(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 9 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች ሆይ! ግንቦት 12 የተወዳጁ አባታችን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት እንደ መኾኑ ስለ ሊቁ ከዚህ በፊት ከምናውቀው በተጨማሪ አንዳንድ ነገሮችን እንድንነጋገር ወድጃለሁ፡፡
በዚሁ የመጀመሪያ ክፍልም ስለ ተወለደባትና ስላደገባት ከተማ ስለ አንጾኪያ የተወሰኑ ነጥቦችን እንነጋገራለን፡፡ መልካም ንባብ!
በአራተኛ መ.ክ.ዘ. አጋማሽ ላይ በሮማ ክፍለ ግዛት እጅግ በጣም ከሚታወቁት ከተሞች አንዷ አንጾኪያ ነች፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት አንጣክያ ተብላ በምትታወቀው የደቡብ ቱርክ ውስጥ የምትገኝ የሶሪያ ልሳነ ምድር ነች፡፡
ይህቺ ከተማ በ300 ቅ.ል.ክ. የታላቁ እስክንድር ጀኔሮችሎች አንዱ በሚኾን በሴሉከስ ቀዳማዊ ኒካቶር በደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኝ ባሕሩ በሚፈስ ኦሮንቶስ በተባለ ወንዝ ዳር የተመሠረተች ናት፡፡ አጥሯ ግንብ ሲኾን 10 ኪሎ ሜትር ያህል ይረዝማል፡፡ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 508 ሜትር ከፍታ ያለውና በደን የተሸፈነ ተራራ አላት፡፡ ዋናው መንገዷ በእብነ በረድ የተነጠፈ፣ በኹለቱም አቅጣጫ ኹለት ፎቅ ባላቸው ሕንፃዎች የደመቀ፣ ሌሊት ሌሊት በዘይት በሚሠሩ መብራቶች ያሸበረቀ ነው፡፡ ከተማይቱ እጅግ አስደናቂ በኾኑ ሕንፃዎች የተዋበች፣ በቂ የሚባል የውኃ ተደራሽነት ያላት፣ 18 የሚኾኑ የመዋኛ ሥፍራዎችና ቲአትር ቤቶች እንዲሁም የሰረገላ እሽቅድድም ቦታዎች የሚገኙባት ናት፡፡ ከከተማይቱ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 8 ኪሎ ሜትር ላይ ነፋሻማ ቦታ ላይ የተሠሩ ቪላ ቤቶች፣ አሁንም በጥቅም ላይ ያሉ ፏፏቴዎች፣ አፖሎ የተባለ ጣዖት ቤትና የኦሎምፒክ ውድድር በየጊዜው የሚካሔድበት ሥፍራ የሚገኙባት ከተማ ነች፡፡