Wednesday, May 9, 2012

አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ =+=በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ =+=


ወንድሞቼ ሆይ! ወደ ቤተ ክርስቲያን ውድ ስጦታዎችን ይዛችሁ ስትመጡ አያለሁ፡፡ መልካም አድርጋችኋል፡፡ ነገር ግን ስትመለሱ ደግሞ መበለቶችን፣ ደሀ አደጎችንና ሕጻናትን ስትበድሉ አያችኋለሁ፡፡ ታድያ ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ምሥዋዕና ጽዋዕ ብታቅረቡ ምን ይጠቅማችኋል? ለምንስ መሥዋዕቱን ማክበር ስትፈልጉ አስቀድማችሁ ልባችሁን መባ አድርጋችሁ አታቀርቡም? ልባችሁ በጭቃ ተጨማልቆ ምሥዋዑ እንኳን ወርቅ ፕላቲንየምስ ቢሆን ምን ይረባችኋል? ምንስ ይጠቅማችኋል?

       ተወዳጆች ሆይ! አመጣጣችን በወርቅ የተለበጠ መሠዊያ ለማቅረብ ሳይሆን ይኸን ከልብ በመነጨ ለማቅረብ ይሁን፡፡ ከልባችን የምናቀርበው ነገር ሁሉ ከወርቅ የበለጠ መባ ነው፡፡ ልብ በሉ! ቤተ ክርስቲያን የወርቅ ወይም የነሐስ ማቅለጫ ቦታ አይደለችም፤ ለቅድስና የተጠሩ ሁሉ እና የመላእክት ኅብረት እንጂ፡፡ ስለዚህ ከስጦታችሁ በፊት ልባችሁን ይዛችሁ ኑ፡፡ እግዚአብሔር ሥጦታችንን የሚቀበለው ደሀ ሆኖ ሳይሆን ስለ ነፍሳችን ብሎ ነውና፡፡
 ክርስቶስን ማክበር ትወዳላችሁን? እንግዲያስ ዕራቆቱን ስታዩት ችላ አትበሉት፡፡ እናንተ ወደ ቤተ መቅደስ ስትመጡ እጅግ ውድ በሆኑ ልብሶች አጊጣችሁ ስትመጡ እርሱ በብርድና በመራቆት ሊሞት ነውና ብያንስ ትንሽ እንኳን እዘኑለት፡፡ ቤተ መቅደስ ረግጣችሁ ቤተ መቅደስ አትምጡ፡፡ በቃሉ “ይህ ሥጋዬ ነው” ያለው ጌታ በተመሳሳይ ቃሉ “ተርቤ ስታዩኝ አላበላችሁኝም፤… ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” ይለናል /ማቴ.25፡42፣45/፡፡ በእውነት ይህ ምሥዋዕ ልብሳችሁን ሳይሆን ልባችሁን ነው የሚፈልገው፤ እነዚህ የተራቡት ግን ልብስም ምግብም ያስፈልጋቸዋል፡፡
ስለዚህ በሕይወታችን ክርስቶስ እርሱ እንደሚወደው ማክበርን እንማር፡፡ እከብር አይል ክቡር የሆነው እርሱ ደስ የሚያሰኘው ክብር እኛ ውድ ነው ብለን የምናቀርበው ሳይሆን እርሱ ሊቀበለው የወደደውን ስናቀርብለት  ነው፡፡ ጴጥሮስ ጌታን ያከበረ መስሎት እግሩን መታጠብ እምቢ አለ፤ ይህ ግን በጌታ ዐይን ማክበር ሳይሆን ተቃራኒው ነበር፡፡
        ስለዚህ ጌታን ማክበር ስትፈልጉ ገንዘባችሁን አስቀድማችሁ በድሆች ላይ አውሉት፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚፈልገው ወርቃማ ምሥዋዕን ሳይሆን ወርቃማ ነፍሳትን ነውና፡፡ ይህን ሁሉ የምላችሁ ግን መባ እንዳትሰጡ እየከለከልኳችሁ አይደለም፤ ይልቁንም ከዚሁ ጐን ለጐን እንደውም አስቀድማችሁ መመጽወትን እንድትለማመዱ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ለምሥዋዑ ያመጣችሁትን መባ ይቀበላል፤ ለድሆች የምትሰጡትን ደግሞ ከዚሁ በበለጠ ይቀበላችኋል፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ብታመጡ ተጠቃሚዎች እናንተ ብቻ ናችሁ፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ድሀውም እናንተም ትጠቀማላችሁ፡፡ ለምሥዋዕ የሚሆን ወርቅ ስትሰጡ ውዳሴ ከንቱ ሊያመጣባችሁ ይችላል፤ ለድሆች ስትሰጡ ግን ርኅራኄንና ሰው ወዳድነትን ያመጣላችኋል፡፡ ጌታ ተርቦ ሳለ ምሥዋዑ በወርቅ ቢንቆጠቆጥ ምን ጥቅም አለው? ከሁሉም በፊት ጌታ ተርቦ ስታገኙት አብሉትና ከዚያም ምሥዋዑን አስጊጡት፡፡ ነገር ግን እርሱ አንድ ኩባያ ውኃ እንኳን ሳያገኝ እናንተ ጽዋውን የወርቅ ጽዋ ታደርጉታላችሁን? እርሱ ገላውን የሚሸፍንባት ቁራጭ ጨርቅ እንኳን አጥቶ እናንተ ምሥዋዑን በወርቅ ልብስ ታስጌጡታላችሁን? ከዚሁ የምታገኙት መልካም ነገርስ ምንድነው? እስኪ ንገሩኝ! እርሱ የሚበላውን ዳቦ አጥቶ እናንተም ረሀቡን ሳታስታግሱለት ወደ ቤተ መቅደሱ መጥታችሁ ምሥዋዑን በብር ስታስጌጡት የሚያመሰግናችሁ ይመስላችኋልን? የማይቆጣችሁስ ይመስላችኋልን? እንደገና አንድ ሰው ቁራጭ ጨርቅ ለብሶ ብርድና ሐሩር እያፈራረቀ ሲያቆራምደው እየተመለከታችሁ ምንም ልብስ ሳትሰጡት በቤተመቅደስ መጥታችሁ “ይህ ሥጦታ ለጌታዬ ክብር ነው” ብላችሁ ምሥዋዑን በወርቅ ብታስጌጡት ጌታ፡- “ፌዘኞች!” ብሎ እንደሰደባችሁት የማይቈጥረው ይመስላችኋልን?
 እርሱ መጠለያ ፈልጐ እንግዳና መንገደኛ ሆኖ ሲዞር እናንተ ግን ባለ ብዙ ክፍል ቤት እያላችሁ ችላ ብላችሁታል፡፡ ቤታችሁ በተለያዩ የመብራት ዓይነት አጊጦ ሳለ ክርስቶስ ግን በእስር ቤት ነው፤ ልታዩት እንኳን አልወደዳችሁም፡፡ ወንድማችሁ በጣም ተቸግሮ እያያችሁት እናንተ ግን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ለማስጌጥ ትሮጣላችሁ፤ ነገር ግን አማናዊው ቤተ መቅደስ ከሕንጻው የበለጠ ወንድማችሁ ነበር፡፡
                       ወንድሞቼ! ልንገራችሁና እናንተም አድምጡኝ! ለሕንጻው ቤተ መቅደስ የምታመጧቸው ጌጣጌጦች አንድ ኢአማኒ ንጉሥ፣ ወይም ጨካኝ መሪ፣ ወይም ሌባ ሊዘርፋቸው ይችላል፡፡ ወንድማችሁ ሲራብ፣ እንግዳ ሆኖ ሲመጣ እና ሲታረዝ የምታደርጉለትን ማንኛውም ነገር ግን እንኳንስ ጨካኝ መሪ፣ እንኳንስ ጨካኝ ሌባ የጨካኞች አባት የሆነው ዲያብሎስም መውሰድ ይቅርና ሊያይባችሁም አይችልም፡፡ ገንዘባችሁ ሁሉ በአስተማማኝ ቦታ ይከማቻል፡፡
                 ምጽዋት የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ትከፍታለች፡፡ “ጸሎትህ እና ምጽዋትህ ለመታሰብያ እንዲሆን ዐረገ” እንዲል /ሐዋ.10፡4/፡፡ ምጽዋት ከመሥዋዕት ሁሉ ትበልጣለች፡፡ “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠለውም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማውቅ እወዳለሁ” እንዲል /ሆሴ.6፡6/፡፡ ምጽዋት ኃጢአትን ታነጻለች፡፡ “የሚወደድ ነገርስ ለምጽዋት ስጡ፤ ሁሉም ንጹሕ ይሆንላችኋል” እንዲል /ሉቃ.11፡41/፡፡ እንግዲያስ አብዝተን እናጭድ ዘንድ አብዝተን እንዝራ፡፡
 ይህን ሁሉ እንድናደርግና የሚመጣውን ዓለምም በቸርነቱ እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!

