዳይሔድ የዘገየው በእናቱ ተማጽኖ ነው፡፡ በ372 ዓ.ም. ግን እናቱ ስላረፈች ይጓጓለት ወደነበረው ገዳም ሔደ፡፡ የገዳሙ ስም ሲልፕዮስ ይባላል፡፡ ሲልፕዮስ እጅግ ጫካ የተሞላበት የጽሞና ሥፍራ ነው፡፡
ጰላድዮስ እንደሚነግረን ቅዱስ ዮሐንስ ወደዚህ እንደ ደረሰ አንድን አባት አገኘ፤ አባ ሲሲኮስ ይባላሉ፡፡ አራት ዓመትንም ከእርሳቸው ጋር ቆየ፡፡ በዚህ አራት ዓመት ውስጥ ከእኒህ አባት በዓት አጠገብ የራሱ የኾነ በዓት ነበረው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ እንደዚሁም ከቀኑ አብዛኛውን ሰዓት በበዓቱ ያሳልፍ ነበር፡፡ አብዝቶ ይጸልያል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነባል፡፡ በተለይ በዚህ ገዳም የጽሞና ሕይወት በእጅጉ ይተገበር ነበር፡፡ የሚተኛው በሳር በተጎዘጎዘ መሬት ላይ ነበር፡፡ የሚለብሰው የፍየልና የግመል ቆዳ ነው፡፡ የሚበላው በቀን አንዴ ሲኾን ዳቦ በጨው ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ይህ ኹልጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የኾነው ሕይወት፡- “አዳም ከመበደሉ በፊት የነበረው ሕይወት ነው” ብሎ የማቴዎስ ወንጌልን ሲተረጉም በ38ኛው ድርሳኑ ላይ ገልጾታል፡፡ አባ ሲሲኮስ ብዙ አምላካዊ ራዕዮችን እያዩ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የወደፊት ታላቅነቱን ዐይተዋል፡፡