☞ (በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጎመችውና ከአራት ዓመት በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ ታትማ ግንቦት አንድ ቀን በገበያ ከምትውለው - የትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ - መጽሐፍ የተቀነጨበ፣ ገጽ 17-19)
☞ … ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስትህ ለአንተ ትገዛልህ ዘንድ ትሻለህን? ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት አንተም እንዲሁ ለሚስትህ አድርግላት፡፡ ሕይወትህን ስለ ርሷ አሳልፈህ መስጠት ካለብህ ስለርሷ ሕይወትህን አሳልፈህ ስጥ፤ መከራም መቀበል ካለብህ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ፡፡
አንተ ይህን ብትፈጽመው ስንኳ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ካደረገላት ጋር ሲነጻጸር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንተ ይህን ያደረግኸው ከአንተ ጋር ፈጽማ ለተዛመደችህ ለአንዲት ሴት ነው፡፡ “But He for one who turned on Him and hated Him” “እርሱ ግን ከእርሱ ለተመለሰችውና ለጠላቸው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡” ርሱ ከርሱ የተመለሰችውንና የጠላችውን እንዲሁም ያቃለለችውን ገንዘቡ ሲያደርጋት በማስፈራራት፣ በማስገደድ ወይም ይህን በመሳሰሉ ነገሮች አልነበረም፤ ነገር ግን ኀዘን ባልተቀላቀለበት ፍጹም በሆነ ፍቅር በመሆን ነበር፡፡ አንተም ለሚስትህ እንዲሁ አድርግላት አዎን! ምናልባት ሚስትህ አንተን ልታመናጭቅህ፣ ልትንቅህ፣ ልታፌዝብህም ትችላለች፤ ቢሆንም ግን አንተ ለርሷ ካለህ አርቆ አሳቢነት ንጹሕ ፍቅርና ኀዘኔታ የተነሣ ልትታገሣት ይገባሃል፡፡
ከሰው ሁሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖርም ከእነዚህ የተሻሉ ነገሮች ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተለይም ለባልና ለሚስት፡፡ አንድ ሰው አገልጋይ ባሪያውን በማስፈራራት ለመግዛት ቢሞክር ለጥቂት ጊዜአት ሊገዛለት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባሪያ እንዲህ ዓይነት አገዛዝ ስለማይመቸው ከእርሱ ፈጥኖ ይሸሻል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የሕይወቱን አጋር፣ የልጆቹን እናት፣ የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ሚስቱን በፍቅርና በፍጹም አክብሮት እንጂ ልክ እንደ ባሪያ በፍርሃት ሰንሰለት በማሰር ወይም በማስጨነቅ ርሷን ሊገዛት መሞከር አይገባውም፤ ሚስት በባልዋ ምክንያት የምትሸበር ከሆነ አንድነታቸው ምን ዓይነት አንድነት ነው?