Tuesday, May 8, 2012

ድንግል ማርያም በቅ/ገብርኤል ሠላምታ (ክፍል 1)=+= በመምህር ቃለአብ ካሳዬ=+=

በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩  አምላክ አሜን

  እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስትድንግል ማርያም በዓለ ልደት በሠላም አደረሳችሁ!
     ድንግል ማርያም በቅ/ገብርኤል ሠላምታ(ክፍል 1)

በታሪክ ፍሰት ውስጥ ድንግል ማርያም ከቅዱስ ገብርኤል የተቀበለችውን ያህል ሠላምታ የከበረ ሠላምታ አይገኝም። መልአኩ ያቀረበላት ይህ ተወዳጅ ሠላምታ የዓለምን መዳን ዜና ያዘለ የአርሷንም የክብሯን መጠን ያሳየ ነበረ። የእመቤታችን የልደቷም ምሥጢር ፍቺ የጌታ መወለድ ነው።

ጌታ ቅድመዓለም ከአብ ለመወለዱ ጡት የምታጠባው ምድራዊት እናት፣ ድኅረ ዓለም ከድንግል ማርያም ለመወለዱ ለዘር ምክንያት የሚሆን ምድራዊ አባት የለውም። ባለሁለት ልደቱ ጌታ ግን አንድ ነው። ባለበገናውም፡-
 “በአባትህ ስም ስንጠራህ
ወልደ ማርያም በላይ ነህ” በማለት ተቀኝቶለታል። ይህም የአብ የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የበላይ አስተዳዳሪ፣ ገ™ ነህ ማለት ነው።

ከዚህ ቀጥለን የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ቃለ ብሥራት ከጌታ ፍቅር ባሻገር ክብረ ማርያምንም ወለል ያደርግልናልና በጥቂቱ    እንዳስሰው!

  “በሰድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ”ስድስተኛው ወር…. ይህ ወር ቅድስት ኤልሣቤጥ በስተርጅናዋ ዘመን ጸንሳ” ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያሰወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል” ስትል ራሷን ከሰወረችባቸው ከ5ቱ ወራቶች ቀጥሎ የሚመጣ ነው።

ናዝሬት ገሊላ… ናዝሬት በገሊላ አውራጃ ይገኙ ከነበሩ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነች፣ ብዙ የማይጠበቅባትና የተናቀች ነበረች (ዬሐ1.47)ከዳዊት ወገን ለሆነው ለዮሴፍ ..ዮሴፍ በመልአኩ” የዳዊት ልጅ “ተብሎ ተጠርቷል(ማቴ 1÷20)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌላዊው ማቴዎስ የትውልድ አቆጣጠር የዳዊት ልጅ የተባለው በአሳዳጊው በዮሴፍ በኩል  በተዘረዘረው ትውልድ ነው። (ማቴ.21÷9) (ማቴ. 12÷23) (ማር.10÷47)ወደታጨች… መታጨት፡- መታሰብ፣ መመደብ፣ መመረጥ ማለት ነው። 

