Thursday, April 28, 2016

ደም ለበሰች

ያቺ ውብ ጨረቃ በጣም የደመቀች
                ውቢቷ ጨረቃ፤
ደም ለበሰች አሉኝ
             በኃይል ተጨንቃ፡፡
እርቃኑን ሲያስቀሩት የዓለም ፈጣሪ
    ከላይ ተመልክታ ከልቧ አዘነች፤
ይህን አላደርግም ድምቀቴ በሱ ነው
                ብላ ራሷን ጣለች፡፡
ደሙ ሲፈስ አይታ፤
ህመም ግርፋቱን እሷም ተመልክታ፤
ጌታ ሲንገላታ፤
አይ አይሆንም አለች
          አይኖቿን ጨፈነች፤
የጭንቀቷ ብዛት
         እሷም ደም ለበሰች፡፡

Tuesday, April 26, 2016

ስግደት (ክፍል 4)

በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 18 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በሰሙነ ሕማማት የግዝት በዓል ቢሆን እንኳን ይሰገዳል!
የዘንድሮው የስቅለት በዓል 21 የሚውል በመሆኑና ዕለቱም የግዝት በዓል በመሆኑ ይሰገዳል ወይስ ይተዋል የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሡ ይስተዋላል፡፡ በዚህ በአራተኛ ክፍል ስግደትን በተመለከተ ጽሑፋችን ስግደትን ከሰሙነ ሕማማት ጋር አያይዘን እናነሣለን፡፡ በቀደሙት ክፍሎች መሠረታዊ የኦርቶዶክሳዊ ስግደት ይዘትንና ሥርዐትን የዳሰስን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ 
በሰሙነ ሕማማት የግዝት በዓል ቢሆን እንኳን ይሰገዳል፡፡ ለዚህ ምክንያቶችን ላስቀምጥ፡-

Monday, April 25, 2016

ስግደት ክፍል - 3



በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 17 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ስግደት ለመላእክት ይገባልን?
መጽሐፍ ቅዱስ ለመላእክት መስገድ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ሰዎች ለእግዚአብሔር መላእክት ይሰግዱ ነበር፡፡ የሚከተሉትን በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡
በለዓም ባልታዘዘው መንገድ ሲሔድ፣ መሔዱን እግዚአብሔር አልወደደምና የእግዚአብሔር መልአክ ሊከለክለው መጣና ከመንገዱ ቆመ፡፡ በለዓም መልአኩን ማየት ባይችልም የበለዓም አህያ ግን ከፊቷ የቆመውን መልአክ ዐይታ አልሔድም ብላ ቆመች፡፡ በለዓምም ሦስት ጊዜ ደበደባት፡፡ በመጨረሻም አህያይቱ በሰው አንደበት አናገረችው፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር የበለዓምን ዐይን ከፈተና መልአኩን ማየት ቻለ፡፡ ለመላእክት ስግደት ይገባልና ወዲያውም ሰገደለት፡፡ መልአኩም አልተቃወመውም፡፡እግዚአብሔርም የበለዓምን ዐይኖች ከፈተ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ በመንገድ ላይ ቆሞ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ይዞ ዐየ ሰገደም፤ በግንባሩም ወደቀ፡፡ዘኁ. 2231፡፡

Sunday, April 24, 2016

ስግደት - ክፍል 2



በዲ/ን ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 16 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
በክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ስግደት ምንነት በወዲቅ በአስተብርኮ በአድንኖ የሚሰገዱ የስግደት አይነቶችን ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሰገድ የባሕሪይ ስግደትን ለቅዱሳን የሚሰገድ የጸጋ ስግደትን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን አይተናል፡፡ ለቅዱሳን እንድንሰግድ ያስተማረን እግዚአብሔር መሆኑንም በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃነት ተመልክተናል፡፡
በዚህ በሁለተኛው ክፍል ትምህርታችን ደግሞ የሚሰገድባቸውና የማይሰገድባቸው ጊዜያት ለመላእክት፣ ለቅዱሳንና ለቅዱሳን ንዋያት የሚሰገድ ስግደትን የእግዚአብሔር መልአክ ባለራእዩ ዮሐንስን አትስገድልኝ የማለቱን ምሥጢር እናያለን፡፡

FeedBurner FeedCount