የእመቤታችን ለዩሴፍ መታጨት ለጋብቻ ከመታጨት ወይም በእንግሊዘኛው betrothal ከሚባለው የተለየ ነው። የእመቤታችን መታጨት መመረጥን የሚወክል ነው። መጽሐፍ ቅዱስም መታጨትን “መመረጥ” እያለ በቀጥታ እንደሚተረጉም መረዳት እንችላለን (2ኛ ቆሮ 11÷2) (ሆሴ 2÷21)። የድንግል ማርያምና የዮሴፍንም ስንመለከት “እጮኝነቱ” መመረጥ በሚለው ትርጓሜ የሚነበብ እንጂ ሌላ መላምት የሚቀርብበት አይደለም። ቅዱስ ዮሴፍና እመቤታችን ለጋብቻ የማይሆን የዝምድና ትስስር፣ የእድሜ አለመመጣጠን የሚያግዳቸው ከመሆኑም ባሻገር እንዲህ የሚያስቡትን መጽሐፍ ቅዱስ “የተሰናከሉ” መሆናቸውን በግልጽ አማርኛ አስቀምጧል (ማር. 6÷3)። የኪንግ ጀምስ የእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስም የሚመሰክረው ይህንኑ ነው። በአማርኛ “እጮኛ” የሚለውን እንግሊዘኛው” espouse” ብሎ ጠርቶታል። ይህም “አንድን ዓላማ ወይም አሳብ የሚደገፍን አካልን “ ያመለክታል። ለጋብቻ መታጨትን የሚመለክት ቢሆን ኖሮ የድንግል ማርያም ለዮሴፍ መታጨት “befrothed” ተብሎ ይጻፍ ነበር። /long man dictionary of  contemporary English 1987).

ወደ አንዲት ድንግል … ልዩ ድንግል በመሆን አንድ ናትና “አንዲት!” ብሎ ገለጻት። ሌሎች  በሥጋ ድንግል ይሆኑ ይሆናል። እርሷ ግን በሥጋም በኀሊናም ድንግል ናት “ርግቤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት፣ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት” (መኀመኀ.6÷9)። ጠቢቡ በትንቢት መንፈስ ሆኖ፡-ርግቤ አላት የየዋሕነቷን
መደምደሚያዬ አላት የሞትን ታሪክ የሚደመድመውን ትውልዳለችና ለወለደቻትም የተመረጠች ናት፡- የተወለደ ሁሉ ምርጥ አይደለም። ድንግል ማርያም ግን እንኳን ለወለደቻት ለወለደችውም የተመረጠች ናት።

ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፡- ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ የሚናገረው እውነት ነውና ::

የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ፡- ማርያም ማለት ጸጋወሀብት ማለት ነው። ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ልጅ ሆና ተሰጥታለች በፍጻሜው ግን የጸጋ እናት ሆና ለልጆቿ ሁሉ ተሰጥታለችና። መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ፣ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፣

ደስ ይበልሽ…ይህንቃል የተናገራት ቅዱስ ገብርኤል ቢሆንም መልአክቱ የመጣው ግን ከሰማይ ነው። ጌታ ደስ ይበልሽ አላት። ደስ ይበልሽ ያላት በመጀመርያ ድኅነተ ዓለም ስለደረሠ ሲሆን ቀጥሎ ደግም እርሱን ለመውለድ ክብር በመመረጧ ነው። አንዳንዶች ግን ጌታን ደስ ያሰኙት እየመሰላቸው “ደስ ይበልሽ” ያላት እናቱን “ይሰድቡለታል”!

ጸጋን የሞላብሽ ሆይ

           ከቅዱስ ሕዝብ ወገን ጸጋ ያለው እንጂ ጸጋ የሞላበት የለም። አንድ ሁለት ጸጋ ይሞላበት ይሆናል፣ ጸጋ ሁሉ ግን አይሞላበትም። የጸጋ ስጦታ ልዮ ልዩ ነውና (1ቆሮ. 12÷4)። ድንግል ማርያም ግን “ ምልዕተ ጸጋ” የሚለው ማዕርጓ ጸጋ ሁሉ እንደሞላባት የሚያሳየን ነው። እንዴት በሉ?

    1ኛ- ጌታ ከነ ጸጋ ስጦታው ሁሉ ጋር  በማኀፀኗ በማደሩ ነው። ታዲያ አባቶች ” የጸጋ ግምጃ ቤት” ቢሏት ተሳስተው ይሆን?
    2ኛ- ፍጹሙ ጸጋ እርሱን  ጌታን መውለድ ነውና።
ጌታ ከአንቺ ጋር ነው

አንዳንዶች ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ላይ..” አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? “ ብሏታል። ስለዚህ ማርያም ማርያም አትበሉ ሲሉ ብዙ ጊዜ ሰምተናል (ዮሐ. 2÷4)። አንድን ጹሑፍ ላልተጻፈበት ዓላማ ማዋል አለመታደል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘይቤ “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ” ማለት “ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?” ማለት እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም መልአኩ ግን በቀጥተኛ መልዕክት “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው”ይላታል። “ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” የሚለው የእግዚአብሔር መልእክተኛ ከሆነ “ጌታ ከእርሷ ጋር ምን አለው?” የሚለውስ የማን መልእክተኛ ነው ትላላችሁ? ተወዳጆች ሆይ፡- ጌታ ከእርሷ ጋር ባይሆን ዛሬ እኛ ከእርሱ ጋር አንሆንም ነበር፣ የእርቃችን ሰነድ፣ የአብሮነታችን ምስጢር፣ የመገናኛ ድንኳናችን ናት። አማኑኤል ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተባለው ከእርሷ ሰው ሆኖ አይደለምን? (ማቴ.1÷23)። ፍቅርን እየወደደ የፍቅርን ሀገር የሚጠላ ማነው? ፍቅር ጌታን እየወደደ ሀገረ ፍቅር ድንግል ማርያምንስ የሚጠላ ማነው? እርሱ ይመለካል፣ እርሷን ብጽዕት እንላለን! እርሱ ታላቅ ገናና ነው፣ እርሷ ታላቅ ሥራ ተደርጎባታል (ሉቃ.1÷49)።  እርሱ አምላክ ነው፣ እርሷ እናቱ ናት። የልባችን መሻት እንዲሞላ እርሱ ከእርሷ  ጋር እንደሆነ እርሷም ከእርሱ ጋር ናት።

 ሴትየዋ በዕድሜ የገፉ ናቸው፣ አንዱ በመንገድ አስቁሞ “ቃል ላካፍልዎት” ይላቸዋል። እርሳቸውም “ተወኝ ባክህ ልጄ ልደትዬን ተሣልሜ እየተመለስሁ እንደመሆኔ ደክሞኛል” ይሉታል፣ እርሱም “ ማናት ደግሞ ልደትዬ” ? ይላቸዋል፣ “ድንግል ማርያም ናት“ይሉታል። እርሱም “ጌታ እኮ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ!“ ብሏታል ሲል ደንግጠው “ እናቱን?” አሉ “አዎ”! አላቸው። እርሳቸውም “ለእናቱ ያልሆነ ለእኔ ይሆናል ብለህ ነው” ብለው እንደቆመ ጥለውት ሄዱ። እባካችሁ ለእናቱ የማይሆን ኢየሱስ እኛ ቤት የለም!

   ወሰብሐት ለእግዚአብሔር

በቅ/ገብርኤል ሠላምታ (ክፍል ሁለት)
የዮሐንስ ወንጌል የ10ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የ11ኛ ሳምንት ጥናት

“እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት- ሙሽሪት ከሊባኖስ ትወጣለች!”

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ! 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዛሬ 2019 ዓመት በፊት ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ተወለደች፡፡ ቅድመ አያቶቿ ጴጥርቃና ቴክታ ይህ ቀራቸው የማይባሉ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ እጅግ ባለጸጐች ነበሩ፡፡ 
ከዕለታት በአንዳቸው ቀን ጴጥርቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፡- “እኅቴ ሆይ! እኔ መካን፤ አንቺም መካንይህ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት፡፡ እርሷም፡- “ወንድሜ ሆይ! እግዚአብሔር ከእኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ እርሱም፡- “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃልአላት፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለቱም አዘኑ፤ አለቀሱም፡፡ በዚህ ጊዜ እንባቸው ወደ እግዚአብሔር ደረሰ፡፡ እንባቸውም እንዲሁ አልተመለሰም፡፡ ወዲያው ራዕይ ይዞ መጣ እንጂ፡፡ ራዕዩ ለጊዜው ባይገባቸውም ቴክታ ሴት ልጅ በስተእርጅናዋ ፀነሰች፡፡ ስሟንም እግዚአብሔር ስእለቴን ሰማ ስትል ሄኤሜን አለቻት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ቅድስት ሐናም አካለ መጠን ስታደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡

Monday, May 7, 2012

እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር- የዮሐንስ ወንጌል የ24ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡10-18)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

መጻጉዑ የተፈወሰበት ቀን ሰንበት (በእኛ ቅዳሜ) ነበረ /ቁ.10/። ጌታችን መጻጉዑን በዚህ ቀን የፈወሰው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አይሁድ የሰንበትን አከባበር አዛብተውት ስለነበረና እውነተኛው አከባበር ሊያሳያቸው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ እነዚህ አይሁድ ሰንበትን ሲያከብሩ እነርሱ ራሳቸው በጨማመሩት አከባበር እንጂ እግዚአብሔር እንዲያከብሩት ባዘዛቸው መንገድ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ነበር የተፈወሰው ሰውዬ አልጋውን ተሸክሞ ሲሄድ ቢያዩት ሰንበትን የሻረ ስለመሰላቸው፡- “ዛሬ ሰንበት ነውና አልጋህንም ተሸክመህ ልትሄድ አይገባህም” የሚሉት፡፡ እነርሱ ራሳቸው ግን በሰንበት ይገርዙ ነበረ /ዮሐ.7፡23/፤ እነርሱ ራሳቸው ግን አንድ በግ ወደ ጕድጓድ ቢገባ ያወጡት ነበረ /ማቴ.12፡11/፡፡ ከዚህ በላይ የሚደንቀው ደግሞ መዝሙረኛው ዳዊት “ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፤ ሊገድለውም ይወዳል” እንዳለው ጌታ የታመሙትን ሲፈውስ እነርሱ ግን የተፈወሱትን ሊገድሉ ይፈልጉ ነበር /መዝ.37፡32/፡፡ በዚህ ድርጊታቸው አልጋውን ተሸክሞ ከሄደው ሰውዬ፣ 38 ዓመት ሙሉ እንደ ትኋን ከአልጋው ጋር ተጣብቆ ከነበረው ሰውዬ በላይ እነርሱ ታመው ነበረ፡፡ ምክንያቱም መጻጉዑ ጌታ የነገረውን ምንም ሳያጠራጠር “አሜን” ብሎ ተፈውሶ ሲሄድ እነርሱ ግን ይህን ሁሉ እያዩ ትንሽ እንኳን አልገረማቸውምና፡፡ ከዚያ ይልቅ ውስጣቸው በቅናት ያቃጠልባቸው ነበር እንጂ /St. Cyril The Great, K3 F4/፡፡

 መጻጉዑ እንዲህ በቅናት ተቃጥለው ቢያያቸው በዚያ ንዴታቸው ላይ ሌላ ክፉ ንግግርን አልጨመረባቸውም፡፡ ከዚያ ይልቅ እነርሱም ይህን መዳን ቸል እንዳይሉ “ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ፤ ስለዚህ ይህን የማደርገው ጌታዬ ባዘዘኝ መሠረት እንጂ እኔው በራሴ ሥልጣን አይደለም” ይላቸው ነበረ /ቁ.11/። እነርሱ ግን ሰውዬው በመዳኑ ስላልተደሰቱ “የፈወሰህ ማን ነው?” ብለው ከመደነቅ ይልቅ በክፋት “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው?” ይሉታል /ቁ.12/። ዳሩ ግን ፈርቷቸው ሳይሆን አሁን ንዴታቸው በእጅጉ ስለጨመረ እስኪያልፍላቸው ድረስ ጌታችን ከዚያ ፈቀቅ ብሎ ነበረ፡፡ ስለዚህም መጻጉዑ ሰማያዊው ሐኪሙን ሊያሳያቸው አልቻለም /ቁ.13 ፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 37/፡፡ ከዚህ በኋላ መጻጉዑ አምላኩን ለማመስገን ወደ ምኵራብ ሄደ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ስላደረገለት ነገር፡- “ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ፡፡ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ኢየሩሳሌም ሆይ በመካከልሽም ሃሌ ሉያ” እያለ ያመሰግን ነበረ /መዝ.116፡17-19/፡፡ ጌታችንም የዳነው መጻጉዕ እዚያው ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘውና በፍቅር አንደበቱ፡- “ልጄ! እነሆ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” ይሏል /ቁ.14/። እውነት ነው! ይህ መጻጉዕ ከዚህ በፊት ይዞት የነበረው ደዌ ዘሥጋ ነው፤ ከዚህ የባሰ ደግሞ ደዌ ዘነፍስ አለና እንዲህ አለው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 479/፡፡ ከዚህ በኋላ “ሰውዬው ሄዶ ያዳነው እርሱ ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው” /ቁ.15/። ይህን የሚያደርገው አይሁድ ጌታን እንዲወግሩት ፈልጐና አሳልፎ እየሰጠው ሳይሆን አስቀድመው “ይህን አድርግ ያለህ ማን ነው?” ብለውት ስለነበረ እየመሰከረላቸው ነው፡፡ ያዳነው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይነግራቸው ነበር፡፡ አይሁድ ግን “ይህ ማን ይሆን? ሙሴ ይመጣል፤ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ያሉት መሲሕ ይሆንን? ይህ በኃይልና በሥልጣን ደዌ ዘሥጋ ብቻ ሳይሆን ደዌ ዘነፍስም የሚፈውስ ሰው ማን ነው?” ብለው ተገርመው ስለ ክርስቶስ መጠየቅና ማወቅ ሲገባቸው የባሰ በሰንበት ድውይን ስላዳነ ያሳድዱት ነበር፤ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር /ቁ.16/። ኢየሱስ ግን ሁል ጊዜ እንደሚያደርገው እንዲህ ይላቸው ነበር፡- “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እናንተ ስነፍጥረትን በስድስት ቀን ፈጥሮ ጨረሰ፤ ከዚያ በኋላም ዐረፈ ብትሉም አባቴ ግን በሰባተኛው ቀንም ፍጥረቱን መንከባከቡና መግቦቱን አላቆመም፡፡ ቀና ብላችሁ ይህን መመልከት ትችላላችሁ፡፡ ፀሐይ መመላለሷን አላቆመችም፤ ነፋሳት መንፈሳቸውን አላቋረጡም፤ ወቅታት መፈራረቃቸውን አልዘገዩም፤ ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ መዝነቡ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አባቴ በዚህች ቀን ይህ መጻጉዕ በተፈወሰበት የሰሊሆም መጠመቅያ እንኳን አንዳንድ ድውያን መፈወሱን አላቆመም፤ ስለዚህ ይህ ሰባተኛው ቀን አባቴ ፍጥረቱን ደስ የሚያሰኝበት ፍቅሩንም የሚያሳይበት የሥራ ቀን ነው፡፡ እናንተም ብትሆኑ በዚሁ በሰባተኛው ቀን ወንድ ልጅን ስትገርዙ ኖራችኋል፤ ካህናቶቻችሁ መሥዋዕትን ሲያቀርቡበት ኖረዋል፤ ልጆቻችሁ በዚሁ ቀን በጐቻቸውን ውኃ እየቀዱ ሲያጠጥዋቸው ኖረዋል፡፡ እነዚህ መልካም ሥራዎች ግን ሰንበትን አልሻሩትም፡፡ እኔም ደግሞ ይህን የፍቅር ሥራ እሠራለሁ፤ አባቴ ስነፍጥረትን ይንከባከብ እንደነበረ እኔም ደግሞ ይህን የፍቅር ሥራ ይህን የመንከባከብ ሥራ እሠራለሁ” ይላቸው ነበረ /ቁ.17፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 38፡2/። ይህ ብቻ ሳይሆን ከአባቱም ጋር የተካከለ እንደሆነ ነገር ግን የሰው ልጅ ከወደቀበት ውድቀት ለማንሣት ብሎ የባርያውን መልክ ይዞ መጣ ይነግራቸው ነበረ /Augustine, On The Gospel Of St. John, Tracte 20:9/፡፡ ከዚህ በኋላ እንደነርሱ እይታ “ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ ሳይሆን ራሱንም ከእግዚአብሔር አብ ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፤ አንድ ባሕርይ፣ አንድ ሥልጣን፣ አንድ መለኰት አለኝ ስላለ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” /ቁ.18/። በእርግጥም አንዳንዶች እንደሚያስቡት እርሱ ወልድ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ያነሠ አይደለም፡፡ ከአባቱ ያንሣል ብለው ዮሐንስ 14፡28ን የሚጠቅሱ እነዚህ ሰዎች እርሱ “የባርያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ” የሚለውን የሐዋርያው ቃል ያላስተዋሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ብለው የሚናገሩ ሰዎች “እኔና አብ አንድ ነን” ያለውን ቃል ቢመለከቱ ይጠቅማቸው ነበር /St. Ambrose, Of The Christian Faith, Book, Ch.18:224/፡፡

    ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይሁን እና ከተዋሕዶ እምነት ውጪ ያላችሁ ወንድሞቼና እኅቶቼ ይህን የከበረ ቃል ቸል አትበሉት፡፡ እነዚህ አይሁድ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ከአባቱ ጋር እኵል እንደሆነ ሲነግራቸው ስለ እነርሱም መዳን ብሎ እንደመጣ ሲነግራቸው እነርሱ ግን እንዴት እንዲህ ይላል ብለው ሊገድሉት ድንጋይ እንዳነሡ እንዴት ሊሆን ይችላል የምንል አንሁን፡፡ እኔና አብ አንድ ነን ካለን አሜን ብለን ማመን መቀበል እንጂ ሊመረመር የማይቻለውን ምሥጢር በአመክንዮ ለመደገፍ አንሞክር፡፡ እነዚህ ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚከባበሩት ከበሬታ እንዳይቀርባቸው ብለው የሕይወትን ቤዛ እንዳልተቀበሉት በዘመን መጨረሻ የምንገኝ እኛም ቃሉ ያለ ምክንያት አልተጻፈልንምና ከሰው ደካማ ፍልስፍና ወጥተን ወደ አምላካችን ወደ ክርስቶስ እንቅረብ፡፡ እርሱ መድኃኒታችን ነው፤ እርሱ ዓለማትን በቃሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ የዘላለም አባት ድንቅ መካር ኃያልም አምላክ ነው፤ እርሱ ክርስቶስ በሥጋ የመጣ ከሁሉም በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን /ሮሜ.9፡5/፡፡ 

(እግዚአብሔር ቢፈቅድ ደግሞም ብንኖር ሳምንት እንገናኛለን!) 

 ተመሳሳይ ገጾች

የዮሐንስ ወንጌል የ8ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የ9ኛ ሳምንት ጥናት

የዮሐንስ ወንጌል የአራተኛው ሳምንት ጥናት

ድንግል ማርያም

ፕሮቴስታንት ለጠየቀኝ የተለያዩ ጥያቄዎች

FeedBurner FeedCount